Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊአነጋጋሪው የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት

አነጋጋሪው የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ ለመስቀል ደመራና ለሕዝባዊ አደባባይነት ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ እያገለገለ የሚገኘው መስቀል አደባባይን መልሶ የማልማት ፕሮጀክት ቁፋሮ መጀመሩን ተከትሎ፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ድምፃቸውን እያሰሙ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚያሠሩትና 2.5 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚወጣበት የተገለጸው ፕሮጀክት ለሕዝባዊ አደባባይነት (ፐብሊክ ስፔስ) በሚመጥንና በዘመናዊ ሁኔታ ሲገነባ፣ 1,400 ተሽከርካሪዎች ለማቆም የሚያስችል የመሬት ውስጥ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ)፣ ፋውንቴን (የውኃ ፏፏቴ) አረንጓዴ አፀድ፣ የካፌና የሬስቶራንት አገልግሎት፣ የመፀዳጃ ቤት መዝናኛ ማዕከላት ይኖሩታል ተብሏል፡፡

መጋቢት 30  ቀን 2012 ዓ.ም. አደባባዩን ከዋናው አውራ ጎዳና የሚለይ አጥር ከመሥራት ባሻገር፣ የጥልቅ ቁፋሮና ጠረጋው ሥራው ተጀምሮ እየቀጠለ ነው፡፡

- Advertisement -

ለኅብረሰቡም ሆነ ለባለድርሻ አካላት በተለይም ከአደባባዩ ጥንተ ታሪክ ጋር ትስስር ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተቃውሞ ድምጿን አሰምታለች፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡

ሊቀ ጳጳሱ በደብዳቤያቸው ‹‹የበዓለ መስቀል ማክበሪያ ቦታ … ምንነቱ ላልታወቀ ፕሮጀክት እንዲውል ሲደረግ፣ የበዓሉም ሆነ የቦታው ጥንታዊ ባለቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያኒቱ ሳትጠየቅና በጉዳዩ ላይ ሳታምንበት ግልጽነት በጎደለው ሁኔታ ወደ ትግበራ መግባቱ ቤተ ክርሲቲያኒቱን በእጅጉ አሳዝኗል፤›› ብለዋል፡፡

በተያያዘም የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ጃንሜዳ ለገበያ ማዕከልነት መዋሉ ተገቢ አለመሆኑን ያወሱት ሊቀ ጳጳሱ፣ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ወካይ ቅርስነት የተመዘገቡት ሁለቱ ዓበይት በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ፋንታ አለማድረጉ ከማሳዘኑም በላይ፣ በአሁኑ ወቅት ከ50 ሚሊዮን በላይ በሆኑት የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣና ቅሬታን በማስከተሉ የመልካም አስተዳደር ችግር እየፈጠረብን ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹መስቀል አደባባይ ለክብረ በዓል፣ ለአምልኮት፣ ለተቃውሞ፣ ለሩጫ፣ ለውድድር፣ ለእግር ኳስ፣ ለማረፊያ፣ ለስብሰባ፣ ለዳንስ፣ ለፓርኪንግ፣ ለማስታወቂያ፣ ወዘተ የሚውል የአዲስ አበባ ሕዝባዊ አደባባይ (Open Space) ነው፤›› የሚሉት ፕሬጀክቱን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማ ፕላን ባለሙያው አርክቴክት ብሩክ ተክለ ሃይማኖት ናቸው፡፡

ፕሮጀክቱ ግልጽነት እንደሚጎድለው የገለጹት አርክቴክቱ፣ በምን አኳኋን እየተሠራ እንደሆነ ይፋ መደረግ ነበረበት ይላሉ፡፡ ‹‹ቀደም ባለው ጊዜ እንዲህ ዓይነት ቀርቶ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ያለ ጨረታ የሚታሰቡ አልነበረም፡፡ የዲዛይን ውድድርም ይደረጋል፡፡ ዋናው ነገር እንዲህ ዓይነት ነገር በዲዛይን ውድድር መሠራት ነበረበት፡፡ ብዙ ባለድርሻ አካላት ያሉት ስለሆነ ለሕዝቡም ይፋ መደረግ ነበረበት፤›› ብለው፣ ከቴክኒክ አንፃር ፓርኪንግን አስመልክቶ ያሳሰቡት ነጥብ አለ፡፡

‹‹ያ ሁሉ ሕዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ ከታች ፓርኪንግ እንዴት ይደረጋል?›› በማለት ጠይቀው፣ ‹‹ከመስከረም 11ዱ (9/11) ጥቃት በኋላ በዩኤን ስታንዳርድ ሕዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ ፓርኪንግ አይደረግም፡፡ ምክንያቱም ለሽብር ጥቃት ስለሚያጋልጥ ነው፡፡ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የተፈጠረው ዓይነት ነገር ቢፈጠር? የመደርመስ አደጋ ቢደርስና በሌሎችም ነገሮች ላይ መነጋገር ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

መስቀል አደባባይ ከነባር ይዞታዎቹ ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ መሄዱን ያወሱት ባለሙያው፣ በምሳሌነት ሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ያረፈበት የአደባባዩ አካል እንደነበረ፣ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢም በተመሳሳይ እንደነበረ ቦታው ላይ እንዴት እንደሚሠራ ሒደቱ አይታወቅም ይላሉ፡፡

