Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበለት የምርጫ ውሳኔ ሐሳብ ላይ ለውሳኔ ሊሰበሰብ ነው

ፓርላማው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበለት የምርጫ ውሳኔ ሐሳብ ላይ ለውሳኔ ሊሰበሰብ ነው

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጪው ነሐሴ ወር ሊካሄድ ታስቦ የነበረውን አጠቃላይ ምርጫ በተመለከተ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ መክሮ ውሳኔ ለማሳለፍ፣ ሐሙስ ሚያዚያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ይሰበሰባል።

ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አንድ የሪፖርተር ምንጭ እንደገለጹት፣ የፓርላማው ስብሰባ የሚያተኩረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮ አጠቃላይ ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በመጪው ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ለማካሄድ እንደማይችል በመግለጽ፣ ፓርላማው ውሳኔ እንዲሰጥበት ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ ለመወሰን ነው።

በዚሁ መሠረት ምርጫ ቦርድ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫውን ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ማካሄድ እንደማይችል ያቀረባቸውን ዝርዝር ምክንያቶች፣ እንዲሁም ቦርዱ ለፓርላማው የመፍትሔ ውሳኔ መነሻ ከሆነ ብሎ ያሰናዳውን በዳሰሳ ጥናት ላይ የተመሠረተ የቢሆን መፍትሔ አማራጭ በምክር ቤቱ በአካል ተገኝቶ እንደሚያቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን በሌላ ጊዜ ለማካሄድ በመፍትሔ አማራጭነት የሚያቀርባቸውን ሐሳቦች ምክር ቤቱ ካዳመጣ በኋላ፣ በሕገ መንግሥቱ ዓውድ ውስጥ ተገቢ የሚሆነው ሕጋዊ ውሳኔ ሊወሰን እንደሚችል ይጠበቃል።

 የፓርላማው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት በመጪው ሐሙስ መደበኛ ስብሰባ እንደሚካሄድ ለሪፖርተር የገለጸ ቢሆንም፣ ውይይት ስለሚደረግበት አጀንዳ ግን መረጃ እንደሌለው አስታውቋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መግለጫ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት በፈጠራቸው ተግዳሮቶች፣ እንዲሁም በዚህ ምክንያት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ባወጧቸው ክልከላዎች ምክንያት ምርጫውን በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ማከናወን እንደማይችል ማስታወቁ ይታወሳል።

በዚህ የተነሳም ለምርጫው የተዘጋጀውን የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ መከናወን ያለባቸው የምርጫ ዝግጅት ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ መወሰኑ አይዘነጋም። በማከልም በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው ድንጋጌ መሠረት በሥራ ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥልጣን ጊዜው ከሚያበቃበት አንድ ወር አስቀድሞ ቦርዱ አጠቃላይ ምርጫውን ማድረግ የማይችል መሆኑን ሕዝብ ተገንዝቦ፣ ውሳኔ እንዲሰጥበት ምክረ ሐሳብ እንዳቀረበም በዚሁ በመግለጫው ማመልከቱ እንዲሁ።

 ምርጫ ቦርድ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምክር ቤቱ የሥልጣን ጊዜው ከማብቃቱ በፊት ውሳኔ እንዲሰጥበት የጠየቀው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58(2) መሠረት የምክር ቤቱ የሥልጣን ዘመን አምስት ዓመት በመሆኑና በሥራ ላይ ያለው ምክር ቤት የሥልጣን ዘመን በዚሁ ድንጋጌ መሠረት በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የሚጠናቀቅ በመሆኑ ነው።

የምክር ቤቱ የሥልጣን ዘመን ከማብቃቱ በፊት አጠቃላይ ምርጫ ተካሂዶ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ሥልጣን የሚይዘው አዲስ ምክር ቤት ካልታወቀ፣ በአሁኑ ወቅት ሥልጣን ላይ የሚገኘው ምክር ቤትም ሆነ በእሱ የተመሠረተው መንግሥት በሥልጣን ላይ መቀጠል የማይችሉ በመሆናቸው የሥልጣን ክፍተት እንደሚያጋጥም የሕግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ደግሞ በየአምስት ዓመቱ አጠቃላይ ምርጫ እንደሚካሄድ ካስቀመጠው ድንጋጌ ውጪ ምርጫ ማከናወን የማይቻልበት ከአቅም በላይ የሆነ እክል ቢያጋጥም ምርጫ ማራዘም ስለሚቻልበት፣ ወይም የሥልጣን ክፍተቱ እንዴት ሊሞላ እንደሚችል የሚያስቀምጠው ድንጋጌ አለመኖሩን ያስረዳሉ።

 በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫ ለማካሄድ ሲባል በሥራ ላይ ያለውን ፓርላማ የሥልጣን ዘመን ከማብቃቱ በፊት እንዲበተን የውሳኔ ሐሳብ በማቅረብ፣ በምክር ቤቱ በሚሰጠው ውሳኔ ምክር ቤቱ የሚበተንበት ሥነ ሥርዓት ተደንግጓል።

 በዚህ መንገድ ምክር ቤቱ በተበተነ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንደሚካሄድና በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ምርጫውን ከማስፈጸምና የዕለት ተዕለት አገር የማስተዳደር ተግባር ውጪ፣ ሕግ ማውጣትም ሆነ መሻር እንደማይችል በዚሁ አንቀጽ ሥር ባሉ ንዑስ አንቀጾች ተደንግጓል።

አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች ይኼንን አንቀጽ በመጠቀም አሁን ያጋጠመውን ሁኔታ ማለፍ እንደሚቻል ቢገልጹም፣ ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች በበኩላቸው ይህ አንቀጽ የተቀመጠው በምርጫ የተመሠረተ መንግሥት የሥልጣን ዘመኑ ጅማሮ ወይም መካከል ላይ ቅቡልነቱን ቢያጣ አዲስ ምርጫ (Snap Election) ለማካሄድ እንጂ፣ የምርጫ ጊዜን ለማራዘም እንዳልሆነ ይከራከራሉ። የተለየ ሐሳብ የሚያንፀባርቁ የሕግ ባለሙያዎች በበኩላቸው አሁን በተፈጠረው የቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ፣ ለተጨማሪ ስድስት ወራት እንዲራዘም በማድረግ ምርጫው እንዲገፋ ማድረግ እንደሚቻል ይገልጻሉ።

እነዚህ ባለሙያዎች ይህንን አማራጭ የሚያነሱት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ማድረግ፣ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት (ከአራት አንቀጾች ውጪ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስኪያበቃ ድረስ ተፈጻሚነት እንዳይኖረው የሚያደርግ ውጤትን የሚያስከትል በመሆኑ ነው። ነገር ግን ይህ ሐሳብ በሌሎች የሕግ ባለሙያዎች ተቀባይነት የለውም።

ምክንያቱ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንድ የገጠመን እክል ለማለፍ ጥቅም ላይ የሚውል እንጂ፣ ምርጫን ለማራዘም የሚሠራ አለመሆኑንና ሥልጣንን ያላግባብ እንደ መጠቀም እንደሚቆጠር ይገልጻሉ።

አሁን ከምርጫው ጋር ተያይዞ የገጠመው ችግር የሕገ መንግሥቱ ውስንነት መሆኑን አምኖ መቀበል እንደሚያስፈልግ፣ ምርጫውን ለማራዘም ሌሎች የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎችን እንደ አማራጭ መጠቀም ድንጋጌዎቹን ከመሠረታዊ ዓላማቸው ውጪ ሥልጣን ለማራዘም እንዲውሉ ማድረግ መሆኑን፣ ይህንን ማድረግም ‹‹ሥልጣንን ያላግባብ እንደ መገልገል (Abuse of Incumbency) ይቆጠራል›› ይላሉ፡፡

በመፍትሔነት የሚያነሱት ደግሞ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 58(2) ማሻሻል ነው፡፡ ሚዛን የሚደፋ ከሆነ የተባለውን አንቀጽ ለማሻሻል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 105(2) መሠረት የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ ማሻሻያውን በሁለት – ሦስተኛ ድምፅ ማፅደቅ፣ እንዲሁም ከዘጠኙ ክልሎች የክልል ምክር ቤቶች ሁለት – ሦስተኛዎቹ ማሻሻያውን በአብላጫ ድምፅ ማፅደቅ ይኖርባቸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...