የአገሪቱ የበላይ ሕግ የሆነው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የፖለቲካ ሥልጣን የሚያዝበት ብቸኛው መንገድ ምርጫ መሆኑን፣ ይኸውም በየጊዜው መካሄድ (Periodically) እንዳለበት ያስቀምጣል።
ይህንን መርህ መሠረት በማድረግም በምርጫ አማካይነት የሚያዝያ የፖለቲካ ሥልጣን ዘላቂ ሳይሆን የጊዜ ገደብ የሚደረግበት፣ በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥም ማኅበረሰቡ የፖለቲካ ፍላጎቱን መሪዎቹን ከሥልጣን በማውረድ፣ በመቀየር ወይም በማስቀጠል የሚገልጽበትን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ተክሏል። ይህ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በዋናነት የተደነገገው በአንቀጽ 58(2) ላይ ሲሆን ድንጋጌውም፣ ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው። የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሄዶ ይጠናቀቃል፤›› የሚል ነው። በዚህ መሠረት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ በየአምስት ዓመቱ አምስት አጠቃላይ ምርጫዎች (ዴሞክራሲያዊነቱ ላይ ከሚነሳው ክርክር ባሻገር) ተካሂደዋል፡፡
ይሁን እንጂ በተቀመጠው የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ምርጫ ለማከናወን የማይቻልበት ከአገሪቱ አቅም በላይ የሆነ ዕክል ቢከሰትና በሥልጣን ላይ የሚገኙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤቶች የሥልጣን ዘመን ቢጠናቀቅ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ያስቀመጠው ይህ ዓይነቱን ሁኔታ ማለፊያ ሕገ መንግሥታዊ ሥነ ሥርዓት የለም።
ይህ ሕገ መንግሥት ባለፈባቸው 25 ዓመታት የተከናወኑ ምርጫዎች ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት እክል ሳይገጥማቸው የተከናወኑ በመሆናቸው፣ ይኼንን የሕገ መንግሥቱን ጉድለት ቀድሞ ያስተዋለና መፍትሔ ለመስጠት የሞከረ የለም።
በመሆኑም የሕገ መንግሥቱ ጉድለት ዘንድሮ (2012 ዓ.ም.) በገሃድ ከመጣበት ተግዳሮት ጋር ሲፋጠጥ ፍንትው ብሎ ታይቷል። በ2007 ዓ.ም. በተደረገው አጠቃላይ ምርጫ የተመረጡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም በእነሱ የተቋቋሙት የፌዴራልና የክልል ሥራ አስፈጻሚ መንግሥታት የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸውን በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም. የሚያገባድዱ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እነሱን የሚተኩ ምክር ቤቶችን ለመምረጥ በነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. አጠቃላይ ምርጫ ለማካሄድ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ዝግጅቶችን በማከናወን ሒደት ላይ ነበር።
ይሁን እንጂ በጥር ወር 2012 ዓ.ም. ገደማ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት መከሰቱና ወደ ኢትዮጵያም ተዛምቷል። የቫይረሱ ሥርጭት ከነበረበት መለስተኛ የሥርጭት ሁኔታ በማየሉ፣ የዓለም የጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢና የሕዝብ ጤናን የሚጓዳ ወረርሽኝ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን፣ ይኼንንም ተከትሎ በርካታ አገሮች የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን በማወጅ የሰዎች እንቅስቃሴ እንዲገደብ፣ እንዲሁም የሰዎች በአንድ ቦታ መሰባሰብ እንዲገታ የማድረግ ዕርምጃዎችን ወስደዋል።
በኢትዮጵያም መሰል ዕርምጃዎች በመንግሥት የተወሰዱ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን በተያዘው ወቅት ለማካሄድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በማስተጓጎሉ የምርጫ ሰሌዳውን እንዲሰርዝ አስገድዶታል።
በዚህም የተነሳ ምርጫውን ለማካሄድ እንደማይችል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማሳወቅ፣ ምክር ቤቱም ሚያዚያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የቦርዱን ውሳኔ ተቀብሎ አፀድቆታል።
በተጨማሪም ምርጫውን ለማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ በመፈጠሩና ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥልጣን ዘመኑን ማጠናቀቁ የሚፈጥረውን የሥልጣን ክፍተት ወይም በሥልጣን ላይ መቆየት የሚያስከትለውን የቅቡልነት ጥያቄ እንዴት መፍታት እንደሚቻል፣ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን መሠረት ያደረገ የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብለት ኃላፊነቱን የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዚሁ ቀን ሰጥቷል።
ከሰሞኑም ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትና ፖለቲከኞች ይህንን ሕገ መንግሥታዊ ቅርቃር ለመፍታት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጉድለቱን ወደ መልካም ፖለቲካዊ አጋጣሚ ለመቀየር ከፍ ዝቅ እያሉ ይገኛሉ። ከዚሁ ጎን ለጎንም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የሕገ መንግሥት ምሁራንና ተመራማሪዎች ውስብስቡን ለመፍታት የበኩላቸውን ትኩረት በመስጠት መውጫ ምክረ ሐሳብ እየሰነዘሩ ናቸው።
መንግሥት ለውይይት ያቀረባቸው አማራጮች
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በራሱ የአሠራር ሥነ ሥርዓት የመፍትሔ አማራጮች ተጠንተው እንዲቀርቡለት ውሳኔ ሲያሳልፍ፣ ከዚህ ቀደም ብሎ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ገለልተኛ ምሁራንን በማሰባሰብ በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ይኼንን ሕገ መንግሥታዊ ቅርቃር ለማለፍ የሚቻልባቸውን የመፍትሔ አማራጮች እንዲጠኑ በማድረግ፣ የጥናቱን ውጤት ለፖለቲካ ፓርቲዎች አቅርቦ ምክክር እያደረገበት ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት ለውይይት እንዲቀርብ የተደረገውን ባለ አራት ነጥብ የመፍትሔ አማራጮች የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የሌሎች ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተገኙበት ያቀረቡት ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ናቸው። እሳቸው ባቀረቡት በዚህ የጥናት ውጤት ላይ የተካተቱት ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረጉ አራት የመፍትሔ አማራጮች ናቸው።
እነዚህም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60 መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲበተን ማድረግ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 (ሀ) መሠረት ተጥሎ በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማራዘም፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105 (2) መሠረት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 እና 84 መሠረት የሕገ መንግሥት ትርጉም በመጠየቅ መፍትሔ ማበጀት የሚሉ ናቸው።
ጌዲዮን (ዶ/ር) ያቀረቧቸውን አራት የመፍትሔ አማራጮች ሕጋዊነት፣ እንዲሁም ጥንካሬና ደካማ ጎናቸውን በመዘርዘር ከቀረቡት አማራጮች ውስጥ በአራተኛ አማራጭነት የቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚለው የተሻለ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የአማራጮቹን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በተመለከተ ባቀረቡት ትንታኔም አማራጭ አንድ የቀረበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን በሚል የቀረበው አማራጭ አንድ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60 (1) ላይ የተደነገገ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክር ቤቱ የሥልጣን ዘመን ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ማድረግ እንደሚችሉ የሚገልጽ ነው።
በዚህ አንቀጽ እንደ ሠፈረው ምክር ቤቱ የተበተነ እንደሆነ ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲረደረግ የሚደነግግ ሲሆን፣ ይህንን አንቀጽ ተግባራዊ ማድረግ ምርጫውን እስከ የካቲት ወር 2013 ዓ.ም. ለማራዘም እንደሚያስችል አመልክተዋል። ይህንን አንቀጽ ተግባራዊ ለማድረግ የሚጠይቀው የምክር ቤቱን አብላጫ ድምፅ ማግኘት በመሆኑ፣ ሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥትም በምክር ቤቱ ያለው መቀመጫ ይህንን በቀላሉ ለመተግበር የሚያስችለው መሆኑን በጥንካሬ አንስተውታል።
ይህ አካሄድ በፓርላሜንታዊ ሥርዓት የተለመደና የራሱ ውስንነቶች እንዳሉት የገለጹት ጌዲዮን (ዶ/ር)፣ በዚህ አማራጭ ምክር ቤቱ እንዲበተን በማድረግ ምርጫውን ለማካሄድ ተጨማሪ ስድስት ወራትን ማግኘት የሚያስችል ቢሆንም፣ የራሱ ጉድለቶች እንዳሉት ጠቁመዋል።
ለአብነትም ምክር ቤቱ ከተበተነ በኋላ አገሪቱን የሚመራው የፖለቲካ ድርጅት የመንግሥትን የዕለት ተዕለት ሥራ ከማከናወንና ምርጫን ከማካሄድ በስተቀር አዲስ አዋጆችን፣ ደንቦችንና ድንጋጌዎችን ማውጣት ወይም ነባር ሕጎችን መሻርና ማሻሻል የማይችል መሆኑን፣ ይህም ለተለያዩ ፈተናዎች በቂ ምላሽ ለመስጠት የሚችል ሙሉ መንግሥት እንዳይኖር እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በክልሎች ሕገ መንግሥት መሠረት ተመሳሳይ አማራጭ የሌለ በመሆኑ፣ አማራጩን የተሟላ እንደማያደርገው በድክመትነት አውስተዋል። በሁለተኛ አማራጭነት የቀረበው የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 93 በመጠቀም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማራዘም በድንጋጌው እንደ ሰፈረው ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 1፣ 18፣ 25 እና 39 (1) እና ( 2 ) በስተቀር ሌሎች የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎችን መገደብ የሚያስችል በመሆኑ፣ የአስቸኳይ አዋጁ ጊዜ እስከሚጠናቀቅበት የሕግ አግባብ ድረስ የምርጫ ጊዜን ማራዘም እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ይህ አማራጭ አስፈላጊው ሥልጣንና ኃላፊነት ያለው መንግሥት በሥልጣን ላይ እንዲቆይ የሚያስችልና በአገር አቀፍ ደረጃም ተፈጻሚነት የሚኖረው መሆኑ በጥካሬነት ተጠቅሷል።
ነገር ግን ይህ አማራጭ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የሚካሄድ ምርጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ያጠላበት ስለሚሆን፣ የምርጫውን ተዓማኒነትና ነፃነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚጥልና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዳይዳብር አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
በሦስተኛ አማራጭነት የቀረበው ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል መፍትሔ አዎንታዊ ገጽታው ሕገ መንግሥታዊ መሆኑ ብቻ እንደሆነ አመልክተዋል። መላውን ሕዝብ ያሳተፈ ውይይት ማድረግ።
ይኼንን አማራጭ ተግባራዊ ለማድረግ የሚጠይቀው የማሻሻያ ሐሳቡን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በሁለት – ሦስተኛ ድምፅ እንዲያፀድቁት፣ በተመሳሳይም ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት የክልል ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ እንዲያፀድቁት ማድረግን እንደሚጠይቅና አሁን ሥልጣን ላይ ለሚገኘው ፓርቲ በቀላሉ ሊተገበር የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።
ነገር ግን ይህ አማራጭም የራሱ ውስንነቶች እንዳሉት፣ ከእነዚህም መካከል የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ ዜጎችን ማወያየት የሚጠይቅ መሆኑና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ይህንን ማድረግ የማይቻል በመሆኑ፣ የዜጎችን በአገራቸው ጉዳይ የመሳተፍ መብት የሚገድብ እይደሆነ ገልጸዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚደረግ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የቅቡልነቱ ጥያቄ እንደሚያስነሳ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሚነሱ ሌሎች የማሻሻያ ፍላጎቶችን አብሮ ለማየት ምቹ ጊዜ አለመሆኑን በአሉታዊ አማራጭነት ሥር የሚወድቅ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።
በአራተኛ አማራጭነት የቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(1) እና አንቀጽ 84(1) መሠረት የሚቻል መሆኑን ያወሱት ጌዲዮን (ዶ/ር)፣ ይህ አማራጭ የሕገ መንግሥት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችል የተለመደ አሠራር መሆኑንና በሕገ መንግሥቱ የተሻለ ተቀባይነት ያለው አካሄድ እንደሆነ ተናግረዋል። በዚህ አማራጭ ውስጥ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38 ላይ የተደነገገውን የዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብት፣ በአንቀጽ 58 ላይ ስለምክር ቤቱ የሥራ ዘመን የተቀመጠውን ድንጋጌና በአንቀጽ 93 ላይ ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተመለከተውን ድንጋጌ አጣምሮ በመመልከት፣ የሕገ መንግሥቱን ጉድለት ለማስወገድ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
ይህ አማራጭ ከሌሎቹ የተሻለ ቢሆንም የራሱ ውስንነቶች እንዳሉት፣ ከእነዚህም መካከል በዚህ ሒደት የሚገኘው ውጤትን በእርግጠኝነት ቀደም ብሎ መተንበይ የማይቻል መሆኑን፣ እንዲሁም የአሳታፊነት ውስንነት ጥያቄ ሊነሳበት የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል።
የገለልተኛ ምሁራንና የፖለቲከኞች ምልከታ
በመንግሥት የቀረቡትን አማራጮች የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተቀበሏቸው የመሆኑን ያህል አማራጮቹን ሙሉ በሙሉ የሚቃወሟቸውም አሉ። እነዚህ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል ዕይታቸው የሚጋሩት አንድ ነጥብ አገሪቱ አሁን የገጠማትን ቀውስ ለማለፍም ሆነ የፖለቲካ መረጋጋትን ለማስፈን ጠቃሚው፣ የሽግግር መንግሥትን በአማራጭ መፍሔነት የሚያነሱ መሆናቸው ነው።