‹‹መስቀል አደባባይ ላይ በአንድም ሆነ በሌላ ትዝታ የሌለው የለም፡፡ የጋራ ቦታ በጋራ ውሳኔ ነው መሠራት ያለበት፡፡ ዴሞክራሲ፣ ፖለቲካና አስተዳደር ላይ ብቻ ሳይሆን በእንደዚህ ዓይነት አፈጻጸም ላይም መኖር አለበት፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ 

አስተያየት የሚሰጡት እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶችን ባለማድነቅ ሳይሆን በማድነቅም መሆኑ የገለጹት ሌላዋ ባለሙያ አርክቴክት ማርሸት መንግሥቱ፣ በተለይ የከተማ ዲዛይን ደረጃ የጠበቀ ፕሮጀክት ማከናወን አዎንታዊ መሆኑን በመግለጽ በመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ያዩትን ክፍተት ሳይተቹ አላለፉም፡፡ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ምንም እንደማይታወቅና አደባባዩ ድንገት ታጥሮ መቆፈሩ እንዳሳዘናቸውም ገልጸዋል፡፡ ‹‹መደባበቁ ለምን አስፈለገ? የሚሠራው በመንግሥት ፈንድ ነው? ለግልጽ ቦታ ግልጽ ያልሆነ አቀራረብ መመረጡ በጣም ከንክኖኛል፤›› ብለዋል፡፡ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ በሌሎችም እንደ አርክቴክቶችም ሆነ እንደ ማኅበር የሚታመነው የሕዝብ ጥቅም ያላቸውን ሥፍራዎች የዲዛይን ውድድር ማካሄድ፣ ከብዙ ጭንቅላቶች መካከል የተሻለ ሐሳብና ውጤት ለማግኘት እንደሚረዳም ጠቁመዋል፡፡

ከኪነ ሕንፃና ከከተማ ፕላኒንግ ጋር የተያያዙ የሙያ ማኅበራት ስለግንባታው ያወያያቸው እንደሌለ ይወሳል፡፡ ‹‹ባለሙያዎች አለን መድረኩን ግን አጣን፣ በነፃ ሐሳብ እናበርክት ብንልም መድረኩ አይሰጠንም፤›› ባሉት የአርክቴክቸርና የከተማ ዲዛይን ባለሙያዋ አገላለጽ፣ ለብዙ አሠርታት የሚቆይ ፕሮጀክት ሲሠራ ቅደም ተከተል መከተል ግድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

‹‹አዲስ አበባ እስካሁን የኖርንባት ከተማ ናት፣ ወደፊትም እንኖርባታለን፡፡ ጥሩ ነገር እንዲሠራልን ነው የምንፈልገው፡፡ ስህተት ሰልችቶናል፡፡ የምንደጋግመው ሒደት አሰልቺ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መስቀል አደባባይም ሆነ ጃንሜዳ ዓበይት ክብረ በዓላቷን መስቀልንና ጥምቀትን የምታከብርባቸው፣ ዩኔስኮም ከአደባባይ በዓል ጋር ባህላዊና አገራዊ ይዘቱንም ጨምሮ እስከ መከወኛ ሥፍራዎች በዓለም ወካይ ቅርስነት እንደ መዘገባቸው የሚናገሩት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፎክሎር ባለሙያ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው አገላለጽ የቅርሱ አካላዊ መገለጫዎች ከአደባባዮቹ ተለይተው የሚታዩ አይደሉም፡፡ ስለበዓሉ አከባበር ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ዕውቀት ማስተላለፊያ ከሆኑ መንገዶች መካከል በመስቀል አደባባይ የሚፈጸመው ክዋኔ በመሆኑ፣ ይህን ኩነት በፕሮጀክቱ ላለማስተጓጎሉ ምን ማስተማመኛ አለ በማለት ይጠይቃሉ፡፡

የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትን አስመልክተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ፌቨን ተሾመ ሚያዝያ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ ፕሮጀክቱ 2.5 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙ ሥራው በአጠቃላይ ስምንት ወራት የሚወስድ መሆኑን ከመስከረም ወር በፊት በአራት ወራት ውስጥ አደባባዩ እየሰጠ የነበረውን አገልግሎት መስጠት እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ ኃላፊዋ አካባቢውን ማዘመን ከዚህ በፊት መስቀል አደባባይ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት፣ በተሻለ መንገድ እንዲሰጥ የሚያስችለው ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጥናት ድርሳናት እንደሚያሳዩት መስቀል አደባባይ በ1950ዎቹ መጀመርያ ስያሜው ከማግኘቱ በፊት በእስጢፋኖስ አደባባይነት እንደሚታወቅ፣ ከ1967 ዓ.ም. መገባደጃ ጀምሮ በዘመነ ደርግ ‹‹አብዮት አደባባይ›› ይባል ነበር፡፡

ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ከያዘ በኋላ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ቀድሞው መጠሪያ መስቀል አደባባይ መመለሱ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...