Friday, December 8, 2023

ኮሮና ቫይረስን ለመግታት የሚፈለገው ትብብር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኮሮና ኖቭል ቫይረስን (ኮቪድ-19) የትኛውም አገር ብቻውን መከላከል አልተቻለውም፡፡ ኃያላኑም ሆኑ ደሃ አገሮች ወረርሽኙን ለመከላከል የአገር ውስጥና የውጭ ዕርዳታን አጣምረው ለመሥራትም ተገደዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትም ወረርሽኙን ለመከላከል ብሎም ለማስቆም አገሮች በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ይመከራል፡፡ ትብብር ሲባል ደግሞ ለሕክምና ግብዓት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ብቻ መጋራት ሳይሆን፣ በሽታውን ለመከላከል የተቀመጡ መፍትሔዎችን መተግበርንም ይመለከታል፡፡

ከ190 በላይ አገሮችን ያሸማቀቀውን ወረርሽኝ ተባብሮ ለመወጣት፣ ያላቸው አገሮች ወደ ሌላቸው አገሮች ቁሳቁሶችና የሕክምና ባለሙያዎችን እየላኩ በሚገኙበት፣ ሁኔታ በየአገሮቹ የሚታዩ መዘናጋቶች ዋጋ ሊያስከፍሉ እንደሚችሉ የሚናገረው የዓለም ጤና ድርጅት፣ አገሮች እርስ በርስ ከመረዳዳት ባለፈ፣ በሽታውን ለማቆም መፍትሔ ተብለው የተቀመጡትን እንዲተገብሩ በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ቤት ውስጥ መቀመጥ፣ እጅን በሳሙናና በውኃ መታጠብ፣ ማስነጠስ፣ ማሳልና ትኩሳት ካለ ወደ ሕክምና መሄድ፣ በተቻለ መጠን አፍና አፍንጫን መሸፈንና ሌሎች የጥንቃቄ መንገዶችን መተግበር እንደሚገባ በተደጋጋሚ ቢነገርም፣ ከአቅምም ሆነ ከግንዛቤ ማጣት እነዚህ ተሟልተው ሲተገበሩ አይስተዋሉም፡፡ በተለይ በአፍሪካና በሌሎች ታዳጊ አገሮች ቅድመ ጥንቃቄውን ለመተግበር የኢኮኖሚ ማነቆዎች አሉ፡፡ ባደጉት አገሮች ደግሞ ጉዳዩ ከመብትና ካለመታዘዝ ጋር ተያይዞ ችግሩ እየተስተዋለ ነው፡፡

በሠለጠኑና ባደጉ አገሮች ደግሞ ሕዝቦች ከቤት የመውጣት ነፃነታቸውን በእጅጉ ናፍቀዋል፡፡ አሜሪካ ብትወሰድ እንኳን በአንዳንድ ግዛቶቿ ያሉ ሕዝቦች ቤት ውስጥ መቀመጥ ላይ የተጣለ ገደብ እንዲነሳላቸው ጠይቀዋል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የአሜሪካ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ የታገዱ እንቅስቃሴዎችን ገደብ እንደሚያነሱ አስታውቀዋል፡፡

ኮሮና ቫይረስን ለመግታት የሚፈለገው ትብብር

 

የሕክምና ባለሙያዎች ቫይረሱን ለመከላከል የሚቻለው የሕዝብ እንቅስቃሴንና ስብሰባን በመግታት እንደሆነ ቢያሳውቁም፣ ትራምፕ ይህንን እምብዛም አልተቀበሉትም፡፡ ይልቁንም በከፍተኛ ሙቀትና በወበቅ በሽታው ሊመከት እንደሚችል በመናገር ሕዝቡ እንዲዘናጋ በር ከፍተዋል፡፡

ትራምፕ በዚህ ንግግራቸውና የተዘጉ እንቅስቃሴዎችን እከፍታለሁ በማለታቸው በተለይ ከዴሞክራቶቹ የሰላ ትችትን አስተናግደዋል፡፡

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ ምንም መደናገጥ አይገባም፣ ሁሉም ነገር በቁጥጥር ሥር ነው ብለው ጥር ማብቂያ ላይ በተናገሩ ማግሥት፣ ከአገሪቱ ግዛቶች በተለይ ኒውዮርክ በቫይረሱ ክፉኛ መጠቃቷ፣ ትራምፕ ከተተቹባቸው ጉዳዮች ከቀዳሚዎቹ ነበር፡፡ ለቫይረሱ ቦታ አለመስጠታቸው አሜሪካን ዋጋ አስከፍሏታል፡፡

እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ከቀኑ 10 ሰዓት ድረስ በአሜሪካ 988,469 በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ማዕከል መረጃ መሠረት ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ 56,253 ሲሞቱ፣ 111,583 ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል፡፡ በየግዛቶቹ የተወሰዱ ዕርምጃዎች በሽታውን ለመቆጣጠር የነበራቸው ሚና የጎላ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም የሥርጭቱን መጠን ለመቀነስ ችለዋል፡፡

ኒውዮርክ የመንቀሳቀስ ገደብን ወረርሽኙ ከመስፋፋቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብላ  ጥላ ቢሆን ኖሮ፣ ከ50 እስከ 80 በመቶ ሞትን ማስቀረት ትችል እንደነበር የገለጸው ሲኤንኤን፣ ሲያትል ይህንን በማድረጓ ሥርጭቱን መቆጣጠር መቻሏን አመልክቷል፡፡

በዓለም ከፍተኛው ሥርጭትና ሞት በአሜሪካ ቢመዘገብም ትራምፕ በግዛቶች ላይ የተጣለውን ገደብ እንደሚያነሱ ተናግረዋል፡፡ ከአንዳንድ ግዛቶች ተቃውሞ ቢገጥማቸውም፣ የእሳቸውን ሐሳብ የደገፉም አልታጡም፡፡ እሳቸውን ደግፈው ሠልፍ የወጡ ዜጎችም ቤት ውስጥ መቀመጥ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል፡፡

የሕክምና ባለሙያዎችም ሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት የትራምፕን ንግግር አይቀበሉትም፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ጥንቃቄ ያልታከለበት የገደብ መነሳትና ማኅበራዊ ቅርርብ ወረርሽኙን የከፋ ያደርገዋል ብሏል፡፡ ይህንን ተከትሎ አገሮች ገደብ የማንሳት አካሄዳቸውን ቀስ በቀስ ለማድረግ ወስነዋል፡፡ የአውሮፓ አገሮችም በሒደት ገደብ እንደሚያነሱ አሳውቀዋል፡፡

በዓለም በመሪ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ በመያዝ ቀዳሚ የሆኑት የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ ከቫይረሱ አገግመው ወደ ሥራ ሲመለሱ በሰጡት መግለጫ፣ የኮሮናን ወረርሽኝ ለመግታት የተቀመጡ ሕጎችን ማላላቱ ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ መክረዋል፡፡

አካላዊ ርቀትን አሁን ላይ ማላላት አደገኛ ሊሆን እንደሚችል፣ ከቫይረሱ ለመዳን ያሉት መፍትሔዎች ከባድ ቢሆኑም፣ ይህንን ማድረግ ግድ እንደሚልም ተናግረዋል፡፡

ከ21,000 በላይ ሰዎች በሞቱባት እንግሊዝ፣ አዲስ ከሚመዘገቡና ከሚሞቱ በተጨማሪ ኢኮኖሚው ሊደቅ እንደሚችል ቢነገርም፣ ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሕክምና ባለሙያዎችና ሕዝቡ እየከፈሉ ያሉትን መስዋዕትነት ዋጋ እንዲኖረው በቤት ውስጥ መቆየቱ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

በእንግሊዝ የተጣለው የመንቀሳቀስ ገደብ ዳግም የሚከለሰው ሚያዝያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲሆን፣ በዚህን ጊዜ የተወሰኑ ገደቦች ሊላሉ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ለመቆጣጠርና ብሎም ለማጥፋት ከአገር እስከ ግለሰብ የዕርዳታ እጁን እየዘረጋ ይገኛል፡፡ ቻይና፣ ኩባ፣ ሩሲያና ሌሎች አገሮች የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ የሕክምና ቁሳቁሶችን ቫይረሱ ወደበረታባቸው አገሮች እየላኩ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ አገሮች ክትባት ለማግኘት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ለክትባቱ መሞከሪያ ራሳቸውን በበጎ ፈቃደኝነት የሰጡ ግለሰቦችም በርካታ ናቸው፡፡ ከሳይንስ እስከ ባህል ሕክምና ዘርፍ የተሰማሩ ቫይረሱን ለማጥፋት እየተረባረቡ ሲሆን፣ የኢኮኖሚ ውድቀት እንዳይበረታም ዓለም አቀፍ ባንኮችና አበዳሪዎች ዕርምጃ እየወሰዱ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ደግሞ ከዚሁ ጎን ለጎን በግለሰቦች ዘንድ ሊወሰዱ የሚገቡ ጥንቃቄዎች ቀዳሚውን ሥፍራ ስለሚይዙ፣ ሕዝቦች የበሽታው ቀዳሚ መድኃኒት የሆነውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -