Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአንፀባራቂው የ79 ዓመቱ ድል

አንፀባራቂው የ79 ዓመቱ ድል

ቀን:

‹‹ሚያዝያ 27 ቀን 1933 .. ንጉሠ ነገሥቱ በከፍተኛ አጀብ እኩለ ቀን ስድስት ሰዓት ላይ ከታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት አደባባይ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ዓላማችንን መልሰው ሰቀሉት፡፡ የክብር ዘብ ተሰልፎ፣ በራስ አበበ አረጋይ የሚመራው አሥር ሺህ አርበኞች ያሉት ጦር ዙሪያውን በሀገር ፍቅርና በብሔራዊ ስሜት እንደቆፈጠነ፣ በሱዳን በኩል የመጣውና በሻለቃ ዊንጌት የሚመራው የጌዲዮን ጦርም ተሰልፎ፣ መድፍ ተደጋግሞ እየተተኮሰ ሰንደቃችን በክብር ከፍ አለ፡፡››

የታሪክ ጸሐፊው ዘውዴ ረታ ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት›› በሚለው መጽሐፋቸው ስለ ታሪካዊቷ ሚያዝያ 27 ቀን የጻፉት ነው፡፡

ፋሺስት ጣሊያን አዲስ አበባን በያዘበት ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን (1928 ..) በሕዝቡና በአርበኞች ተጋድሎ የኢትዮጵያ የድል ቀን የተበሰረው ሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን (1933 ..) ነበር፡፡ ዘንድሮ 79 ዓመቱ ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2012 .. ተከብሮ ውሏል፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከስደት መልስ መናገሻ ከተማቸው ሚያዝያ 27 ቀን ገብተው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከማውለብለባቸው አራት ወር ግድም በፊት ጥር 12 ቀን ሱዳን ድንበርን ተሻገረው ኢትዮጵያ ገብተው ያውለበለቡት ኦሜድላ ላይ ነበር፡፡

አንፀባራቂው የ79 ዓመቱ ድል

የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አቤቱታ

በወቅቱ በነበረው የመንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) መቀመጫ ጄኔቭ በመገኘት፣ ለዓለም መንግሥታት አቤቱታቸውን ያሰሙት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) በሸንጎው ላይ ካደረጉት ዲስኩር የሚከተለው ኃይለ ቃል ይገኝበታል፡፡

‹‹…ከእግዚአብሔር መንግሥት በቀር የፍጡር መንግሥት ሁሉ አንዱ ከአንዱ የማይበልጥ ሥራ የለውም፡፡ ነገር ግን በምድር ላይ ኃይለኛ የሆነው መንግሥት ምንም በደል የሌለበትን የሌላውን መንግሥት ሕዝብ ለማጥፋት የሚገባው መስሎት በተነሳበት ጊዜ ተጠቂው ወገን ለመንግሥታት ማኅበር የተበደለውን የሚያቀርብበት ሰዓት ነው፡፡ እግዚአብሔር ታሪክ ለምትሰጡት ፍርድ ለመንግሥት ማኅበርም ምስክር ሆነው ይመለከታሉ…››

በአንድ በኩል የጣሊያኑ አምባገነን ቤኒቶ ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን በመጠቅለል በአፍሪካ የጣሊያን ግዛት መመሥረቱንና አገሪቱንም መያዙን ሲያውጅ፣ አዲስ አበባንም ፋሺስቶች ሚያዝያ 27 ቀን 1928 .. ከመያዛቸው አስቀድሞ የተሰደዱት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሙሶሎኒን መግለጫ በመቃወም ለመንግሥታቱ ማኅበር አቤት ቢሉም ድጋፍ አላገኙም፡፡ አብዛኛዎቹ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል አገሮች ለጣሊያን ወረራ እውቅና ሰጥተው ነበርና፡፡  የአርነት ተጋድሎው ግን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ቀጥሏል፡፡

ከሰማንያ ሁለት ዓመታት በፊት የተፈጸመው የፋሺስት ጣሊያን ወረራ በኢትዮጵያ ላይ ብዙ መከራዎችን ትቶ ማለፉ አይዘነጋም፡፡ እርመኛ አርበኞች አገራዊ ነፃነት ለማስከበር የሕዝቡን ልዕልና ለማስጠበቅ ያደረጉት ተጋድሎ የትየለሌ ነው፡፡

በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሰሜንና በደቡብ በምሥራቅና በምዕራብ በተደረጉት ተጋድሎዎች ከዘመቱት ሴቶች መካከል ከአርሶ አደር ቤተሰብ እስከ ልዕልታቱ ይገኙባቸዋል፡፡ ፊታውራሪ በላይነሽ ገብረ አምላክ፣ እመት ዘነበች ወልደየስ፣ ልዕልት ሮማነ ወርቅ ኃይለ ሥላሴ፣ / ላቀች፣ / ሸዋነሽ አብርሃም፣ እመቤት ሆይ ከበደች ሥዩም መንገሻ፣ / ቀለመወርቅ ጥሩነህ፣ የውስጥ አርበኛዋ / ሸዋረገድ ገድሌሕክምናን በተመለከተ / ስንዱ ገብሩና / ጽጌ መንገሻ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 

አንፀባራቂው የ79 ዓመቱ ድል

 

ጣሊያን በዓድዋ ላይ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል 40 ዓመት ቆይታ በኋላ በፋሺስታዊ መንግሥቷ አማካይነት በአምስቱ ዘመን የሠራችው ግፍ ተነግሮ አያልቅም፡፡ ወረራውን በፈጸመች ባመቱ በየካቲት 12 ቀን 1929 .. በአዲስ አበባና በአካባቢው ከፈጸመችው ግፍ አንስቶ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢው ብዙ ጥፋትን አድርሳለች፡፡ ከእነዚህም መካከል የመጀመሪያው የፋሺስት ወንጀለኞች የኢትዮጵያን ሠራዊት የፈቱበት በተምቤንና በሐሸንጌ በመርዝ ጋዘ ያደረሱት እልቂት ይጠቀሳል፡፡

የፋሺስት ወንጀለኞች የኢትዮጵያን ሠራዊት የፈቱበት፣ በተምቤንና በሐሸንጌ በመርዝ ጋዝ ያደረሱትን እልቂት ትኩረት ሰጥተው ከጻፉት ደራስያን አንዱ አቶ ጥላሁን ጣሰው ናቸው፡፡ ይህንኑ የፋሺስት ክስተት፣ የአርበኞችና የሕዝቡን ተጋድሎ የሚያወሳ ታሪካዊ ልብ ወለድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፈዋል፡፡

‹‹Trying Times (ትራዪንግ ታይምስ) ብለው የሰየሙት መጽሐፍ፣ በአንድ በኩል የፋሺስት ጣሊያን ወረራን ታሪክ ሲያሳይ በሌላ ገጹ ልብ ወለዳዊ ነው፡፡ ለቤተሰባቸው ሳያሳውቁ ከገጠር የዘመቱ ሴቶች ታሪክም ይዟል፡፡ ታሪክና ልብ ወለድን አጣምሯል፡፡ በልብ ወለዱ ታዋቂ የሆኑ አርበኞች እነራስ አበበ አረጋይ፣ በሻህ አቦዬ፣ ግዛቸው ኃይሌ፣ መኩሪያ መንገሻ ተጠቅሰዋል፡፡

ታሪኩን በእንግሊዝኛ መጻፍ ያሰኛቸው 700,000 ያህል ሰዎች በኬሚካል ጦርነት ያለቁበትን ሁኔታና አተያይ ከኢትዮጵያ አንጻር ለውጩዎቹ ለማሳየት ነው፡፡ ‹‹በተምቤን ጦርነት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ ባልሆኑ መሣርያዎች ድል አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ድል በማድረጉ ፋሺስት የኬሚካል ጥቃቱን ፈጸመ፡፡ በዚያን ጊዜ ያለቁት 700,000 የሚደርሱ ናቸው፡፡››

ደራሲው በተምቤን ጦር ግንባር አዛዥ የነበሩት ራስ ካሳ በመጽሐፋቸው የገለጹትን፣ ከፈረንሣይኛ ተተርጉሞ ያገኙትን አውስተዋል፡፡

‹‹የተምቤን ጦርነት ጊዜ አሸነፍን፣ ዋናው ነገር [ጣሊያን] ሩቅ የሚመታ መሣርያ አላቸው፣ እኛ በቅርብ ሆነን ማጥቃት እንችላለን፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ተዝናንተን ሳለን አንድ ቀን የእነርሱ አውሮፕላኖች ቢመጡ እንፈትሻቸዋለን ስንል በጣም ከርቀት ሆነው አውሮፕላኖቹ ለእርሻ አረም ማጥፊያ በሚሆን መርጪያ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ ጥይት የሚደርስበት አይደለም፡፡ ዝም ብሎ ይወርዳል ኬሚካል ሰልፈር (ድኝ) አለው፡፡ መስተርድ ጋዝና ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ጣሉ፡፡ ሰውም መቃጠል አገርም በሙሉ መቃጠል ጀመረ፡፡ ዋሻው ውስጥም ሆኖ መቋቋም አይቻልም ሰው ሁሉ አለቀ፡፡ አንድም ጣሊያን ከዚያ በኋላ አልሞተም፡፡››

የውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች በተለይ የፋሺስት ደጋፊ የሆኑት፣ በተምቤን ስለተካሄደው ጦርነት ‹‹የመጀመርያው የተምቤን ጦርነት›› ‹‹ሁለተኛው የተምቤን ጦርነት›› በማለት ታሪኩን ያዛባሉ፡፡

‹‹የመጀመርያው የተምቤን ጦርነት የሚሉት ኢትዮጵያውያኑ የተወሰነ ድል አገኙ፡፡ ሁለተኛው የተምቤን ጦርነት ላይ ግን በራስ ካሳና ራስ እምሩ ሥዩም የሚመራውን ጦር አሸነፉት ይላሉ፡፡›› አቶ ጥላሁን እነዚያን ጸሐፍት ከመሞገት አልተመለሱም፡፡

‹‹ሁለተኛ የተምቤን ጦርነት የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ሒሮሺማና ናጋሳኪ ላይ የአቶሚክ ቦንብ በመውደቁ የሒሮሺማና የናጋሳኪ ጦርነት የሚባል ነገር እንደሌለ ሁሉ አንድም ሰው በውጊያ ባልሞተበት በአውሮፕላን በተረጨ መርዝና ከሰልፈር (ድኝ) እና በተቀጣጣይ ፈንጂ በተደበላለቀ ሁሉ ማለቁን ያወሩናል፡፡

በሐሸንጌ ሐይቅ ስለደረሰው እልቂት የራስ ካሳ እይታንም ደራሲው አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ሁሉም የቀይ መስቀል ፈረንጆች ሠራተኞች ከተመለሱ በኋላ በሐሸንጌ ሐይቅ ሜዳ ላይ የሔዱት ሰዎች ሐይቁ ከተመረዘ በኋላ በሙሉ ያልቃሉ፡፡››

ይህ ዘግናኝ ክስተት በውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች ሲቀርብ የተገለጸው ‹‹የንጉሠ ነገሥቱ ጦር መሸነፉን በሐሸንጌ ሐይቅ ውስጥ በሞላው ሬሳ አወቅነው፤›› ተብሎ ነው፡፡
የዚያን ጊዜ ያለቁት ከወንድሞቻቸው ጋር ወደ ጦር ሜዳ የሔዱ በአብዛኛው ሴቶች፣ ሲቪልና ጥቂት ቁስለኞች መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ጥላሁን፣ አጽንዖት የሰጡበት ነገርም አለ፡፡

‹‹እኛ አዲስ አበባ ውስጥ ስለተደረገውና ጥቂት ሺሕ ሰዎች ስላለቁበት እናስባለን፡፡ ያኛው በገጠር የተከናወነው ግን እየተረሳ ይሔዳል፡፡ ከተሞች ውስጥ የሚሞተው ሁልጊዜ ይታወሳል፡፡ ገጠሮች ላይ የሚሞተው ይጠፋል፡፡››

አንድ ደራሲ እንደከተበው፣

‹‹…ቢነገር ቢወራ ቢተረክ ቢጻፍ

      ፍጻሜ የለውም የፋሺስቶች ግፍ››፡፡

ከ80 ፈሪ ዓመት በፊት የድሉን ብሥራት አስመልክተው ባለቅኔው የእንጦጦ ራጉኤሉ ሊቅ ብርሃኑ ድንቄ፡– ‹‹ኢትዮጵያ ከማር ለሚጣፍጥ ለስምሽ አጠራር ሰላም ይገባል፡፡ ባምላክ እጅ ለተሠራ ለራስ ፀጉርሽም ሰላምታ ይገባል፡፡ ምሳሌ የሌለሽ መቅደስ ኢትዮጵያ ጠላት ጣሊያን ስላረከሰሽና መሠዊያሽን ስላጠፋ ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ ተቀደሽ፣ ኃይልንም ገንዘብ አድርጊ›› ብለው ተቀኝተውላት ነበር፡፡ ‹‹እናታችን ኢትዮጵያ ሆይ ለታረዙ ልብስ ነሽና በባንዲራሽ ጥላ ሰብስቢ ልጆችሽን›› እያሉም ዘመሩላት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...