Sunday, February 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኮንትሮባንድ በብረታ ብረት ዘርፍ ላይ ከባድ ፈተና ደቅኗል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በርካታ የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች መርካቶ በገፍ እንደሚገቡ መንግሥት መረጃው አለኝ ብሏል

በኮሮና ምክንያት ምን ያህል ጉዳት እንደሚደርስ ጥናት እየተካሄደ ነው

የብረታ ብረት ዘርፍ አሁንም ኮንትሮባንድ ከባድ ፈተና እንደጋረጠበት ተገለጸ፡፡ ‹‹ኮንትሮባንድ በሕጋዊ መንገድ ሲከናወን ቆይቷል፡፡ የመንግሥት አመራሮችና መዋቅሮች ጭምር የሚሳተፉበት ነው፡፡ እነዚህን ድርጅቶች እንዳትፈትሿቸው የሚል ሰርኩላር ደብዳቤ በመሥሪያ ቤታችን ውስጥ አግኝተናል፤›› በማለት በአንድ ወቅት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተናገሩት የቀድሞዋ የገቢዎች ሚኒስትር፣ አሁን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡

የኮንትሮባንድ ንግድ ሲወሳ የአፋሯ አባኣላ የገጠር ከተማ ሁሌም የምትጠቀስ ሥፍራ ነች፡፡ በዚህች ከተማ 55 ዓለም አቀፍ ሆቴሎችን ለመገንባት 43 ግለሰቦች የቀረጥ ነፃ መብት ተፈቅዶላቸው፣ ብረታ ብረትና ሌሎች የሆቴል ዕቃዎች በገፍ ሲያስገቡ ኖረዋል፡፡ ሆቴሎችን ለመገንባት የቀረጥ ነፃ መብቱ ከተሰጣቸው መካከል አንድ ግለሰብ ብቻውን 28 ጊዜ የሆቴል ዕቃዎችንና የግንባታ ብረት ማስገባቱን፣ ወ/ሮ አዳነች ለፓርላማ አስረድተው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ‹‹ለማስመሰል እንኳ›› የተካሄደ አንድም ግንባታ እንዳልተገኘ ገልጸውም ነበር፡፡

እንዲህ ያሉ ክስተቶች የሚታዩበት ኮንትሮባንድ በተለይ በብረታ ብረትና በቆርቆሮ ምርቶች ላይ ብሶበታል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ በመሆኑ፣ ያለ ደረሰኝ የሚሸጡ የብረታ ብረት ነጋዴዎች እጅ ከፍንጅ ሲያዙና መደብሮቻቸው ሲታሸጉ ታይቷል፡፡ ሕገወጥ ንግዱና ኮንትሮባንዱ ግን አልተገታም፡፡

የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን ሙሉጌታ ስለዚህ ጉዳይ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የኮንትሮባንድ ችግሩ እየተባባሰና የኮሮና ቫይረስን ተገን በማድረግ ጭምር ሕገወጦች እንቅስቃሴያቸውን እያስፋፉ ናቸው ብለዋል፡፡ በተለይም የቆርቆሮና የአርማታ ብረቶች በሕገወጥ መንገድ በገፍ ሲዘዋወሩ በመንግሥት ጭምር እየታዩ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው የሚንቀሳቀሱ አካላት ድርጊት አሥጊ በመሆኑ ከፍተኛ ክትትል ይፈልጋል፤›› ያሉት አቶ ሰሎሞን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በኮንትሮባንድና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ እየተመካከሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ብረትና ቆሮቆሮ ምርት ምን ያህል የገንዘብ መጠን ይሆናል ለሚለው ጥያቄ ይህ ነው የሚባል አኃዝ ባይጠቀስም፣ አቶ ሰሎሞን ከሆነ ግን በሰፊው ገበያውን ያጥለቀለቁ የቆርቆሮና የአርታማ ብረቶች እንደሚገኙ እየታየ ነው ብለዋል፡፡

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ሺበሺ ሥዩም በበኩላቸው፣ የኮንትሮባንድ ጉዳይ በተደጋጋሚ እየተነሳ የሚገኝ ችግር ነው ይላሉ፡፡ በተለይ የአርማታ ብረትና የቆርቆር ምርት ምን ያህል በኮንትሮባንድ እንደሚንቀሳቀስና ከውጭ እንዴት እንደሚገባ የሚያሳይ ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል፡፡ በቅርቡም ከብርታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ተዋንያንና ማኅበራት፣ እንዲሁም ከሌሎች አካላት ጥያቄው ሲቀርብ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

በቅርቡም በጥናት ተለይተውና በክትትል የተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽንና የፀረ ኮንትሮባንድ ግብረ ኃይል እንዲያውቁት መደረጉን የገለጹት አቶ ሺበሺ፣ በተለይ በቆርቆሮ ምርት የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያመላክት ደብዳቤ በሚያዝያ ወር ለጉምሩክ ኮሚሽን መላኩን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹መርካቶ ድረስ ገብቶ እየተሸጠ እንደሚገኝ አረጋግጠናል፡፡ ግዙፍና ረዣዥም እጆች ያሉበት ሕገወጥ ሥራ በመሆኑም ሁሉም አካል እየሠራበት ይገኛል፤›› ያሉት አቶ ሺበሺ፣ እንደ ሶማሌ ክልል ባሉ አካባቢዎች የድንበር ላይ እንቅስቃሴው ከድንበሩ ስፋት አኳያ በርካታ ሕወገጥ የኮንትሮባንድ ድርጊቶች እየታዩ በመሆናቸው፣ እስከ ታችኛው አስተዳደር ዕርከን ድረስ ጉዳዩን ተረድተው ክትትል እያደረጉበት እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

በርካታ የኮንትሮባንድ ብረታ ብረቶችና የቆሮቆሮ ምርቶች ያለ ደረሰኝ ጭምር በአደባባይ ሲሸጡ ከሚታዩባቸው አካባቢዎች መካከል፣ በመርካቶና በመገናኛ ከዚህ ቀደም ዕርምጃ ቢወሰድም አሁንም ድረስ ችግሩ ጎልቶ እየታየ ነው ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እንቅስቃሴ በግብዓት እጥረት እየተፈነ ይገኛል ያሉት አቶ ሺበሺ፣ ከውጭ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎችን ለማስመጣት በኮሮና ሰበብ የተደረጉ የጉዞ ክልከላዎች ከውጭ ምንዛሪ ዕጦት ጋር ተዳምረው አቅርቦቱን አስቸጋሪ እንዳደረጉት አብራርተዋል፡፡ የምርት ሥራ እንዳይቋረጥ መንግሥት በማስታወቁ የብረት ጥሬ ዕቃ ከውጭ ማስመጣት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በአገር ውስጥና ከጎረቤት አገሮች በሚገኙ ቁርጥራጭ ብረቶች የምርት ሥራ እንዳይቋረጥ አምራቾች ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኮንስትራክሽን ዘርፉ መቀዛቀዝ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪው ገበያ እንዲያጣ እያስገደደው መሆኑን፣ የትራንስፖርት ሥርዓቱ ላይ የተቀመጡ አሠራሮችና የሠራተኞች የጤና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ግዥና መሰል ወጪዎች እየተደራረቡ አምራቾቹን ጫና ውስጥ እየከተቷቸው እንደሚገኙም ተጠቁሟል፡፡ መንግሥት ለጉዳት ተጋልጠዋል ካላቸው ዘርፎች አንዱ የሆነው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ የደረሰበት የጉዳት መጠን ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ ጥናት እየተገባደደ እንደሚገኝ፣ በገንዘብ ሲተመን ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል የሚሳይ ትንታኔ እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ ሺበሺ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች