Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ አስተዳደር ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል 39 ድርጅቶችና ግለሰቦች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ልዩ ልዩ ድጋፎችን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለግሰዋል፡፡ ሐሙስ ሚያዝያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እነዚህን ድጋፎች ተቀብሏል፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ ድጋፍ ያደረጉት ድርጅቶችና ግለሰቦች በዓይነት፣ በጥሬ ገንዘብና በአገልግሎት ቅናሽ ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ ድጋፍ ከሰጡት ውስጥ ሰንሻይን ፍላንትሮፒ ፋውንዴሽን ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የስንዴ፣ የዘይት፣ የንፅህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርና የፊት መሸፈኛ ጭንብሎችን አበርክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ 600 ሺሕ ብር እንዲሁም 50 መኝታ ክፍሎች ያሉት የእንግዳ ማረፊያ ለድጋፍ ለአስተዳደሩ በመስጠት ከሚጠቀሱት ውስጥ ናቸው፡፡

በዕለቱ ከተደረጉት ድጋፎች ውስጥ በ14 ተሽከርካሪዎች የተጫነ ስንዴን ጨምሮ ሳኒታይዘርና የፊት ጭምብል፣ ዘይትና የመሳሰሉትን ያበረከተው ሰንሻይን ፋውንዴሽን፣ ለከተማው አስተዳደር የለገሰውን ጨምሮ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ተመሳሳይ ምርቶችም ለደብረ ብርሃን፣ ለወልቂጤና ለዱከም ከተሞች እንደሚያስረክብ አስታውቋል፡፡ በደብረ ብርሃን፣ ዱከምና ወልቂጤ ከተሞች የሚበረከቱት ምርቶች 2.5 ሚሊዮን ብር ዋጋ እንደሚያወጡ አስታውቋል፡፡ ለደብረ ብርሃን የአረጋውያን ማዕከልም የአንድ ሚሊዮን ብር እንደሚለግስ ተገልጿል፡፡

ሰንሻይን ኮንስትራክሽንም ከሌሎች ኮንትራክተሮች ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ሲያበረክት፣ የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ድርሻ ሁለት ሚሊዮን ብር እንደሆነ የገለጹት የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ፣ በአጠቃላይ ለኮሮና ድጋፍ የሚውል ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ መለገሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ወረርሽኙ እያስከተለ ባለው ተፅዕኖ ምክንያት አንድም ሠራተኛ ከኩባንያዎቻቸው እንዳልተቀነሱ የገለጹት አቶ ሳሙኤል፣ ለጥንቃቄ ሲባል በአራት የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ባሉበት ሆነው እንዲሠሩ፣ ከቦታ ቦታም እንዳይንቀሳቀሱ ለማበረታታት ጉርሻ ወይም ቦነስ በመስጠት ጭምር ሥራቸውን ተረጋግተው እንዲሠሩ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ፋውንዴሽኑ በሥሩ ድጋፍ እየሰጠ ለሚያስተምራቸው 1,350 ተማሪዎች በየወሩ የሚቀርብላቸው የኪስ ገንዘብና የመምህራን ደመወዝ እንዳይቋረጥ በማድረግ በየወሩ 780 ሺሕ ብር ወጪ በማድረግ የሚያደርጋቸው ድጋፎች እንደማይቋረጡ አረጋግጠዋል፡፡

በሌላ በኩል 600 ሺሕ ብርና 50 አልጋ ያለውን የእንግዳ ማረፊያ ለድጋፍ ያበረከተችው የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢያሱ ኤልያስ በበኩላቸው፣ ዕርዳታው በአዲስ አበባ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እንደተሰበሰበ ገልጸዋል፡፡ ድጋፉ ትንሽ ቢሆንም ፍቅርና አክብሮትን ለመግለጽ ጭምር የተደረገ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ከዚህ ችግር ወጥተን ወደ ልማትና ዕድገት ጉዟችን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንመለሳለን በማለት እምነታቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ተደጋግፎና ተባብሮ ይህንን ጊዜ ማሳለፍ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡   

በዕለቱ የተሰጠውን ድጋፍ የተረከቡት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ወንድአወቅ አብጤ (ኢንጂነር) የብዙ አገሮችን ቅስም የሰበረው ይህ ወረርሽኝ ሲያጠቃና ሲቀጥል እንጂ ሲመጣ የማይታወቀውን ይህንን በሽታ ሁላችንም ተባብረን የበኩላችንን መወጣት አለብን ብለዋል፡፡ ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል ለሚደረገው ርብርብ እጃችሁን በመዘርጋትና ያላችሁን በማካፈል ይህንን ጊዜ ተጋግዘንና ተባብረን እንድናልፍ ላደረጉት ዕገዛ የዕለቱን ድጋፍ ሰጪዎች አመስግነዋል፡፡ እንዲህ ያሉ በጎ እጆች አሁንም ያስፈልጉናልም ብለዋል፡፡

በዕለቱ በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ካደረጉት መካከል ሀሮን ኮምፒውተር 300 ሺሕና  አዲስ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ አክሲዮን ማኅበር 500 ሺሕ ብር በመስጠት አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡ አቶ ብርሃኔ ግደይ፣ ተወልደ ብርሃን ጎይቶም፣ ፋኑኤል ተመስገን፣ ፊልጆና ቤተሰቡ፣ መሰማ ሺኢቦ ሰሜን ሆቴል ደግሞ 100 ሺሕ ብር ከሰጡት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

በዕለቱ ለተከታዮች ዋጋ መቀነሳቸውን ካስታወቁት ውስጥ ቤቶ ሪል ስቴት፣ ዳማ ትሬዲንግ ለተከራዮች የ50 በመቶ ቅናሽ አድርገዋል፡፡ ይህም አንድ ሚሊዮንና 1.5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ነው፡፡ በተመሳሳይ ዲኤች ገዳ ታወር ለሦስት ወር የሚቆይ የ50 በመቶ ቅናሽ አድርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች