Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከጥራዝ ነጠቅነት ወደ ጠቢብነት የተደረገ ሽግግር!

እነሆ መንገድ! ከሜክሲኮ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ጎዳናው በባለርስቶቹ ዘመን ብዙ ለምዶ ኖሮ እንደተወረሰ ሰፊ እልፍኝ ባዶውን ቀርቶ፣ ‹አቤት አቤት አልኩኝ ብቻዬን ቀርቼ. . .› ይባልበት ይዟል። እልፍ ብንሆንም ብቻ ለብቻ ቆመናል ወይም ተራርቀናል። ሐሳቦቻችንና ውጥኖቻችን በሕይወት መድረክ ላይ የተጠላለፉ ደብዛዛ መስመሮች ሆነዋል። ወንድሜ እንደማያውቀኝ፣ ያቺ እህቴ እንዳልተወለደችኝ አቀርቅራ ትጓዛለች። ዋላችሁ መቀራረብ አይቻልም ተብለን ቅርብ ብንሆንም ተራርቀናል፡፡ ርቀት መጠበቃችን መልካም ሆኖ ሥጋት ላያችን ላይ ቤቱን ሠርቷል፡፡ ፍርኃታችንን የተገነዘቡ ጩልሌዎች ደግሞ አንዴ ነብይ ሌላ ጊዜ መልዓክ እየመሰሉ በሰይጣናዊ ክንፎቻቸው ሥር ሊወትፉን ይራወጣሉ፡፡ ሥጋችንን እንደ ቅርጫ ተካፍለው አጥንታችንን ለመቀራመት ይዘላብዳሉ፡፡ አንዱ መድኃኒቱ በእጄ ላይ ነው ሲል፣ ሌላዋ ተቃቀፉ ትላለች፡፡ አንደኛው በራዕይ አይቼው ነበር እያለ ሲንጎማለል፣ አንደኛዋ ደግሞ ሰማይ ተከፍቶ ፈውስ ተሰጥቶኛል ትለናለች፡፡ መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ ምድረ ወንበዴ ሲያናፋና የዋሆችን እንደ በግ ሲነዳ፣ የሕግ ማስከበሪያው አካል እያንቀላፋ ሆኖ እንጂ መቼ መጫወቻ እንሆን ነበር፡፡ ለማንኛውም ‹ቀን እስኪያልፍ ያለፋል› እያልን አለን!

እንባና ሳቅ ሰው የመሆን ዕዳ ተፈጥሮአዊ አካል ናቸው። ጎዳናው አፍ ባይኖረውም ብዙ ይናገራል፡፡ ይህ የጎዳና ላይ ብሶት ትርክት ነው፡፡ በአንዱ ሥቃይ ሌላው ሲደሰት፣ በአንዱ ሐዘን ሌላው እንጀራ ሲበላ፣ የሚለፋው ሳይሆን የሚዘርፈው ሲከብር፣ ምሥጉኑ ተዋርዶ ወንበዴው ኖር ሲባል፣ ታታሪው ተንቆ ሰነፉ ሲከበር፣ አገር የሚያፈርሰው ከለላ አግኝቶ አገር አስከባሪው ለጥቃት ሲጋለጥ… ዓለም ዘጠኝ ናት አሥር አትሞላም እየተባለ ሲዘመር ተኖረ፡፡ ውጤቱ ምን ሆነ? አበው እንደሚሉት፣ ‹‹በሠፈሩት ቁና መሠፈር አይቀርም›› የሚባለው ደረሰ የሚሉ ወገኖች መቼም አበዛችሁት አይባልም፡፡ ታክሲያችን ላይ ከተሳፈሩት አንዱ ኑሮ ባለ በሌለ ኃይሉ የደቆሰው ምስኪን ይመስላል፡፡ ‹‹ይህም ኑሮ ሆኖ ምቀኛ በዛበት…›› ይላል እየደጋገመ፡፡ ከእሱ ኋላ ያለው ወንበር ላይ የተቀመጠ ወጣት፣ ‹‹ጀለስ ምነው ችግር አለ እንዴ?›› ሲለው፣ ‹‹ዙሪያህን በችግር ተከበህ መፍትሔ ለመፈለግ ሳትጥር ለምን ትጠይቀኛለህ?›› እያለ ወደ ውጭ ሲመለከት ወጣቱ በሐሳብ ጭልጥ አለ፡፡ እንደ ቀልድ ያነሳው ጥያቄ ያላሰበውን ጥያቄ ሲያስነሳበት፣ የገዛ ሕይወቱን ኦዲት ማድረግ የጀመረ ይመስል ነበረ፡፡ ስንቶቻችን እንሆን ውጣ ውረዳችንን የምንፈትሽ? እንጃልን ያሰኛል!

ጉዟችን ተጀምሯል። ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ እናት፣ ‹‹ክብሩ ይስፋ ለመድኃኔዓለም…›› ሲሉ፣ ‹‹ምናለበት እንደ እናቶቻችንና አባቶቻችን አንደበታችን ለምሥጋና ቢከፈት?›› ይላል መሀል መቀመጫ ላይ የተቀመጠ ጎልማሳ። ‹‹ልጄ ፈጣሪን ማመሥገን ያለብን ችግር ሲኖር ጭምር ነው፡፡ ይቅር ባይና መሐሪ ስለሆነ ልመናችንን በምሥጋና ስናጅበው መቅሰፍቱን ያባርርልናል፡፡ እኛ አልመቸው ብለን በዘርና በሃይማኖት ስንጨራረስ ገላጋይ አድርጎ ኮሮና የምትሉትን መቅሰፍት እንደላከብን ነው የሚሰማኝ፡፡ ከድርጊታችን ስንታቀብ ግን ለደጋጎች ሲል በምሕረቱና በይቅርታው ይጎበኘናል…›› ሲሉ ልባችንን ከፍተን አዳመጥናቸው፡፡ ወያላው በጣም ተደንቆ ነው መሰል፣ ‹‹ውይ እማምዬ እርስዎ እኮ በቴሌቪዥን ቀርበው ንግግር ቢያደርጉ ፖለቲከኛ የለ አክቲቪስት፣ ነቢይ የለ ጠንቋይ ልካቸውን ያሳዩልን ነበር…›› ሲላቸው፣ ‹‹ወዴት ወዴት እባክህ! እኔ እኮ አዲስ ነገር አይደለም የተናገርኩት…›› ከማለታቸው ያ ምስኪን ሰውዬ ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹እናታችን እግዜር ከእርስዎ ጋር ይሁን፡፡ ነገር ግን እዚህ አገ­ር በምክርም ሆነ በጉልበት መልፋት የሌሎች ሰለባ መሆን ስለሆነ ምክርዎ ከቀባሪ ከጎረቤቶችዎና ከጧሪ ከቤተሰቦችዎ አይለፍ፡፡ ሌላው ልፋት ነው፡፡ ያውም ድንጋይ ላይ ውኃ ማፍሰስ…›› እያለ ሲብሰከሰክ የበደል ኑዛዜ የተሸከመ ይመስል ነበር፡፡ ስንቱ ይሆን ውስጡ እየተቃጠለ የሚኖረው!

