Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከኃላፊነታቸው የለቀቁባቸውን ምክንያቶች አስታወቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ከሃያ ዓመታት በላይ የመሩት አረጋ ይርዳው (ዶ/ር)፣ ከሚያዝያ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነት መልቀቃቸውን በደብዳቤ አስታወቁ፡፡ ለመልቃቸው ምክንያት የሆኑ አራት ምክንያቶችን አቅርበዋል፡፡ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ አል አሙዲ፣ መልቀቂያቸውን በመቀበል ሚያዝያ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. የስንብት ደብዳቤ ጽፈውላቸዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከእሳቸው ጋር የአክሲዮን የባለቤትነት ድርሻ የያዙበትን ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩ መሆኑን፣ በእሳቸው ቦታ የኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌታቸው ሐጎስን በጊዜያዊነት መሾማቸውን ሼክ አል አሙዲ አስታውቀዋል፡፡

አረጋ (ዶ/ር) ለነበራቸው ቆይታ ምሥጋና አቅርበው እስካሁን በየዕለቱ በሥራቸው ያጋጥሟቸው የነበሩ ተግዳሮቶችን በከፍተኛ ሙያዊ ኃላፊነትና ግብረ ገብነት ሕግን መሠረት በማድረግ፣ ራሳቸውን ከሠራተኞች በላይ ሳያደርጉ መወጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በየአቅጣጫው ከሚያጋጥሙ ፈተናዎች በተጨማሪ፣ ራሳቸውን በሚድሮክ ላይ የሾሙ ባሉዋቸው በስም ባልገለጹዋቸው ግለሰቦች በሚፈጸሙ የእጅ አዙር ጫናዎች ክብራቸውንና ኃላፊነቶቻቸውን የሚፈታተኑ ድርጊቶች ሲከናወኑ፣ እሳቸውና የማኔጅመንት አባሎቻቸው ጭምር በትዕግሥት ሲመለከቱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

‹‹ሕግን መርህ ላደረገ ሠራተኛ እንዲህ ዓይነት ጫና አስቸጋሪ ፈተና መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ውጤቱም ችግር ይኖረዋል፤›› ብለው፣ ከላይ የተገለጸው እንዳለ ሆኖ በዓበይት ጉዳዮች ላይ የደረሱ ጫናዎችን ከማገዝ ፈንታ ይባስ ብሎ አሉታዊ ጫናዎች እየተፈጠሩ መሥራት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ ‹‹መሥራትና ውጤታማ መሆን አዳጋች ስለሆነብኝ አሁን ያለውን የሥራ ኃላፊነቴን መተውና በሌላ መስክ አገሬን ለማገልገል መወሰኔን ስገልጽ በልዩ ስሜት ነው፤›› ሲሉ፣ ለመልቀቅ የወሰኑባቸውን አራት መሠረታዊ ምክንያቶች በደብዳቤያቸው አሥፍረዋል፡፡

በምክንያትነት ካነሱዋቸው የመልቀቂያ ሐሳቦች መካከል አንደኛ የሁዳ ሪል ስቴት ኩባንያ ጉዳይ ነው፡፡ አረጋ (ዶ/ር) በደብዳቤያቸው ለሼክ አል አሙዲ፣ ‹‹የሁዳ ሪል ስቴት ኩባንያን ሕጋዊ አቋም በሚሸረሽር መንገድ ሕጋዊ ያልሆነና ክብር የሚነካ ተግባር፣ በሕጋዊነት የሁዳ መሪዎች ወይም ሠራተኞች ባልሆኑ የሥራ ባልደረቦችዎ በተከታታይ ሥራዬ እንዲታወክና እንዳይመች በመደረጉ ይህም እንዳስቸገረኝ፣ ለእርስዎ ላቀረብኩት የመመርያ ይሰጠኝ መልስ በማግኘት ፈንታ ሁኔታው እየተባባሰ እንዲሄድ መሆኑ፤›› ሲሉ የመጀመርያውን ምክንያት ጠቁመዋል፡፡

‹‹በሚድሮክ ወርቅ ዙሪያም እነዚሁ ተዋንያን ሚድሮክ ወርቅና እኔ ያልተቋረጠ ልዩ አግባብ ያለው ጥረት ከመንግሥት ጋር በምናደርግበት ወቅት ዕገዛ ከማድረግ ይልቅ፣ ተጨማሪ ተግዳሮት በመፍጠርና ጣልቃ በመግባት ተገቢው ድጋፍ ከባለሀብቱ እንዳናገኝ የሚደረገው አላስፈላጊ ሥራ ስላስቸገረኝ፤›› በማለት ሁለተኛውን ምክንያት አስታውቀዋል፡፡

‹‹በኤልፎራ ኩባንያ በተለያዩ የእርሻ ሥራ (በተለይም በሻሎ) ሥምሪታችን፣ ሥራ በተቸገሩ ወጣቶች የመሬት ስጡን ጥያቄ ሥራችን ሲስተጓጎል ኖሯል፡፡ ለጥያቄዎቹ የኤልፎራ ማኔጅመንትና እኔ ከካርታ ይዞታ ውስጥ መሬት ቆርሶ መስጠት የእኛ ሥራ ሳይሆን የባለሀብቱ ውሳኔ መሆኑን ለዓመታት ብናስረዳም፣ ባለሀብቱ እንዳይሰጡን ማኔጅመንቱ ነው በማለት ብዙ ትንኮሳዎችንና ችግሮችን ማኔጅመንቱ አሳልፏል፤›› ያሉት አረጋ (ዶ/ር)፣ ‹‹በመጨረሻም ከይዞታ ቀንሶ መሬት የመስጠት ጥያቄ ለእኛ ሳይሆን ለባለሀብቱ መቅረብ ያለበት መሆኑን በተደጋጋሚ ባለመሰልቸት ስላሳሰብን፣ ይህንንም በመጨረሻ የመንግሥት ተቋማት አምነውበት ጥያቄውን በስምዎ በተጻፈ ደብዳቤ አቅርበዋል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ፍትሐዊ ውሳኔ ከእርስዎ ብቻ የሚጠብቁ ስለሆነ መልስ በእኔ በኩል መስጠት ተቀባይነት እንደማያስገኝ ያቀረብኩልዎትን ሐሳብ በበጎና በዘላቂ መንገድ ስላልተቀበሉት በማዘን፣ የወጣቶቹ ጥያቄ በመንግሥትና በእርስዎ በኩል ካልተመለሰ ለወደፊቱ ሥራ መሥራት እንደማይቻል የ15 ዓመት ልምድ ስላለኝና አሁንም እምነቴ በመሆኑ ከእኔ የተሻለ አመራር ጉዳዩን እንዲፈጽም ራሴን ማግለል አማራጭ መሆኑን በማመን፤›› ሲሉ ሦስተኛውን ምክንያት አቅርበዋል፡፡

በአራተኛነት ያነሱት ሌላው ምክንያት ደግሞ፣ ‹‹ለትምህርት ያለኝን ልዩ ትኩረት በመገንዘብ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ መሳተፍ መቻሌን በልዩ ፀጋ ተቀብዬ የቀረውን የሕይወት ዘመኔን በትምህርት ዓለም ውስጥ ማሳለፍ ብችል ለአገሬ አስተዋጽኦ ማድረግ ምኞቴ መሆኑን ስገልጽ፣ እርስዎም ለትምህርት ያለዎትን በጎ አስተሳሰብ በመገንዘብና ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲም በአክሲዮን በሁለታችን በመሆኑና አሁንም በፕሬዚዳንትነት እየመራሁት ስለሆነ በዚሁ ብቻ የመቀጠል ፍላጎት ስላለኝ፣ ይህ ቢመቻች መልካም መሆኑን በማመን ውሳኔዎን እጠባበቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ለ25 ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑበትን ኃላፊነታቸውን በመተው 26ኛውን ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የሼክ አል አሙዲንን መልካም ፈቃድ ጠይቀዋል፡፡

ሼክ አል አሙዲ በጻፉላቸው ከኃላፊነት የመነሳት ስንብት ደብዳቤ ዕድሜያቸው ከፍ ያለና ዕረፍት እንደሚያስፈልጋቸው መገንዘባቸውን በማስታወቅ፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዳቃታቸውና ሥራ ለመሥራት እየፈሩ መሆኑን በስልክ እንደ ገለጹላቸው አስታውሰዋል፡፡

‹‹ስለሆነም እስካሁን ላበረከቱት አገልግሎት እያመሠገንኩ ከሚያዝያ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሥራ ኃላፊነትዎ በስተቀር ከሁሉም የሚድሮክ ግሩፕ ኃላፊነትዎ፣ እንዲሁም ከሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኤግዘኪዩቲቭ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሥራ ኃላፊነትዎ እንዲሰናበቱ የወሰንኩ መሆኑን እየገለጽኩ በእጅዎ የሚገኙ ማናቸውም ሰነዶችና ንብረቶች፣ እንዲሁም ቀጣይነት ያላቸውን ሥራዎች ለአቶ ጌታቸው ሐጎስ እንዲያስረክቡ መወሰኑን አስታውቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡ የሚድሮክ ኢትዮጵያ እህት ድርጅቶች በጊዜያዊነት ለተሾሙት አቶ ጌታቸው ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አረጋ (ዶ/ር) በሼክ አል አሙዲ በማናቸውም የኢትዮጵያ  ባንኮች ውስጥ የተከፈቱ የባንክ ሒሳቦችን በሙሉ ከሰኞ ሚያዝያ 19 ቀን ጀምሮ እንዳያንቀሳቅሱ በማስታወቅ፣ ለቀሪ ሕይወታቸው መልካም በመመኘት አሰናብተዋቸዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች