Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርወይ አለመታደል?

ወይ አለመታደል?

ቀን:

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመንግሥት አስተዳደር ዘመን ወደ መጨረሻው ጊዜ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መሬት ለአራሹ ለላብ ‹‹አፍሳሹ›› የሚል መፈክርን አንስተው እያለ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ይቋቋማል፡፡ ከዚያም የገጠር መሬትን አዋጅ ካወጣ በኋላ አከታትሎ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት ‹‹የመንግሥት›› ለማድረግ ሁለተኛ አዋጅ ያወጣል፡፡

የተማሪዎች የመሬት ለአራሹ ሠልፍ የእንቅስቃሴ መነሻ ቀደም ባለው ጊዜ የገጠር መሬት አብዛኛው በመሳፍንቱና በመኳንንቱ እጅ ሆኖ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለከበርቴው ጢሰኛ ሆኖ እንደ ባለ መሬቱ ፍላጎት ‹‹ግማሽና ሲሶ›› በሚባለው የክፍፍል ሥርዓት አብዛኛውን የድካሙን ፍሬ ለባለ መሬቱ አስረክቧል፡፡ ከዚያም በላይ በጊዜው ጢሰኛው ለባለ መሬቱ ሁለተኛ አሽከር ሆኖ ጉልበቱንም ጭምር ይበዘብዝ እንደነበር በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይታወቅ የነበረ ነው፡፡

ወታደራዊው ስብስብ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መሪነት የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በሚል መጠሪያ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ፣ በ1967 ዓ.ም. የመሬት ለአራሹን አዋጅ ከማውጣቱ አስከትሎ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት በሚል ሁለተኛውን አዋጅ ያወጣል፡፡

በመሠረቱ የገጠሩም ሆነ የከተማ ቦታው የመንግሥት የመደረጉ ጉዳይ ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ተብሎ የተፈጸመ በመሆኑ አነጋጋሪ ሊሆን አይችልም፡፡

ለጥያቄው መልስ የማይገኝለት መሠረታዊ ጉዳይ ግን ከከተማ ቦታ ጋር የግለሰቦች ቤቶች ‹‹ትርፍ ቤት›› ተብለው መወረሳቸው ነው፡፡ ይህ አፈጻጸም በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ አሳዛኝ እንደሆነ እስካሁን ቆይቷል፡፡

የደሃውን ንብረት ያለ አግባብና በማን አለብኝነት መንፈስ በመውረሱና በየአቅጣጫው የነበረበትን የጦርነት ውጥረት ለመቋቋም ባለመቻሉ፣ ደርግ በውርደት ከሥልጣን መውረዱ ይታወቃል፡፡

ኢሕአዴግ ባደረገው ትግል ደርግን ከአሸነፈና መላውን ኢትዮጵያ ከተቆጣጠረ በኋላም ‹‹በትግራይ ከተሞች በትርፍነት የተወረሱ›› ቤቶችን ለባለንብረቱ እንዲመለሱ አድርጓል፡፡

በዚህ መነሻ እንደ ትግራይ ሁሉ በአዲስ አበባና ቦሌ ሌሎቹም ክልሎች በትርፍነት ተወርሰው የነበሩት ቤቶች እንዲመለሱላቸው ባለንብረቶች በተደጋጋሚ ጊዜ በሰላማዊ ሠልፍ አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም፣ ምንም ዓይነት ምላሽ ሳይሰጣቸው ቀርቷል፡፡ ከዚያም የሰላማዊ ሠልፍ ፈቃድ እንዳይሰጣቸው መታገዱ ብቻ ሳይሆን አቤቱታውን ለመቀጠል የሞከሩትንም በማዕከላዊ እስር ቤት በማሰር በማስጠንቀቂያ በመለቀቃቸው ከዚያ በኋላ አቤቱታው ሊያቋርጥ ችሏል፡፡ እዚህ ላይ የትግራይ ባለንብረቶች ትርፍ ቤታቸው ሲመለስ የመሀል አገር ነዋሪዎች ተነጥለው መቅረታቸው እጅግ በጣም አሳዛኝ እንደሆነ እስካሁን ቆይቷል፡፡

ይህ አፈጻጸም ከአንድ የመንግሥት አመራር የማይጠበቅ በመሆኑ በዚህ ረገድ ኢሕአዴግን ሲያስወቅሰው የኖረ ጉዳይ ሲሆን፣ የደርግ ዘመን ባለሥልጣናትን ለፍርድ አቅርቦ የሞት ፍርድ ከተሰጠባቸው በኋላ በነፃ ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሰላም የሚኖሩ መሆናቸውም ይታወቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የመንግሥት አመራር በተለያየ ወንጀል ምክንያት ታስረው በወህኒ ቤት ይገኙ የነበሩ እስረኞች በነፃ ተለቀው በአገራቸው በሰላም እንዲኖሩ ከማድረጋቸውም በላይ፣ በተለያየ የፖለቲካ ምክንያት ከ20 ዓመት በላይ በየውጭ አገሩ በስደት የቆዩት ሁሉ ወደ አገራቸው ተመልሰው በነፃነት እንዲኖሩና ንብረታቸውም ተመልሶላቸው በሰላም እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡

ምንም ዓይነት ጥፋት ያልፈጸሙና በፊትም አሁንም እንደሚታወቀው ለኑሯቸው መደጎሚያ ሠርተው በማከራየት ላይ የነበሩት የቀደሙት ባለቤቶች ግን ተነጥለው በመንግሥት ላይ ወንጀል የፈጸሙ ይመስል የደከሙበት ንብረታቸው እስካሁን ሳይመለስላቸው በመቆየቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትርና ካቢኔያቸው የደረሰባቸውን በደል ተገንዝበው የደሃውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረት እንዲመለስ ቢያደርጉ በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ እንደማያስከፍል ምንም አጠራጣሪ አይሆንም እላለሁ፡፡

(ከተበዳዮቹ አንዱ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...