Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከመገናኛ እስከ አያት አደባባይ ያለው የእግረኛ መንገድ መቆፈር ጥያቄ አስነሳ

ከመገናኛ እስከ አያት አደባባይ ያለው የእግረኛ መንገድ መቆፈር ጥያቄ አስነሳ

ቀን:

‹‹ሁሉን ያሟላ ለማድረግ በጥራት ለመሥራት ነው››

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን እያሠራው የሚገኘው ከመገናኛ እስከ አያት አደባባይ የሚደርሰው የእግረኞች ግራና ቀኝ መንገድ፣ የተጋነነ ብልሽት ሳይኖረው መፍረሱ ነዋሪዎችን አስቆጣ፡፡

በግራ ቀኙ የእግረኞች መንገድ ላይ የተነጠፈው ታይልስ (ሸክላ) በሌሎች መንገዶች ከተሠሩ የእግረኛ መንገዶች የተሻሉና በጥሩ ሁኔታ ላይ ያሉ ቢሆንም፣ ምክንያቱን እንኳን ሳያሳውቁ መቆፈራቸው ለሕዝብ ያላቸውን አመኔታ የሚሸረሽር መሆኑን ሰለሞን ፍፁም (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ አዛለች ተሰማ፣ ሲስተር ትህትና አላምረውና አቶ ኃይልዬ መንበሩ የተባሉ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ፣ በእግረኛ መንገዱ ላይ የነበረው ችግር ከመንገዱ ዳርና ዳር ላይ ያሉ የተለያዩ ንግድ ቤቶች በመንገዱ ላይ የሚያስቀምጡዋቸው ዕቃዎች ናቸው፡፡ መንገዱን ነፃ ማድረግ ሲገባው ባለሥልጣኑ በጀት መድቦ ደህናውን መንገድ እንዲፈርስ ማድረጉ ትክክለኛ አካሄድ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

የምሕንድስና ባለሙያ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ሳሙኤል ገረሱ (ኢንጂነር) ያላቸው አስተያየት ደግሞ የተለየ ነው፡፡ እግረኛ መንገዱ ላይ የተነጠፈውን ታይልስ (ሸክላ) ተጠግተው እንዳዩት፣ ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት የማገልገል አቅም እንዳለው ማረጋገጣቸውንና የባለሥልጣኑ አመራሮች በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱትም ጠይቀዋል፡፡ ይኼ የእግረኛ መንገድ ንጣፍ ተነስቶ በሌላ ታይልስ እንዲነጠፍ የተደረገው፣ ታይልስ አቅራቢውን ወይም ኮንትራክተሩን ለመጥቀም ካልሆነ በስተቀር ለመንገደኛው ምቾት ታስቦ አለመሆኑን እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢ ያሉ የእግረኛ መንገዶች በመበላሸታቸውና አባጣ ጎርባጣ ሆነው መንገደኛውን እስከ መሰበር እያደረሱ በመሆናቸው፣ በጀቱን ወደ እነዚህ መንገዶች አዙሮ ማሠራት ሲቻል ደህናውን እያፈረሱ ለመጠገን መንቀሳቀስ ጥፋት እንጂ ልማት እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡ አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች፣ እንዲሁም የመንገድ መብራቶች በአብዛኛው ስለማይበራ በጨለማ የሚጓዙ ነዋሪዎች እየገቡ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸውና እስከ ሞት የሚያደርሳቸውን ያልተዘጋ ቱቦ እንደ መዝጋት፣ ያልተበላሸ የእግረኛ መንገድ እያፈረሱ በከፍተኛ በጀት እንዲሠራ ማድረግ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እና ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲታረም ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ያነሱትን ተቃውሞና ያቀረቡትን አቤቱታ በሚመለከት ምላሽ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው፣ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ሀብት ዘርፍ አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕይወት ሳሙኤል የእግረኛ መንገዶቹ መፍረሳቸውን አምነዋል፡፡

‹‹ትክክል ነው ከመገናኛ እስከ አያት አደባባዩ ያሉት ግራና ቀኝ የእግረኛ መንገዶች ፈርሰዋል፡፡ ይኼ የተደረገው ደግሞ ሁሉን ያሟሉ ማለትም የአካል ጉዳተኞችንም የሚያስተናግዱ የተሻለ መንገዶች ለማድረግ ነው፡፡ በዋናነት የእግረኛ መንገዱ ታይልስ (ሸክላ) ንጣፍ እንዲነሳና በሌላ እንዲተካ ማድረግ የተፈለገው፣ በኤሌክትሪክ አገልግሎትና በኢትዮ ቴሌኮም ተቋማት በመቆፈር መበላሸት ስለገጠማቸው አልፎ አልፎ ቢሆንም ወጥ አድርጎ ለመሥራት ሁሉም እንዲፈርሱ ተደርገው እየተሠሩ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የእግረኛ መንገድ ማሻሻያ ፕሮጀክት›› በሚል ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞ፣ ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ የእግረኛ መንገዶችን ለመሥራት ባለሥልጣኑ ለ2012 በጀት ዓመት በጅቶ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡ ከመገናኛ እስከ አያት አደባባይ ግራና ቀኝ ያለው የእግረኛ መንገድ 16.6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መሆኑን የገለጹት ሕይወት (ኢንጂነር)፣ 16 ኮንትራክተሮችና 48 ጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት እየሠሩት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በምን ያህል በጀት እየተሠራ እንደሆነ ለጊዜው እጃቸው ላይ ማስረጃ እንደሌላቸው ገልጸው፣ ሥራው በዚሁ በጀት ዓመት እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

የእግረኛ መንገዱ ሳይበላሽ የተቆፈረው ከታይልስ አምራቾችና ከኮንትራክተሮች ጋር በመመሳጠር ጥቅም ለማግኘት ተብሎ የታሰበ ነው መባሉ ‹‹ተራ አሉባልታ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እንዲህ ያለ አስተያየት የሚሠራን ኃይል እንዳይሠራ ከማድረጉም በተጨማሪ፣ ያልሆነ ስም የሚያሰጥና የለውጥ ኃይሉን የሚያዳክም አስተያየት በመሆኑ ጥሩ አይደለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞች ከታይልስ አምራቾች ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ ጠቁመው፣ ጨረታ ተጫርተው የተጠየቁትን መሥፈርቶች ካሟሉ አምራቾች ጋር ማንኛውም ሠራተኛ ግንኙነት የለውም ብለዋል፡፡ በእግረኛ መንገዶች ላይ ወረዳው፣ ክፍለ ከተማውና ሌላውም ስለሚያዝበት፣ ኅብረተሰቡ መንገዱን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ ባለሥልጣኑ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መንገዱን በተለየ ሁኔታ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌሎች የተበላሹ መንገዶች እያሉ ሙሉ በሙሉ ያልተበላሸውን መሥራት ያስፈለገበት ምክንያት፣ በጣም የተጎዳው የእግረኛ መንገድ ከዋናው መንገድ ጋር አብሮ መታደስ ስላለበት ከመገናኛ አያት አደባባይ ያለው እግረኛ መንገድም በዚህ ምክንያት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...