በሌላ በኩል የተለያዩ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የሕገ መንግሥት ምሁራን በጉዳዩ ተስበው የበኩላቸውን ሙያዊ ዕይታ በማኅበራዊ ድረ ገጾች እያቀረቡ ይገኛሉ። የሰብዓዊ መብትና የሕገ መንግሥት ጉዳዮችን ያጠኑት የሕግ ምሁሩ በሪሁን አዱኛ (ዶ/ር)፣ በመንግሥት በኩል ከቀረቡት አማራጮች መካከል የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ ተመራጭ ከሚሆን ይልቅ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ የተሻለ መሆኑን ይከራከራሉ። የተከሰተውን የሕገ መንግሥት ውስብስብ ለመፍታት የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ ከሌሎቹ አማራጮች ይልቅ ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ ውጤት አነስተኛ በመሆኑ አተመራጭ ቢመስልም ይኼንን ለመተግበር የትርጉም ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የማቅረብ ኃላፊነት ከመንግሥት ወይም የመንግሥት ኃላፊነትን በያዘው ብልፅግና ፓርቲ ላይ የወደቀ መሆኑን፣ ትርጓሜውን የሚሰጠውም አካል በዚሁ የፖለቲካ ፓርቲ የተያዘ በመሆኑ የሚሰጠው ትርጓሜ የመንግሥትን ፍላጎት የሚጠቅም የመሆኑ አይቀሬነት መፍትሔውን የቅቡልነት ችግር ውስጥ ይከተዋል ይላሉ።
ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል የተሻለ መፍትሔ እንደሆነ የሚመክሩት በሪሁን (ዶ/ር)፣ ይህ አማራጭ የተሻለ ነው ያሉበትን ምክንያት ሲዘረዝሩም ሒደቱ የተለያዩ ባለድርሻዎችን ለተሳትፎ የሚጋብዝና የሐሳብ ሙግቶችን የሚፈጥር እንደሆነ፣ ይህም በሥልጣን የሚቀጥለው መንግሥት ቅቡልነትን እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ያወሳሉ።
በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ሒደት በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ የሚከናወን በመሆኑና በአጣብቂኝ ወቅት ውስጥም ችግሩን ለመፍታት ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ መሆንን በድርጊት ለመግለጽ የሚያስችል መሆንን በመግለጽ፣ ይህ መፍትሔ ተግባራዊ እንዲደረግ ይመክራሉ።
ሌላው የሕገ መንግሥት ምሑርና የሕግ አማካሪ የሆኑት ያሬድ ለገሠ (ዶ/ር) ግን፣ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል በአማራጭነት አይቀበሉትም። አሁን ያለውን ቅርቃር የፈጠረው የቫይረስ ወረርሽኝ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ወሳኝና ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ የሆነውን የሕዝብ ተሳትፎ ማረጋገጥ የማያስችል በመሆኑ ተገቢ አማራጭ ሊሆን እንደማይችል የሚገልጹት ያሬድ (ዶ/ር)፣ በሕዝብ ተሳትፎ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል የሚቻል ከሆነ ምርጫውንም ማከናወን የሚቻል በመሆኑ ጉዳዩን በአማራጭ መፍትሔነት ማንሳትም እንደማያስፈልግ ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ምርጫውን ለማራዘም ውሳኔ ከሚሰጡት ተቋማት መካከል ዋነኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ፣ ይኼንን አማራጭ መከተል ምክር ቤት የራሱን የሥልጣን ዘመን እንዲያራዝም የመፍቀድ ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ አሉታዊ አንድምታን እንደሚያስከትል ያስረዳሉ።
እንደ እንግሊዝ ባሉ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ምክር ቤት (ፓርላማ) የራሳቸውን የሥልጣን ዘመን ማራዘም የሚችሉ ቢሆንም፣ ይህ የሆነበት ምክንያት በእነዚህ አገሮች ፓርላማዎች የሉዓላዊነት መገለጫ ከመሆናቸው እንደሚመነጭ ያስረዳሉ። በኢትዮጵያ ግን የሉዓላዊነት መገለጫ ሕገ መንግሥቱ በመሆኑ፣ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል የኢትዮጵያ ፓርላማ የራሱን የሥልጣን ዘመን እንዲያራዘም መፍቀድ ሕገ መንግሥቱን መጣረስ እንደሆነ ይሞግታሉ።
በመፍትሔነትም ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ መጠየቅ የተሻለ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ያሬድ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።
ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም የተለያዩ አማራጮችን እየሰነዘሩና የምሁራን ሙያዊ ክርክር የጎላበት ሁኔታ የተፈጠረውን የሕገ መንግሥት መወሳሰብ ለመፍታት እየተጠበቀ፣ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ በአጭር ጊዜ እንዲያቀርብ የታዘዘው የውሳኔ ሐሳብ ምን ዓይነት መልስ ይዞ እንደሚመጣ በርካቶች በጉጉት እየጠበቁት ነው።