Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለመዳን ማዳን ይቅደም!  

ዓለም በሕመም ውጋት እያማጠች ትገኛለች፡፡ ከሁሉም አቅጣጫ የሕመምና የሥቃይ ድምፆች እየተስታገቡ ነው፡፡ ሀብትና ሥልጣኔ የማይመክቱት ወረርሽኝ ሚሊዮኖችን በሕመም፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ትንፋሽ አሳጥቶ ለሞት አብቅቷቸዋል፡፡

በየደቂቃው በኮሮና ምክንያት ሰዎች ይሞታሉ፡፡ በየደቂቃው በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥራቸው የትዬ ለሌ እየሆነ ነው፡፡ ‹‹ከቤት አትውጡ››፣ ‹‹እጃችሁን አዘውትራችሁ ታጠቡ››፣ ‹‹ርቀታችሁን ጠብቁ›› እየተባለ ከሚስተጋባው ሌላውም ዓይነት የጥንቃቄ መመሪያ በቀር ፈውስ ያልተገኘለት የኮሮና ወረርሽኝ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ መላ ተገኝቶለት የዓለም ሰቆቃና ጥፋት መቀነስ የሚችልበት የተስፋ ጭላጭል ስለመኖሩ ደፍሮ መናገር አልተቻለም፡፡ በመሆኑም ሞት እየበረከተ ነው፡፡

በበሽታው ምክንያት የሚከሰተው ስቃይና ሞት፣ ከዚህ በመለስ እያደረሰ የሚገኘው ሥነ ልቦናዊ ቀውስ እየጨመረ ነው፡፡ ወረርሽኙን አስከፊ የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ የሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መባባሱ ነው፡፡ አገሮች እንቅስቃሴ አቁመዋል፡፡ ምርት ተቋርጧል፡፡ አምራች ኃይሎች ያለ ሥራ ቤት ውለዋል፡፡ በፈረጠመ የኢኮኖሚ ጉልበታቸው፣ በመጠቀው ቴክኖሎጂያቸው ዓለምን የተቆጣጠሩ አገሮች፣ በአመራራቸው ስንፍናና ችግር ጭምር ከወርሽኙ አደጋ መውጣት ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡ ቢሊዮን ዶላሮች የወጡባቸውና ቢሊዮን ዶላሮች የሚያንሳቅሱ አውሮፕላኖቻቸው እንደዘበት በየኤርፖርቱ ታጭቀው ያለ ሥራ ለመቆም ተገደዋል፡፡ ንሥረ ሰማዮች፣ የሰማዩን ደመና የሚቀዝፈው ክንፋቸው ታጥፏል፡፡ ፋብሪካዎች ድምፃቸው ተለጉሟል፡፡ ዓለም ኦና ሆናለች፡፡ የሰው ልጅ ማኅበራዊ ማንነቱን ተነጥቋል፡፡ ገብይቶ፣ ሸቅጦና ሸምቶ መግባት  አልቻለም፡፡ የሚሠሩ እጆች እንዲሰበሰቡ ተገደዋል፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ ለበሽታ ተንበርክኳል፡፡ ዓለም ወድቃለች፡፡

ችግሩን ወደ ክፍለ አኅጉራችን አምጥተን ስናየው፣ ወረርሽኙ ከወረራቸውና ከዘረራቸው ሀብታም አገሮች የከፋ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል በርካቶች ያስተጋባሉ፡፡ ይህ በእጅጉ ያሳስባል፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት በአፍሪካ የተጠቁና የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከአውሮፓና ከሰሜን አሜሪካ ብሎም ከእስያ አኳያ አነስተኛ ነው፡፡ ነገር ግን አፍሪካ ካላት ደካማ የጤና ሥርዓት አኳያ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ብዛት በቅጡ ለመለየት አዳጋች እንደሚሆን የሚያመላክቱ መረጃዎች መበራከታቸው የአፍሪካውያንን ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

እርግጥ ነው በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ተገቢውን የጥንቃቄና የመከላከል ሥራ በመሥራት የበሽታውን መስፋፋት መግታት እንደሚቻል የሚያምኑና ስለ በሽታው የሚሠራጩ መረጃዎች ‹‹አሸባሪ ናቸው›› በማለት ጭምር የሚሞግቱ አልታጡም፡፡ የምዕራቡ ዓለም መንግሥታት ቸልተኛነትና ግዴለሽነት ያስከተለው ቀውስ እዚህ እንዳይከሰት መከላከልና መጠንቀቅ እስከተቻለ ድረስ ችግሩን ያለ ከባድ ኪሳራ ማለፍ እንደሚቻል የሚጠቅሱ ድምጾች ልብ ያላሉት ሌላ ዳፋ አለ፡፡ የኢኮኖሚ ጉዳት፡፡

በአብዛኛው የአፍሪካ ክፍልም ሆነ በአገራችን አስፈሪ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል የሚጠቀሰው በምዕራቡ ዓለም ከሚታየው የጤና ቀውስ አኳያ ብቻም ሳይሆን፣ በደካማ ኢኮኖሚያቸው ላይ ተጨማሪ ተፅዕኖ የሚፈጥር ብርክ ብርክ የሚያሰኘው አደጋ መከሰቱ ነው፡፡ የቱንም ያህል ዝቅተኛ የኮሮና ታማሚዎችና ሟቾች ቁጥር እያስተናገዱ ቢገኙም፣ ከወዲሁ ከባድ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አደጋ እያንዣበባቸው ይገኛሉ፡፡

ስለዚህ ኮሮና ለእኛ የሚያስፈራን ከዜጎቻችን ሞት ባልተናነሰ ኢኮኖሚያዊ ድቀቱ ይዞት የሚመጣው ወይም ይዞት የመጣው መዘዝ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍልና ይህም ገና ከአሁኑ የመታየቱ ነገር ሥር ከመስደዱ በፊት ባለ ኃይልና አቅም መፍትሔ ማፈላለጉ ላይ በርትቶ መሥራት ይጠይቃል፡፡

ስለዚህ የእኛ ፈተና ገና እየጀመረ እንደመጣ የሚያሳዩ ምልክቶችና ተፅዕኖዎች እየታዩ ነው፡፡ በመሆኑም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችን ለመቀነስ የሚረዱ የመከላከል ጥረቶች ላይ መትጋት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

በአገራችን ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሲደረግ የሚታየው ርብርብ፣ በመንግሥት ውሳኔዎች እየተደገፈና እየተመራ ሕዝብም የአቅሙን እያገዘ ቢሆንም፣ ውጤታማ እንዲሆን ግን ተቀናጅቶ መሥራትና መናበብ እንደሚያስፈልገው የታመነ ነው፡፡ እሳት የማጥፋት ሥራው እንደተጠበቀ ሆኖ ችግሩን መሻገር እስኪቻል ድረስ የትኛው አካባቢ፣ የትኛው የሥራ መስክና ዘርፍ የበለጠ ሊደገፍና ሌላውን ሊደግፍ ይችላል? የሚለውን በሚገባ መርምሮ፣ ፈትሾና ተመካክሮ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ በተጠና፣ በተደረጃና በተባበረ ክንድ ሁሉንም የሚያሰልፉ ዕርምጃዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ከሁሉ በላይ የአስቸኳይ ጊዜ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ በሚገባ የታሰበባቸው ውሳኔዎች በአግባቡ መተግበራቸውን ማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተናበው አንዱ ለሌላው መውደቅ ሳይሆን፣ ለሌላው መነሳት ዕድል የሚሰጡበት ሁኔታ እንዲፈጠር መደረግ አለበት፡፡

በጠቅላላው የሁሉንም ወገን ርብርቦሽ የሚጠይቁ፣ በስምምነትና በመደጋገፍ በሚሠሩ ሥራዎች አማካይነት ኢኮኖሚው የበለጠ እንዳይጎዳ ሁሉም የጀመረውን ዳር ማድረስ አለበት፡፡ የአንዱ ህልውና ለሌላው መሠረት የሆነበት ጊዜ ላይ እንገኛለንና መተባበርና መተጋገዝ የመንግሥት ወይም የእገሌ የሚባልበት ምርጫ የለም፡፡

በአገር ጉዳይ መምከርና መላ መፈለጉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ቁልፍ አጀንዳ ግን ሕዝብ ነው፡፡ የሕዝብና የአገር ሕልውና ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም የውዴታ ግዴታ የሚጠይቅ ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ሰዎች ለሕግ ተገዥ ካልሆኑ ራስንም አገርንም ወደፊት ማራመድ አይችልም፡፡

ከሰሞኑ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚሰነዘሩ አላስፈላጊ ንትርኮች ያለንበትን ወቅት የማይመጥኑ ሆነዋል፡፡ በቅን ልቦና ለኢኮኖሚው መፍትሔ አማራጭ ሐሳቦችን በመተግበር ሌላውን ሌላ ጊዜ እንደርስበታለን ማለት ካልተቻለ አደጋው ይበረታል፡፡ የከፋ ውድቀት ያመጣል፡፡ ኃይላችንን በንትርክ ከማዳከም መንግሥትም ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያደርገውን እልህ አስጨራሽ እንቅስቃሴ ከማስተጓጎል መቆጠብ ለራስ ነው፡፡ ለፖለቲካ ጥቅም ተብሎ ግድፈትን እያገዘፉ መጯጯህ ብዙ አያራምድም፡፡ ጊዜው ውስጣዊ ጥያቄን በውስጥ ይዞ በትብብር በአንድ ክንድ የሚሠራበት ነው፡፡ አገር የምትጋፈጠውን ቀውስ ምንም እንዳልተፈጠረ በማስመሰል የሚያዘናጋ አጀንዳ ማራገብ ለአስከፊ የበሽታ እልቂት የሚጋብዝ፣ ለረሃብ አደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ ኢኮኖሚውን መታደግ ይገባል፡፡ ሕዝብን ማሻገር ካልተቻለና ኢኮኖሚውን በሚደግፉ ሥራዎች ላይ ካላተኮርን በቀር በራሳችን ችግር የተሳነ በአስቀያሚ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ለማለፍ እንገደዳለን፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት