Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመጪውን ምርጫ ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ በተባሉ አማራጮች ላይ የተለያዩ ሐሳቦች እየቀረቡ ነው

የመጪውን ምርጫ ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ በተባሉ አማራጮች ላይ የተለያዩ ሐሳቦች እየቀረቡ ነው

ቀን:

ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ለመካሄድ የጊዜ ሰሌዳ የወጣለት መጪው ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በመራዘሙ፣ መንግሥት ሰሞኑን አራት አማራጮችን ቢያቀርብም የተለያዩ ሐሳቦች እየቀረቡበት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ረቡዕ ሚያዝያ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በወረርሽኙ አስገዳጅነት የተራዘመውን ምርጫ አስመልክቶ፣ ከተለያዩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ‹‹ኮቪድ-19 ምርጫን ማራዘምና የሕግ አማራጮች›› በሚል ርዕስ ተወያይተዋል፡፡

የውይይቱ መነሻ የሆነው በምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) አማካይነት የቀረቡት አራት የአማራጭ ሐሳቦች ሲሆኑ፣ በተነሱት አራት የአማራጭ ሐሳቦች ላይም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ያላቸውን ሐሳብና ምልከታ አቅርበዋል፡፡ ከውይይቱ በኋላም ሌሎች ወገኖችም የተለያዩ ሐሳቦችን እያቀረቡ ነው፡፡

በምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የቀረቡት አራቱ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ ሕገ መንግሥት ማሻሻል፣ እንዲሁም የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉት ናቸው፡፡

አገሪቱ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተያዘው ዓመት ሳይጠናቀቅ በፊት አጠቃላይ ምርጫ የማከናወን ግዴታ የሚኖርበት ቢሆንም፣ ዓለም አቀፍ ክስተት በሆነው የኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫውን ማከናወን እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ በዚህም ምክንያት የአገሪቱን ሕግና ነባራዊ እውነታን መሠረት ባደረገ መንገድ መንቀሳቀስ አስፈላጊ በመሆኑ እነዚህ አራት አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦች ሕገ መንግሥቱን ሳያፋልስ መቅረባቸውን ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ የውይይቱ መካሄድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው ‹‹መንግሥት እኔ ብቻ ነኝ  የመፍትሔ ሐሳብ አፍላቂ›› ከሚለው አስተሳሰብ ወጥቶ ለውይይት የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት መጋበዙ ትልቅ አንድምታ አለው በማለት፣ የውይይቱን ጠቀሜታ ገልጸዋል፡፡

በቀረቡት ሐሳቦች ላይ ደግሞ ፓርቲው ምርጫው በመራዘሙ ምክንያት የራሱን ሥራዎች ሲያከናውን እንደነበር ጠቅሰው የፓርቲው ሕግ ክፍልም ሦስት የመፍትሔ ሐሳቦችን አቅርቧል ብለዋል፡፡ እነዚህ የቀረቡት ሐሳቦች መንግሥት ካቀረበው ሐሳብ ጋር ተመሳሳይ እንደሆኑ፣ በፓርቲው ያልታየው አራተኛው አማራጭ ማለትም የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚለው ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ፓርቲው ቀደም ብሎ የተወያየባቸውንና በመንግሥት በኩል የቀረቡትን የአማራጭ ሐሳቦችን አስመልክቶ የፓርቲውን አቋም ለመወሰን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሰኞ ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ስብሰባ እንደሚደረግ የገለጹት አቶ ናትናኤል፣ የፓርቲው አቋምና ውሳኔም በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ ሊሆን እንደሚችል አክለው ገልጸዋል፡፡

ላለፉት በርካታ ወራት ምርጫው ተራዝሞ የሽግግር መንግሥት መቋቋም እንደሚያስፈልግ ሲወተውት የሰነበቱት የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፣ ረቡዕ ዕለት የተካሄደው ውይይት አካሄዱ ትክክል አልነበረም ብለዋል፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ፣ ‹‹ከልብ የሚደረግ ውይይት ቢሆን ኖሮ ከሁለት ወይም ሦስት ቀናት አስቀድሞ ፓርቲዎች ማወቅ ነበረባቸው፡፡ ከተቻለም አጀንዳ ወይም የተዘጋጀ የውይይት ሰነድ ሊደርሳቸው ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ስብሰባው ነገ ጠዋት ሊደረግ ዛሬ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለውይይት ትፈለጋላችሁ የተባልነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ውይይቱ ምን እናድርግ የሚል ሳይሆን እነሱ የደረሱበትን ውሳኔ የማሳወቅና እንዲሁ አሳትፌያለሁ ለማለት የተደረገ ነገር ነው፡፡ በዚህም ምክንያትም ውይይቱ ልባዊ አልነበረም፤›› በማለት አካሄዱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡

በቀረቡት አማራጭ የተባሉት ሐሳቦች ላይ በዝርዝር አስተያየት ከመስጠት ይልቅ፣ ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ተፈጥሯል የሚለው ሐሳብ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ልደቱ፣ ‹‹አሁን አምነን መቀበል ያለብን ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ መፈጠሩን ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ደግሞ በሕገ መንግሥት ሳይሆን የሚታረመው በፖለቲካ ውይይትና ድርድር ነው፤›› በማለት፣ አሁንም መንግሥት ራሱን ለድርድር እንዲያቀርብ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ስንጥቆች ማመላከቱን የሚገልጹት በርካቶች ሲሆኑ አቶ ልደቱም፣ ‹‹አሁን ላለንበት የሕገ መንግሥት ቀውስ የኮሮናና ሕገ መንግሥቱን ያረቀቁ ሰዎችን መርገም ነው ያለብን፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹አሁን ካለንበት አጣብቂኝ ለመወጣት መፍትሔ የሚሆነው ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ መፈጠሩን አምኖ መቀበልና ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የሚሳተፉበት ውይይት ማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለዚህም እንደ መከራከሪያ የሚያቀርቡት ደግሞ፣ ‹‹ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ በአገሪቱ ያለን የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ እኩል ነን፡፡ ከዚያ ወዲያ ፖለቲካዊ ሥልጣን የሚኖራቸው ፕሬዚዳንቷ ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥታዊ ቀውሱ አገራዊ ቀውስ እንዳይሆን ውይይት ቢያመቻቹ፤›› የሚል ነው፡፡

ከቀረቡት አማራጮች የተለያዩ አስተያየቶች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እየተንፀባረቁ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱና ዋነኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራድረው ስምምነት መድረስ አለባቸው የሚለው ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ ክፍተት የአሁኑን ችግር መድፈን ስለማይችል ቀውስ ውስጥ ላለመግባት መደራደርን አማራጭ የሚያደርጉ አሉ፡፡ የአሁኑ ፓርላማ የሥልጣን ጊዜ አብቅቶ ተተኪው ፓርላማ የማይራዘም ከሆነ አገሪቱ መንግሥት አይኖራትም የሚል ነው፡፡ በመሆኑም ወደ ቀውስ ላለማምራት በትብብር ላይ የተመሠረተ ድርድር መኖር አለበት ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ድርድሩና ስምምነቱ ሐሳቡ ጥሩ ቢሆንም፣ የሕዝብ ውክልና የሌላቸው ፓርቲዎች አጋጣሚውን ሥልጣን ለመጋራት ሊጠቀሙበት ሲሉ ቀውስ ለመፍጠር ያሴራሉ ይላሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ አለመረጋጋት በመፍጠር ከዚህ ቀደም የታየውን ግጭት ለመቀስቀስ ይጠቀሙበታል ሲሉም ያክላሉ፡፡ ስለዚህ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ሕጋዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ ማፈላለግ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ይህ ማለት ግን መንግሥት ገደብ የሌለው ሥልጣን ማራዘሚያ ውስጥ እንዳይገባ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በድርድር ስም ያልተገባ ተግባር ውስጥ እንዳይገቡ ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም ሲባል የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል ውይይት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...