የስደተኞቹ መብዛት በምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል የወረርሽኝ ሥርጭት እንዳይስፋፋ ሥጋት ፈጥሯል
ከጂቡቲ የሚመለሱ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ከረዥም ርቀት በእግራቸው በመጓዝና በረሃብ ተዳክመው፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢዎች ወድቀው እየተገኙ መሆናቸው ተገለጸ።
ስደተኞቹ በድካም ወድቀው ከተገኙባቸው አካባቢዎች መካከል የሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን፣ በሶማሌ አዋሳኝ የድሬዳዋ ቀበሌዎችና በተወሰኑ የአፋር ክልል አካባቢዎች ይገኙበታል። ‹‹ሚያዝያ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ብቻ ከጂቡቲ በእግራቸው ተጉዘው የተመለሱ 16 ስደተኞች በድሬደዋ ገጠራማ አካባቢዎች ወድቀው አግኝተናል፤›› ሲሉ ሁኔታውን ለሪፖርተር የገለጹት የድሬዳዋ አስተዳደር የጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ፣ ‹‹የመውደቃቸው ምክንያት ረሃብ እንጂ ሌላ ነገር አይደለም፤›› ብለዋል።
በመሆኑም በአፋጣኝ ምግብና ውኃ አግኝተው እንዲጠነክሩ በማድረግ ወደ ማቆያ ማዕከላት እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል። ስደተኞቹ በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ካለባት ጂቡቲ እየተመለሱ መሆናቸው፣ በኢትዮጵያ የቫይረሱ ሥርጭት እንዳይስፋፋ ሥጋት ፈጥሯል።
የጂቡቲ መንግሥት ዓርብ ሚያዝያ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 999 መድረሱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህም በአንድ ሳምንት ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸውን ቁጥር በዕጥፍ ያሳደገ ነው።
በዚህም ምክንያት ተመላሽ ስደተኞቹ በማቆያ ማዕከላት እንዲቆዩ በድሬዳዋ አስተዳደር፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ማዕከላት ተዘጋጅተው እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን፣ ስደተኞቹ በአስቸጋሪና ሕገወጥ ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ከማኅበረሰቡ እንዳይቀላቀሉ ለማድረግ የድሬዳዋ አስተዳደር፣ ሁለቱ ክልሎችና በአካባቢው በድንበር ጥበቃ ላይ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች መምከራቸውን ሪፖርተር ከድሬዳዋ የጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ለምለም ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከዚህ በተጨማሪም በፌዴራል ደረጃ የተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ድንበር የሚጋሩ ክልሎች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞችን በተመለከተ ኃላፊነት ወስደው እንዲሠሩ መመርያ መስጠቱንም ገልጸዋል።
በዚህ መሠረት በእግራቸው ከጂቡቲ እየተመለሱ የሚገኙ ስደተኞችን በተመለከተ፣ ከጂቡቲ የሚዋሰኑት የሶማሌና የአፋር ክልሎች ኃላፊነቱን እንዲወስዱ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የቫይረሱ ሥርጭትን ለመቆጣጠር በተቀመጠው አሠራር መሠረት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የሚጠበቅ መሆኑን ወ/ሮ ለምለም አስረድተዋል፡፡
በድሬዳዋ ከጂቡቲ ተመላሾችንና ሌሎች በቫይረሱ የሚጠረጠሩትን ለይቶ ለማቆየት፣ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በማዕከልነት ተሰናድቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።
በጂቡቲ ባለው የቫይረሱ ሥርጭት ምክንያት ተመላሽ ስደተኞችም ለቫይረሱ የተጋለጡ ስለሚሆኑ፣ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማቆያ ማዕከል እንዲገቡ ከተደረጉ ተመላሾች መካከል በ574 ግለሰቦች ላይ ምርመራ ተደርጎ ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ወ/ሮ ለምለም አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ሁለት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች በድሬዳዋ መኖራቸውንና በተደረገላቸው ሕክምና አገግመው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንደተቀላቀሉ ያስታወሱት ኃላፊዋ፣ በድሬዳዋ ቫይረሱ የተገኘባቸው በሙሉ ከውጭ የተመለሱ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ነገር ግን ከጂቡቲ የሚመለሱ ስደተኞች ራሳቸውን እየሸሸጉ በመሆናቸውና ወደ ማዕከል እንዲገቡ የተደረጉትም ወደ ማቆያ ከመግባታቸው አስቀድሞ ከማኅበረሰቡ ጋር ንክኪ እንደሚኖራቸው በመታመኑ፣ በድሬዳዋ የቫይረሱ ሥርጭት ወደ ማኅበረሰቡ ገብቶ እንደሆነ ለማረጋገጥ በዚህ ሳምንት ውስጥ በተመረጡ ተጋላጭ አካባቢዎች ፈቃደኝነትን መሠረት በማድረግ ከማኅበረሰቡ ለላብራቶሪ ምርመራ ናሙና መውሰድ እንደሚጀመር ገልጸዋል።
የዚህ ውጤት ከታወቀ በኋላ የተጠናከረ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል፣ ቫይረሱ በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዳለ በዚህ ምርመራ ከተረጋገጠ ከተማዋን ሙሉ በመሉ የመዝጋት ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚችልም ጠቁመዋል። በተመሳሳይ የአፋር ክልል ከጂቡቲ የሚመለሱ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ለይቶ ማቆየት የጀመረ ሲሆን፣ ወደ ለይቶ ማቆያ ላለመግባት ተሸሽገው ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ 21 ተጠርጣሪዎች በመከላከያ ሠራዊት በቁጥጥር ሥር ውለው በአፋር ክልል በተዘጋጀ የማቆያ ማዕከል እንዲገቡ መደረጉን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
የአማራ ክልልም ከአፋር ክልል ጋር በሚያዋስኑት አካባቢዎች ከጂቡቲ የሚመለሱ ስደተኞችን፣ ወደ ኅብረተሰቡ ሳይቀላቀሉ ተለይተው እንዲቆዩ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጉ ተገልጿል። ከጂቡቲ እየተመለሱ ያሉ ስደተኞች ቁጥር የጨመረበትን ምክንያት ለማወቅ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቢሮ መረጃ ለማግኝት ቢሞከርም፣ መረጃው የሚሰጠው ቫይረሱን ለመከላከል በተዋቀረው አገር አቀፍ ቡድን እንደሆነ ገልጿል።
ሪፖርተር ከሌሎች ምንጮቹ ባደረገው ማጣራት ከጂቡቲ የሚመለሱት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣ ከሞላ ጎደል በጂቡቲ አድርገው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለመግባት በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ተጉዘው የነበሩ ናቸው፡፡ በቫይረሱ ወረርሽኝ ምክንያት ወደ መዳረሻቸው መግባት ያልቻሉ፣ በመረጧቸው መዳረሻዎች የቫይረሱ ሥርጭት ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት ፈርተው ወደ አገራቸው እየተመለሱ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በቀን እስከ ሁለት ሺሕ የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንደሚሰደዱ በቅርቡ በተደረገ ዓለም አቀፍ ጥናት ይፋ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጂቡቲ የስደተኞቹ መሻገሪያ እንደሆነች ታውቋል። በዚህም የተነሳ የስደተኞቹ ምልሰት በቀጣዮቹ ቀናትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠበቃል ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ መንግሥት በጂቡቲ በሚገኘው ወታደራዊ ጦር ሠፈሩ፣ ከቫይረሱ ሥርጭት ጋር በተገናኘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ያወጣ መሆኑ ታውቋል። ይህ አዋጅ ጂቡቲ በሚገኘው የጦር ሠፈሩ በሚገኙ 4,500 የጦርና ሲቪል አባላት ላይ የሚፈጸም መሆኑ ታውቋል።