Monday, March 4, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ታላቁ የአርበኝነትና የጀግንነት ተጋድሎ ሲዘከር መዘንጋት የሌለባቸው ቁምነገሮች!

ጀግኖቹ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ወራሪውን የፋሽስት ጣሊያን ሠራዊት ለአምስት ዓመታት ተዋግተው ድል የነሱበት 79ኛ ዓመት መታሰቢያ፣ ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ይዘከራል፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም የሽምቅ ውጊያን ያስተማረችበት የጀግኖቹ አርበኞች ታሪካዊ ገድል ሲዘከር፣ አሁን ያለው ትውልድ ዙሪያውን የከበቡትን ችግሮች እንዴት በድል መወጣት እንደሚችል ትምህርት መቅሰም ይኖርበታል፡፡ ከሃምሳ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያለቀበት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ በፊት፣ በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በተከለከሉ የመርዝ ጋዞች ከማንም በፊት ዕልቂት የተፈጸመበት ጀግናው ሕዝባችን፣ ታሪክ በማይረሳው ታላቅ ተጋድሎ አገሩን ተከላክሏል፡፡ ጀግኖቹ አርበኞች ስንቅና ትጥቅ ሳይቀርብላቸው ልጆቻውንና የትዳር አጋሮቻቸውን ጭምር በማሠለፍ፣ እንዲሁም በዘመኑ የነበረው ውስጣዊ ሽኩቻ ሳይበግራቸው እግራቸውን ለጠጠር ደረታቸውን ለጦር ሰጥተው እናት አገራቸውን በከፍተኛ ፍቅርና ጀብዱ ከፋሽስቶች ወረራ ታድገዋል፡፡ ኢትዮጵያን ብቸኛዋ ለቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከከች አፍሪካዊት አገር በማድረግ ስሟን በደማቅ ቀለም አሥፍረዋል፡፡ ይህ ታላቅ ተጋድሎ ሲዘከር ይህ ሁሉ ውለታ መታወስ አለበት፡፡

እንደሚታወቀው ታላቁ የዓድዋ ጦርነት በኢትዮጵያውያን አስደናቂ ተጋድሎ በድል ተጠናቆ መላው ዓለምን ያስገረመ ክስተት ሲፈጠር፣ እንዲሁም የዓለም ጥቁር ሕዝቦች በድሉ ተምሳሌትነት በመበረታታት ለነፃነት ትግል ተነሳስተው ቅኝ ገዥዎችን ሲያስደነግጡ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን በድሉ በመኩራራት በፈጠርነው መዘናጋት ለወራሪዋ ጣሊያን የቂም በቀል ዝግጅት ዕድል አመቻቸን፡፡ የቬኒቶ ሞሶሎኒ ፋሽስት ፓርቲ በጣሊያን ሥልጣን ሲይዝ የመጀመርያ ተግባሩ፣ ዓድዋ ላይ ድባቅ የተመታችውን አገሩን ታላቅነት ለማስመለስ ባለ በሌለ ኃይሉ ኢትዮጵያን በመውረር አስገብሮ ለዓለም ማሳየት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በዘመኑ እጅግ በጣም የሠለጠነ ሠራዊት፣ ዘመኑ ያፈራቸው ጠመንጃዎች፣ መትረየሶች፣ መድፎች፣ ታንኮች፣ የጦር አውሮፕላኖች፣ የሠራዊትና የስንቅና ትጥቅ ተሸከርካሪዎችና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በማካተት ወረራ ፈጸመ፡፡ ጀግኖቹ ኢትዮጵያዊያን የማይበገሩ መሆናቸው ስለሚታወቅ፣ በጦር አውሮፕላኖች አማካይነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ከፍተኛ መጠን ያላቸው የመርዝ ጋዞች ታከሉበት፡፡ በዚህ መጠን ከታጠቀ የፋሽስት ኃይል ጋር የተጋፈጡት ጀግኖች አርበኞች ከጎራዴ፣ ከጦርና ጋሻ፣ ከአሮጌ ነፍጦች፣ በዓድዋ ጦርነት ከተማረኩ ውስን ኋላቀር መድፎች በስተቀር ምንም ባይኖራቸውም፣ በእናት አገር ፍቅርና በጀግንነት ወኔ ወደር የሌለው ተጋድሎ አድርገው ኢትዮጵያን ለተከታዩ ትውልድ አስረክበዋል፡፡ ይህ ትውልድ ይህንን አንፀባራቂ ታሪክ ማስከበርና የራሱንም ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

የጀግኖቹ ኢትዮጵያዊያን ተጋድሎ ሲወሳ ለአምስት ዓመታት የተደረገ እልህ አስጨራሽ ትግል መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ይህ መራር ትግል ፅናትን የሚፈታተን፣ መፈጠርን የሚያስጠላ፣ የገዛ አባት ወይም እናት፣ ወንድም ወይም እህት ሳይቀሩ በፋሽስቶች ጭካኔ የተጨፈጨፉበት፣ ሞት በየዕለቱ በርካቶችን ያጋዘበት፣ በፋሽስቶች አውሮፕላኖችና መድፎች መንደሮች ሲወድሙ የሕፃናትና የእናቶች እሪታ ከዕልቂት ጋር በየዕለቱ የተሰማበት፣ ለፋሽስቶች ባደሩ ባንዳዎች ስመ ጥር አዋጊዎች ሳይቀሩ በሽምቅ የተገደሉበትና የፋሽስቶች ፕሮፓጋንዳ እየተነዛ መወላወል የተስተዋለባቸው ፈታኝ ሥቃዮች እንደታለፉ በታሪክ ድርሳናት ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ፊት ለፊት ከገጠመ ግዙፍ አውሮፓዊ ጠላት ጋር ከሚደረገው ትንቅንቅ ባልተናነሰ በግለሰብ አመራሮች መካከል በሚፈጠር አለመግባባት፣ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ተስፋ አስቆራጭ አጋጣሚዎች እንደነበሩም ይታወሳል፡፡ የሆነ ሆኖ ብዙኃኑ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ለተጋድሎ የተሠለፉበትን መሠረታዊ ዓላማ በሚገባ ያውቁ ስለነበር፣ ከምንም ነገር በፊት አገራቸውን በማስቀደም በውድ ሕይወታቸው የማያልፍ ታሪክ አኑረው መስዋዕት ሆነዋል፡፡ የፋሽስቶች ግፍ ከመጠን በላይ ሆኖ ንፁኃን ሳይቀሩ በመርዝ ጋዝ ተጨፍጭፈዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በሩዶልፎ ግራዚያኒ ላይ በተወረወረ ቦምብ ምክንያት ከ30 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያን ለመጨፍጨፋቸው፣ ስድስት ኪሎ የሚገኘው የሰማዕታት አደባባይ ምስክር ነው፡፡ ፋሽስቶች በታሪክ ዘግናኝ የሚባለውን ጭፍጨፋ የፈጸሙት ዘር፣ ፆታ፣ ቋንቋ፣ እምነትና የመሳሰሉትን ሳይለዩ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊያንም የአርበኝነት ተጋድሎ ያደረጉት ልዩነቶች ሳይገድቧቸው በአንድነት ተሠልፈው መሆኑን፣ ይህ ትውልድ እውነተኛውን ታሪክ በመመርመር መረዳት ይኖርበታል፡፡

የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ከመጀመሩ አንድ ዓመት አስቀድሞ በ1927 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የቼክ ሪፐብሊክ ተወላጅ ካፒቴን አዶልፍ ፐርለሳክ ‹‹ሐበሺስካ ኦዴሳ›› ወይም ‹‹የሐበሻ ጀብዱ›› በተባለው ዝነኛ መጽሐፋቸው፣ የኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች ተጋድሎን በዓይን ምስክርነት ተርከዋል፡፡ በወቅቱ የሰሜን ጦር ግንባር ጠቅላይ አዛዥ ለነበሩት ለራስ ካሳ ኃይሉ የጦር አማካሪ እንዲሆኑ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተሾሙት እኚህ ሰው፣ ኢትዮጵያዊያኑ ጀግኖች አርበኞች አውሮፕላን በጠመንጃ በመጣል ወይም ታንክ በጎራዴ በመማረክ የፈጸሙትን የጦር ሜዳ ውሎ ሲተርኩ በታላቅ አድናቆት ነው፡፡ ከግብርና ውጪ የጦር ትምህርት ያልነበራቸው እነዚያ ጀግኖች ጠላትን ጥለው ለመውደቅ ያደርጉ የነበረውን ፉክክር ሲገልጹ፣ ወኔን በሚፈታተን ሁኔታ መድፍ እያጓራና መትረየስ እያሽካካ የተፋፋመው ጦር ሜዳ መሀል በታላቅ ፉከራና ሽለላ ሲገቡ ሞትን ንቀውና ረስተው ነበር ብለዋል፡፡ ሌሎችም የታሪክ ዘጋቢዎች የኢትዮጵያዊያኑን ጀግንነት በተመሳሳይ መንገድ ነበር የገለጹት፡፡ ካፒቴን ፐርለሳክ በቁጭት የሚያስታውሱት ከሃዲዎች ባይኖሩና የአመራር ችግር ባይከሰት ኖሮ፣ ጀግኖቹ ኢትዮጵያዊያን እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የፋሽስት ኃይል አዲስ አበባ ሳይገባ ልክ እንደ ዓድዋው ማይጨው ላይ ድል ይነሱት እንደነበር ነው፡፡ በሕይወታቸው እንዲህ ዓይነት ጀግንነት ገጥሟቸው እንደማያውቅ በመመስከር ጭምር፡፡ ይህ መሠረታዊ ጉዳይ በዚህ ትውልድ ልቦና ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ሊያገኝ ይገባል፡፡ በአንድነት ለአንድ ዓላማ መቆም ሲቻል ማንም እንደማይበግረው መገንዘብ የግድ ይሆናል፡፡ አገር ታፍራና ተከብራ የምትኖረው በእንዲህ ዓይነት አንፀባራቂ ተጋድሎ እንጂ፣ በመከፋፈልና ለጠላት በቀላሉ ዒላማ በመሆን እንዳልሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ወደ አሁኑ ትውልድ መለስ ሲባል በርካታ ውጥንቅጦች አሉ፡፡ አገራቸውን እንደ ቀደመው ትውልድ ከሚያፈቅሩና ማናቸውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ከማያንገራግሩ ቆራጦች፣ ‹ከራስ በላይ ንፋስ› ብለው ግላዊ ጥቅማቸውን ብቻ እስከሚያሳድዱ ከንቱዎች ድረስ በየዓይነቱ ይስተዋላሉ፡፡ ከአገር ይልቅ በማንነት ስም ጠባብ መንደር ላይ ከሚያተኩሩ፣ ለባዕዳን በማጎብደድ ለምን ቅኝ አልተገዛንም ነበር እያሉ የሚቆጩ ድረስ እዚህች አገር ውስጥ ይተራመሳሉ፡፡ የፖለቲካ ሥልጣንና ጥቅም እስከተገኘ ድረስ፣ ለብሔራዊ የጋራ ጉዳዮች ደንታ የሌላቸውም ቁጥራቸው አይናቅም፡፡ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች በመታገል ሽፋን አምባገነንነትን ለማንገሥ የሚክለፈለፉም እንዲሁ፡፡ በመሠረቱ ልዩነቶች መኖራቸው ተፈጥሮአዊ መሆኑን መገንዘብ የግድ ይላል፡፡ ልዩነቶች ግን አገርን ለድርድር የሚያቀርቡ መሆን የለባቸውም፡፡ የፌዴራል ሥርዓት ከ25 ዓመታት በላይ በተዋወቀባት አገር ውስጥ በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊነት እንዴት አብሮ መኖር እንደሚቻል ከበቂ በላይ ልምዶችን መቅሰም እየተቻለ፣ ስለመገንጠልና ስለመበታታን ማሟረትና ማላዘን ካላሳፈረ ለትውልዱ ጭምር ስድብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ደጉንና ክፉውን ጊዜ አብረው እያሳለፉ ተባብረው የዘለቁት፣ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች አንፀባራቂ የሆኑ ገድሎችን በማከናወን ተምሳሌት በመሆን እንደሆነ ታሪክን ደጋግሞ ማስታወስ የግድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ትርክት የሚያመራው ወደ ውድቀት ጎዳና ነው፡፡ ከውድቀት ደግሞ ውርደት እንጂ ክብር አይገኝም፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ስትሆን፣ አሁን ደግሞ በሰው ሠራሽ ችግሮች ላይ የኮሮና ወረርሽኝ ከባድ ሥጋት ደቅኗል፡፡ ዓለምን ከሥር ከመሠረቱ ያንቀጠቀጠው ይህ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ፣ ልክ እንደ ፀረ ፋሽስት የአርበኝነት ትግሉ ለአንድ ዓላማ መቆም የግድ ነው፡፡ የጥንቃቄ መመርያዎችን በጋራ በማክበርና በማስከበር የወረርሽኙን ሥርጭት ማስቆም የመንግሥት ወይም የጤና አካላት ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡ ኢኮኖሚውን ለመታደግም የሁሉም ወገኖች ርብርብ አስፈላጊ ነው፡፡ ከጤና ሥጋቱ በተጨማሪ ዜጎች ምግብና መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው አቅም በፈቀደ መጠን ሊቀርቡ ካልቻሉ፣ ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ እንደሚፈጠር መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ሌላው አሁንም አስቸጋሪ የሆነው የፖለቲካው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ምርጫንና ሌሎች መሠረታዊ መብቶችን በተመለከተ አገርን እያስተዳደረ ያለው መንግሥትና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች፣ በሰከነ መንገድ ተቀምጠው በመነጋገር መግባባት መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን ከባድ ጊዜ ውስጥ ሆኖ የተለመደውን ቁማር ማስቀጠል አይቻልም፡፡ የሚያዋጣው ሕጋዊውን መንገድ ተከትሎ ሥርዓት ያለው ስምምነት ላይ መድረስ ብቻ ነው፡፡ በሕዝብ ስም እየነገዱ መቆመር ለማንም አያዋጣም፡፡ ከምንም በፊት የምትቀድመው ኢትዮጵያ ስትሆን፣ በሕዝብ ላይ መቅሰፍት ይዞ የተነሳው ወረርሽን ደግሞ ከፍተኛ ትኩረት ይሻል፡፡ የታላቁ የአርበኝነትና የጀግንነት ተጋድሎም አገርንና ሕዝብን የማያስቀድም እርኩሰት ይፀየፋል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...

ምርጫ ቦርድ ፓርላማው ያፀደቀለትን 304 ሚሊዮን ብር አለማግኘቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ 2016 ዓ.ም. በአራት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰብዓዊ ቀውስና በውድመት የታጀቡ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው የሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተጀመረው...

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...