Thursday, March 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንገዶች ባለሥልጣን የ21 መንገዶችን ጨረታ በመሰረዝ በድጋሚ ለማውጣት መገደዱን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በበጀት ዓመቱ መፈረም ከነበረባቸው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሃያ አንዱን ጨረታዎች በመሰረዝ፣ በድጋሚ ጨረታ ለማውጣት መገደዱን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ 91 የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን በመፈራረም ወደ ሥራ ለመግባት ዕቅድ የነበረው ቢሆንም፣ በዕቅዱ መሠረት ለማከናወን እንዳይችል የተለያዩ ችግሮች እንደገጠሙት ገልጿል፡፡

በበጀት ዓመቱ ግንባታቸውን ለማከናወን ካወጣቸው ጨረታዎች ውስጥ 17 ያህሉ ጨረታቸው ተሰርዞ በድጋሚ ጨረታ እንዲወጣ የተደረጉ ሲሆን፣ አራቱ ደግሞ በተመሳሳይ ተሰርዘው በድጋሚ ጨረታቸው እንደሚወጣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ማክሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ሰባት የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማስገንባት በተካሄደው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ወቅት አስታውቋል፡፡  

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር)፣ ጨረታዎቹ በዚህን ያህል ደረጃ ለመሰረዛቸው አንዱ ምክንያት ተወዳዳሪዎች አለመገኘታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሌላው ዓበይት ምክንያት ደግሞ እጅግ የተጋነኑ ዋጋዎች በመቅረባቸው ጨረታውን ለማፅደቅ ባለመቻሉ ነው፡፡

በተያያዘም ከወሰን ማስከበር ጋር  እየገጠሙ ያሉ ችግሮችና በኮንትራክተሮች ላይ እየታየ ያለው የአቅም መዳከም በሒደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን በተፈለገው ደረጃ ለማከናወን አላስቻሉም ተብሏል፡፡ ባለሥልጣኑ በአንድ የበጀት ዓመት እነዚህን ያህል ጨረታዎችን ደግሞ እንዲያወጣ የተገደደበት ሁኔታ አጋጥሞ እንደማያውቅ ተጠቁሟል፡፡

ሌሎች ተደራራቢ የሆኑ ችግሮች ስለመኖራቸው የጠቀሱት (ኢንጂነር) ሀብታሙ፣ ፕሮጀክቶችን ለኮንትራት ሰጥቶ ለማስጀመር እንዲቻል፣ የባለሥልጣኑ ቦርድ አንዳንድ መሥፈርቶችን እስከማሻሻል መድረሱንም ጠቁመዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ዘርፉ ፈተና ውስጥ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑ ተገልጿል፡፡  

በመንገዶች ግንባታዎች የሚታዩ ችግሮች በበጀት ዓመቱ የኮንትራት ውላቸው ይፈረማል የተባሉ ፕሮጀክቶችን፣ በዕቅዱ መሠረት እንዳይከናወኑ እያደረጉ መሆናቸው ተወስቷል፡፡ ‹‹እስካሁን ድረስ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም ዕቅድ ይዘን ስንሠራ ነበር፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹በበጀት ዓመቱ ለኮንትራክተሮች እንዲተላለፉ ካወጣናቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ‹‹17 ያህሉ በድጋሚ ጨረታ ለማውጣት ተገደናል፤›› ብለዋል፡፡ በአራቱ ደግሞ ድጋሚ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ይህ ትልቅ መልዕክት ያለው ነው፤›› ያሉት ሀብታሙ (ኢንጂነር)፣ በተለይ ለጨረታዎቹ መደናቀፍ ምክንያት እየሆኑ ካሉት ውስጥ የወሰን ማስከበር ችግር አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡ ‹‹ባለፉት ሁለት ዓመታት ብዙ ስንጮህበት የነበረ ቢሆንም ችግሩ ባለመቀረፉ፣ አሁን ግን  ትልቅ ችግር እየሆነ ነው፤›› በማለት የማቴሪያል አቅርቦትና የፀጥታ ችግርም ከዚሁ ችግር ጋር የሚያያዝ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቶች በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች ያሉ የታች አመራሮች ድጋፍ አለማድረግ፣ እየገጠሙ ላሉ ችግሮች ምክንያት መሆኑ ከዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የግዥ ጉዳዮች የከፋ ተግዳሮት ሆነዋል፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ እስካሁን 36 ፕሮጀክቶች መፈረም እንደነበረባቸው፣ ሆኖም እስካሁን የተፈረሙት 15 መሆናቸው የችግሩን ስፋት ያሳያል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ነገር ግን በቅርብ ጊዜ ውስጥ 25 ፕሮጀክቶችን እንፈራረማለን፡፡ 25 የሚሆኑት ደግሞ ሒደት ላይ በመሆናቸው ወደ 50 የሚደርሱ ፕሮጀክቶችን ለመፈረም እየተሠራ ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ እንደ ችግር የሚታዩ ሌሎች ጉዳዮችንም አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች