ኖቭል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) በዓለም ላይ ከተከሰተ አምስት ወሩን ይዟል፡፡ ይሁን እንጂ በሽታውን ለማከም ሆነ ይህ ነው ብሎ የተሟላ መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ የመተላለፊያ መንገዶቹን ለይቶ በማውጣት ሕዝቦች የራሳቸውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከማድረግ ባለፈ ለኮቪድ 19 የሚመጥን መድኃኒት አልተገኘም፡፡ የታመሙ ሰዎች የሚያገግሙበት፣ የሚድኑበት ወይም የሚሞቱበት ምክንያት ከየትኛው አካላዊ ሥርዓት መዛባት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ለማወቅ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ተመራማሪዎች በምርምሩ ሥራ ተጠምደዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅትም ስለበሽታው አጠቃላይ ሁኔታ የሚያሰፍርበት ድረ ገጽ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ከሚሰጠው ማብራሪያ ግርጌ ብዙዎቹ ነገሮች በጥናት ላይ መሆናቸውንና ጥናቱ ሲጠናቀቅ ተጨማሪ መረጃዎች እንደሚለቀቁ አስቀምጧል፡፡
የመተንፈሻ አካልን ብሎም ኩላሊትን በመጉዳት ከዝቅተኛ ሕመም እስከ ሞት የሚያደርሰውን ኮቪድ 19 ለመግታት አገሮች ርብርብ ቢያደርጉም ሕዝባቸውን ከበሽታው ለመከላከልም ሆነ ከሞት ለመታደግ አላስቻላቸውም፡፡ ሩብ ሚሊዮን አካባቢ ሲሞቱ ከሦስት ሚሊዮን በላይ በበሽታው ተይዘዋል፡፡ ከተያዙት አንድ ሦስተኛ ያህሉ ደግሞ አገግመዋል፡፡
መንግሥታትና የጤና ባለሙያዎች የታመሙትን ለማዳን ከሚጥሩት ጎን ለጎን በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በአፍሪካና በእስያ መድኃኒትና ክትባት ፍለጋ የተለያዩ ምርምሮች እያካሄዱ ነው፡፡ አሜሪካና እንግሊዝ በምርምር ላይ ያለ ክትባት በሰው ላይ ከሞከሩ አገሮች ይጠቀሳሉ፡፡ በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ የተነሳባት ቻይና በሽታውን ከተቆጣጠረችበት የባህል መድኃኒት ጭምር በመነሳት ሰፊ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነችም ትገኛለች፡፡ ለኮቪድ 19 የሚሆን መድኃኒትም ሆነ ክትባት ለመሥራት ግን ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅና የአንድ አገር የምርምር ተቋም ብቻውን ሊወጣው አይችልም፡፡ በመሆኑም የምርምር ተቋማትን በገንዘብ መደገፍ ግድ ይላል፡፡
ዓለም ገንዘብ በማሰባሰብም ሆነ ለቫይረሱ ክትባት ለማግኘት በጥምረት መሥራት እንዳለበት ያስታወቀው አውሮፓ ኅብረት፣ ከአገሮች ገንዘብ ለማሰባሰብ የኦንላይን ኮንፍረስን ሰኞ ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. አካሂዷል፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው የአውሮፓ አገሮች መሪዎች ኦንላይን ባደረጉት ስብሰባ ለኮሮና ቫይረስ ክትባት ለማግኘት የሚያስችሉ ምርምሮችን ለመደገፍ የሚውል 8.3 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ቃል ገብተዋል፡፡
በኮቪድ 19 በመጠቃታቸው ለሦስት ቀናት በፅኑ ሕሙማን ክፍል ክትትል ተደርጎላቸው ያገገሙትና ባለፈው ሳምንት ሥራ የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን ለክትባት ምርምር፣ ሙከራና ሕክምና እንግሊዝ 388 ሚሊዮን ፓውንድ እንደምትለግስ አስታውቀዋል፡፡
በእንግሊዝ፣ ካናዳ፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ኖርዌይ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና በአውሮፓ ኮሚሽን አስተባባሪነት በተዘጋጀው ‹‹ክትባት የማበልፀግ ድጋፍ›› ኮንፍረንስ 8.3 ቢሊዮን ዶላር ቃል የተገባ ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳይንቲስቶች፣ በኢንዱስትሪዎች፣ በመንግሥታት፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በዕርዳታ ድርጅቶችና በጤና ባለሙያዎች መካከል ትብብር እንዲፈጠር መነሻ ይሆናል ተብሏል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ክትባቱን በትብብር መሥራት ከተቻለ ለመላው ዓለም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የቀረበ የሕዝብ መጠቀሚያ ይሆናል ሲሉም የአውሮፓ አገሮች አስታውቀዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ካለው የማይጨበጥ የሥርጭት ባህሪ አንፃር ክትባት በቶሎ ማግኘቱ ውስጥ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሰዎች ወደቀደመ አኗኗራቸው መመለስ የሚችሉት ክትባቱ ከተገኘ ብቻ ነው ሲል ገልጿል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ምርምሮች እየተሠሩ መሆኑ በኮንፍረንሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ምርምሮቹ ወደ መፍትሔ እንዲያቀኑ አገሮቹ ድጋፋቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉም ይሆናል፡፡
ገንዘቡን ለመለገስ ቃል የገቡ አገሮችም በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወቀሳ የተሰነዘረባቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖምን (ዶ/ር) እንደሚደግፉም አስታውቀዋል፡፡
ትራምፕ፣ ዶ/ር ቴድሮስ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን አስመልክቶ የሰጡት መረጃ በቂ አልነበረም በማለት አሜሪካ ለድርጅቱ የምትለግሰውን ገንዘብ ማቋረጧን መናገራቸው ይታወሳል፡፡ የአውሮፓ መሪዎች ግን ድጋፋቸውን ለዶ/ር ቴድሮስ መስጠታቸውን ለክትባት ገንዘብ ለማሰባሰብ በተቀመጡበት ኮንፍረንስ ላይ ተናግረዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለምን ወሳኝ ሆነ?
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለኮሮና ቫይረስ ክትባት ካልተገኘ የሰዎች አኗኗር ወደቀድሞው መመለስ ይከብዳል ሲል ያስታወቀው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ቫይረሱ አሁን ላይ ባለው መረጃ እንደሌሎቹ የጉንፋን ዝርያ በሽታዎች በቀላሉ የሰው ልጆች የሚቋቋሙበት አይደለም፡፡ ነገር ግን በቀላሉ ከሰው ወደሰው ይተላለፋል፡፡ አብዛኛው የዓለም ሕዝብም ለበሽታው ተጋላጭ ነው፡፡ በመሆኑም ክትባቱን ማግኘት የሰዎችን በሽታውን የመከላከል አቅም በመገንባት እንዳይታመሙ ያደርጋል፡፡
ይህም አገሮች መሉ ለሙሉና በከፊል በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ የጣሉትን ገደብ ለማንሳትና ሕይወትን ወደቀደመው ለመመለስ ያስችላል፡፡
እስካሁን ክትባት የማግኘት እመርታው ምን ይመስላል?
ጥናቶች እየተከናወኑ ነው፡፡ በዓለም 80 ያህል ቡድኖች ክትባት ላይ ምርምር እያደረጉ ሲሆን፣ ጥቂቶቹ ክሊኒካል ሙከራ ላይ ናቸው፡፡ ከወር በፊት በሲያትል በሰው ላይ የክትባት ሙከራ ተደርጓል፡፡ ለአውሮፓ የመጀመርያው የሆነው የሙከራ ክትባት ደግሞ ከሳምንት በፊት በኦክስፎርድ በሰው ላይ ተሞክሯል፡፡ የፋርማሲው ዘርፍ ጉምቱዎች ሳኖፊ እና ጂኤስኬ ክትባቱን ለመሥራት ተጣምረዋል፡፡
የአውስትራሊያ ተመራማሪዎች ለኮሮና ቫይረስ ሊውሉ የሚችሉ ሁለት አቅም ያላቸውን የክትባት ዓይነቶች በእንስሳት ላይ ሞክረዋል፡፡ በቅርቡም በሰዎች ላይ እንደሚሞክሩ አሳውቀዋል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በሌሎች አገሮችም ምርመራና ሙከራ እየተደረገ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የትኛውም እየተሞከረ ያሉት ክትባቶች አዋጭ ይሆኑ ይሆን? የሚለው ያልተመለሰ ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም እስካሁን ድረስ አራት ዓይነት የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች በሰው ልጆች ላይ ጉዳት ያደረሱ ቢሆንም፣ ለሁሉም ክትባት አልተገኘላቸውም፡፡ ነገር ግን ሁሉም የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች የመደበኛው ጉንፋን ዓይነት ምልክት የሚያሳዩ ናቸው፡፡
አሁን እየተሞከሩ ያሉ ክትባቶች ከሠሩ እ.ኤ.አ. በ2021 አጋማሽ ጀምሮ ለተጠቃሚው እንደሚደርሱ ቢገመትም፣ የጤና ባለሙያዎች ሰዎች ቅድመ ጥንቃቄዎቹ ላይ በማተኮር ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲከላከሉ ይመክራሉ፡፡