Monday, July 22, 2024

ኮሮናን ለመከላከል በጥናት የተደገፈ ስትራቴጂ እንጂ ፍልስፍና አያስፈልገውም!

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኮሮና ቫይረስ በአገራችን ለመጀመርያ ጊዜ ከተከሰተበት ከመጋቢት 4 ቀን 2012 .. ጀምሮ መንግሥት ወረርሽኙን ለመግታት የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ዜጎች ንጽሕናቸውን እንዲጠብቁ ከማስተማር አንስቶ ትምህርት ቤቶችን እስከ መዝጋት፣ ማኅበራዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ፣ ከዚህ ቀደም ሕዝብ የሚበዛባቸው  አካባቢዎች እንቅስቃሴዎች እንዲቀንሱ፣ ዜጎችም ወደ እነዚህ አካባቢዎች እንዳይሄዱ፣ ከተቻለም ቤት እንዲቆዩ፣ የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው የመጫን አቅም በግማሽ እንዲቀንሱ ከማድረገስ አልፎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ መደንገግ የደረሱ  ዕርምጃዎች ተወስደዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣቱን ተከትሎ እስከ ዛሬ ድረስ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የፀጥታ አካላት የሚያደርጉት ቁጥጥር በእጅጉ የሚያስመሠግን ተግባር ነው። አብዛኛው ሕዝብ በተለይ በመዲናይቱ እያሳየ ላለው ትብብርም ምሥጋና ይገባዋል። የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የመንግሥት ላፊነት ከፍተኛ መሆኑ አያከራክርም፡፡ ምክንያቱም በሽታው ከተስፋፋ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት አሳሳቢና ለመቋቋምም ከባድ በመሆኑ ነው። ለዚህም ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ በበሽታው ዙርያ መልዕክት የሚያስተላልፉት። ለጽሑፌ መነሻ ወደሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጉዳይ ልግባ፡፡ በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት ለአገርና ለሕዝብ አደጋ የሆኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ እንደሚችል ተደንግጓል።

በአንቀጽ 93 ቁጥር 1. () መሠረት፣ ‹‹የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት›› የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እንደሚቻል ተቀምጧል። ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ ለመላው ዓለም ጭምር ሥጋት የሆነውን የኖቭል ኮሮና ቫይረስን ሥርጭት ለመግታት መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማወጅ አስፈላጊ ስለመሆኑ የሚያከራክር አይመስለኝም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስችሉ መመርያዎችን ለማውጣት ሥልጣኑ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ስለተሰጠው የኮሮና ሥርጭትን ለመቀነስ ወይም ለመከላከል እንደሁኔታውና እንደአስፈላጊነቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣት የመብት ዕገዳዎችን መጣልና ዕርምጃ መውሰድ እንደሚችል ያመለክታል።

በመሆኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያለውን ነባራዊና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ሙያዊ ትንተናና ጥናትን መሠረት በማድረግ ቫይረሱን ለመከላከልና ሥርጭቱን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመግታት የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን በከፍተኛ ጥንቃቄና የኃላፊነት ስሜት መውሰድ ያስፈልጋል። የአስቸካይ ጊዜ አዋጁ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 .. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በአብላጫ ድምፅ መጽደቁን ይታወሳል፡፡ በዚህ መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ አውጥቷል። በምክር ቤቱ ይፋ ከተደረገው መመርያ፣ የትራንስፖርት ዘርፍን ለማስፈጸም የወጣው መመርያ ቁጥር 1/2012 ይገኝበታል።

ይህ 19 አንቀጾች ያሉት መመርያ በትራንስፖርት ዘርፍ በተለይ በብዙኃን ትራንስፖርት መስክ ሕዝብን ለኮሮና በሽታ ሊያጋልጡ የሚችሉ ሁኔታዎችን በሚገባ በማጥናት እንደተዘጋጀ የሚያመለክት ሲሆን፣ በተቃራኒው ኮድ ሁለት የቤት ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ የተጠቀሰው ክልከላ ግን ፈፅሞ ጥናትን መሠረት ያላደረገ፣ አሳማኝ ያልሆነና የዘፈቀደ ውሳኔ ይመስላል። በመጀመርያ ሕዝብን ለዚህ በሽታ ሊያጋልጡ የሚችሉ ሁኔታዎች ጥናትን መሠረት በማድረግና ባለሙያዎችን በማሳተፍ መለየት ያስፈልጋል። የግል ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ የተፈለገበት ምክንያት በእርግጥ የቫይረሱን ሥርጭት ሊቀንሰው ስለሚችል ነው ወይ በሚለው ነጥብ ላይ እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል። ችግሩን ሊቀርፈው ከቻለ ግን መቀነስ ብቻም አይደለም፤ ላልተወሰነ ጊዜ መንገዱን እንዳይጠቀሙ ቢደረግ ምንም አልነበር።

የግል ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ በግማሽ ስንቀንስ ግን እነዚህ ሰዎች ሥራ አቁመው ቤት ይቀመጣሉ ወይስ ምን ሲያደርጉ ይውላሉ ብሎ ማሰብም ያስፈልጋል። እንግዲህ ጥናት እነዚንም ጎኖች ያያል። ደግ ደጉን ብቻ ማሰብ ውጤታማ አያደርግም፡፡  አደጋውን ለመቀነስ ካስፈለገ ጥሩውን ትተን መጥፎውንም (The Worst Scenario) ማሰብ ያስፈልጋል

የኮድ ሁለት ተሽከርካሪዎች ሌሎች አማራጮችን ተጠቅመው ወደ ተለያዩ ቦታዎች ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ፡፡ ሌሌች አማራጮች ሲባል ታክሲ፣ አውቶቡስ፣ ኮንትራት ወይም ባቡር እንዲጠቀሙ ይገደዳሉ። ይህ ደግሞ እንኳንና በኮሮና ዘመን ቀድሞውንም ከፍላጎት ጋር ሊጣጣም ያልቻለውን የትራንስፖርት ዘርፍ የበለጠ ጫና ውስጥ የሚከት በመሆኑ፣ የቫይረሱን ሥርጭት ለመቀነስ ያግዛል የተባለው ዕርምጃ ለመፈላሰፍ ካልሆነ በቀር በየትኛውም ቀመር አሳማኝ አይሆንም፡፡

የቤት ተሽከርካሪዎች ቫይረሱን ለመግታት የሚያበረክቱትን አገልግሎትም መረዳት ያስፈልጋል። ድንገት በቤተሰብ ውስጥ በበሽታው የተያዘ ሰው ቢኖር ወደ ጤና ተቋም ለመውሰድ በታክሲ ወይም በኮንትራት መኪና ከመጠቀም ይልቅ በቤት መኪና ማድረሱ ተመራጭ ነው፡፡ ምክንያቱም በቫይረሱ መያዙ ከታወቀ በኋላ ከታማሚው ጋር ንክኪ ያላቸውን ግለሰቦች በቀላሉ ለመለየት ያስችላል። በእኔ አስተያየት የግል ተሽከርካሪዎች መንገዱን በተራ እንዲጠቀሙ መወሰኑ ምክንያታዊነትን መሠረት ያላደረገና በሌላ ጎኑ የሚያስከትለውን ጉዳት በሚገባ ያልተመለከተ ውሳኔ ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው አካል በውሳኔው ላይ ጥናት ቢያደርግና የኅብረተሰቡንም ስሜት ቢያደምጥ የተሻለ ይሆናል።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን የትምህርት ሚኒስቴር የግል ትምህርት ቤቶችን በሚመለከት ባወጣው መመርያ ላይም አስተያየት መስጠት እፈልጋለሁ። በሚኒስትር ዲኤታ ገረመው ሁሉቃ (ዶ/ር) ተፈርሞ በአባሪ ለሁሉም ክልሎችና ለሁለቱ የከተማ አስተዳደር የትምህርት ቢሮዎች በተላከው ሦስት ገጽ ደብዳቤ ውስጥ ከተጠቀሱ ተግባራት መካከል ወላጆች ከ50 እስከ 75 በመቶ ወርኃዊ ክፍያ መክፈል እንዳለባቸው ተገልጿል።

ምህርት ቤቶቹም ለተማሪዎቻቸው በቴክኖሎጂ ተደራሽ መሆን አለባቸው የሚል ቅድመ ሁኔታ ተቀመጧል። ከ50 እስከ 75 በመቶ ይክፈላሉ ተብሎ የተቀመጠው አኃዝ በራሱ ያከራክራል፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ውስጥ ማንኛው ወላጅ ግማሹን እንደሚከፍልና ሦስት አራተኛውን ማን መክፈል እንዳለበት በግልጽ የተቀመጠ መሥፈርት ስለሌለው ነው። ወላጆችም ቢሆኑ በአብዛኛው ትንሹን የክፍያ መጠን የሚመርጡ ይመስለኛል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ውሳኔ ሲወስን ትምህርት ቤቶቹ ሊጠቀሙበት የሚገባ ወጥ የሆነ የቴክኖሎጂ ዓይነት ማስቀመጥ ነበረበት፡፡ ቤተሰቦች የሚከፍሉት ልጆቻቸው ለሚያገኙት አገልግሎት ነው። ለነገሩ ከደብዳቤውም አጻጻፍ ጀምሮ በችኮላ የተወሰነ ጉዳይ ስለመሆኑ የሚያመላክቱ ነገሮች አሉ።

ተቋሙ የትምህርት ሚኒስቴር በመሆኑ በተለያዩ ሙያዎች የተካኑ ምሁራን የሚገኙበት ነው፡፡ ጥራት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መርህ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ። የተቋሙ ዓርማ ያረፈበት መሸኛ ወረቀት ግርጌ ላይ ‹‹ራዕያችን ብቁ ዜጋ የሚያፈራ፣ ጥራትና ፍትሐዊነት ያረጋገጠ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓት በቀጣይነት መገንባት ነው፤›› የሚል መፈክር ተቀምጧል። ወደ ዝርዝር ተግባራቱ ስንገባ ግን ያለ በቂ ውይይትና ጥናት በችኮላ የተጻፈ መመርያ ማስተላለፉን የሚያመላክት የችኮላ ሥራ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከትምህርት ሚኒስቴር ደብዳቤ ወይም ሰነድ ወጪ ሲደረግ ከሌሎች ተቋማት የተለየ የቋንቋ ጥራት ያለውና ደረጃውን የጠበቀ መሆን አለበት ለማለት እፈልጋለሁ፡፡

በዚህ ከባድ የፈተና ጊዜ በመንግሥት ተቋማት የሚተላለፉ ውሳኔዎችና መመርያዎች የግል ስሜቶችን በማሸነፍ በቂ ጊዜ ተወስዶባቸው፣ ሙያዊ ትንተናን መሠረት በማድረግ፣ በጥናት ላይ በመመርኮዝና ውጤታማነታቸውን በመገምገም በከፍተኛ ኃላፊነት እንዲታገዙ ማድረግ ይበጃል እላለሁ።

(ደረጀ ጉደታ ቱራ፣ ከአዲስ አበባ/ፊንፊኔ)

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -