በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ዋዜማ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት መንስዔ የሆነችው ውሃን ከተማ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴዋ መመለስ መጀመሯ እየተነገረ ይገኛል፡፡
ኮቪድ-19 ከሰው ልጆች ሕይወት ባሻገር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጉዳት ያልዳሰሰው ምድራዊ ኃይል የለም፡፡ ወረርሽኝ በእጅጉ ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል ስፖርቱ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ታላላቆቹ የአውሮፓ ክለቦችን ጨምሮ ሁሉም የስፖርት ዘርፍ ወረርሽኙ ጋሬጣ ሆኖባቸዋል፡፡ ቀጣዩ የ2021 የውድድር ዓመት ቅድሚያ ሰጥቶ የሚከውነው በኮቪድ 19 ምክንያት ለተንከባለሉት ፕሮግራሞች ወይስ ለራሱ የሚለው እስካሁን መልስ ያላገኘ ጉዳይ ሆኗል፡፡
በ2020 የውድድር ዓመት መከናወን ከነበረባቸው ውድድሮች በየአራት ዓመቱ የሚዘጋጀው የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን ጨምሮ መቶ ሺዎችን የሚያሳትፉ የጎዳና ላይ ውድድሮች፣ የአውሮፓ፣ የደቡብ አሜሪካና የአፍሪካ ዋንጫ እንዲሁም የመኪና (ፎርሙላ ዋን)፣ የብስክሌት፣ የቅርጫት ኳስ፣ ሜዳ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ክርኬትና ሌሎችም በዓለም ላይ በእጅጉ የሚዘወተሩ ስፖርቶች ሁሉም ወደ 2021 የውድድር ዓመት እንዲሸጋገሩ ኮቪድ 19 አስገድዷል፡፡
የቶኪዮ ኦሊምፒክ 2020 ስያሜውን እንደያዘ በ2021 እንደሚከናወን ቀን የተቆረጠለት አሁን ላይ ወረርሽኙ እያስከፈለ ካለው የሕይወት ጉዳት በመነሳት ቫይረሱ ክትባት ካልተገኘለት ጃፓናውያን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ ያደረጉበትን ኦሊምፒክ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚሉም አልታጡም፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በብዙ ፈተናዎች ያለፈውና የዓለም ሕዝቦችን ለማቀራረብ እንዲሁም ለዓለም ሠላም በእጅጉ የሚናፈቀው የኦሊምፒክ ጨዋታ፣ “እንዲራዘም ስንጠይቅ ከልብ እያዘን ነው፣ ምክንያቱም ብዙ ለፍተንበታል ብዙ ገንዘብም አውጥተንበታል፣ ቫይረሱ ከአቅማችን በላይ ነው፤” በማለት ያስተላለፉት መልዕክት ቫይረሱ በቁጥር ሥር ካልዋለ ኦሊምፒክ ዕውን በ2021 ይደረጋል ወይ የሚለውን ጥርጣሬ እንዲጎላ ያደርገዋል፡፡
ይህ ከመርሐ ግብሩ ሽግሽግ ውጪ ሁሉም ስፖርቶች በተያዘላቸው ፕሮግራም መሠረት ባለመካሄዳቸው ካስከተለው ኪሳራ ውጪ ያለው መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ኮቪድ 19 አሁን ላይ ካስከተለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ በተጓዳኝ በችግሩ ምክንያት ወደ 2021 የተሸጋገሩ መርሐ ግብሮች በራሱ ብዙ ችግር እንዳላቸው የሚናገሩ አሉ፡፡
ከእነዚህ አስተያየት ሰጪዎች መካከል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የማናጀር ተወካይና አሠልጣኝ የሆኑት አቶ ሐጂ አዴሎ ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ ባለሙያው ከሆነ፣ “ሩጫውን ጨምሮ ሁሉም ውድድሮች በ2021 እንዲከናወኑ ተሸጋግረዋል፡፡ ከአትሌቲክስ ዘርፍ ብቻ የለንደን፣ የቦስተን፣ የአምስተርዳም፣ የፓሪስና የባርሴሎና ማራቶኖች በወረርሽኙ ምክንያት ተሸጋግረዋል፡፡ የሚከናወኑበት ወርና ዕለት እንዲሁም የእያንዳንዱ ውድድር ስፖንሰር የተለያየ በመሆኑ እነማን በየትኛው ውድድር ይሳተፋሉ የሚለው ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው፡፡ አሁን ሁሉም ነገር ተሸጋግሯል የሚል ብቻ በመሆኑ አይደለም የውድድር አዘጋጆች እኔን ጨምሮ ሙያተኞች ለዚህ ቀን የሚል ትክክለኛ ዕቅድ የለንም፣” በማለት የቀጣዩ ዓመት መጨናነቅ ሊያስከትል የሚችለውን ተግዳሮት ያስረዳሉ፡፡
የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር በ2021 ለማካሄድ አስቦት የነበረውን የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ አሁን ባለው ሁኔታ ማካሄድ እንዳይቻል በመረዳት ፕሮግራሙን ወደ 2022 እንዲሸጋገር ማድረጉ ታውቋል፡፡ ውሳኔው ምናልባትም በኮቪድ 19 ምክንያት ለተዳከመው ኢኮኖሚ መጠነኛ እፎይታ እንደሚሰጥ እምነት ያላቸው አሉ፡፡
ከዚህ ባለፈ ማኅበሩ በየአገሮቹ የሚደረጉ የሊግ ውድድሮችን ጨምሮ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግና ኢሮፓ ሊግ ቀደም ሲል በተያዘላቸው ፕሮግራም መሠረት ከፊት ለፊት ባለው ክረምት እንዲጠናቀቁ የሚል ሐሳብ እንዳለው እየተነገረ ይገኛል፡፡ ጣሊያንና ስፔንን በከፍተኛ ሁኔታ ያጠቃው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሁን ላይ መጠነኛ መቀዛቀዝ እያሳየ ነው በሚል የጀርመንና ሌሎችም አገሮች የውስጥ ሊጎቻቸውን ለመጀመር ክለቦቻቸው ወደ ልምምድ ካምፕ እንዲገቡ የማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ የመኪና (ፎርሙላ ዋን) ውድድሮችን ጨምሮ የሌሎች በርካታ ውድድሮች ዕጣ ፈንታ በ2021 ይደረጋሉ ከሚል ባለፈ እነዚህን ሁሉ ውድድሮች በአንድ የውድድር ዓመት ማድረግ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ ሊቃለል የሚችልበት አማራጭ ሐሳብ እየቀረበ አይደለም፡፡