በሔለን ተስፋዬ
ከሥራ መውጫ ሰዓት ላይ ነው፡፡ ሚያዝያ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ስታዲየም አካባቢ ከሚገኘው የአንበሳ አውቶቡስ ማቆሚያ ሥፍራ ያለው የሰው ፍትጊያ የኮሮና ኖቭል ቫይረስ ወረርሽኝ የጠፋ አስመስሎታል፡፡
የተሠለፉ ሰዎች ብዛት ከወትሮው ለየት ያለ ነበር፡፡ ሜክሲኮ አካባቢ ያለው የሰው መሰብሰብና የነበረው የትራንስፖርት እጥረትም የጎላ ነው፡፡ ለባቡር ያለው ወረፋም ከታክሲው የተናነሰ አልነበረም፡፡
የታክሲና የባስ ሠልፎች ከመብዛታቸው ጎን ለጎን ሰው ተጠጋግቶና ተፋፍጎ መሠለፉን ከቦሌ አንስቶ በተለያዩ የትራንስፖርት መነሻ አካባቢዎች የተገኘ መታዘብ ይችላል፡፡ ሠልፉ ከመርዘሙ የተነሳም ለሰዓታት ያህል ትራንስፖርት መጠበቅ የተለመደ ሆኗል፡፡
ታክሲዎች ከአቅማቸው በግማሽ እንዲጭኑ መደረጉ የቫይረሱን ሥርጭት ለመቀነስ ቢያግዝም፣ ታክሲ የሚጠብቁ ሰዎች ቁጥር ከዚህ ቀደሙ በይበልጥ መጨመሩና ተጠጋግቶ መቆሙ ለቫይረሱ ያጋልጣል የሚሉ አልታጡም፡፡
በቅርቡ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የወጣው መመርያ የታክሲ ሥራ እስከ ምሽት 2፡00 ሰዓት ብቻ የሚል ቢሆንም፣ ከዚህ ሰዓት በኋላም ሕዝቡ ተሠልፎ ማየቱ የተለመደ ሆኗል፡፡
የቤት ኪራዩን ለመክፈል፣ የሚበላውን ለማግኘትና የትራንስፖርት እጥፍ ወጪውን ለመሸፈን ከቤቱ ተገዶ የወጣ እንደሚበዛ ለመገመት አይከብድም፡፡ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ የትራንስፖርት መጨናነቁን ላይ ሠልፉ የበዛው ለመዝናናት በወጡ ሰዎች ምክንያት እንዳልሆነም ይገነዘባል፡፡
ታክሲዎችና ሌሎች የትራንስፖርት አማራጮች ከመጫን አቅማቸው በግማሽ እንዲቀንሱ መንግሥት ውሳኔ ከመወሰዱ በፊት፣ ተጨማሪ የትራንስፖርት አማራጮች በበቂ አለመዘጋጀታቸውንም ያለው የትራንስፖርት እጥረት ያሳያል፡፡ መንግሥት ዕርምጃውን የወሰደው ሰው ቤቱ እንዲቀመጥ በማሰብ ቢሆንም ሥራ ሙሉ ለሙሉ ባልተዘጋበት ሁኔታ ትራንስፖርቱ ላይ ገደብ መጣሉ በተገልጋዮች በኩል መንገላታት ብቻ ሳይሆን መጨናነቅንም ፈጥሯል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ስጦታው አበራ የቫይረሱን ሥርጭት ለመቀነስ ሲባል የሚችል ሰው ከቤቱ ባይወጣ፣ ከወጣም ርቀትን በጠበቀ መልኩ አገልግሎቱን ቢጠቀም የተሻለ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ትራንስፖርት ቢሮው የመንግሥት ሠራተኞችን የሚያመላልሱ ፐብሊክ ባሶች ሠራተኛን ካደረሱ በኋላ ለሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡና ከ100 በላይ በተለያዩ ብልሽቶች የቆሙ ባሶች ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
ኃላፊው ኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይገባ በፊትም የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር መኖሩን አስታውሰው፣ የታክሲዎችና የባሶች የመጫን አቅም ከነበራቸው መጠን ግማሽ ሲሆን፣ ችግሩ መባባሱ አይቀሬ በመሆኑ የሚችል ሰው ከቤት ባለመውጣት ቢተገበር መልካም ነው ብለዋል፡፡
የትራንስፖርት ምልልሱን ለማቃለልም ከ200,000 በላይ የሚሆኑ ኮድ ሁለት የቤት መኪናዎች በፈረቃ እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል፡፡ ይህም መንገዶች ክፍት እንዲሆኑ ታስቦ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የትራንስፖርት ቢሮው ሰሞኑን አስቸኳይ ውይይት ካደረገ በኋላ ባለሀብቱን በማስተባበር የትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ አገር አቋራጭ ባሶች በፈቃደኝነት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አስታውሰው፣ ማኅበረሰቡ አሁን ያለውን የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቀነስና የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የበኩሉን ቢወጣ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
ማኅበረሰቡ በትራንስፖርት ቢሮ የተላለፈው ውሳኔ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ታስቦ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት በተቻለው መጠን ከቤት ሲወጣ የፊት ጭንብል በመጠቀም፣ እጅን ለ20 ሰከንድ በመታጠብና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ አቶ ስጦታው መክረዋል፡፡
አሁን የተፈጠረውን የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቅረፍ በትራንስፖርት ቢሮው ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ቤታቸው ቅርብ የሆኑ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች የእግር ጉዞ ቢጠቀሙ መጨናነቁን በተወሰነ መልኩ መቅረፍ ይቻላል ብለዋል፡፡