Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ይህንን ገጠመኝ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ረቡዕ ሚያዝያ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. የቢቢሲ ዜናዎችን በስልኬ አማካይነት ስከታተል፣ አንድ አስገራሚ ርዕስ ዓይኖቼን ስቧቸው ካነበብኩ በኋላ ለአንባቢያን ማካፈል አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡ አንዲት የ49 ዓመት እንግሊዛዊ ከኮሮና ጋር ያደረገችውን ግብግብ የሚተርክ በራሷ የተተረከ ገጠመኝ ሲሆን፣ ርዕሱም ‹‹A Coronavirus Survivor’s Story: ‹I Touched Death››› ይላል፡፡ ማርጋሬት የተባለች የኮሮና ቫይረስ ጥቃትን የተቋቋመች ሴት ጨርሶ ለማገገም እስከ ስድስት ወራት የሚቀሯት ቢሆንም፣ እሷ ግን ሁለተኛ ዕድል ተሰጥቶኛል ብላለች፡፡ እሷ እንደምትለው አንድ ዓርብ ዕለት ለየት ያለ ምቾት የሚነሳ ስሜት ይሰማታል፡፡ ከወትሮው ለየት ያለ ድካም ስለተሰማት ወደ አልጋዋ ትሄዳለች፡፡ ‹‹የሳምንቱ መጨረሻ ቢሆንም ለእኔ ግን ጥሩ አልነበረም›› ያለችው ማርጋሬት፣ ሰኞ ዕለት እግሯን ያማት ጀመር፡፡ መንቀሳቀስ አቃታት፡፡ የነርቭ መሸምቀቅ መስሏት ፓራሴታሞል ብትወስድም፣ ነገር ግን ቆይታ ሆስፒታል ስትሄድ ሐኪሞች ቫይረስ ጡንቻዎቿ ውስጥ በቀጥታ መግባቱን ነገሯት፡፡ ሳል ቢኖራትም ዘወትር እንደሚነገረው ተከታታይ አልነበረም፡፡ ለአንድ ሳምንት ያህል ቤት ተኝታ በአካባቢዋ የሚገኝ ነዳጅ ማደያ ግሮሰሪ ምግብና ምግብ ነክ ዕቃዎችን ለመግዛት ትሄዳለች፡፡

ማርጋሬት እንደምትለው ይህን ጊዜ ነው ያላሰበችው ከባድ የሕመም ጡንቻ ያረፈባት፡፡ ከነዳጅ ማደያው ግሮሰሪ ስትመለስ ሰውነቷ ወደ በረዶ ተለውጦ መንዘፍዘፍ ትጀምራለች፡፡ በአንድ ጊዜ ሶፋዋ ላይ አራት የሞቀ ውኃ የያዙ ጠርሙሶች ታቅፋና ሁለት ብርድ ልብሶች ደራርባ፣ ምንም ዓይነት ሙቀት ሊሰማት አልቻለም ነበር፡፡ ቆይቶ ግን ነገር መጣ፡፡ በሕይወቷ አጋጥሟት ወይም ሲባል ሰምታው የማታውቅ ትኩሳት ጀመራት፡፡ ‹‹ሰውነቴ በእሳት የተያያዘ ነበር የሚመስለኝ…›› ብላ፣ ጭንቅላት የሚፈልጥ ራስ ምታት እንደ ጀመራት፣ በወቅቱም ምንም ዓይነት የምግብ ፍላጎት እንዳልነበራት፣ ነገር ግን በተደጋጋሚ እንደሚያስመልሳትና በራስዋ ላብ እንደ ትሾቃለች፡፡ ከዚህ በኋላ ለመተንፈስ ሥቃይ ሆነባት፡፡ በዚህ ላይ የአስም ሕመም አለባት፡፡ ቤት ውስጥ ለቀናት ከተሰቃየች በኋላ፣ ልጅዋ ለድንገተኛ የሕክምና አገልግሎት ደውሎ አምቡላንስ መጥቶ ሆስፒታል ሲወስዳት፣ የአምቡላንሱ ሾፌር በጭንቀት ውስጥ ሆኖ በከፋ ሁኔታ ውስጥ ስለሆነች ወደ ውስጥ ልናስገባት ይገባል ሲል በሰመመን ይሰማት እንደነበርና የኦክስጂን ዕርዳታ እየተደረገላት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

በታማሚዎች ብዛት ምክንያት ለሦስት ሰዓታት ያህል አምቡላንሱ ወረፋ ጠብቆ፣ ተራዋ ሲደርስ ዊልቼር ላይ አስቀምጠዋት ለእሷ የሚሆን ማከሚያ ሥፍራ ይጠፋል፡፡ ምክንያቱም በዚያ ወቅት በጣም ብዙ ሰዎች በኮሮና ተይዘው መጥተው ሆስፒታሉን አጨናንቀውታል፡፡ በሰመመን ውስጥ ብትሆንም ጥድፊያዎችና የስልክ ጥሪዎች ይሰሙዋት ነበር፡፡ በአጠቃላይ የሚያስፈራ ነበር፡፡ ከብዙ ቆይታ በኋላ አንድ ነርስ መጥቶ ጉሮሮዋ ውስጥ እንጨት መሳይ ዘንግ ከቶ የሚያማትን ክፍል በመጎርጎር ናሙና ወስዶ ሄደ፡፡ ቆይቶ ሲመጣ እንደገና ከአፍንጫዋ ቀዳዳ ውስጥ በሆነ ነገር ወደ ውስጥ ገብቶ ናሙና ሲወስድ ሕመሙ ከባድ ነበር፡፡ በመቀጠል የደምና የደረት ራጅ ምርመራ ተደረገ፡፡ ይሰማት የነበረው በቡጢ እንደ ተመታ ሰው ነበር፡፡ አንዲት ነርስ መጥታ በኤክስሬይ ውጤቱ መሠረት የሳንባ ምች ስለተያዘች ካሁን በኋላ 24 ሰዓት ሙሉ በኦክስጂን ነው የምትተነፍሽው ስትላት፣ የኮንክሪት ሙሌት እንደ ወደቀበት ሰው ደረቷን ከባድ ሕመም ይሰማት ጀመር፡፡ ሳንባዎቿ በመጠቃታቸው ምክንያት የማደንዘዣ ሞርፊን ሲሰጣት መላ ሰውነቷ የሚያሰቃይ ሕመም ተሰማው፡፡ ሥቃዩ መፈጠርን የሚያስጠላና ሕይወት በቃኝ የሚያሰኝ ነበር ብላለች፡፡

ሕመሙ ከመጠን በላይ ስላዳከማት የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ቀናት ባታስታውሳቸውም፣ በመቀጠል ግን በአካባቢዋ ምን እየተካሄደ እንደነበር በሰመመን ቢሆንመ አትዘነጋም፡፡ ነርሶች ያለማቋረጥ ወጣ ገባ ሲሉ ይራወጣሉ፣ የፅዳት ሠራተኞች ርጭት በማካሄድ ተዋህሲያንን ለመከላከል ይዋከባሉ፣ ለነርሶች አብዛኛውን ጥሪ የምታደርገው ማርጋሬት ስትሆን ምክንያቱ ደግሞ የምትጎነጨው ውኃ ፍለጋ ነው፡፡ በወቅት ከመጠን በላይ ተዳክማ የነበረች ብትሆንም፣ ነርሶቹን ስታያቸው በትንሹ ለ12 ሰዓታት ያለ ዕረፍት ስለሚሠሩ ምን ያህል ከባድ ድካም እንደ ነበረባቸው በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል፡፡ እንደ ማርጋሬት የሴቶችን ክፍል ከሞሉት ብዙዎቹ ሞታቸውን የሚጠብቁ መሆናቸው ግልጽ ነበር፡፡

እሷ እንደምትለው አንድ ቀን ሴቶች ክፍል ውስጥ አንድ ወንድ ታይና ነርሶቹን ስትጠይቃቸው፣ ‹‹አንዲት ሴት ልትሞት ስለሆነ ልጅዋ ነው በመጨረሻው ሰዓት አብሯት ያለው…›› ሲላት ራስዋን ትስታለች፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና በቅዠት መልክ በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ካጋጠሟት ሰዎች ጋር የምትነጋገር ሲመስላት፣ ‹‹ሞቻለሁ ወይስ በሕይወት አለሁ… እነዚህ ትውስታዎች ወደ ሞት የሚደረጉ ሽግግሮች ናቸው… በቃ ሳልሞት አልቀረሁም…›› እያለች ሳለ ሴትየዋ መሞታቸው ተሰማ፡፡ ከአንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ አስፈላጊው ተከናውኖ ልክ እንደ ዕቃ ፕላስቲክ ጥቁር ቀረጢት ውስጥ አስከሬናቸው ገብቶ ሊወሰዱ ሲሉ ‹አንድ…ሁለት…ሦስት› ተብሎ ብድግ ሲደረግ፣ በቃ ሴትየዋ ቁጥር ሆነው ቀሩ ትላለች፡፡ ብዙዎች ሲሞቱ አስከሬናቸውን ሊወስድ የሚመጣው ባለ ኩሽኔታ እግር ጋሪ ድምፅ ግን መቼም ቢሆን ሰቆቃው አይረሳም፡፡ ያውም ከሞት ጋር ግብግብ ይዞ ቀኑን ለሚቆጥር፡፡

እዚያ የአደገኛው ኮሮና ቫይረስ ሕሙማን የተኙበት ፅኑ ማከሚያ ዋርድ ውስጥ በከፍተኛ ሥቃይና ድካም ውስጥ ሆና፣ ስንትና ስንት አስከሬኖች በሰቆቃ ስታይ የነበረችውና ሕይወቷን ለማትረፍ የታገለችው ማርጋሬት እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 8 ቀን ሙሉ ጨረቃ እንደታየቻት ታስታውሳለች፡፡ ጨረቃ ዑደት ጨርሳ እንደ አዲስ ሙሉ ሆና ስትጀምር፣ እሷም እያገገመች መሆኗን በመረዳት ጠነከረች፡፡ በዚህ መሀል አሁንም ሞት አለ፡፡ ጋሪው ይመላለሳል፡፡ አንድ ቀን የታደገ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ጠንከር ማለተቷን የተረዳ አንድ ነርስ፣ ‹‹ሐኪሙ ሲያነጋግርሽ አሁን በርትቻለሁ ጥንካሬ ይሰማኛል በይው፡፡ ፈፅሞ እስካገግም እንድቆይ እንዳትይው፡፡ ሲጠየቁ እዚህ የተወሰነ ጊዜ እናገግም ብለው የቀሩት በሙሉ ዳግም በቫይረሱ ተይዘው አልቀዋል፡፡ ይህ የተረገመ ቦታ ስለሆነ ቤትሽ አገግሚ፡፡ አንቺ ጠንካራ ስለሆንሽ ቤትሽ ይሻልሻል…›› ሲላት ምክሩን ተቀበለች፡፡ ሐኪሙ የምርመራዋን ውጤት ይዞ ትግሉን እንዳሸነፈች ሲነግራት፣ በዕድለኝነቷና ሁኔታዋን በከፍተኛ ትጋት ሲከታተሉ በነበሩት ቤተሰቦቿ ድጋፍ ከሞት ወደ ሕይወት ተመለሰች፡፡ ሞት ዘንድ ደርሶ መመለስ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ማርጋሬት ትናገራለች፡፡

ከሐኪሞቹና ከነርሶቹ በተጨማሪ ሕይወቷን የታደጉ የአምቡላንስ ሠራተኞች ከ18 ሰዓታት በላይ እየተራወጡ ሕይወት እንደሚታደጉ ስታወሳ፣ ለእነዚህ ወገኖች ማሰብ እንደሚገባን አበክራ አስገንዝባለች፡፡ የሕሙማን መቀበያ ሥፍራ የሚሠሩ፣ የፅዳት ሥራ የሚያከናውኑ፣ አስከሬን የሚያጓጉዙና በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ሁሉ ለሕይወቷ መትረፍ ትልቅ ዋጋ አላቸው ብላለች፡፡ ካሁን በኋላ ከሦስት እስከ ስድስት ወራት የማገገሚያ ጊዜዋ በመሆኑ አሁን የሕይወቷ ምሰሶ እናቷ ናቸው፡፡ ምግብ እያዘጋጁ በሽንቁር ውስጥ እያቀበሉዋት ይታደጓታል፡፡ ሞትን ነክታው ከተመለሰች በኋላ ማቴሪያላዊ ነገሮች ምኔም አይደሉም ብላለች፡፡ እሷን አሁን የሚናፍቋት ንፁህ አየር መተንፈስ፣ ወፎችን መመልከትና በተፈጥሮ ፀጋዎች መደሰት ብቻ ነው፡፡ ድሮስ ከጤና በላይ ምን አለ?

(ጌዲዮን ካሌብ፣ ከቀበና)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...