ጎልማሳው የምስኪኑን ዓይን ዓይኑን እያየ፣ ‹‹እኔ የምልህ ምን ዓይነት መከራና ሥቃይ ቢደርስብህ ነው እንዲህ ውስጥህ የሚጨሰው?›› ብሎ ሊያስወራው ሲጣጣር፣ ‹‹እኔ ስለራሴ ጉዳይ ቢሆን የምጨነቀው ከአንተ ጋር ታክሲ ለምን እጋፋ ነበር…›› እያለ የለበጣ ሳቁን ለቀቀው፡፡ ወያላው ሒሳብ እየሰበሰበ ነው። ሾፌራችን እንደ ሰደድ እሳት ጨዋታ ሲቀጣጠል፣ ‹‹ታክሲ ውስጥ በህቡዕ መደራጀት ክልክል ነው፤›› እያለ ለወያላው የሬዲዮኑን ድምፅ ጨመር ያደርገዋል። የስፖርት ትንታኔ እናደምጣለን። ‹‹ዘንድሮ ኮሮና ሊቨርፑል ከ30 ዓመታት በኋላ ዋንጫ እንዳያገኝ እንቅፋት በመሆኑ የስፖርት ቤተሰቦች የተሰማቸው ሐዘን በእውነቱበእውነቱ… ቅስም የሚሰብር ነው…›› ይላል አንዱ ሥራ ፈት የራሱን ዕጣ ፈንታ ሳያውቅ። ‹‹ስለራሱ ቅስም አያወራም እንዴ? ለምን የእኛን ይጨምራል?”›› ይላልመጨረሻ ወንበር።እውነት ግን ሊቨርፑል አንጀት ይበላል። ሁሌ እኮ ለዋንጫ ደረሰ ሲባል አይሳካለትም፤›› ስትል ባለስካርፏ፣ ‹‹የተሳካለት ዓይተሽ ታውቂያለሽ?›› ብሎ ጎልማሳው አፈጠጠባት። ‹‹በኳስ መፋጠጡን ትታችሁ አገር ላይ ባፈጠጠው ኮሮና ላይ አትተባበሩም?›› ብሎ አንዱ ከጋቢና ወሬ አስገለበጠ።  ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ወይዘሮ፣ ‹‹በስንቱ ተፋጠን በስንቱ እንቃጠል›› አለችው። ያ ምስኪን መሳይ ሰው ሁኔታችን ደንቆት ነው መሰል፣ ‹‹ቀና ሲታጣ ይመለመላል ጎባጣ…›› እያለ ብቻውን ያወራል፡፡ ስንቶቻችን ይሆን ውስጣችን በታመቀ ነገር የምንብከነከን!  

ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመችው ዘንካታ ቦርሳዋን ስትጎረጉር ሳንቲም ፍለጋ መስሎናል። መጨረሻ ወንበር ከተየሰሙት ሁለት ጓደኛሞች አንደኛው አስግጎ በዓይኑ አብሯት ይበረብራል። ‹‹ኧረ ሰው ይታዘበኛል በል፤›› ይለዋል ጓደኛው። ‹‹እባክህ ፖሊስ አይታዘበኝ እንጂ ሰውማ ታዝቦ ታዝቦ ይረሳል፤›› ይመልሳል አባ ደፋር። ይኼን ጊዜ ቆንጅት ሽቶ አውጥታ ፀጉሯና አንገቷ ሥር ነሰነሰችው። መዓዛው ታክሲዋን አወደው። መሀል መቀመጫ ለብቻው የተቀመጠው ጎልማሳ ደጋግሞ አስነጠሰው። ታክሲዋ ውስጥ የነበርን ሁሉ ኑክሌር የተተኮሰ ያህል ስንበረግግ፣ አይዟችሁ በክንዴ ተሸፍኜ ነው ያስነጠስኩት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ይህች ቆንጆ ላይዋ ላይ የነሰነሰችው ሽቶ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ለሽቶ አለርጂ ነኝ…›› እያለ በዓይኖቹ ጭምር ሲማፀነን፣ አንከብክበን ኳራንቲን የምናስገባው ይመስል ነበር፡፡ ምስኪኑ ሰውዬ ሳቅ እያለ፣ ‹‹አይዞህ ወንድሜ! ምክንያቱንማ በደንብ እናውቃለን፣ ግና ምን ያደርጋል በፍርኃት ኖረን በጭንቀት እንድንሞት የሚያደርጉን ግፈኞች የፈጠሩብን የሥነ ልቦና ውጤት ነው የሚያንጰረጵረን…›› ሲል ውስጣችንን አንብቦ የጨረሰ ፈላስፋ ይመስል ነበር፡፡ እንዲህ ነው እንጂ ብልት አወጣጥ!

‹‹እንኳን ለሽቶ ለቂጣና ለሽሮው እጅ ያጠረው ወገኔ ባልጠገበ አንጀቱ በአንድ ጎን የፍሳሽ ቱቦ ሽታ፣ በሌላ ጎን እንዲህ ያለ ግሩም መዓዛ እየሰነፈጠው ሲያስነጥስ እየዋለ፣ ኮሮና ይዞታል ተብሎ ቢወራ ምን ይገርማል…›› ብሎ አንዱ እያስነጠሰ እጁን ዘርግቶ ሶፍት  ጠየቀ። ‹‹አይዞን! ለቃሪያና ለቲማቲሙስ አላነስንም ነበር። ለመቀባባቱና ለማጌጡ አልተርፍ ብሎን እንጂ…›› ብላ ከቆንጂት ኋላ ወንበር ላይ የተሰየመች ተናገረች። ‹‹ቢተርፈንስ? የክት የሚያስለብስ ሆነ እንዴ ጊዜው? እንኳን ተኳኩለንና እጃችንን ፍትግ አድርገን ታጥበን ወጥተንም የሆዳችንን ጥያቄን አልቻልነውም። ቆይ ግን አገር በልመና ነው እንዴ የምትገነባው?›› ሲል ከወዲያ ጥግ መጨረሻ ወንበር ላይ፣ ‹‹ታዲያ ያለ ማገር ቤት ይቆማል እንዴ?›› ብለው እኚያ እናት ያልገባቸው መስለው ተሳፋሪውን አስፈገጉት። ማን ወራጅ ማን ማገር እንደሆነ አልገባንም እንጂ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሱ አስፈሪ መሆኑ መቼም ገብቶናል። ወያላው የሰበሰበውን ገንዘብ እየቆጠረ አጮልቆ እያየን፣ ‹‹መንግሥት ያለ የሌለ አቅሙን ሰብስቦ ካላቃመሰን ከእጅ ወደ አፍ ኑሮአችን መላም የለው…›› እያለ ጭንቀቱን ሲገልጽ፣ ‹‹አይዞህ ወንድሜ! አጋጣሚውን ከተጠቀምንበት እንኳንስ ከእጅ ወደ አፍ ለትውልድ የሚተርፍ ቅርስ ማፍራት ይቻላል…›› እያለ ምስኪኑ ሰውዬ ሲናገር ሁላችንም ነገም ሌላ ቀን ነው የምንል ይመስል ትኩረት ሰጠነው፡፡ ተስፋ ሲጠፋ ተስፋ የሚዘራ ያሻናልና!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል።ኧሁሁሁ!” ብሎ አንዱ ወደ መጨረሻ ወንበር  በረጅሙ ተነፈሰ።ምነው ታፍነህ ነበር እንዴ?” አሉት እናታችን።የለም በነፃነት መተንፈስ አምሮኝ ነው!” ብሎ መለሰ።ሲያምርህ ይቅር እንዳንልህ አንተም እንደ እኛ ብዙ አምሮህ የቀረ ነገር ስለሚኖር ሌላ ዕጦት አንመኝልህም፤አለችው ቆንጂት።ደግሞ በነፃነት መኖር ያማረው ማን በነፃነት ሲኖር ዓይቶ ነው? ፍጥረት ከዘመነ ባሪያ ፍንገላ እስከ ካፒታሊስት ብዝበዛ ድረስ ምን ያላየው ፍዳ አለና ነው ነፃነት እየተባለ የሚደሰኮርብን?›› የሚለው እስካሁን ድምፁ ያልተሰማው ሾፌራችን ነው፡፡ ‹‹አንተ እንዴት ያለ የጠቢብ ንግግር ነው ያቀረብክልን እባክህ? አየህ ዕውቀት ኃይል ነው የሚባለው እኮ የብዙዎችን ትኩረት በመሳቡ ብቻ አይደለም፡፡ ሥራ ላይ ስታውለው የሀብት በረከት ስለሚያመጣ ጭምር እንጂ…›› ሲሉ እኚያ እናት፣ ‹‹እማማ ዕድሜዎን ያርዝመው፡፡ እዚህ አገር እኮ ከሰው በታች ሆነን የምንኖረው ለዕውቀትና ለምርምር፣ እንዲሁም ለትጉህ መምህራን ቦታ ስለማንሰጥ ነው፡፡ በእጃቸውና በአዕምሮአቸው ለፍተው ለሚሠሩ ሳይሆን፣ ለአስመሳዮችና ለአጭበርባሪዎች ስለምንሰግድ ነው፡፡ ታዋቂን እንጂ አዋቂን ስለማናከብር ነው፡፡ በቃ ምን አለፋዎት ጠቢባንን ሳይሆን፣ ግብዞችንና መረኖችን ስለምናስቀድም ነው…›› ብሎ ያ ምስኪን ሰው ሲያንበለብለው ደነገጥን፡፡ እንዲህ ነው እንጂ!

ዝምታው ሲሰፍን ወያላችንና ሾፌራችን እርስ በእርስ መነቋቆር ጀምረዋል። ‹‹ኧረ በገላጋይ…›› ብሎ አንዱ እንደ ቀልድ መሀላቸው ሲገባ ወያላው ወደ ገላጋዩ ዞሮ፣ ‹‹አይዞህ ዕድሜ ለኮሮና ከብሔርተኝነትና ከጽንፈኝነት ባቡር ላይ ወርደን የሰብዓዊነት ታክሲ ላይ ነን ያለነው…›› ሲለው አንዱ፣ ‹‹እውነትህን ነው እኮ፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ኮሮና ባይመጣ ኖሮ ምርጫው ራሱ የብሔርተኞችና የጽንፈኞች የጦር ሜዳ ይሆን ነበር…›› ያለችው ቆንጂት ናት። ጎልማሳው በበኩሉ፣ ‹‹ሳይደግስ አይጣላምና ኮሮና መቅሰፍት ብቻ ሳይሆን መልካም አጋጣሚ ይዞ መጥቶ ሊሆን ስለሚችል፣ አዕምሮአችንን ካሠራነው ያልታሰበ ዕድል ሊገኝበት ይችላል…›› ብሎ የተሳፋሪዎችን አፍ አስከፈተ። ‹‹ደግሞ ምን ታየህ?›› ሲለው አንዱ፣ ‹‹እንዴት ምን ታየህ ይባላል? እኔ እኮ እያልኩ ያለሁት…›› ብሎ ሳይጨርስ ምስኪኑ ሰውዬ ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹ግልጽ እኮ ነው፡፡ ክፉ ጊዜ ሲያጋጥም በጭንቀትና በፍርኃት ከመርበድበድ አዕምሮን በማሠራት ራስን ለፈጠራ ማዘጋጀት ይቻላል ነው መልዕክቱ፡፡ ለሦስት ሺሕ ዘመን እንቅልፉን ሲለጥጥ የኖረ አገር ውስጥ ምግብ ብርቅ የሆነው እኮ አዕምሮ በመዛጉ ነው፡፡ አሁን ግን ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ቁጭ ብሎ ሞትን ከመጠበቅ ሞትን ድል ነስቶ አሸናፊ ሆኖ ስለመውጣት ይታሰብ፡፡ ጥራዝ ነጠቆች በቀደዱልን ቦይ ሳይሆን የጠቢባንን መንገድ እንከተል…›› ብሎ ቁርጡን ሲነግረን እንደተመካካርን ሁሉ በእናታችን መሪነት አጨበጨብንለት፡፡ ይህንን የመሰለ ጥርት ያለ ሐሳብ እንደ ሽግግር መቀበላችንን በአንድ ድምፅ ተማምነንና ተመራርቀን ወደ ጉዳዮቻችን አመራን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት