Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርከወረርሽኙ በስተጀርባ የሚሰሙ ጉዶች

ከወረርሽኙ በስተጀርባ የሚሰሙ ጉዶች

ቀን:

በጌዲዮን ካሌብ

‹‹ያም ሲያማ እከሌ ለእኔ ብለህ ስማ…›› የሚባለው ዕድሜ ጠገብ ብሂል ለዚህ ዘመን ጭምር የሚያገለግል ስለመሰለኝ፣ ከዓለም ዙሪያ መሰንበቻውን የቃረምኩትን ለአንባብያን ማቃመስ ፈለግኩ፡፡ ኮሮና ቫይረስ ዓለምን ሽብር ውስጥ ከቶ ትርምስ ሲፈጠር በፍርኃት መቆራመድ ሳይሆን መፍትሔው፣ አስፈላጊዎቹን የጥንቃቄ መመርያዎች እየፈጸሙ በጎን የሚባሉ ነገሮችን መከታተል ተገቢም ግዴታም ነው፡፡ ‹‹እሳት ከሌለ ጭስ የለም›› እንደሚባው፣ ጥሬውን ከብስሉ ለመለየት ለመረጃ ቅርብ መሆን ያስፈልጋል፡፡

ከአሜሪካ በስተቀር በዓለም የጤና ድርጅት አስተባባሪነት በርካታ አገሮችና የምርምር ተቋማት ቫይረሱን ለመመከት የሚረዳ ክትባት ለመሥራት ሲተባበሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ትርፍና ሌላ ድብቅ ዓላማ ያላቸው ኃይሎች ደግሞ አስፈሪ ሆነው ብቅ ብለዋል ሲባል ለምን ብሎ መጠየቅ የግድ ይሆናል፡፡ ዓለም በሴራ ንድፈ ሐሳብ ተንታኞች የስንግ ተወጥራ በተያዘችበት በዚህ አስጨናቂ ጊዜ፣ ነገሮችን በሰከነ መንገድ ለመመርመርና ራስን ከማናቸውም ጥቃቶች ለመከላከል ብቁ ሆኖ መገኘት ያዋጣል፡፡ ፈጣሪ ከእንስሳት የተሻለ አዕምሮ የሰጠን የሰጡንን ሁሉ አምነን ለመቀበል ሳይሆን፣ መርምረን የተሻለውን እንድንመርጥ ነው፡፡ ‹‹ሁሉንም መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› እንዲል መጽሐፉ፡፡ 

- Advertisement -

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ በየአገሩ ያሉ አምባገነኖች የኮሮና ወረርሽኝን እንደ መሣሪያ ሊጠቀሙበት ይችላሉ ብለው ሲያስጠነቅቁ፣ የሴራ ንድፈ ሐሳብ ተንታኞች ደግሞ የዓለም ገዥ ለመሆን የሚፈልጉ የድብቁ ዓለም ሰዎች ከምድረ ገጽ ሊያጠፉን እያሴሩ ነው እያሉ ናቸው፡፡ በዳርዊናዊያን አስተሳሰብ በመመራት በምድር ላይ ከሚኖሩ ፍጡራን አላስፈላጊ ናቸው የተባሉትን በቫይረስ ለማስወገድ፣ የዓለም ሥርዓትን በሚፈልጉት መንገድ ለማዘጋጀት ሰይጣናዊ ተልዕኮ ጀምረዋል ሲሉ ይከሳሉ፡፡ ወትሮ ከሚታወቁት አምባገነኖች በበለጠ የሰው ልጆችን መብቶች በመግፈፍ ፍርኃት እያነገሡ፣ ምድራዊ የበላይነትን በመቆጣጠር እንደፈለጉ ሊጫወቱብን ነው ይህንን ቫይረስ የፈበረኩት ይላሉ፡፡

ሁሌም ቢሆን ሕዝቦችና መንግሥታት ዓይጥና ድመት ሆነው በሚኖሩበት በዚህ ዓለም፣ ኮሮና ቫይረስ ከገዳይነቱ በተጨማሪ መጪውን ጊዜ ጭምር የበለጠ ሥጋት እንዲያጠላበት እያደረገ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከመንግሥታት በተጨማሪ የታዋቂ ሰዎች ስም እየተነሳ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ከዓመታት በፊት ማይክሮ ሶፍት ዊንዶው ለዓለም ያስተዋወቀው ቢል ጌትስ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ክትባት ጋር በተያያዘ በሚሰጣቸው መግለጫዎች በብዙዎች ዘንድ በጥርጣሬ ስሙ የሚነሳው ቢሊየነሩ ጌትስ፣ ባለፈው ሳምንት ዘ ኢኮኖሚስትና ዘ አፍሪካ ሪፖርት ላይ በሰጣቸው አስተያየቶቹ ምክንያት መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

ቢል ጌትስ ኮኮሮና ቫይረስ መከሰት ወዲህ በዓለም ዋናው ተዋናይ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ለምን መነጋገሪያ ሆነ? እ.ኤ.አ. በ2015 ዓለምን የሚያስጨንቅ ቫይረስ ስለሚፈጠር ከወዲሁ ዝግጅት መደረገት አለበት ብሎ ማሳሰቢያ የሰጠበት ቪዲዮ በቅርቡ ለዕይታ ከቀቀረበ ወዲህ፣ እሱ ሳይንቲስት ወይም የሕክምና ባለሙያ ሳይሆን ስለኮሮና ቫይረስ ክትባት አስፈላጊነት በተደጋጋሚ መግለጫ መስጠቱ ጥያቄ እያስነሳበት ነው፡፡ እሱ ዋና ዓላማው ሀብት ማካበት ስለሆነ ቀደም ብሎ የተዘጋጀበትን ቫይረስ፣ አሁን በክትባት ስም ትርፍ ሊያጋብስበት ተነስቷል ከሚሉት ጀምሮ ፈጣሪን ለመፈታተን ሰይጣናዊ ድርጊት ውስጥ ገብቷል እስከሚሉት ድረስ በርካታ አወዛጋቢ ጉዶች እየተሰሙ ነው፡፡ ጥቂት ቢሆኑም የሚከራከሩለት አልጠፉም፡፡

እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ላይ፣ ‹‹ያለ ክትባት ሕይወት ወደ ነበረበት አይመለስም›› በሚል ርዕስ ያቀረበው መጣጥፍ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በሰው ዘር ላይ ጭፍጨፋ እየፈጸመ ላላው ኮሮና ቫይረስ ፈውስ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን አንገብጋቢ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ የተነሳ ሐሳብ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የቢል ጌትስን ታሪካዊ ዳራ እናውቃለን የሚሉ ከበስተጀርባው ሸር አለ እያሉ ነው፡፡

የኮሮና ቫይረስ ዓለምን አዳርሶ ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሴራ ንድፈ ሐሳብ ትንታኔዎች በብዛት እየተሰሙ ነው፡፡ የዓለም የፖለቲካ ሥርዓትና ኢኮኖሚ ለመቆጣጠር ሲባል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ከላቦራቶሪ እንዲያፈተልክ ተደርጎ ሰብዓዊ ፍጡራንን ማጥቃት፣ ፋይቭ ጂ (5G) በተሰኘው ኔትሮወርክ አማካይነት ከፍተኛ ጂጋ ኸርዝ ኤሌክትሮ ማግኔቲክ ፊልድ በሰዎች ሰውነት ውስጥ መልቀቅና የመከላከል አቅማቸውን ማዳከም፣ በርካታ ሰዎችን በመግደልና በወረርሽኙ በማስጠቃት ፍርኃትና ጭንቀት መፍጠር፣ የሰዎችን ተፈጥሮአዊ መብቶች በመግፈፍ በግዴታ ቤታቸው ውስጥ እንዲቀመጡ በማድረግ የወደፊቱን የዓለም ሥርዓት መቅረፅና የመሳሰሉ የሥጋት ሐሳቦች እየቀረቡ ነው፡፡ ዴቪድ አይክ የተባሉ እንግሊዛው ጸሐፊና የሴራ ንድፈ ሐሳብ ተንታኝ ለንደን ሪል የተሰኘ ሚዲያ ላይ ቀርበው በርካታ ውዝግብ የሚያስነሱ መላምቶችን በቅርቡ መናገራቸውን ልብ ይሏል፡፡

በሴራ ንድፈ ሐሳብ ተንታኞች ዕይታ ውስጥ ከወደቁ ሰዎች መካከል ቢሊየነሩ ጌትስ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ የማይክሮ ሶፍት መሥራች የሆነው ጌትስ በበርካታ የምርምር ሥራዎች ላይ የሚሳተፉ ኩባንያዎች ሲኖሩት፣ ለዓለም ጤና ድርጅት የገንዘብ አስተዋጽኦ በማድረግ ይታወቃል፡፡ ድጋፉም ከአሜሪካ ቀጥሎ ትልቁ ነው ይባላል፡፡ ሞንሳንቶ በሚባለው ኩባንያው አማካይነት የዘረመል ምህንድስና የተደረገላቸው ምግቦች (GMO) በማምረትና በተለያዩ አገሮች በማስመረት ጭምርም ይታወቃል፡፡ ዘ ኢኮኖሚስት ላይ ባወጣው መጣጥፉ ላይ አስተያየት ከሰጡ ሰዎች መካከል የተወሰኑት፣ የክትባቱን ነገር አደራ ብለው ድጋፋቸውን ችረውታል፡፡ በጣም ብዙ የሚባሉት ግን ነጋዴው ቢሊየነር ያቀረበው ሐሳብ አልጣማቸውም፡፡

የመጀመሪያዋ አስተያየት ሰጪ ጌትስ ከሦስት አሠርት ዓመታት በፊት የኮሌጅ ትምህርቱን አቋርጦ ወጥቶ ማይክሮ ሶፍት ኩባንያን መሥርቶ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኮምፒዩተሮችን ከሸጠ በኋላ ያደረገውን አንረሳውም ብላለች፡፡ የማይክሮ ሶፍት ኩባንያ ሶፍትዌር የተጫነባቸው ኮምፒዩተሮቹ ገበያ ውስጥ ከተቸበቸቡ በኋላ ኮምፒዩተር ቫይረስ የሚባል እንግዳ ነገር ተሰማ ስትል ታስታውሳለች፡፡ ይህ ሆን ተብሎ የተፈበረከ ቫይረስ በርካታ ኮምፒዩተሮች በመላው ዓለም ሲያጠቃ፣ የቫይረሱ ፈጣሪ ‹አንታይ ቫይረስ› የሚባል ሶፍትዌር ይዞ ብቅ በማለት ቢሊዮን ዶላሮችን ቆጠረበት በማለት የሰውየው ደብቅ ገመና ነው ያለችውን እንዳይዘነጋ አለች፡፡ እሱ ከማይክሮ ሶፍት ከወጣ በኋላ ግን ስለቫይረስ ሰምተንም አናውቅም በማለት ሐሳቧን አጠናክራለች፡፡

አሁን ግን ይህ መሰሪ ከዚህ ገዳይ ቫይረስ ጀርባ ላለመኖሩ ምንም ማረጋገጫ ማቅረብ እንደማይገባ፣ ምክንያቱ ደግሞ በማይክሮ ቺፕስ አማካይነት የሚሰጥ ክትባት እያዘጋጀ ስለሆነ ነው የሕክምና ዕውቀት ሳይኖረው ከሳይንቲስቶችና ከተመራማሪዎች በላይ ድምፁ እየተሰማ ያለው በማለት ሐሳቧን ያጠቃለለችው፡፡ ይህ አስተያየቷ የብዙዎችን ድጋፍ ሲያገኝ የተቃወሟትም ነበሩ፡፡ አንዳንዶች ወይ ከዕውቀት ነፃ መሆን ሲሉም ተሳልቀውባታል፡፡

ዘ ኢኮኖሚስት ይዞት የወጣው የጌትስ ጽሑፍ የሚያተኩረው ወደፊት ሊመጣ የሚችለው ክትባት፣ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ፍጥነት ያለውና ከሰብዓዊ ፍጡራን ላይ በሽታውን በማስወገድና የመከላከል አቅማቸውን ከፍተኛ ደረጃ የሚያደርስ መሆኑን ያትታል፡፡ ሕይወትም በፊት በሚታወቀው ሳይሆን ለየት ባለ መንገድ መመራት ይጀምራል ሲልም ያክላል፡፡ እዚህ ላይ ጥያቄ ያነሱ በርካቶች ዘ ኢኮኖሚስት ገጽ ላይ አስተያየታቸውን አሥፍረዋል፡፡

ለክትባቱ የሚደረገው ምርምር ይዘት ምን እንደሚመስል፣ በምርምሩ ላይ የሚሳተፉ ሳይንቲስቶች አስተያየት፣ የወትሮው ሕይወት በነበረበት የማይቀጥልበት ምክንያትና የመሳሰሉት ተሰንዝረዋል፡፡ ጌትስ ምንም እንኳ በሜሊንዳና ቢል ጌትስ አማካይነት በበርካታ የምርምር ዘርፎች ባለው ተሳትፎ መረጃዎች ቢኖሩትም፣ እሱ ግን የኮምፒዩተር ፕሮግራመር ሆኖ ሁሉንም አውቃለሁ ባይነቱ አልጣማቸውም፡፡ እንዲያውም አንድ አስተያየት ሰጪ ከቢሊየነርነት ወደ ትሪሊየነርነት በመሸጋገር ብቸኛው የምድር ገዥ ለመሆን ዕቅድ ስላለው ነው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ እንደ እርጎ ዝንብ ሁሉም ነገር ውስጥ ጥልቅ ማለት ያበዛው ብሏል፡፡

ቢል ጌትስን እንዲህ ማብጠልጠል አይገባም ከሚሉ ወገኖች መሀል ሌላው፣ ሰውየው ያለፉትን 20 ዓመታት የራሱንና የሌላውን ቢሊየነር ዋረን ቡፌት ቢሊዮን ዶላሮች ያፈሰሰው በአፍሪካና በህንድ ፖሊዮን ለማጥፋት መከራከሪያ አቅርቧል፡፡ በተጨማሪም በተቀሩት የዓለም ደሃ አገሮች ለንፁህ ውኃና ለሳኒቴሽን አቅርቦት ተሳትፎ ማድረጉን፣ እንደ ማንኛውም ሰው የሜዲካልና የሳይንስ ጆርናሎችን በማንበብ ስለቫይረሶች ግንዛቤ በማግኘቱ አስተያየቱን ማቅረብ ይችላል ሲል ድጋፍ ሰጥቶታል፡፡ ማንም ሰው የመሰለውን እንደሚናገረው ሁሉ፣ እሱም መናገሩን ወይም መጻፉን መቃወም ተገቢ እንዳልሆነ አስምሮበታል፡፡

ሌላዋ ድጋፍ የቸረችው ደግሞ በሴራ ተንታኞች ወሬ አዕምሮአችንን ማሰር የለብንም ብላ፣ ቢል ጌትስ በዓለም ላይ ምርጥ የሚበሉ ባለምጡቅ አዕምሮ ተመራማሪዎችን ይዞ ለዓመታት የሠራ በመሆኑ መፍትሔ ይዞ ብቅ እንደሚል አትጠራጢ ብላለች፡፡ ምርጥ ምርጥ መጻሕፍትን እንድናነብ ለዓመታት ጥቆማ ሲሰጠን ተጠቃሚ ስለነበርኩ፣ ይህ ሰው ለዓለም መድኅን ይሆናል በማለት ሞግታለታለች፡፡ ጌትስና ሚስቱ ሜሊንዳ በዓለም ትልቅ የሚባለውን የረድኤት ድርጅት መሥርተው በርካታ ድሆች ዘንድ መድረሳቸው ሊዘነጋ አይገባም ስትልም አሳስባለች፡፡

የኮሮና ቫይረስ አደገኛ ጥላ ዓለም ላይ አንዣቦ የመፍትሔ ያለህ እያለ የሰው ዘር ሲጣራ፣ አንድ መሠረታዊ ጥያቄዎች መነሳት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የተራቀቁ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን የታጠቁ ሀብታም አገሮች፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ድባቅ ከተመታች በኃላ በስፓንሽ ፍሉ እንደ ተፍረከረከችው አውሮፓ ለምን በኮሮና ወረርሽኝ ተደፈሩ? ቢል ጌትስ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ማስጠንቀቂያ ከሰጠ ለምን ትኩረት ተነፍጎት ዓለማችን የኮሮና መጫወቻ ሆነች? ቢል ጌትስ ከተለያዩ ወገኖች ውንጀላዎችና ጥያቄዎች ሲዥጎደጎዱለት ችላ ብሎ ለምን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለክትባት ብቻ ያወራል? በሴራ ንድፈ ሐሳብ ተንታኞች የሚቀርቡ አወዛጋቢ ትንተናዎችን የሚሞግቱ ለየት ያለ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች ለምን አይታዩም? ወዘተ የሚሉት ምላሽ ይሻሉ፡፡

በቢሊየነሮች የሚዘወሩት ታዋቂዎቹ የቴሌቪዥንና የጋዜጣ ጎምቱዎች በቫይረሱ ስለተጠቁና ስለሞቱ ሰዎችና ስለኢኮኖሚ ድቀት ከማወራት በዘለለ፣ ድብቅ ተደርገዋል ስለሚባሉ ሴራዎች ለምን ትንፍሽ ማለት አቃታቸው? ዶናልድ ትራምፕ እንደ ሳኒታይዘር ያሉ ፀረ ተዋህሲያንን ለክትባት መጠቀም ቢሞከር በማለት ሐሳብ አቀረቡ ብሎ ከመሳለቅ (በእርግጥ የሰውየው ወፈፌነት ይገርማል)፣ ኮሮና ቫይረስ ከምን ተነስቶ ዓለምን እንዳሸበረ የታለ የምርመራ ጋዜጠኝነቱ? ድብቅ ሴራ ከሌለም እኮ ግራና ቀኙን አጣርቶ ለጊዜው እውነታው ይህ ነው ማለት ለምን አቃተ? እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች መልስ ካላገኙ የሴራ ትንተናው ይቀጥላል፡፡

አገራችንን በተመለከተ ግን አሁንም ከዚህ መቅሰፍት ለመትረፍ የጥንቃቄ መመርያዎችን ማክበር እንደሚያስፈልግ ማሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ በአንዳንድ የዓለማችን ከፍሎች ከአውሮፓና ከአሜሪካ በተሻለ የቫይረሱ ሥርጭት ዝቅተኛ ቢሆንም፣ አሜሪካና አውሮፓ ሙሉ በሙሉ የቤት ውስጥ መክተትን ረገብ እያደረጉ እንቅስቃሴ ለመጀመር ሲሉ ሥርጭቱ እየቀነሰ እንደሆነ ቢናገሩም፣ ኮሮና ቫይረስ የባህሪ ለውጥ እያደረገ ሁለተኛ ዙር አደገኛ ምት ሊያሳርፍ እንደሚችል መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡ እንደ አውሮፓና አሜሪካ የበረታ ክንዱን ባላሳየባቸው እንደ አፍሪካ ባሉ ደሃ አገሮች ላይ ከፍተኛ ጥፋት ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ማሳሰቢያው አሁንም ቀጥሏል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እንዳሉት ቫይረሱ ከእኛ ጋር ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ስለሚችል፣ እንዲሁም ከዓለም ዙሪያ ከሚሰሙ አወዛጋቢ መረጃዎች አኳያ በድቡቁ ዓለም ሰዎች የሚጎነጎን ሴራ ስለሚኖር አሁንም ጥንቃቄው ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ቫይረሱ ባህሪውን ስለሚለዋውጥ አደገኛነቱንም ሊጨምር ስለሚችል፣ በዚህ ከባድ የፈተና ጊዜ ከመጠንቀቅ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ሌላው ነገር ሕይወትን መታደግ ሲቻል ይደረስበታል፡፡ ከላይ ለመጠቆም እንደሞከርኩት ፈጣሪ የሰጠንን አዕምሮ በመጠቀም አስተዋይ መሆን አለብን፡፡ ‹‹ጥበብ ከጥፋት ያድንሃል አለማስተዋል ለጥፋት ይዳርግሃል›› እንደሚባለው፣ የጥንቃቄ መመርያዎችን በሙሉ በማክበር፣ ለጥፋት የተዘረጉ እጆችንም ሆነ አደገኛውን ወረርሽኝ በብቃት መመከት የዘመኑ ሰው ኃላፊነትም ግዴታም መሆኑን እንደ አንድ ተራ ዜጋ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ ግራና ቀኙን የሚያስተውል በቀላሉ አይወድቅምና፡፡

ፈጣሪ አገራችንንና ሕዝባችንን በይቅርታውና በምሕረቱ ይጎብኝ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...