በሸዋዬ ተስፋዬ
ሥራ የሰው ልጅ ዓብይ የሕይወት ተግባር በመሆኑ በግልም ይሁን በቡድን ሥራ ስኬታማ አስተዋጽኦ ለማበርከት የሠራተኞች ተሳትፎ፣ እንዲህም ምርታማነትን የሚያስችል የሥራ ምኅዳር በቅድሚያ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በአገራችን የልማት ሒደት አመች የሥራ ምኅዳር መኖር ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ይህ ጽሑፍ አጠቃላይ አስተያየት ይሰነዝራል፡፡
በዓለም አገሮች የሥራ ምኅዳር ቅኝት
ይህ ጽሑፍ ጋሎፕ (Gallup) እ.ኤ.አ. በ2017 ያጠናቀረውን የዓለም አገሮች የሥራ ምኅዳር ዘገባ (State of the Global Workplace Report) መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን ተቋሙ በተለያዩ ዘርፎች የሕዝብ አስተያየት በማጠናቀርና በመተንተን ለድርጅቶችና ለሥራ መሪዎች የመፍትሔ ምክረ ሐሳብ በማቅረብ ይታወቃል፡፡ የተቋሙ የዓለም አገሮች የሥራ ምኅዳር ዘገባ በ155 አገሮች በእያንዳንዳቸው 1000 ከ23 እስከ 65 ዓመት ጎልማሶችን እ.ኤ.አ. ከ2014 – 2016 በናሙና ጥናት በማካተት ለመጠይቅ ከሰጡት ምላሽ የተጠናቀረ ነው፡፡ የጥናቱ ውጤት የአገሮችን የሥራ ምኅዳር በንፅፅር ከማሳየት በተጨማሪ አገሮችና ድርጅቶች ከሠራተኞች ባህርይና ዝንባሌ በመነሳት የሰው ሀብትን በብቃት በመጠቀም የነፍስ ወከፍ ምርታማነትን የሚያሻሽሉበትን ሥልት ይጠቁማል፡፡
የተቋሙ የሥራ ምኅዳር ቅኝት በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች ብዛትና የሥራ ተሳትፎ አመልካቾች የሚያተኩር ሲሆን፣ እነዚህም የሰዎች የሕይወት ጥራት ደረጃን ከማመልከት በተጨማሪ ለድርጅቶች ምርታማነትና ትርፋማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች በአንድ ድርጅት በቅጥር ሥራ በሳምንት ቢያንስ 30 ሰዓት የሚያገለግሉ መሆናቸውንና ከእነዚህ ሠራተኞች ውስጥ የሥራ ተሳትፎ የሚያሳዩ (Engaged)፣ የሥራ ተሳትፎ የማያሳዩ (Not Engaged)፣ እና በንቃት የሥራ ተሳትፎ የማያሳዩ (Actively Disengaged) ሠራተኞችን ድርሻ የተቋሙ ጥናት ያመለክታል፡፡
በዚህ መሠረት ከ23 እስከ 65 ዓመት ጎልማሶች መካከል በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች ድርሻ ዝቅተኛው በኒጄር 5%፣ ከፍተኛው በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ 72%፣ እንዲሁም በዓለም አገሮች በአማካይ 32% ነው፡፡ በአንፃሩ በአሜሪካና በካናዳ በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች ድርሻ 56% በመሆኑ ከ39 ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች አማካይ ድርሻ 14% በንፅፅር አራት እጥፍ ይልቃል፡፡ በኢትዮጵያ በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች ድርሻ 8% ብቻ ሲሆን፣ ይህም ከዓለምና ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች አማካይ ድርሻ በንፅፅር እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ ከፍተኛ የሠራተኞች ስምሪት ካላቸው የአፍሪካ አገሮች መካከል ሞሪሸስ 42%፣ ግብፅ 28%፣ ደቡብ አፍሪካ 27%፣ ኬንያ 22% እና ኡጋንዳ 19% ቅድሚያ ይዘዋል፡፡
በሌላ በኩል ከ23 እስከ 65 ዓመት ጎልማሶች መካከል በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ ያልተሰማሩ ሠራተኞች ድርሻን ብንመለከት፣ የዓለም አገሮች አማካይ 68 በመቶ፣ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች አማካይ 86 በመቶ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ 92 በመቶ ያህል ከፍተኛ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ በአገራችን ያለው ተግዳሮት እጅግ የላቀ ነው፡፡ በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ ሥምሪት በአገሮች መካከል ካለው ልዩነት በተጨማሪ በወንዶችና በሴቶች መካከል ጉልህ የፆታ ልዩነት በመኖሩ ምክንያት በዓለም አገሮች ወንዶች 42 በመቶ እና ሴቶች 23 በመቶ፣ እንዲሁም ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች ወንዶች 19 በመቶ እና ሴቶች ዘጠኝ በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡ በተለይ በአካባቢ ባህልና ልምድ ምክንያት በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሰሜን አፍሪካና በደቡብ እስያ አገሮች ሴቶች ከወንዶች በንፅፅር ዝቅተኛ ጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ ሥምሪት ያላቸው መሆኑ፣ የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ትኩረት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች በሥራ ያላቸው የተሳትፎ ደረጃ በድርጅቶች ምርታማነትና ትርፋማነት ጉልህ ልዩነት የሚያስከትል በመሆኑ፣ ይህን የተቋሙ ጥናት በሦስት ፈርጆች የሚመድብ ሲሆን እነዚህም፣
የሥራ ተሳትፎ የሚያሳዩ ሠራተኞች (Engaged) – በሥራ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ የሚያሳዩና በዚህም እርካታ የሚሰማቸው፣ እንዲሁም በሥራ ቦታ የባለቤትነት ሥነ ልቡና ያላቸው በመሆኑ ምክንያት ለሥራ አፈጻጸምና ለፈጠራ የላቀ ፍላጎት በማሳየት ድርጅታቸውን ለዕድገት የሚያበቁ ናቸው፡፡
የሥራ ተሳትፎ የማያሳዩ ሠራተኞች (Not Engaged) – ከሥራቸውና ከድርጅታቸው ጋር የሥነ ልቡና ቁርኝት የሌላቸው፣ ፍላጎታቸው ያልተሟላ በመሆኑ ምክንያት ተሳትፎ የማያሳዩ፣ እንዲሁም ለድርጅታቸው የሥራ ጊዜ የሚሰጡ ቢሆንም በራሳቸው ፍላጎትና ተነሳሽነት እምብዛም አስተዋጽኦ የማያበረክቱ ናቸው፡፡
በንቃት የሥራ ተሳትፎ የማያሳዩ ሠራተኞች (Actively Disengaged) – ፍላጎታቸው ባለመሟላቱ ምክንያት በሥራቸው ደስታ የማይሰማቸውና የጥላቻ ስሜት የሚያሳዩ፣ ደስተኛ ያለመሆናቸውን በግብር የሚገልጹ፣ እንዲሁም የሥራ ጓደኞቻቸው ለሚያስገኙት ውጤት ምንጊዜም አነስተኛ ግምት ያላቸው ናቸው፡፡
በዚህ መሠረት በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ ከተሰማሩ ሠራተኞች መካከል የሥራ ተሳትፎ የሚያሳዩ ሠራተኞች ድርሻ በዓለም አገሮች በአማካይ 65 በመቶ፣ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች በአማካይ 17 በመቶ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ስምንት በመቶ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ድርሻ ከዓለምና ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከአፍሪካ አገሮች ከፍተኛ የሥራ ተሳትፎ ካላቸው መካከል ጋና 19 በመቶ፣ ዛምቢያ 19 በመቶ፣ ኬንያ 18 በመቶ፣ ሩዋንዳ 17 በመቶና ደቡብ አፍሪካ 15 በመቶ ቅድሚያ ይዘዋል፡፡ በአንፃሩ በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ ከተሰማሩ ሠራተኞች መካከል የሥራ ተሳትፎ የማያሳዩ ሠራተኞች ድርሻ በዓለም አገሮች በአማካይ 67 በመቶ፣ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች በአማካይ 65 በመቶ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ 66 በመቶ ነው፡፡ ከዚህም ይልቅ በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ ከተሰማሩ ሠራተኞች መካከል በንቃት የሥራ ተሳትፎ የማያሳዩ ሠራተኞች ድርሻ በዓለም አገሮች በአማካይ 18 በመቶ፣ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች በአማካይ 18 በመቶ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ 26 በመቶ ያክላል፡፡
በዚህ መሠረት በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ ከተሰማሩ ሠራተኞች መካከል የሥራ ተሳትፎ የማያሳዩ ሠራተኞች ጥምር ድርሻ በዓለም አገሮች በአማካይ 85 በመቶ፣ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች በአማካይ 83 በመቶ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ 92 በመቶ ያህል ከፍተኛ ሲሆን፣ ይህም በሥራ አፈጻጸም እንዲሁም በነፍስ ወከፍ ምርታማነት አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትል መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ የሠራተኞች በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ ሥምሪትና የሥራ ተሳትፎ ከዓለምና ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች በንፅፅር እጅግ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የነፍስ ወከፍ ምርታማነትንና የሕይወት ጥራት ደረጃን ለማሻሻል የሚያስችል የሰው ሀብት ልማት ሥልት የሚያስፈልግ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በዚህ ረገድ በአገራችን የመንግሥት ተቋማት ከሚስተዋሉ ተግዳሮቶች መካከል ዝቅተኛ ክፍያ፣ የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር ሕግና መመርያ ችግሮች፣ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ የኃላፊዎች በየጊዜው መለዋወጥ፣ ተገቢ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ሥርዓት ያለመከተል፣ የሙያና የደረጃ ዕድገት ግልፅ አሠራር ያለመከተል፣ እንዲሁም በቂ የማትጊያና የማበረታቻ ሥልት ያለመኖር የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሆኖም በግል ድርጅቶች እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የሚያግዝ የሥራ አመራር ነፃነት ከመኖሩ በተጨማሪ፣ በገበያ ውድድር አፈጻጸምን ለማሻሻል የሚያስችል የሥራ ምኅዳር ማመቻቸት የሚጠበቅ ቢሆንም እንኳ በዚህ ረገድ በበርካታ የግል ድርጅቶች ያለው ሁኔታ እምብዛም ከመንግሥት ድርጅቶች የተሻለ አይመስልም፡፡ የሥራ ተሳትፎ ምርታማነትን፣ የሥራ ላይ ደህንነትንና የምርትና አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ማንኛውም ድርጅት አመች የሥራ ምኅዳር ለመገንባት ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ ይህም ለምርታማነትና ትርፋማነት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ዓይነተኛ ጥቅሞችን የሚያስገኝ ሲሆን እነዚህም፣
- ሠራተኞች በሥራ ቦታ በመገኘትና በመቆየት የበለጠ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ፣ ምርታማነትን በየጊዜው እንዲያሻሽሉ፣ እንዲሁም ረዥም ጊዜ ድርጅቱን እንዲያገለግሉ ይረዳል፣
- ሠራተኞች ምርትና አገልግሎትን በጥንቃቄ በመከወን የጥራት ጉድለትን እንዲቀንሱ ያስችላል፣
- ሠራተኞች የሥራ ቦታ ግንዛቤ እንዲያዳብሩ፣ የሥራ ቦታ ደህንነት የአሠራር ሒደቶችን በግልጽ እንዲያውቁና እንዲተገብሩ በማድረግ ለሥራ ባልደረባዎችና ለደንበኞች ደህንነት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ በዚህም የሕመምና የአደጋ ጉዳት ጥቂት እንዲሆን ያግዛል፣
- ሠራተኞች ምንጊዜም በሥራ ቦታ በመገኘት የምርትና አገልግሎት ጥራትን፣ እንዲሁም የሥራ ቦታ ደህንነትን ለማረጋገጥ ፅኑ ፍላጎት እንዲያሳዩ፣ የላቀ የደንበኛ አገልግሎት በመከወን የደንበኞች ግንኙነትን ለማሻሻልና የሽያጭ ገቢን ለማሳደግ ያስችላል፣
- ከላይ የተመለከቱ ጥቅሞች፣ የሠራተኞች በሥራ ቦታ መገኘት፣ ምርታማነትን የሚያስችል አፈጻጸም፣ የደንበኞች ፍላጎትን ለማርካት ትኩረት መስጠት፣ የአሠራር ሒደቶችንና የአፈጻጸም ሥልቶችን በጥንቃቄ መከተል በጥምር የድርጅት ትርፋማነትን በየጊዜው ለማሻሻል ያስችላሉ፡፡
የሠራተኞች የሥራ ተሳትፎ እንዲኖር የሥራ ምኅዳር ለማመቻቸት የሚያስችል አስፈላጊ ሥልትና ዕርምጃዎች ይፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ከዚህ በታች የተመለከቱ ጉዳዮችን መገንዘብ የሚያስፈልግ ሲሆን እነዚህም፣
- የሠራተኞች ተሳትፎን ማበረታታት ከመሪዎች ወይም ኃላፊዎች የሚጀምር ተግባር መሆኑን መገንዘብ፣
- የሠራተኞችን ተሳትፎና ምርታማነት የሚያሻሽል ድጋፍ መስጠት የመሪዎች ኃላፊነት መሆኑን ማወቅ፣
- በየደረጃው በሚገኙ የሥራ ክፍሎች ወሳኝና ቀጥተኛ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ሥልት መከተል፣
- በየጊዜው በሥራ አፈጻጸም ምዘና መሠረት የኃላፊዎች ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑ፣
- የሠራተኞች ተሳትፎን የሚያስችሉ ፍላጎቶችን በቅድሚያ ማሟላት የድርጅት ተልዕኮን ለማሳካት አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ፣
- የሠራተኞች ተሳትፎ በራሱ ግብ ያለመሆኑን በመገንዘብ የተሳትፎ ባህል ለሚያስገኘው ውጤት ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ያካትታሉ፡፡
በተለይ ደግሞ የሥራ አፈጻጸምን ለማሻሻል የሚያስችሉ አራት የሠራተኞች ፍላጎቶችን በማሟላት ረገድ የሥራ መሪዎች ትኩረት መስጠት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ እነዚህም መሠረታዊ ፍላጎቶች፣ የግል ፍላጎቶች፣ በቡድን የመሥራት ፍላጎቶች፣ ዕውቀትና ክህሎት የማጎልበት ፍላጎቶች ናቸው፡፡ አመቺ የሥራ ምኅዳር ምርታማነትን ለማሻሽል አስፈላጊ በመሆኑ ማንኛውም ድርጅት ከጠንካራ ጎኖች በመነሳት ይህንን ማበልፀግ ያለበት ሲሆን፣ ነገር ግን ድክመቶችን በጥንካሬ በመለወጥ የሚያተኩር የሥራ አመራር ሥልት ውጤት የማያስገኝ መሆኑን የተቋሙ ጥናት ይጠቁማል፡፡ ከዚህ በማያያዝ አመች የሥራ ምኅዳር ተልዕኮ ከክፍያ ይልቅ ሠራተኞች የድርጅታቸውን ዓላማና ተልዕኮ በውል እንዲገነዘቡና በዕውን እንዲያሳኩ ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ በማጎልበት ትኩረት የሚያደርግ በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ ማንኛውም ድርጅት አራት ሥልቶችን መከተል ያለበት ሲሆን እነዚህም፣
የመሪነት ክህሎት – የሥራ አመራርና የተግባቦት ዘዴዎችን በድርጅቱ የሥራ ክፍሎች መተግበር፣
የሠራተኞች ማበረታቻ – ሠራተኞች ከሥራ መደብ፣ ከኃላፊነት ድርሻና ከሥራ ዝርዝር የሚልቅ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ክህሎታቸውን በየጊዜው ማጎልበት፣
የሠራተኞች ተሳትፎ – ሠራተኞች በጠንካራ የሥራ ባህል በሚመሩ የሥራ ቡድኖች በመሳተፍ እርካታ እንዲሰማቸው ለብዝኃነትና የቡድን ሥራ ክብር የሚቸር የሥራ ምኅዳር ማመቻቸት፣
የሠራተኞችን ክህሎት ማጎልበት – ክፍያ አስተዋጽኦን የሚመጥንና የሥራ ዕድገት ሠራተኞች የተሻለ ከሚከውኑት የሥራ መደብ አኳያ የሚያደርግ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ሥልት መከተል፣ እንዲሁም የተግባር ሥልጠና ሠራተኞች ባላቸው ዕምቅ ኃይልና የሙያና ደረጃ ዕድገት መሠረት እንዲሆን ማመቻቸት ናቸው፡፡
የሥራ ምኅዳር ማሻሻያ ትኩረት ጉዳዮች
በአግባቡ ጥቅም ላይ ያልዋለው የሰው ሀብት በመጪው ዘመን በአገሮች የልማት ሒደት ቁልፍ ግብዓት መሆኑን በመጠቆም፣ በዚህ ረገድ አገሮች በማኅበረሰብ፣ በብሔራዊ የግልና የመንግሥት ተቋማትና በግለሰብ ደረጃ የሰው ሀብት ልማት ሥልት እንዲከተሉ የተቋሙ ጥናት ይመክራል፡፡ ይህም ሦስት ውጤቶችን የሚያስገኝ ሲሆን፣ እነዚህም በጥሩ ወይም አስደሳች ሥራ የሠራተኞች ሥምሪት ዕድገት፣ የነፍስ ወከፍ ምርታማነት ማደግና የሕይወት ጥራት መሻሻል ናቸው፡፡ በመሆኑም አገሮች እነዚህን በዕውን ለማሳካት የሚያስችሉ አስፈላጊ ድጋፎችን በግለሰብ፣ በቀጣሪ ድርጅቶች፣ እንዲሁም በማኅበረሰብ ደረጃ ማመቻቸት እንደሚገባቸው የተቋሙ ጥናት ያስገነዝባል፡፡
የግለሰብ ድጋፍ
የግለሰብ ድጋፍ በጠንካራ ጎኖች ላይ በመመሥረት ምክርና የተግባር ሥልጠና በመስጠት፣ እንዲሁም ጠንካራ ጎኖችን በመለየትና ይበልጥ በማጎልበት የሚያተኩር መሆኑን ያመለክታል፡፡ በዚህ ረገድ በቅድሚያ በትምህርትና ሥልጠና መሳተፍና አስፈላጊ የአካልና የሥነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሥራ ሥምሪት የሥራ ዝርዝር ድርሻን በጥንቃቄ በመገንዘብ ኃላፊነትን በብቃት መወጣትና ምንጊዜም የግል ክህሎትን ለማጎልበት ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም ከመደበኛ ሥልጠና በተጨማሪ በአሠልጣኞች የአንድ ለአንድ ምክር በመሳተፍ፣ ተዛማጅ መጻሕፍትን በማንበብ፣ እንዲሁም በመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ ዘዴዎች አማካይነት የግል ክህሎትን ማጎልበት አስፈላጊ ነው፡፡
የቀጣሪ ድርጅቶች ድጋፍ
