Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ትዝብቴን የምጀምረው ዕድሜ ጠገብ በሆነ ምሳሌ ነው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ አገር ንጉሡ ሕዝብ ስለሳቸው ምን እንደሚል ለማወቅና የተለያዩ ትኩስ ወሬዎችን ለመስማት በማሰብ አንድ ዕቅድ ያወጣሉ፡፡ በዕቅዳቸው መሠረት ሕዝቡ ውስጥ የሚነገሩትን ነገሮች በሙሉ ልቅም አድርጎ የሚያመጣላቸው ሰው ይሾማሉ፡፡ የእሳቸው ዋነኛ ዓላማ የሚባለውን መስማትና በዚያ ላይ ተመሥርተው መንግሥታቸው የሕዝቡን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ፍላጎታቸውን በሚገባ አስረድተው ሹሙን ወደ ሥራ ያሰማሯቸዋል፡፡

ንጉሡ ለአንድ ወር ያህል ቢጠብቁ ከሹሙ በኩል የሚመጣ ወሬ የለም፡፡ ምናልባት የዕለቱንና የሳምንቱን አንድ ላይ አጠናቅሮ ሊያመጣልኝ ይችል ይሆናል ብለው በትዕግሥት ቢጠብቁም ጠብ የሚል ነገር ጠፋ፡፡ ቢቸግራቸው ሹሙን አስጠርተው ለማናገር ወሰኑ፡፡ ንጉሡ እንደ ወትሮው ጎርደድ እያሉ፣ ‹‹እስካሁን ብጠብቅህ ምንም ዓይነት መረጃ አላመጣህም፣ ችግሩ ምንድነው?›› አሉት፡፡ ሹሙ ሁለት እጆቹን አጣምሮ አንገቱን እንደ ደፋ፣ ‹‹ንጉሥ ሆይ ከሾሙኝ ጊዜ ጀምሮ ሰው ጭጭ ብሏል፤›› አላቸው፡፡ ንጉሡ በመገረም እያዩት፣ ‹‹ለምን?›› ሲሉት፣ ‹‹እኔ እንጃ ሁሉም ሰው እኔን ሲያየኝ የጀመረውን ወሬ አቋርጦ ዝም ይላል፤›› በማለት የገጠመውን ነገራቸው፡፡

‹‹በል ተወው›› ብለው በሌላ መንገድ ነገሩን ለማጣራት በመፈለግ የአገር ሽማግሌዎችን ይሰበስባሉ፡፡ ከሽማግሌዎቹ ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ካደረጉና አቤቱታ ከተቀበሉ በኋላ፣ ‹‹ለመሆኑ ለምንድነው የእኔ ሹመኛ ሲኖር ሕዝቡ ዝም የሚለው?›› በማለት ድንገተኛ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ከሽማግሌዎቹ መካከል አንዱ ብድግ ይሉና እንዲናገሩ እንዲፈቀድላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ንጉሡ ሲፈቅዱላቸው፣ ‹‹ንጉሥ ሆይ እኛ ከእርስዎ ጋር ባልሆነ ምክንያት መጣላት ስለማንፈልግ ነው፤›› አሏቸው፡፡ ንገሡ በመገረም፣ ‹‹ለምን ትጣሉኛላችሁ?›› በማለት ሲጠይቁ፣ ሽማግሌው አንዴ ንጉሡን ሌላ ጊዜ ሌሎቹን ሽማግሌዎች እያዩ፣ ‹‹ግርማዊነትዎ የላኩብንን ሹመኛ እናውቀዋለን፡፡ እኛ የምንፈልገውንና የምናምንበትን ሐሳባችንን ገልብጦ ካቀረበው በመጨረሻ ንጉሥና ሕዝብ ጠብ ውስጥ ልንገባ ነው፡፡ ስለዚህ እሱ ሲመጣ ዝም በማለታችን ቢያንስ ሰላም እንዳይደፈርስ አድርገናል፤›› ሲሉ ንጉሡ በመደነቅ ተመለከቷቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የሕዝቡ አስተያየት ከሽማግሌዎቹ ጋር በሚደረገው የምክክር መድረክ እንዲሰማ ወስነው ሽማግሌዎቹን አሰናበቷቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንግሥትና ሕዝብ በሚገባ መደማመጥ ጀመሩ ይባላል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማየው አሳሳቢ ሁኔታ ይህንን ዕድሜ ጠገብ ምሳሌ አስታወሰኝ፡፡ ባለፈው ሳምንት ሽሮሜዳ አካባቢ ለጉዳይ ሄጄ ስመለስ፣ አራት ኪሎ ፓርላማው የትራፊክ መብራት ላይ ከፊት ረድፍ መኪናዬን አቁሜ አካባቢውን ሳማትር ዓይኔ አንድ ነገር ላይ አረፈ፡፡ ከታላቁ ቤተ መንግሥት ወዲህ በቅስት መልክ የተሠራ የሁለት ግዙፍ አዕዋፋት ቅርፅ ነበር የሚታየኝ፡፡ ዓይኔን ባለማመን በመስኮት አንገቴን አውጥቼ አሁንም አፍጥጬ ስመለከት፣ የሚያብረቀርቅ ቀለም ያላቸው ፒኮኮች ቅርፅ ነው የሚታየኝ፡፡ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚገኘውን አዲሱን ፓርክ ስጎበኝ፣ የፒኮክ ቅርፅ አይቼ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ አሁን ግን በዚህን ያህል ግዝፈትና መጠን የአገር ዓርማ ይመስል ፒኮክ እዚህ ሥፍራ ሲገኝ ግን አልዋጥልህ አለኝ፡፡ አንበሳ የጀግንነት ተምሳሌት በሆነበት አገር የወፍ ዝርያ ይወክልሃል ስባል ደስ አይለኝም፡፡ እኔ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ የሚንሸራሸሩ ወጎችን ይዤ አይደለም ለመሞገት የተነሳሁት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ፣ በንግግሮቻቸውም ሆነ በብዙ ተግባራቶቻቸው ከልብ የምደግፋቸው ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ይህንን ስል ደግሞ ሕግ ከማስከበርና ከመሳሰሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ደግሞ የምቃወምባቸው ነጥቦች አሉኝ፡፡ እሳቸው የወደፊቱን ባላውቅም በበርካታ ጉዳዮች ተስፋ የሚጣልባቸው መሆናቸውንም እረዳለሁ፡፡ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን ብርቱ አማካሪዎች ያስፈልጉዋቸዋል፡፡ ለማመን የሚያዳግቱ ተግባራትን የሚያከናውኑ ብርቱ ሰው ሆነው ሳለ፣ በአንዳንድ ጉዳዮች ለትችት ራሳቸውን የሚያጋልጡ ነገሮችን ችላ ሲሉ እበሽቃለሁ፡፡ እሳቸው ወታደራዊ ከፍተኛ መኰንን፣ የደኅንነት ባለሙያና ልሂቅ ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው ከቀድሞ ባልደረቦቻቸው እስከ ዎል ስትሪት ሰዎች ድረስ እንዳሉም ይታወቃል፡፡ በርካታ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ ጉዳዮች፣ የሕግ ባለሙያዎችና የመሳሰሉት በዙሪያቸው አሉ፡፡ ይህ ሁሉ አማካሪ ባለበት ለወቀሳና ለትችት መጋለጥ አይገባም፡፡ 

የትራፊክ መብራቱ ላይ የእኔን መገረምና መደነቅ ያየ የሚኒ ባስ ታክሲ ሾፌር፣ ‹‹ዓብይ ከአንበሳ ወደ ዶሮ አሸጋግሮናል…›› ብሎ እየሳቀብኝ አረንጓዴ በመብራቱ ወደፊት ሲንደረደር፣ እኔ ግን እንኳን ለመሳቅ ፈገግ ለማለትም አልቻልኩም፡፡ ከኋላዬ የቆመው አሽከርካሪ በጥሩንባው ሲያንባርቅብኝ ነው ዓይኖቼን ፒኮኮቹ ላይ እንደተከልኩ መንቀሳቀስ የጀመርኩት፡፡ ምን እንደሆነ አላውቅም በጣም ነበር የተናደድኩት፡፡ በእርግጥም በዚህ ዘመን ቆፍጠን ያሉ አማካሪዎች ከጠፉ እንደ ንጉሡ ዘመን የሽማግሌ መካሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ዞር ብሎ ከሚያሙ አጉል አማካሪ ተብዬዎች እውነቱን ተናግረው ፈር የሚያሲዙ ሽማግሌዎች ያሹናል፡፡ አሁንም ጊዜው አልረፈደምና ይታሰብበት፡፡

(ንጋቱ መክብብ፣ ከብሥራተ ገብርኤል)  ህን

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...