Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለዚህ ዓመት ከታቀዱ መንገዶች መካከል ሰባቱ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ተመደበላቸው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በዚህ ዓመት ለማስገንባት ካቀዳቸው መንገዶች ውስጥ ከ11.6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ ሰባት መንገዶችን ግንባታ ለማስጀመር ከስድስት ተቋራጮች ጋር ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 20 ቀን 2012 ዓ.ም.  በተካሄደው የግንባታ ስምምነት ከሰባቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ስድስቱን አገር በቀል ተቋራጮች ተረክበዋል፡፡ አንዱን መንገድ  የወሰደው የቻይና ተቋራጭ ነው፡፡

ስምምነት የተፈረመባቸው መንገዶች በጠቅላላው 509.11 ኪሎ ሜትር ይሸፍናሉ፡፡ ለግንባታ የሚያስፈልገውን ከ11.6 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚሸፍነው የኢትዮጵያ መንግሥት ከራሱ በጀት እንደሆነ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ተገልጿል፡፡

የሚገነቡት መንገዶች ደብረ ብርሃን-ደነባ-ለሚ መገንጠያና ጅሁር-ደነባ፣ ፊቅ-ሰገግ-ገርቦ ደነን (ሎት ሦስት ዮአሌ-ደነን) ሁምቦ-ጠበላ-አባያ፣ ዳዬ-ግርጃ-ክብረ መንግሥት (መልካ ደስታ) እና መለያ-መጆ መገንጠያ፣ ጅግጅጋ-ገለለሽ-ደገሃምዶ-ሰገግ (ኮንትራት ሁለት)፣ ሀወላቱላ-ወተራራሳ-ያዩ-ውራቼና ዛላምበሳ-አሊቴና-መረዋ-እዳጋሐሙስ (ሎት አንድ ዛላምበሳ-አሊቴና መገንጠያ) የተባሉ መንገዶች ናቸው፡፡

ተቋራጮቹ የተረከቧቸውን መንገዶች ገንብተው ለማጠናቀቅ ከሦስት እስከ አራት ዓመታት የጊዜ ገደብ ተሰጧቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት መንገዶቹ በጠጠር ደረጃ የተገነቡና ለትራንስፖርትም የማይመቹ ናቸው፡፡ እንደ አዲስ እንዲገነቡ በተደረገው ስምምነት ደረጃቸው ወደ አስፋልት እንደሚያድግ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

የመንገዶቹ የጎን ስፋት በገጠር ሰባት ኪሎ ሜትር፣ በከተማ ከአሥር ሜትር ጀምሮ ስፋት ይኖራቸዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የስትራክቸር ሥራ፣ የአነስተኛ መፋሰሻ ቱቦና ድልድዮች ሥራም ይካተታሉ፡፡ የግንባታ ስምምነት ከተደረገባቸው መንገዶች መካከል ከደብረ ብርሃን-ደርባ-ለሚ መገንጠያና ጅሁር-ደነባ ድረስ የሚዘረጋውን መንገድ ለመገንባት ያሸነፈው ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ነው፡፡ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን መንገዱን በአስፋልት ደረጃ የሚገነባው ሲሆን፣ መንገዱ አዲስ አበባ-ደብረ ብርሃን-ደሴ ከሚሄደው ዋና መንገድ ተገንጥሎ ከአዲስ አበባ-ሙከጡሪ-ዓለም ከተማ መንገድ ጋር የሚያገናኝ መንገድ ነው፡፡ የደብረ ብርሃን የኢንዱስትሪ መንደር የመዳረሻ መንገድና ከደነባ ተነስቶ ወደ ጅሁር ወረዳ የሚያገናኝ መንገድንም እንደሚያካትት ተጠቅሷል፡፡ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ በገጠር በአማካይ አሥር ሜትር ስፋት ሲኖረው በቀበሌ፣ በወረዳና በከተሞች ተጨማሪ ስፋት ኖሮት ይገነባል፡፡ አነስተኛና ከፍተኛ ፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎችና ከልቨርቶችም ይካተታሉ፡፡

ሌላው ዌላ-ቱላ-ወተራረሳ-ያዩ-ወራቼ መንገድ ዲዛይንና ግንባታ ሥራ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ይህ መንገድ ጠቅላላ 85.45 ኪሎ ሜትር ርዝመት ኖሮት በአስፋልት ደረጃ የሚገነባ ነው፡፡ የሐዋሳ-ዲላና አለታ-ወንዶ-ዳዬ መንገዶችን የሚያገናኝ መንገድ ነው፡፡ መንገዱ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ በገጠር በአማካይ አሥር ሜትር ስፋት ሲኖረው፣ በከተሞች 19 ሜትር ስፋት ይኖረዋል፡፡ ይህም አነስተኛና ከፍተኛ ፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ከልቨርቶችና ድልድዮችን ያካትታል፡፡ ለግንባታው በጨረታ ተወዳድሮ በ1.8 ቢሊዮን ብር በማሸነፍ የውል ስምምነት የሚፈርመው፣ ዮቴክ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለው አገር በቀል ተቋራጭ ነው፡፡

ጅግጅጋ-ገለለሽ-ደጋሀመዶ-ሰገግ ሎት 2 እና 3 መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ለመገንባት ጨረታውን ያሸነፈው ቤኤካ ጠቅላላ የንግድ ድርጅት ነው፡፡ ይህ መንገድ ጠቅላላ 109.8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ኖሮት በአስፋልት ደረጃ የሚገነባ ሲሆን፣ መንገዱ ከጅግጅጋ ተነስቶ ሰገግ-ገርቦ-ደነን መንገድ ላይ የሚገጥም የረዥም የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የመጨረሻ ምዕራፍ ግንባታ ፕሮጀክት ነወ፡፡ መንገዱ፣ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ በገጠር በአማካይ አሥር ሜትር ስፋት ሲኖረው ይህ ግንባታም አነስተኛ፣ ከፍተኛ ፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎችና ከልቨርቶች የሚያካትት ይሆናል፡፡ ቤኤካ ጠቅላላ የንግድ ድርጅት የመንገዱ ግንባታ ጨረታ ተወዳድሮ ያሸነፈበት ዋጋ 1.8 ቢሊዮን ብር በማሸነፍ ነው፡፡

ዳዬ-ግርጃ-መልካ ደስታ መንገድና መለያ-መጆ መገንጠያ መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ይህ መንገድ የሚገነባው በአስፋልት ደረጃ ሲሆን፣ በጠቅላላው 63.75 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይኖረዋል፡፡ መንገዱ የባሌ፣ የሲዳማና የጉጂ ዞኖችን የሚያገናኝ ረዥም የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አካል ነው፡፡ የመንገዱን ጠቅላላ ግንባታ ጨረታ ተወዳድሮ 1.55 ቢሊዮን ብር በማሸነፍ የውል ስምምነቱን የፈረመው China Tiesiju Civil Engineering Group Co.Ltd የተባለ ተቋራጭ ነው፡፡

ለገግ-ገርቦ-ዳነን (ፈቂ-ሰገግ-ገርቦ-ዳነን) ሎት 3 ያኦሌ-ዳነን መንገድ ሥራ ፕሮጀክት 83.84 ኪሎ ሜትር ርዝመት ኖሮት በአስፋልት ደረጃ የሚገነባ ሲሆን፣ መንገዱ ከባቢሌ-ፊቅ-ሀሜሮ-ኢሚ የሚሄደውን መንገድና ከኢሚ-ጎዴ-ቀብሪደሃርን የሚያገናኘውን ሌላኛውን መንገድ ደግሞ በ1.11 ቢሊዮን ብር በማሸነፍ የውል ስምምነቱን የተፈራረመው ክሮስላድ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለ አገር በቀል ሥራ ተቋራጭ ነው፡፡

ሱር ኮንስትራክሽን ከዛላምበሳ-አሊቴና-መረዋ-እንዳጋሐሙስ ሎት 1 ዛላምበሳ-አሊቴና መንገድ ሥራ ፕሮጀክትን ለመገንባት ውለታ የፈጸመ ድርጅት ሆኗል፡፡ ይህ መንገድ በጠቅላላው 32 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው በአስፋልት ደረጃ የሚገነባ  ነው፡፡ መንገዱ የዞን መቀመጫን ከአዲስ አበባ-መቀሌ-አዲግራት-ዛላምበሳ ከሚሄደው ዋና መንገድ ጋር የሚያገናኝ መንገድ ነው፡፡ ይህንን ሥራ በጨረታ ያሸነፈው ሱር ኮንስትራክሽን ያሸነፈበት ዋጋም 935 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ በአማካይ አሥር ሜትር ስፋት የሚኖረው ሲሆን፣ የግንባታ ሥራው አነስተኛና ከፍተኛ ፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎችና ከልቨርቶች የሚያካትት ይሆናል ተብሏል፡፡

የሀምቦ (ጠበላ)-አባያ /ሆርቲካልቸር/ ዲዛይንና ግንባታ ኩባንያ ሥራ ፕሮጀክት 26 ኪሎ ሜትር ርዝመት ኖሮት በአስፋልት ደረጃ የሚገነባ ሲሆን፣ መንገዱ ለሆርቲካልቸር እርሻ የምርት ማውጫ መዳረሻ መንገድ ነው፡፡ መንገዱ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ በገጠር በአማካይ አሥር ሜትር ስፋት ሲኖረው በቀበሌ፣ በወረዳና በከተሞች ተጨማሪ ስፋት ይኖረዋል፡፡ ይህ ግንባታም አነስተኛ፣ ከፍተኛ ፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦዎችና ከልቨርቶች የሚያካትት ነው፡፡ ለግንባታው በጨረታ ተወዳድሮ በ699 ሚሊዮን ብር አሸንፎ የውል ስምምነት የፈረመው ክሮስላድ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለ አገር በቀል ሥራ ተቋራጭ ነው፡፡

የመንገዶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከዚህ በፊት በአካባቢው የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ የአካባቢው ኅብረተሰብ በቀላሉ ወደ ፈለገው ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፣ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት እንዲችሉና ሌሎች ባለሀብቶችም በአካባቢ ኢንቨስት ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡

በተጨማሪ በየአካባቢው የሥራ ዕድል እንዲፈጠር በማስቻል በየአካባቢ የሚገኙ ትንንሽ መንደሮችና ከተሞችን ዕድገት ከማፋጠን እንዲሁም የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት እንዲስፋፉ ከማድረግ አንፃር የእነዚህ መንገዶች መገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ እንደሚታመን ተጠቅሷል፡፡

መንገዶቹ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት በሚጀምሩበት ወቅት በየክልሎቹ ውስጥ የሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎችን እርስ በርስ ያስተሳስራል፡፡ ከዚህም ባሻገር የተሽከርካሪዎችን የጉዞ ጊዜና ወጪን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀነስ ከመሆኑም በተጨማሪ የምርትና የሸቀጥ ልውውጥ ያለምንም እንግልት በቀላሉ እንዲከናወን ለማድረግ ያስችላል፡፡

ከሰባቱ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ያለውንና ከሌሎች መንገዶች አንፃር ሰፋፊ ሥራዎች ያካተተውን መንገድ ለመገንባት የተመረጠው ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ነው፡፡ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን በጨረታ አሸናፊ ሆኖ ውለታ የፈጸመበት መንገድ ከደብረ ብርሃን-ደነባ-ለሚ- መገንጠያና ጅሁር-ደነባ የመንገድ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ይህንን 108.2 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውን መንገድ ለመገንባት በጨረታ ያሸነፈበት ዋጋ 3.61 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

ኩባንያው ለተረከበው የመንገድ ግንባታ ሥራ አራት ዓመታት ተሰጥቶታል፡፡ የግንባታ ስምምነቱን የፈረሙት የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ታፈሰ፣ መንገዱ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንደሚጠናቀቅ፣ ለዚህም ሥራ በቶሎ እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳሬክተር በበኩላቸው፣ ሰንሻይን ለመንገዱ በተያዘው የጊዜ ገደብ ውስጥ ግንባታውን እንደሚጨርስ እምነታቸው ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ከአገር በቀል ኮንትራክተሮች በጥሩ አቋም ላይ ከሚገኙ አንዱ በመሆኑም ለግንባታው በተቀመጠው የጥራት ደረጃ ገንብቶ እንዲያስረክብ አሳስበዋል፡፡

የዛላምበሳ-አሊቲና መንገድ ሥራ የተረከበው ሱር ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ የማነህ፣ ለመንገድ ግንባታው በመመረጣቸው ደስታቸው ገልጸው፣ ድርጅታቸው 50 መንገዶች ገንብቶ ማስረከባቸውንና በዚሁ ልምድ መሠረት አዲሱን  መንገድ በተቀመጠለት ጊዜ አግባብ እንደሚያጠናቀቅ ቃል ገብተዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ከሰባቱ ፕሮጀክቶች ውስጥ ስድስቱን አገር በቀል ተቋራጮች መረከባቸው የአገር ውስጥ ድርጅቶችን እንደሚያበረታታ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በስምምነቱ ላይ ከየአካባቢው የተወከሉ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት፣ የመንገድ ግንባታ ለብዙ ጊዜ ሲጠብቁት እንደቆዩና አሁን ወደ ግንባታ መምጣቱ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎችም በገቡት ቃል መሠረት ሥራው እንዲጀመር በማድረጋቸው ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

አቶ ሀብታሙም ፕሮጀክቶቹን ወደ ግንባታ ለማምጣት አስፈላጊውን ጥረት እንደተደረገ አስታውቀዋል፡፡ መንገዶቹ በሚያልፉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አመራሮችና ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡ በተለይም ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ጉዳዮች፣ ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች