Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሜይደይ እንዳይከበር ባስገደደው ኮሮና ሰበብ ሠራተኞችን የሚበድሉ ተቋማት መታየታቸውን ኢሠማኮ አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በየዓመቱ በመላው ዓለም የሚከበረው የዓለም የሠራተኞች ቀን እንደቀደሙት ዓመታት በአደባባይ በሚሰናዱ ዝግጅቶችና ቀኑን ለመዘከር በሚካሄዱ ትዕይቶች ዘንድሮን ማክበር አልተቻለም፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ሚያዝያ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. የዋለውን የሠራተኞች ቀን፣ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት እንደ ቀድሞው ለማክበር ባለመቻሉ ዕለቱን በመግለጫ ብቻ ለማለፍ እንደተገደደ አስታውቋል፡፡ በየዓመቱ ለዕለቱ መግለጫ መሪ ቃል በማዘጋጀት የሚያከብረውን ‹‹ሜይዴይ›› ዘንድሮ አልፎታል፡፡

ወረርሽኙን ለመከላከል በጋራ እየተረባረቡና የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚመለከታቸው ሁሉ እየሠሩ እንደሚገኙ በተለይም በዚህ ወቅት መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት ያደነቁት የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ በሌላ በኩል ግን በዚህ አስከፊ ወቅት የሠራተኞችን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራት እንደተስተዋሉ አስታውቀዋል፡፡

ሚያዝያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ስለዘንድሮ ሜይዴይ አቶ ካሳሁን በሰጡት መግለጫ፣ ይህ የዓለም ሠራተኞች የመብት ትግል የሚዘከርበት ዕለት፣ ከወትሮው ይልቅ ፈታኝ በሆነ ወቅት ተከብሯል ብለዋል፡፡ መላው ሠራተኛ በያለበት በዓሉን የሚዘክረው፣ መላው ዓለምን በፍጥነት በማዳረስ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ብሎም የሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ የሚገኘውን የኮሮና ወረርሽኝ  የመከላከል ሥራዎች እየተስፋፉ የሚገኙበት ጊዜ በመሆኑ ነው፡፡

‹‹ራሳችንና ማኅበረሰባችንን ከወረርሽኙ በመከላከል ምርታማነትን እናስቀጥል፤›› በሚል መሪ ቃል ሠራተኛው ክፍል ሜይዴይን አስቦት እንዳለፈ አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡ ይህ ወረርሽኝ ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ሠራተኞች ላይ ጥቁር ደመናውን በማጥላት ከ200 ሺሕ በላይ ሰዎችን የቀጠፈ በሽታ ነው ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ኃያላን መንግሥታትን ያንበረከከ፣ መድኃኒት ያልተገኘለትና በአንድ ጊዜ ዓለምን ያዳረሰ፣ ዓለም አቀፍ ቀውስ ያስከተለ ወረርሽኝ በመሆኑ ለመከላከለል ርብርብ ማድረግ ግድ እንደሚል ገልጸዋል፡፡ ወረርሽኙን መንግሥት ለብቻው አልያም አሠሪው ያለ አጋዥ፣ ሠራተኛው ወገን ብቻውን ሊወጣው የማይቻለው ከባድ አደጋ በመሆኑ በመተባበርና በመደጋገፍ ማለፍ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ በኮሮና ምክንያት የሠራተኛውን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች እየተከሰቱ እንደሚገኙ የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል ከመንግሥትና ከአሠሪዎች ጋር በመተባበር ሠራተኞች ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ በተፈጠረው ቀውስም የድርጅቶች ህልውናና የሠራተኛው የሥራ ዋስትና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የሚደግፍ የሥራ ቦታ ፕሮቶኮል መውጣቱን አቶ ካሳሁን አስታውሰዋል፡፡ አብዛኛዎቹ አሠሪዎችና ባለሀብቶች ተግባራዊ ቢያደርጉትም ይህንን ስምምነት የጣሱ ተግባራት ታይተዋል ብለዋል፡፡ ጥቂት አሠሪዎችና ባለሀብቶች በሽታውን ለመከላከል በሥራ ቦታ መተግበር የሚጠበቅባቸውን የቅድመ ጥንቃቄ ሥርዓት ባለመተግበር ብሎም የሠራተኛውን የሥራ ዋስትና ችግር ላይ በመጣል ስምምነቱን እየጣሱ ይገኛሉ፡፡

በመንግሥት በሥራ ቦታና ከሥራ ውጭ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች የተቀመጡ አሠራሮች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ክፍተቶች እየታዩ በመሆናቸውም እንዲታረሙ ተጠይቋል፡፡

‹‹አገራችን ደሃ ነች፡፡ እንዲህ ላለ ያልተጠበቀ ግዙፍ ወረርሽኝ መከላከለያ እርሾ የላትም፡፡ ስለዚህ መንግሥት እንደሌሎች አገሮች ሕዝቡን ይደጉም ቢባል ብዙ ሥራ አጥ ባለበት፣ ሥራ ላይ ያለውም ተጨምሮበት የመሸከም አቅም ያንሰዋል፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ድርጅቶች የቀጠሩትን ሠራተኛ ብቻም ሳይሆን ሌላውንም ማኅበረሰብ እንደሚደግፉ በመግለጽ ለሠራተኛው ዋስትና መሆን እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡ ‹‹እናንተ ቀጥራችሁ በድርጅታችሁ ሲያመርት የነበረውን ይቅርና ሌላውንም ማኅበረሰብ ስትረዱ እናያለን፡፡ ይህ የተቀደሰ፣ የሚበረታታና ምሥጋናም የሚያስፈልገው ተግባር ነው፡፡ ሠራተኞቻችሁ የቤተሰባችሁ አባላት እንደ ማለት ናቸው፡፡ የሕግ አንቀፅ እያነሳን የምንከራከርበት ጊዜ ሳይሆን፣ ያለው ለሌለው እያካፈለ የሰው ሕይወት ለማዳን የምንረባረብበት ጊዜ ነው፤›› በማለት ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን ከሥራ ገበታ እንዳያፈናቅሉ ተማጽነዋል፡፡  

መንግሥት ለሠራተኞች በማሰብ ጭምር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለድርጅቶችና ለባለሀብቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገንዝበናል ያሉት አቶ ካሳሁን፣ የወረርሽኙን አደጋና ቀውስ ለመከላከል እየወሰደ ላለው ፈጣንና ተከታታይ ዕርምጃ መመስገን አለበት፡፡

በሌላ በኩል የመላው ሠራተኞች መብትና ጥቅሞቻቸው፣ በተለይም መሠረታዊ የመደራጀትና የመደራደር መብቶች ከወረርሽኙ በፊትም በሕግ አግባብ በአንዳንድ ድርጅቶች ሳይተገበሩ ቢቆዩም፣ በአሁኑ ወቅትም ቢሆን እነዚህን መብቶችና ጥቅማ ጥቅሞች ለማስከበር የመብት ጥያቄ የሚያስተጋባበት ወቅት እንዳልሆነ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በአንፃሩ በዚህ ክፉ ጊዜ ከሥነ ምግባር ጉድለት ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ መውሰድ ይቻላል በመባሉ ምክንያት፣ አጋጣሚውን እየተጠቀሙ በሕገወጥ መንገድ ሠራተኛውን ከሥራ የማገድና የማሰናበት ዕርምጅ የሚወስዱ አሠሪዎች እየታዩ ነው ብለዋል፡፡ 

ከዚህ አልፎም የሠራተኛ ማኅበራትን የሚያፈርሱ ድርጅቶች እንዳሉም አቶ ካሳሁን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ፍርድ ቤቶችም በአብዛኛው ዝግ በመሆናቸው ቅሬታ አቅርበው መፍትሔ የሚያገኙበት መንገድ ባለመኖሩ፣ ያለ ጥፋታቸው በአሠሪው ብያኔ ከሥራ ተባረው ከነቤተሰቦቻቸው ለረሃብ ተጋልጠዋል፤›› በማለት ሁኔታውን አብራርተዋል፡፡ ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅጁን የማስፈጸም ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግሥት አካላት በአስቸኳይ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስዱ ኢሠማኮ ጥሪ ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች