Thursday, February 22, 2024

የክልሎች ምርጫ የማከናወን መብቶችና ገደቦች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዓለም አቀፍ ክስተት በመሆን የዓለም አገሮችን እየተፈታተነ የሚገኘው የኮሮና ወረርሽኝ ዓለም ከዚህ ቀደም በነበረችበት ትቀጥላለች? ወይስ አዲስ የዓለም የኃይል አሠላለፍና አመራር ሊያስከትል ይችላል? በሚሉ ሁለት ወገኖች መካከል ሙግቱ ተሟሙቆ ይገኛል፡፡

ከዚህ ሙግትና ትንበያ ባልተናነሰ ግን ከዚህ ቀደም የአገሮችን የፖለቲካ ተዋናዮች፣ እንዲሁም የማኅበራዊና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ወትዋቾችን የውይይትና የክርክር አቅጣጫም ቀይሮታል፡፡ ፅንፍ በያዙና አሉታዊ አስተያየቶች የሚታወቁ የማኅበራዊ የትስስር ገጾች ተዋናዮችም ሙሉ በሙሉ ቫይረሱን መከላከል ሊወሰዱ የሚገቡ ዕርምጃዎች ላይ ተጠምደዋል፣ ወይም ደግሞ ዝምታን መርጠዋል፡፡

ይህ ዓለም አቀፍ መገለጫ በኢትዮጵያም የሚስተዋል ሲሆን፣ በቅድመ ኮሮና ወረርሽኝ ወራት ይስተዋሉ የነበሩት ፖለቲካዊ ይዘቶች የሚያተኩሩባቸው የቃላት ጦርነቶችና ሙግቶች፣ ወይ ወረርሽኙን እንዴት ማቆምና መከላከል እንችላለን ወደሚል ወይም ደግሞ ሌሎች ከቫይረሱ ጋር ወደ ተያያዙ አስተያየቶች ተሸጋግረዋል፡፡

ወረርሽኙ ከመከሰቱ  በፊት በነበሩት ጊዜያት  በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የብሔር ፖለቲካውና ፖለቲከኞች በከፍተኛ ሁኔታ ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን የሚያስተላልፉባቸው የማኅበራዊ ትስስር ገጾች፣ አሁን እምብዛም በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ሲሉ አይስተዋልም፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ላለፉት ስድስትና ሰባት ወራት የአገሪቱን የፖለቲካ ልሂቃን ሲያወዛግብ የነበረው የምርጫ ጉዳይ፣ በዚህ ወረርሽኝ ሳቢያ ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉ እንኳን የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ውይይት አላስተናገደም፡፡

ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት በነበሩት ወራት የምርጫው ጉዳይ አነታራኪ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው፣ ምርጫው በጊዜው ይካሄድ ወይም የለም ምርጫው መራዘም አለበት በማለት የፖለቲካው ተዋናዮች የሚያቀርቡት ክርክር ነበር፡፡

ከዚህ ባለፈም ምርጫው ይራዘም አይራዘም በሚል አጀንዳ በመታጠር ከመከራከር፣ ይህንን ሊያስፈጽም የሚችል የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎችም ነበሩ፡፡

እንዲህ ላሉ ሙግቶች የመጨረሻ ምላሽ የሆነው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መጪው ጠቅላላ ምርጫ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚካሄድ የወሰነው ውሳኔ ነበር፡፡

ምንም እንኳ ቦርዱ ነሐሴ 23 ቀን ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድበት እንደሆነ በመወሰን አስፈላጊ ያላቸውን ሥራዎች እያከናወነ የነበረ ቢሆንም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ዕቅዶቹን በታሰበላቸው ጊዜ ማከናወን እንደማይችል በመግለጽ የምርጫው መራዘም ግድ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከዚህ ባሻገርም በአገር ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ ታውጇል፡፡ ይህም በተለያየ መንገድ ከምርጫ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን እንደ ሕዝብ መሰብሰብ፣ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ወዘተ መብቶችን የሚገድብ ከመሆኑ አንፃር የምርጫው መራዘም ብዙም ውዝግብ አላስከተለም፡፡

ከምርጫው መራዘም ጋር ተያይዞ የተነሳ ተቃውሞ ቢኖር ፓርቲዎች በውሳኔው ሒደት ላይ አልተወያየንም የሚል እንጂ፣ መራዘም የለበትም ወይም ደግሞ ለምን ተራዘመ ከሚል የመነጨ አልነበረም፡፡

ምርጫውን ለማራዘም በነበረው ሒደት የአንድ ዙር ውይይት በቦርዱና በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እንዲሁም በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተካሂዶ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ የመጀመርያም የመጨረሻም ውይይት ላይ ቦርዱ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ሆኑ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ማንኛውም ዓይነት ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት ለቀጣይ ውይይት እንደሚጠራቸው መግለጹን በማስታወስ፣ የውሳኔውን ሒደት የተቃወሙት ደግሞ ለውይይት ሳይጠሩ ውሳኔው መተላለፉን ነበር፡፡

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ ከዚህ ምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ዳግም መራገብ ጀምረዋል፡፡ ለዚህ ጉዳይ ዳግም መራገብ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች ዋነኛው ምክንያት ደግሞ በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ የወጣው፣ የ2012 ዓ.ም. ምርጫን የተመለከተው አቋም ነው፡፡

ምንም እንኳን በዚህ በድርጅቱ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ የወጣው ጽሑፍ በኅዳር ወር ላይ እንደተጻፈ የሚገልጽ ቢሆንም፣ በዚህ ወቅት እንደ አዲስ በገጹ ላይ መስተናገዱ አሁን ለምን የሚል ጥያቄዎችን በብዙዎች ዘንድ ያስነሳ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምርጫ ይካሄዳል የሚል አቋም ይዟል በሚል፣ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በተለይም በትዊተር ምን ዓይነት ፖለቲካዊና ሕገ መንግሥታዊ አንድምታ ሊኖረው ይችላል በሚል የፖለቲካ ሳይንስና የሕገ መንግሥት ምሁራን ዘለግ ያሉ ውይይቶች ሲያካሂዱ ተስተውሏል፡፡

በሕወሓት ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ የወጣው ጽሑፍ ኅዳር 2012 ዓ.ም. መታተሙን ከመግለጽ በዘለለ፣ አሁን የክልሉ አቋም ተመሳሳይ ይሁን ወይም ደግሞ የተለወጠና ከምርጫ ቦርድ የተራዘመ የምርጫ ዕቅድ ማዕቀፍ ጋር የተሰናሰለ መሆኑን የሚገልጽ፣ ምንም ዓይነት የተጨመረ ሐሳብም ሆነ አባሪ ማግኘት አልተቻለም፡፡

ከክልሉ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ሆኖም የትግራይ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊያ ካሳ የትግራይ ክልል መንግሥት ዘንድሮ ሊካሄድ ዕቅድ ወጥቶለት የነበረው አገራዊ ምርጫ በወቅቱ መካሄድ ይገባዋል በማለት ለዶቼቬለ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አንፃር የሕገ መንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ለፌዴራሊዝም ዋነኛው የልዩነት መፍቻ መንገድ ድርድር መሆኑን በመግለጽ፣ የትኛውም ወገን ወደ ተካረረ ፖለቲካዊ መንገድ መግባት ለማንም እንደማይበጅ በማሳሰብ ላይ ናቸው፡፡

ሕገ መንግሥቱና የክልሎች ምርጫ የማከናወን ሥልጣን

ከዚህ ቀደም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች መምህሩ አቶ እንዳልካቸው ገረመው፣ ‹‹በመጀመርያ ደረጃ አሁን ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የተመለከትነው ሰሞነኛ ጉዳይ፣ በክልሉ መንግሥት ይፋዊ የሆነ አቋም ተይዞበት የተላለፈ ውሳኔ ከሆነ እጅግ በጣም ጥንቃቄ የሚያስፈልገው አንገብጋቢ ፖለቲካዊና ሕገ መንግሥታዊ እንደሆነ ይሰማኛል›› በማለት፣ ጉዳዩ ከሕገ መንግሥትም ሆነ ከፖለቲካዊ አቅጣጫዎች መታየት ያለበትና አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ በአጠቃላይ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ምኅዳር ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያደርስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡

ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊም ፖለቲካዊም እንደሆነ የሚያስረዱበት ምክንያት ደግሞ፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት አጠቃላይ ጠቅላላ ምርጫ ሊደረግ ታቅዶ በነበረው የምርጫ ሰሌዳ ላይ በዓለም ላይ ተከስቶ ከሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ አገር አቀፍ ተፈጻሚነት ያለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለአምስት ወራት አውጆ በመተግበር ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ የምርጫውም ሁኔታ በዚህ መንገድ ላልተወሰነ ጊዜ ሊራዘም እንደሚገባው›› ቦርዱ ማሳወቁን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

ይህ ውሳኔ ባለበት ሁኔታ የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው መንግሥት ምርጫ መደረግ አለበት በማለት፣ ከዚህ ቀደም ሲያራምደው የነበረ አቋሙን አሁንም እየገፋበት ከሆነ ግን፣ ‹‹በክልሉና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል መስተጋብር ላይ የሚኖረው አንድምታን ከባድ ያደርገዋል፤›› በማለት ሕወሓት ምርጫውን በተያዘለት ጊዜ የማካሄድ አቋሙ ላይ ከፀና፣ በክልሉና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ያለ ግንኙነት ላይ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ አገራዊ ፖለቲካዊ ምኅዳሩ ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ከባድ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የፌዴራል ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ከምርጫ አስተዳደር ጋር በተገናኘ ሁለት ዓይነት ዘዴዎች በዋነኛነት የሚስተዋሉ መሆኑን የሚገልጹ በርካታ ጽሑፎች ሲኖሩ፣ እነዚህም የተማከለና ያልተማከለ የምርጫ አስተዳደር ሥርዓት ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት ለተማከለው የምርጫ አስተዳደር ሥርዓት በፌዴራል ደረጃ የሚዋቀረው የምርጫ ቦርድ ወይም ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ ምርጫዎችን የማስፈጸም ሥልጣን ሲኖረው፣ ባልተማከለው ሥርዓት ደግሞ በክልላዊ ምክር ቤቶች የሚደረጉ ምርጫዎችን ማስፈጸም የሚል ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የሕገ መንግሥት ምሁሩ፣ ‹‹የክልል ምክር ቤትን በተመለከተ ሙሉ በሙሉ ምርጫ ማካሄድ መብታቸው ነው፡፡ አንዱ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መገለጫ ስለሆነ፤›› በማለት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ይገልጹታል፡፡ ነገር ግን፣ ‹‹ክልሎች የራሳቸውን ምርጫ ቦርድ እንዲያቋቁሙም ሆነ የራሳቸው የሆነ የምርጫ ሕግ እንዲያወጡ ሕገ መንግሥቱ  አይፈቅድላቸውም፤›› ብለው፣ በኢትዮጵያ ያለውን የክልሎችና የፌዴራል መንግሥት ከምርጫ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ግንኙነት አስረድተዋል፡፡

እንዲህ በሆነበት ሁኔታ ምርጫ በትግራይ ክልል ከአገር አቀፍ ሁኔታው ተነጥሎ ቢካሄድ፣ የሚያስነሳቸው ሕገ መንግሥታዊ ጥሰቶች በርካታ ይሆናሉ ማለት ነው በማለት አክለው ያብራራሉ፡፡

ለአብነት ያህልም በክልሉ ምርጫ ቢደረግ የሚያስፈጽመው ማን ነው? ምርጫውን ለማከናወን የሚያስፈልገው የበጀት ምንጭ ከየት ነው? ምርጫ ቦርድ ባልተሳተፈበት ሁኔታ ምርጫ ቢካሄድና የተመረጡት ሰዎች  በፌዴራል ፓርላማው መግባት/መወከል የሚችሉት እንዴት ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሹ ናቸው፡፡

እንዲህ ላሉ መሠረታዊ የሕገ መንግሥት መፋለስ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ጥያቄዎች ደግሞ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ባልተደረገበት ሁኔታ መፍታት የሚቻለው፣ በበሰለ የልሂቅ የፖለቲካ ድርድር መሆኑን የሚያሳስቡ በርካቶች ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ሁለት ዓመታት ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅም ሆነ ሲፀድቅ ያልተስተዋሉ ክፍተቶች መስተዋላቸው ይጠቀሳል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ክፍተቶች መሙላትና ማረቅ የሚቻለው በፌዴራሊዝም ሥርዓት ከፍተኛ ሥፍራ  በሚሰጠው የመንግሥታት ግንኙነት አማካይነት  መሆኑን በመጥቀስ ሁሉም ወገን ለመፍትሔው በቅን ልቦና መሳተፍ እንጂ፣ የተካረረና ፅንፍ የያዘ የፖለቲካ አቋም አላስፈላጊ የሆነ ሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ማስጠንቀቂያ አዘል ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -