በቁምላቸው አበበ ይማም
መጋቢ ኤልደር ዊርዝሊንስ ሰሞነኛውን ስቅለትና ትንሳዔን ታሳቢ በማድረግ፣ ‹‹ዛሬ ዓርብ ቢሆንም እሑድ ይመጣል፤›› የሚል ዘመን ተሻጋሪና ወርቅ ይትበሀል ትተውልን አልፈዋል፡፡ ጨለማ፣ የምድር መናወጥ፣ ክረምት፣ ሰደድ እሳት፣ በረዶ፣ ጎርፍ፣ መገፋት፣ መዋረድ፣ መገረፍ፣ መቸንከር፣ መሰቀል፣ መከዳት፣ መሸጥ፣ መሰቀል፣ ወዘተ ዓርብ ቢሆንም፣ መንጋቱ፣ ብርሃን በጨለማ ላይ መንገሡ፣ የምድር መናወጡ መቆሙ፣ ብራ ፀደይ መምጣቱ፣ መከበሩ፣ መፈወሱ፣ ትንሳዔ፣ ቀን መውጣቱ፣ የተሻለ ጊዜ መምጣቱ፣ ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ እንደተነሳበት እሑድ ሁሉ ለእኛም ሆነ ለአገራችን ከችግር፣ ከድህነት፣ ከተመፅዋችነት፣ ከኋላቀርነት፣ ከፈተና፣ ከወረርሽኝ፣ ከጭቆና፣ ከአፈና፣ ከጥላቻ፣ ወዘተ ነፃ የምንወጣበት አንገታችን በክብር ቀና የምናደርግበት፣ ትንሳዔያችንንና ህዳሴያችንን የምናይበት ቀን ይመጣል፡፡ እሑድ ይመጣል፡፡ ‹‹ዛሬ ዓርብ ቢሆንም እሑድ ይመጣል፤›› እያልን በእምነትና በተስፋ እንጠባበቃለን፡፡ ደግሞም ይሆናል፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት ባጋጠመኝ አደጋና የጤና ዕክል ሙሉ በሙሉ ሽባ ሆኜ ቤት ለመዋል፣ ተሽከርካሪ ወንበረ (ዊልቼር)፣ አጓጓዥ (ወከር) እና ከዘራ ለመጠቀም ተገድጄ ነበር፡፡ ለመልበስ፣ ለማውለቅ፣ ውኃ ለመጠጣት፣ ለመመገብ፣ ለመታጠብ፣ ለመተኛትና ለመነሳት የሰው ዕርዳታ ያስፈልገኝ ነበር፡፡ ስልክ ለማነጋገርና የቴሌቪዥን ቻናል ለመቀየር ዕርዳታ ያስፈልገኝ ነበር፡፡ ሁሉ ነገሬ በሰው ዕርዳታ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ መላ ሕይወቴ ተመሰቃቅሎ ነበር፡፡ ሥራዬን አጣሁ፡፡ በጋዜጠኝነትና በኮሙዩኒኬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪዬን ለመያዝ ጥቂት ሲቀረኝ ተቋረጠ፡፡ ህልሜ ተስፋዬ ተጨናገፈ፡፡ በመጨረሻም ለጭንቀትና ለድብርት ተዳርጌ ነበር፡፡ ዓርብ ነበርና!
እንዲህ ዓይነት ብዙ የሕማማት ‹‹ዓርቦችን›› በሕይወቴ እንዳሳለፍኩት ሁሉ፣ እናንተም ደረጃው ይለያይ ይሆናል እንጂ በሕይወታችሁ መውደቅ መነሳቶችን፣ ሕማማትን፣ ዓርቦችን ማሳለፋችሁ አይቀርም፡፡ በግል ሕይወታችሁ፣ በትምህርታችሁ፣ በፍቅራችሁ፣ በትዳራችሁ፣ በንግዳችሁ፣ በህልማችሁ፣ በራዕያችሁ፣ በድርጅታችሁ፣ በሃይማኖታችሁ፣ በጤናችሁ፣ በቤተሰባችሁ፣ በማኅበረሰባችሁ፣ በሕዝባችሁ፣ በአገራችሁ፣ ወዘተ ላይ ዓርብ ሆኖባችሁ (ቀን ጨልሞባችሁ) እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍርድ ተዛብቶባችሁ፣ ተገምድሎባችሁ፣ ታስራችሁ፣ ተገርፋችሁ፣ ተሰቅላችሁ፣ ተቸንክራችሁ፣ ተዋርዳችሁ፣ ተፈትናችሁ፣ ባመናችሁት ተከድታችሁ፣ በባልንጀራችሁ በ‹33› ብር ተላልፋችሁ ተሰጥታችሁ፣ ሰማይ ተደፍቶባችሁ፣ ወዘተ ይሆናል፡፡ ዛሬም በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያለፋችሁም ሊሆን ይችላል፡፡ ዓርብ ነውና!
ካለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ወዲህ ያሉትን ጊዜያት እንኳ ብንወስድ እንደ ሕዝብና እንደ አገር ሺሕ ዓርቦችን በድርቅ፣ በረሃብ፣ በቸነፈር፣ እናት ልጇን እስከ መብላት የተገደደችበት እንደ ክፉ ቀን ያለ እንደ 65ቱ በረሃብ የሞተች እናቱን ጡት የሚጠባበት፣ እንደ …77 … 87 … ወዘተ ያሉ ጠኔዎችን፣ ችጋሮችን አሳልፈናል፡፡ ዛሬም ከዚህ አዙሪት በቅጡ ሰብረን መውጣት አልቻልንም፡፡ እንደ ኅዳር በሽታ፣ ፈንጣጣ፣ ከ76 ወዲህ ደግሞ በኤችአይቪ/ኤድስ፣ ካለፉት 40 ቀናት ወዲህ ደግሞ ኮቪድ 19 የዕልቂት ጥላውን አጥልቶብናል፡፡ በግብፅ፣ በደርቡሽ፣ በቱርክ፣ በእንግሊዝ፣ በጣሊያን፣ በሶማሊያ፣ በኤርትራ ተወረናል፡፡ ዛሬም የክተት ነጋሪት የሚያስጎሹምብን አልጠፉም፡፡ በመቶዎች ሊቆጠሩ በሚችሉ የእርስ በርስ ግጭቶች አልፈናል፡፡ ከዘመነ መሳፍንት እንኳ ብንጀምር በመሳፍንቱ፣ በመኳንንቱ፣ በነገሥታቱ መካከል ለሥልጣን፣ ለዘውድ ሲባል በተካሄደ የእርስ በርስ ግጭት ጦርነት ወገናችን ተጨራርሷል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስ፣ አፄ ምኒልክ፣ ልጅ እያሱ፣ ንግሥት ዘውዲቱ፣ ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንንና መንግሥቱ ጉዳቱ፣ ጥፋቱ ይለያይ እንጂ ሁሉም በእርስ በርስ ግጭት፣ ጦርነት ተፈትነዋል፡፡ የአገርና የሕዝብ ዓርብ ነበርና!
ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ በተቀነቀነ የማንነት ፖለቲካ የተነሳ አገራችን በጥላቻ፣ በቂም በበቀል፣ በልዩነት ተጎሳቁላለች፡፡ ጎሳን፣ ሃይማኖትን፣ አይዶሎጂን መሠረት አድርገን ተጋጭተናል፣ ተጋድለናል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትን፣ መስጊዶችን አቃጥለናል፡፡ ቀይና ነጭ ሽብር ተባብለን ተጨራርሰናል፡፡ እናት አባት በቀይ ሽብር የተገደሉ ልጆቻቸውን ሬሳ ሲለምኑ የጥይት ዋጋ ተጠይቀዋል፡፡ የዚህችን አገር ታሪክ እስከ ወዲያኛው ሊቀይር የሚችል ፍም እሳት የሆነ አንድ ትውልድ አልቋል፡፡ በእርስ በርስ ጦርነት በብዙ አሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አጥተናል፡፡ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ አገር አጥተናል፡፡ ዛሬ ድረስ ከዚህ የዞረ ድምር አልወጣንም፡፡ የአገር የሕዝብ ዓርብ ነበርና!
በተለይ በቀዳማዊ ትህነግ /ኢሕአዴግ 27 ዓመታት በፖለቲካ አመለካከታችን፣ በጎሳችን በጅምላ ተገርፈናል፣ ተገልብጠናል፣ ተሰቃይተናል፣ ተግዘናል፣ ተሰደናል፡፡ ሰው በመሆን ብቻ ከፈጣሪ የተቸርናቸውን የማሰብ፣ የመናገር፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመሰብሰብ መብቶች ተረግጠዋል፡፡ በደምሳሳው ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻችን ተጥሰዋል፡፡ በገዛ ወንድሞቻችን እንደ ባሪያ ተገዝተናል፣ ተረግጠናል፣ ተገፍተናል፡፡ ሀብታችንንና አገራችንን በቀን በአደባባይ ተዘርፈናል፡፡ አገር በቁሟ በአውሬዎች ተግጣለች፡፡ የደሃ ጉሮሮ ታንቆ በእኛ ድህነት ጥቂቶች በተድላ፣ በቅንጦት፣ በደስታና በፍሰሐ ተንደላቀዋል፡፡ እየተንደላቀቁም ነው፡፡ ዓርብ ነበርና!
ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ዴሞክራሲና ነፃነትን መሸከም ተስኖን፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋትን እንደ እኩይ አጋጣሚ ተጠቅመን ዜጎችን በማንነታቸው አፈናቅለናል፣ ገድለናል፣ ሮማውያን እንኳ ያላደረጉትን ዘቅዝቀን ሰቅለናል፡፡ ከእነ ሕይወታቸው በእሳት አቃጥለናል፡፡ ወደ ገደል ጥለናል፡፡ ሩጦ ተጫውቶ ያልጠገበን ሕፃን ብላቴና ብልት ሰልበናል፡፡ እህቶቻችንን ደፍረናል፡፡ ዛሬ ድረስ አግተናል፡፡ በሕዝብ፣ በክልልና በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት እንዲቀሰቀስ የማንነት ግጭት እንዲቀጣጠልና አገር ወደ ለየለት ቀውስ እንድትገባ በአደባባይ ቀስቅሰናል፣ ለፍፈናል፡፡ ዓርብ ነበርና!
ለእሑድ መዳረሻ፣ ለትንሳዔ፣ ለንስሐ፣ ለጥሞና፣ ለአንድነት፣ ለፍቅር፣ ለሰላም፣ ለይቅርታና ለህዳሴ መጀመሪያ በግብፅ አንድ አደረገን፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንቆም አስቻለን፡፡ ካለፉት 40 ቀናት ወዲህ ደግሞ ወደ ሰውነታችን፣ ወደ ቀደመው ማንነታችን እንድንሸበለል ያለ ልዩነት የሰው ልጅንና ኢትዮጵያውያንን የሚያጠቃ ቫይረስ ሰደደብን፡፡ ኮሮና ቫይረስን፡፡ ሊካሄድ ታስቦ የነበረውን ምርጫ ተክትሎ አንዣቦ ከነበረ የሥጋት፣ የግጭት፣ የብጥብጥ፣ የቀውስና የደባ ዳመና በመለኮታዊ ኃይሉ ታደገን፡፡ የእሑድ አጥቢያ ነውና!
ዛሬ በኮሮና ቫይረስ የተነሳ የሰው ልጅና የዓለም ህልውና ላይ አደጋ ተደቅኗል፡፡ ሁሉም ነገር ተመሰቃቅሏል፡፡ ተገለባብጧል፡፡ ፍርኃት፣ ጭንቀትና ሞት በሰማዩ ረቧል፡፡ ሞት እንደ ጥላችን ይከተለን ጀምሯል፡፡ ከምንወዳቸው ተለይተናል፡፡ በየቤታችን ከተናል፡፡ በአጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤያችን ተቀይሯል፡፡ ከአብያተ ክርስቲያናት፣ ከመስጊድ ደጆች ተባረናል፡፡ ከሥራ ታቅበናል፡፡ ተገድበናል፡፡ የዕለት ጉርሳቸውን በየዕለቱ እየሠሩ የሚያገኙ ወገኖች ለችግር ተዳርገዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች በወረርሽኙ የተነሳ በራቸውን በመዝገታቸው ተማሪዎች ቤት ለመዋል ተገደዋል፡፡ የአገርና የሕዝብ ኢኮኖሚ ክፉኛ እየተጎዳ ነው፡፡ ከኅዳር በሽታ፣ ከኤችአይቪ/ኤድስ፣ ከኩፍኝና ከፈንጣጣ፣ ከፖሊዮ፣ አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች በአንድ ላይ ተደምረው፣ ከ9/11 የሽብር ጥቃት በላይ የሰው ልጅ ህልውናን የሚፈትን ወረርሽኝ ዙሪያችንን ከቦናል፡፡ አስደንብሮናል፡፡ ዓርብ ነውና!
‹‹ዛሬ ዓርብ ቢሆንም እሑድ ይመጣል!›› እያልኩ እየተፅናናሁ ተስፋ አደርግ ነበር፡፡ ዛሬ ድቅድቅ ጨለማ ቢሆን የማይነጋ፣ ዙሪያው ገደል፣ ተራራና ተስፋ ቢስ ቢመስልም ነገ ቀን ይወጣል፣ ይነጋል፣ ደልዳላ ይሆናል፣ እሑድ ይመጣል እያልኩ እፅናና ነበር፡፡ እምነቴም አምላኬም አላሳፈረኝም፡፡ ዛሬ ጤናዬ በእጅጉ መሻሻል አሳይቷል፡፡ በቅርብ ሙሉ በሙሉ ይሻለኛል ብዬ አምናለሁ፡፡ የምወደውን የጋዜጠኝነት ሙያዬን በደጋግ ሰዎች ዕገዛና ማበረታት በነፃነት ጀምሬያለሁ፣ ተስፋዬ ለምልሟል፡፡ በዋሻው መውጫ ብርሃን እየታየኝ ነው፡፡ ያቋረጥኩትን ትምህርቴን አጠናቅቄ ሦስተኛ ዲግሪዬን እሠራለሁ፡፡ በዚህች አገር የሚዲያ ኢንዱስትሪ የዜግነት ድርሻዬን እወጣለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ዛሬ ላይ እንዲህ ህልመኛ የሆንኩት ዓርብ አልፎ እሑድ እንደሚመጣ በማመኔና ተስፋን በመሰነቄ ነው፡፡ ከስቅላቱ በኋላ ትንሳዔው እንደሚከተል በማመኔ ነው፡፡ እሑድ ይመጣል!
እየሱስ ክርስቶስ ከተዋረደበት፣ ከተተፋበት፣ ከተገረፈበት፣ ከተቸነከረበት፣ እንደ ወንበዴና ወንጀለኛ አንዳች መተላለፍና ነቀፋ ሳይገኝበት፣ ሞት የተፈረደበት፣ በመስቀል ተቸንክሮ ከተሰቀለበት፣ ጎኑ ከተወጋበት በኋላ ‹‹ዓርብ›› እንደ ተቀሩት የሳምንቱ ቀናት የጊዜ መለያ ብቻ አልሆነም፡፡ የጨለማ፣ የሥቃይ፣ የመከራ፣ የፈተና፣ የውርደት፣ የግፍ፣ የበደል፣ የመገፈፍ፣ የራቁትነት፣ የመሰቀል፣ ወዘተ ተምሳሌት ጭምር እንጂ፡፡ ኤልደር ‹‹ዛሬ ዓርብ ነው›› ያሉት ይኼን መሰሉን ቀን፣ ዓመት፣ ዘመን ነው፡፡ ዛሬ ዓርብ ነውና!
ሆኖም መግነዙን ፈቶ፣ የመቃብሩን ቋጥኝ አንከባሎ፣ ሞትን ድል አድርጎ፣ በብኩርና በሦስተኛው ቀን በድል ተነስቷል፣ አርጓል፡፡ በደሙ ዘላለማዊ ድኅነትን፣ በግርፋቱ ህያው የፈውሱን አክሊል አቀዳጅቶናል፡፡ ኃጢያትን ደምስሶ ከልዑል እግዚአብሔር አስታርቆናል፡፡ ከኦሪታዊ ሕግ፣ ከባርነትና ከኃጢያት ነፃ አውጥቶናል፡፡ እሁድ መጥቷልና!
ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ሕዝብና አገርም እንዲህ ባለ ተመሳሳይ ጨለማ፣ ፈተና፣ መከራ፣ ቸነፈር፣ ውርደት፣ ግርፋት፣ መቸንከር፣ ደም መፍሰስ፣ ሥጋ መቆረስ፣ ጀርባ መተልተል፣ ግማደ መስቀሉን ተሸክሞ ተራራ መውጣት፣ ጎን መወጋት፣ የሾህ አክሊል መድፋት፣ ወዘተ አልፈዋል፡፡ እልፍ አዕላፍ ዓርቦችን አሳልፈዋል፡፡ ዳሩ ግን የትንሳዔው እሑድ ይመጣል፡፡ እሑድ ይመጣልና!
ከዚህ ክፉ ወረርሽኝ፣ ከፖለቲካ ስብራት፣ ከጥላቻ፣ ከስግብግብነት፣ ከደባ ፖለቲካ፣ ከድህነት፣ ከእርዛት፣ ከረሃብ፣ ከኋላ ቀርነት፣ ከልዩነት፣ ወዘተ ወይም ከዓርብ ወጥተን የሐኪሞችን ምክር፣ የመንግሥትን ማሳሰቢያ በመተግበር ዓርብን አልፈን እሑድን እናያለን፡፡ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አክብረን፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ገንብተን ዓርብን አልፈን ለእሑድ እንበቃለን፡፡ የብልፅግና ትልማችንን ለማሳካት ሌት ተቀን በመትጋት፣ ሙስናን፣ ብልሹ አሠራርን፣ ስንፍናን፣ ዳተኝነትን በማስወገድ ዓርብን እጅ ለእጅ ተያይዘን እንሻገራለን፡፡ እሑድን በተስፋ በእምነት እንጠባበቃለን፡፡ ልዩነትን፣ ጥላቻን፣ ጎሰኝነትን፣ የታሪክ እስረኝነትን፣ የሴራ ፖለቲካን ወይም ብዙ ዓርቦችን በፅናትና በብርታት አልፈን ለትንሳዔና ለህዳሴ ለእሑድ እንበቃለን፡፡ ደግሞም እናምናለን ይሆናል፡፡ ‹‹ዛሬ ዓርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል!››
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