የሥራ ምኅዳርን በማሻሻልና የሠራተኞችን ተሳትፎ በማጎልበት በኩል የቀጣሪ ድርጅቶች አስተዋጽኦ ወደር የለውም፡፡ በዚህ ረገድ ከመልካም ወደ ታላቅ – ለምን አንዳንድ ድርጅቶች እመርታ ያሳያሉ … እና ሌሎች አያሳዩም (From Good to Great – Why Some Companies Make the Leap …and Others Don’t) የሚል የጂም ኮሊንስ መጽሐፍ ለሥራ መሪዎች እጅግ ጠቃሚና እንዲያነቡት የሚመከር ነው፡፡ በተለምዶ ብሒል ጥሩ የታላቅ ጠላት ነው (Good is the enemy of great) የሚለው ጥቂት ብቻ ታላቅ ስኬት ያላቸው ኮርፖሬሽኖች ለመኖራቸው አንድ ቁልፍ ምክንያት መሆኑን፣ እንዲሁም ይህ የንግድ ድርጅቶች ችግር ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሰው ልጅን የሚመለከት መሆኑን ጸሐፊው ይጠቁማል፡፡ ይህ መጽሐፍ እ.ኤ.አ. ከ1965 – 1995 በአክሲዮን ገበያ የሚሳተፉና በፎርቹን 500 ዝርዝር የተካተቱ 1435 ኮርፖሬሽኖች መረጃዎችን በማጥናት፣ ከመካከላቸው 11 ለረዥም ጊዜ ታላቅ ውጤት ያስመዘገቡትን ከሌሎች አቻዎች ጋር በማወዳደር ለታላቅ ውጤት አስተዋጽኦ ያላቸው የተግባር መርሆዎችን ይጠቁማል፡፡ እነዚህ የተግባር መርሆዎች በሥራ አመራር መስክ ዘወትር ከሚቀነቀኑ ንድፈ ሐሳቦች በተወሰነ መንገድ የተለየ አቅጣጫ ያላቸው መሆኑን ይገልጻል፡፡
በእነዚህ ድርጅቶች ለረዥም ጊዜ ታላቅ ውጤት እንዲኖር ያስቻሉ ሰባት የተግባር መርሆዎችን ጥናቱ የሚለይ ሲሆን፣ እነዚህም የታላቅ መሪዎች ሚና፣ በቅድሚያ ማን ቀጥሎ ምን፣ አስከፊ እውነታን መጋፈጥ ሆኖም ለስኬት የፀና ምኞት መኖር፣ ጥርት ያለ ቀላልና ግልፅ የስኬት ጽንሰ ሐሳብ፣ ጥልቅ የሥነ ምግባር ባህል፣ የቴክኖሎጂ አስተዋጽኦና የውጤት ዑደት ኃይል ክምችት ናቸው፡፡ እነዚህ ሰባት የተግባር መርሆዎች የንግድ ድርጅቶችን ብቻ ሳይሆን ትምህርት ቤቶችን፣ ቤተ እምነቶችን፣ የመንግሥት ኤጀንሲዎችን፣ ወዘተ. ከጥሩ ወደ ታላቅ ስኬት መድረስ የሚያስችሉ መሆኑን መጽሐፉ ይጠቁማል፡፡ በመሆኑም እነዚህ የተግባር መርሆዎች በአገራችን የሥራ ምኅዳርና የሠራተኞች ተሳትፎ ላይ የሚያስከትሉትን ተፅዕኖ በሚመለከት ማብራራት አስፈላጊ በመሆኑ ከዚህ በታች በአጭር ይቀርባል፡፡
- የታላቅ መሪዎች ሚና
በእነዚህ ድርጅቶች የስኬት ሒደት የታላቅ መሪዎች አስተዋጽኦ በቅድሚያ የሚጠቀስ ሲሆን፣ ለቃለ መጠይቅ መሪዎች በሰጡት ምላሽ መሠረት በሙያ ፍላጎትና የግል ባህርይ ከሌሎች የሚለዩ መሆናቸውን ጥናቱ ያመለክታል፡፡ እነዚህ መሪዎች በሙያ ፍላጎታቸው ድርጅታቸውን ለታላቅ ስኬት ለማብቃት በሚያደርጉት ጥረት ማናቸውም አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥማቸው በፅናት የሚሠሩ፣ ለታላቅ ስኬት የሚያበቃ የአሠራር ሥልት የሚከተሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለአፈጻጸም ጉድለት በቅድሚያ ኃላፊነትን የሚወስወዱ እንጂ፣ ሠራተኞችን የውጭ ሁኔታዎችንና መጥፎ ዕድልን ምክንያት የማያደርጉ ናቸው፡፡ በተጨማሪ በግል ሰብዕናቸው ትሑት ባህርይ የሚያሳዩ፣ የግል ዝናና ዕውቅና የማይሹ፣ ከሌሎች በላይ ራሳቸውን አስፈላጊ በማድረግ የኩራት መንፈስ የማያሳዩ፣ ዝምተኛና ዓይን አፋርና እርጋታ ያላቸው፣ ከሥልጣን ይልቅ በአሠራር ደረጃ ተፅዕኖ በማሳደር ሠራተኞችን የሚያነቃቁ፣ ምትክ መሪዎችን ለማፍራትና ለላቀ ስኬት ለማብቃት የሚጥሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ለድርጅታቸው ስኬት የሠራተኞች የውጭ ሁኔታዎችና የመልካም ዕድል አስተዋጽኦ መኖሩን ዕውቅና በመስጠት የሚያመሠግኑ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር በአገራችን እንኳንስ በመንግሥት ተቋማት ይቅርና በግል ድርጅቶችም ይህ የሙያ ፍላጎትና የግል ባህርይ ያላቸው ታላቅ መሪዎች መኖራቸውን መገመት አያስቸግርም፡፡ በመሆኑም የተግባር ሥልጠናና የልምድ ልውውጥ ማዕከል በማቋቋም የከፍተኛ ሥራ አመራር ኃላፊዎችን ክህሎት ማበልፀግ አንድ የትኩረት ጉዳይ ነው፡፡
- በቅድሚያ ማን ቀጥሎ ምን?
እነዚህ ታላቅ መሪዎች በቅድሚያ ማን ቀጥሎ ምን የሚል የሰው ኃይል አመራር ሥልት የሚከተሉ ሲሆን፣ ይህም ትክክለኛውን የሰው ኃይል በትክክለኛው የሥራ መደብ ማሰማራት፣ እንዲሁም የላቀ የሥራ አስፈጻሚ ቡድን ማደራጀት ለታላቅ ስኬት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በተለይ ደግሞ ትክክለኛውን የሰው ኃይል በትክክለኛው የሥራ መደብ በማሰማራት፣ ታላቅ መሪዎች ከዕውቀትና ሥራ ልምድ በተጨማሪ ለባህርይና ዝንባሌ ትኩረት እንደሚሰጡ ይጠቁማል፡፡ የሰው ኃይል አመራር ውሳኔዎችን በሚመለከት ታላቅ መሪዎች በሦስት ሥነ ምግባር የሚመሩ ሲሆን፣ እነዚህም በሰው ኃይል ምልመላ ጥርጣሬ ሲኖር ሌሎችን መፈለግ፣ የሰው ኃይል ለውጥ አስፈላጊነትን በመገንዘብ ወቅት ወዲያውኑ ይህን መፈፀም፣ እንዲሁም የላቀ ብቃት ያለውን የሰው ኃይል ከከፍተኛ ችግር ይልቅ ከፍተኛ ዕድል ባለው የሥራ መደብ ማሰማራት ናቸው፡፡
በተለይ ደግሞ የሰው ኃይል አመራር ውሳኔዎችን ከሰብዓዊ ርህራሔ ውጪ ከመፈጸም ይልቅ በጥልቅ ሐሳብና በጥንቃቄ መምራት አስፈላጊ መሆኑን፣ እንዲሁም ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው ሠራተኞች ላይ አግባብነት ያለው ዕርምጃ መውሰድ ለድርጅታቸውም ይሁን ለሠራተኞች ጠቃሚ መሆኑን ታላቅ መሪዎች በአጽንኦት ይገልጻሉ፡፡ በአገራችን ሁኔታ አብዛኞች የሥራ ኃላፊዎች ከሰው ኃይል አመራር ይልቅ ለሥልትና ለዕቅድ ዝግጅት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በምልመላና በቅጥር ትክክለኛውን የሰው ኃይል በትክክለኛው የሥራ መደብ ከማሰማራት ይልቅ በዝምድናና በትውውቅ እንደሚከውኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ የሥራ ኃላፊዎች ለሰው ኃይል አስተዳደር የሚሰጡት ትኩረትና የሚያበረክቱት የጊዜና የጉልበት አስተዋጽኦ፣ በሒደት የሚያጋጥሙ በርካታ ችግሮችን ለመቀነስ የሚያግዝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
- አስከፊ እውነታን መጋፈጥ ሆኖም ለስኬት የፀና ምኞት መኖር
እነዚህ ታላቅ መሪዎች አስከፊ ነባራዊ እውነታን በድፍረት ለመጋፈጥ ሆኖም የሚመሩትን ድርጅት ወደ ታላቅ ስኬት ለማድረስ የፀና ምኞት ያላቸው ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በግልጽ የመናገርና የመደመጥ ዕድል የሚያመቻቹ በመሆኑ ሠራተኞች በፍላጎታቸው በመሳተፍ ለምርታማነትና ትርፋማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ በዚህ ረገድ በአገራችን አብዛኞች ድርጅቶች በግልጽ የመናገርና የመደመጥ ባህል ያለመዳበር ምክንያት ሐሜት፣ አሉባልታ፣ የውስጠ ድርጅት ፖለቲካ ከፍተኛ የሰው ኃይል ጊዜና ጉልበት እንዲባክን ከማድረግ በተጨማሪ፣ በድርጅት ምርታማነትና ትርፋማነት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትል መሆኑ ይታወቃል፡፡
- ጥርት ያለ ቀላልና ግልፅ የስኬት ጽንሰ ሐሳብ
ይህ ጃርት እና ቀበሮ (The hedgehog and the fox) ከሚል የግሪክ ጥንታዊ ምሳሌ ቀበሮ በአደን ባላት ታላቅ ዕቅድ በርካታ ተግባራት ላይ ስታተኩር፣ በተቃራኒ ጃርት ጥቃትን ለመከላከል በቀላልና ግልጽ ርዕይ ይህን አንድ ተግባር በጥንቃቄና በትኩረት በመፈጸም በኩል ከሚያሰዩት ባህርይ የሚዛመድ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በጸሐፊው ዕይታ አንድ ድርጅት በሦስት ፈርጆች ጥልቅ ግንዛቤ ላይ በመመሥረት ስትራቴጂ መንደፍ ያለበት ሲሆን፣ እነዚህም የድርጅቱን ጥልቅ ፍላጎትና ዓላማ (deep passion)፣ የኢኮኖሚ ጥቅም መሪ (driver of economic engine)፣ እና በምን መስክ ወይም ተግባር የላቀ ክህሎት ያለው (can be the best) መሆኑን ያካትታል፡፡ በዚህ ዓይነት ጥርት ያለ ቀላልና ግልጽ የስኬት ጽንሰ ሐሳብን (The Hedgehog Concept) በውል ማወቅ፣ እንዲሁም ማንኛውንም ሀብትና ጉልበት ለእዚህ ተግባር ማዋል ለታላቅ ስኬት አስፈላጊ በመሆኑ ቀላልና ግልጽ የስኬት ጽንሰ ሐሳብ የሥራ አመራር ወሳኝ ጥበብ መሆኑን ጸሐፊው አበክሮ ያሳስባል፡፡ በአገራችን የበርካታ ድርጅቶች ስትራቴጂ በቀላልና ግልጽ የስኬት ጽንሰ ሐሳብ የሚመራ ከመሆን ይልቅ ለመረዳት የሚያዳግት ውስብስብ፣ ሁለ ገብና በርካታ ተግባራትን ለመከወን የሚያተኩር፣ እንዲሁም የድርጅት አነስተኛ ሀብትና ጉልበትን ለበርካታ ተግባራት ማስፈጸሚያ በማዋል ታላቅ ስኬት ለማስገኘት የማያስችል ነው፡፡
- ጥልቅ የሥነ ምግባር ባህል
ለረዥም ጊዜ ታላቅ ውጤት ያስመዘገቡ ድርጅቶች ጥልቅ የሥነ ምግባር ባህል በመገንባት በሥነ ምግባር የታነፀ የሰው ኃይል ሥምሪት የሚመሩ፣ የድርጅቱን ዓላማና ስትራቴጂ፣ እንዲሁም ዕቅድ ዝግጅትና የአፈጻጸም ሒደትን በሚመለከት በየጊዜው በጥልቅ ሐሳብ መሠረት ግልጽ ውይይት የሚያካሂዱ፣ እንዲሁም ለታላቅ ስኬት የሚያበቁ ተግባራትን በትኩረት በመከታተል በብቃት የሚከውኑ ናቸው፡፡ በተለይም አስከፊ እውነታን በድፍረት በመጋፈጥ ሆኖም ለስኬት የፀና ምኞት በማሳየት ረገድ የእነዚህ ድርጅቶች ታላቅ መሪዎች በሚከተሉት የአሠራር ባህል ምክንያት፣ የድርጅቱን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ሠራተኞች በየጊዜው በቂ መረጃ እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ ሐሳባቸውን በግልጽ ለመናገርና ለመደመጥ የሚያስችል አሠራር የሚያመቻቹ በመሆኑ፣ ከግል ባህርይና ከሥልጣን ተፅዕኖ ይልቅ ጥልቅ የሥነ ምግባር ባህል በመከተል ለድርጅታቸው ዘላቂ ታላቅ ስኬት ያስገኛሉ፡፡ የሥራ አፈጻጸም – ተግባራትን የመከወን ሥነ ምግባር (Execution – The Discipline of Getting Things Done) በሚሰኝ ርዕስ ላሪ ቦሲዲ እና ራም ቻራን ከቻርለስ ቡርክ ጋር ያሳተሙት መጽሐፍ ከላይ የቀረበውን ማብራሪያ ይበልጥ ያጠናክራል፡፡ በመጽሐፉ ዕይታ መሠረት የሥራ አፈጻጸም ማንኛውም የሥራ መሪ ለመከወን የሚሻውና የሚመራው ድርጅት ይህን ለማሳካት ባለው አቅምና ችሎታ መካከል የሚኖረውን ክፍተት ያመለክታል፡፡ በዚህ መሠረት የሥራ አፈጻጸም ማንኛውም ድርጅት የሚከተለውን ሥልትና ሥነ ምግባርን የሚያካትት በመሆኑ፣ የሥራ መሪዎች ቁልፍ ኃላፊነት ነው፡፡ ይኸውም እንዴትና ምን በሚሉ ጥያቄዎች መነሻ በጥልቅ ሐሳብ ውይይት ማካሄድ፣ ያላሰለሰ ጥብቅ ክትትል ማድረግ፣ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ ሥልት መከተል፣ እንዲሁም ተግባራትን በብቃት ለመከወን የሚያስችሉ ዝርዝር ድርጊቶችን በመለየት ያተኩራል፡፡
የሥራ አፈጻጸም ሦሥት ዓቢይ ሒደቶች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህም የስትራቴጂ ወይም ሥልት፣ የሰው ኃይልና የትግበራ ሒደት ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ የሰው ኃይል ሒደት ከሥልትና ትግበራ ሒደቶች ጋር፣ እንዲሁም የሥልት ሒደት ከሰው ኃይልና ትግበራ ሒደት ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢኮኖሚ ሁኔታና የተወዳዳሪዎች ድርጊት ከድርጅቶች ቁጥጥር ውጭ ቢሆኑም፣ ለሰው ኃይል ጥራት ትኩረት በመስጠት መቆጣጠር የድርጅት ቅድሚያ ተግባር ነው፡፡ ይህም የሰው ኃይል ማንኛውንም ድርጅት በየዓመቱ እጅግ ከፍተኛ ውጤት ለማግኘት የሚያስችል ሀብት በመሆኑና በተለይም የሰው ኃይል ዝንባሌና አመለካከት እንዲሁም የሥራ ልምድና ክህሎት በስኬትና ውድቀት መካከል ልዩነት የሚያስከትል በመሆኑ ነው፡፡
የሥራ ኃላፊዎችን መመልመል፣ ክህሎታቸውን በየጊዜው ማዳበርና ብቁ ማድረግ የሥራ መሪዎች በውዴታ የሚፈጽሙት ተግባር እንጂ፣ በውክልና የሚያጋሩት የሥራ ሒደት ባለመሆኑ የሥነ ልቦና ተነሳሽነት ከማሳየት በተጨማሪ በቂ የጊዜና የጉልበት አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሆኖም በዚህ ረገድ በሥራ መሪዎች በኩል አስፈላጊ ግንዛቤ ቢኖርም፣ አብዛኛውን ጊዜ የሥራ መደቦች በወቅቱና በመጪው ጊዜ ምን ተግባራትን እንደሚያካትቱ፣ እንዲሁም በምን የችሎታና የክህሎት መመዘኛ የሰው ኃይል ምደባ ማካሄድ እንዳለባቸው በጥልቅ ሐሳብና በትኩረት የማይከውኑ ሲሆን፣ ይህም በሰው ኃይል አመራር ሒደት መሪዎች በቁርጠኛነት ተሳትፎ ባለማድረጋቸው ምክንያት ነው፡፡
በዚህ ረገድ በበርካታ ድርጅቶች ከሚስተዋሉ ድክመቶች መካከል በኃላፊነት የሥራ መደቦች የሚሰማራ የሰው ኃይልን አስመልክቶ በመሪዎች ዘንድ በቂ ዕውቀት ያለመኖር፣ ለሥራ መደብ የተሻለ ክህሎት ካላቸው ይልቅ ከመሪዎች የግል ሥነ ልቦና ምቾት አንፃር መመደብ፣ እንዲሁም በሥራ አፈጻጸም ምዘና መሠረት አግባብነት ያለው የሰው ኃይል ውሳኔ በመስጠት በኩል የመሪዎች ድፍረት ማጣት የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በመሆኑም ለሥራው መደብ አስፈላጊ ችሎታና ዝንባሌን በውል መገንዘብ፣ ድርድር የማይኖራቸው የምደባ መመዘኛዎችን መከተል፣ የሥራ አፈጻጸምን በየጊዜው በመከታተል ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው ሠራተኞችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣ የሰው ኃይል ምደባን በታማኝነትና የሥነ ልቦና ምቾት መመዘኛ ከመከወን መቆጠብ፣ እንዲሁም በሰው ኃይል ውሳኔዎች የመሪዎች ተሳትፎ እና የጊዜና የጉልበት አስተዋጽኦ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በሰው ኃይል ምልመላ ሒደት የሥራ መሪዎች ትኩረት መስጠት ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል የሌሎች ሠራተኞችን ተሳትፎና አፈጻጸም ማበረታታት የሚችሉ፣ ለአስቸጋሪ ሁኔታዎች ተገቢ ውሳኔ የመስጠት ችሎታ ያላቸው፣ ልዩ ልዩ ተግባራትን በሌሎች ሠራተኞች አማካይነት ለመከወን የሚችሉ፣ እንዲሁም ተግባራትንና የሠራተኞች አፈጻጸምን በየጊዜው በመከታተል አስፈላጊ ውሳኔ የሚሰጡ ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ሠራተኞችን በልዩ ልዩ ተግባራት በማሳተፍ፣ ከሌሎች ትምህርትና ልምድ እንዲቀስሙ በማመቻቸት፣ የሥራ አፈጻጸም ግልጽ ግብረ መልስ በየጊዜው በመስጠት፣ በሥራ ላይ ምክር በመለገስ፣ እንዲሁም በትምህትና ሥልጠና በማነፅ ልምድና ክህሎት እንዲያዳብሩ በማድረግ በኩል አንድ ድርጅት የሚከተለው የሰው ኃይል ልማት ሥልት የታላቅ ስኬት መሠረት ነው፡፡
በአገራችን ሁኔታ በተነሳሽነትና በትጋት ሥራን በመከወን ረገድ የዳበረ ባህል ያለመኖር፣ የሥራ መሪዎች የሠራተኞች ሥራ አፈጻጸምን በየጊዜው ያለመከታተል፣ በሠራተኞች ዘንድ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖር የሚያስችል የመረጃና ግንኙነት ሥርዓት ያለመከተል፣ እንዲሁም ሠራተኞችን በጥልቅ የሥነ ምግባር ባህል ከማነፅ ይልቅ፣ ከሥራ መሪዎች የግል ባህርይና ሥልጣን ተፅዕኖና ቁጥጥር ሥር ማድረግ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ በተለይም በመንግሥት ኃላፊዎች በኩል የፕሮጀክቶች ትግበራን አስመልክቶ በየጊዜው ክትትል ያለመኖር ምክንያት ከፍተኛ ብክነት የሚደርስ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የመንገድ ግንባታ ሒደትን ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በቅርቡ በአካል በመገኘት በሰጡት መመርያ መሠረት ግንባታው ቀንና ሌሊት እየተጧጧፈ የሚገኝ በመሆኑ፣ ነዋሪዎች ውሳኔውን በከፍተኛ አድናቆት ሲገልጹ ነበር፡፡
- የቴክኖሎጂ አስተዋጽኦ
የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የታላቅ ስኬት መመዘኛ፣ እንዲሁም በራሱ ብቻ ለስኬት የሚያበቃ አለመሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡ ሆኖም ጥርት ያለ ቀላልና ግልጽ የስኬት ጽንሰ ሐሳብ ላይ በመመሥረት፣ ማንኛውም ድርጅት አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ግብዓት በመምረጥና አግባብነት ባለው መንገድ ጥቅም ላይ በማዋል ስኬትን ማፋጠን የሚችል መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በአገራችን ሁኔታ ለምርታማነት አስተዋጽኦ ያለውን የቴክኖሎጂ ግብዓት በመምረጥና ለተገቢው ጥቅም በማዋል ረገድ ከዝቅተኛ የፋይናንስ አቅም በተጨማሪ፣ በመሪዎች ትክክለኛ ግንዛቤ ያለመዳበር ዓቢይ ተግዳሮት ነው፡፡
- የውጤት ዑደት ኃይል ክምችት
ማንኛውም ድርጅት የውጤት ዑደት ኃይልን (The Flywheel Effect) በየጊዜው በማከማቸት የስኬት ዕመርታ (Breakthrough Results) ለመድረስ በቅድሚያ ጥርት ያለ ቀላልና ግልጽ የስኬት ጽንሰ ሐሳብን በውል ለይቶ ማወቅ፣ በመቀጠል ደግሞ የድርጅቱን ሀብትና ጉልበት ለታላቅ ስኬት የሚያበቁ ተግባራት ላይ በማዋል ትኩረት ማድረግ፣ እንዲሁም ጥልቅ የሥነ ምግባር ባህል መከተል ያስፈልጋል፡፡ ይህም ሠራተኞች የድርጅቱን ዓላማና ግብ በውል በመገንዘብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በእዚህም በፍላጎታቸው እንዲሳተፉ ያስችላል፡፡
የማኅበረሰብ ድጋፍ
የማኅበረሰብ ድጋፍ የፋይናንስ አካታችነት፣ የመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ፣ የትምህርት አገልግሎት፣ የጤና ጥበቃ አገልግሎት፣ የመንገድና የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት፣ ማኅበራዊ ደህንነት፣ እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ያካትታል፡፡ እነዚህ ድጋፎች በጥምር የሰዎች የሕይወት ጥራት፣ ክህሎትና ብልፅግናን በማረጋገጥ የሥራ ተሳትፎን ለማበረታታት በዚህም የድርጅቶችን ምርታማነት ለማጎልበት ያስችላሉ፡፡ በተለይም በአገራችን የልማት ሒደት በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሻሻል ትምህርትና ሥልጠና እጅግ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ፣ የከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናን ለማሻሻል የተነደፈውን ፍኖተ ካርታ በብቃት መተግበር በርካታ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል መገመት ይቻላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