Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየተሻለ መንገድ ለተሻለች አዲስ አበባ

የተሻለ መንገድ ለተሻለች አዲስ አበባ

ቀን:

የተከበራችሁ አንባቢያን ይህንን ጽሑፍ ለማቅረብ መነሻ የሆነው ርዕሰ ጉዳይ፣ ሚያዝያ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ታትሞ ለንባብ በበቃው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ‹‹ከመገናኛ እስከ አያት አደባባይ ያለው የእግረኛ መንገድ መቆፈር ጥያቄ አስነሳ›› በሚል ርዕስ ሥር በስም የተጠቀሱ የከተማችን ነዋሪዎች ያቀረቡትን ቅሬታ አዘል አስተያየት ተንተርሶ የሰፈረው ዘገባ ነው፡፡

የአዲስ አበባ የመንገድ ልማት ዋነኛ ተጠቃሚና ባለቤት የሆኑት የከተማችን ነዋሪዎችና እንግዶች፣ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ጎኑ የሚሰጡት አስተያየት፣  መሥሪያ ቤታችን የተሻለ መንገድ ለተሻለች አዲስ አበባ ለመገንባት በሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረት ውስጥ በግብዓትነት የሚወሰዱ ጠቃሚ ሐሳቦችን የምናገኝበት መልካም ዕድል በመሆኑ፣ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችና በአካል ጭምር በመቅረብ አስተያየታቸውን ለሰጡንና ለሚሰጡን የኅብረተሰብ ክፍሎች በእግረ መንገዳችን ከፍ ያለ ምሥጋና ለማቅረብ እንወዳለን፡፡

በቀረበው ዘገባ ላይ በተነሱ አንኳር ነጥቦችና ተያያዥ የመንገድ ግንባታ ጉዳዮች ላይ አንባቢያን በቂ ግንዛቤ ያገኙ ዘንድ ዝርዝር ጉዳዮችን ከማንሳታችን በፊት፣ ጥያቄ ስለቀረበበት ከመገናኛ እስከ አያት አደባባይ መንገድ፣ ጥቂት መሠረታዊ እውነታዎችን እናንሳ፡፡

ከመገናኛ እስከ አያት አደባባይ ያለው መንገድ አሁን ባለው ይዘት ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው በሚያዝያ ወር 2003 ዓ.ም. ሲሆን፣ የመንገዱ ርዝመትም 8.2 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ወደፊት የሚካሄዱ የትራንስፖርት ማስፋፊያ ሥራዎችን ታሳቢ በማድረግ በወቅቱ በመንገድ ዲዛይኑ 50 ሜትር የጎን ስፋት ተሰጥቶት የተገነባው ይህ መንገድ፣ በግራና በቀኝ በኩል ከተዘረጋው የመሄጃና የመመለሻ የአስፋልትና የእግረኛ መንገድ በተጨማሪ፣ ጎዳናውን መሀል ለመሀል ሰንጥቆ የሚያልፍ ቀላል የከተማ ባቡር መስመር የሚገኝበት ሥፍራ በመሆኑ፣ መንገዱ ከሚያስተናግደው ከፍተኛ የተሽከርካሪ ፍሰት በተጨማሪ፣ በርካታ እግረኞችም የሚንቀሳቀሱበት ጎዳና ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ወርልድ ሪሶርስ ኢንስትቲዩት ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመሆን በተለያዩ የከተማዋ መንገዶች ላይ ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው፣ ከዓለም አቀፍ መሥፈርት አንፃር አብዛኞቹ የከተማችን የእግረኛ መንገዶች ለተጠቃሚዎች ምቹ አይደሉም፡፡ እግረኞች ምቹ መንገድ በማጣታቸው ምክንያት አልፎ አልፎ በተሽከርካሪ መተላለፊያ መንገዶች ላይ በመግባት ለአደጋ የሚጋለጡባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ ይህንኑ እውነታ በመረዳት፣ የከተማዋ አስተዳደር የመንገድ ደኅንነት ስትራቴጂ ቀይሶ፣ ጉዳዩ በሚመለከታቸው አስፈጻሚ ተቋማት በኩል ተግባራዊ እያደረገው ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ዓበይት ተግባራት መካከል  ምቹና ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ የእግረኛ መንገድ መገንባት አንዱ ነው፡፡

በመሆኑም የዓለም አቀፉን የመንገድ ቅኝት ፕሮግራም (International Road Assessment Program)፣ የመንገድ ደኅንነት ደረጃን መሠረት ያደረገ፣ በተለይ የእግረኞችን ምቾት የሚጠብቅ የእግረኛ መንገድ እንደገና መሥራት አስፈላጊነቱ ከላይ  ለተጠቀሰው የእግረኛ መንገድ መልሶ ግንባታ እንደ አንድ መነሻ ተወስዷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ሲል ይገነቡ የነበሩ መንገዶች በዋናነት ተሽከርካሪን  ታሳቢ ያደረጉና ለእግረኞች በሚፈለገው ደረጃ ትኩረት ባልሰጡ የአውራ ጎዳና (High way Concept) ደረጃ ይገነቡ ስለነበር፣ አንዳንድ የከተማዋ መንገዶች ለእግረኞች እንቅስቃሴ ይመቻሉ ለማለት አያስደፍሩም፡፡

ይህንን ፍትሐዊ ያልሆነ የመንገድ ግንባታ ጽንሰ ሐሳብ ከመሠረቱ በመቀየር፣ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ የሆነ፣ ዜጎች በከተማዋ መንገዶች ላይ በምቾት በእግራቸው እንዲጓዙ የሚያበረታታና ነዋሪዎች አዘውትረው በሚያደርጉት የእግር ጉዞ  አማካይነት ጤናቸው እንዲጠበቅ ለማስቻል የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ለእግረኛ መንገዶች ዕድሳትና ግንባታ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

አካታች የመንገድ ግንባታ ጽንሰ ሐሳብ (Street Concept) የተሽከርካሪና የእግረኛ እንቅስቃሴን አጣጥሞ በማስኬድ በኩል ተመራጭ ስልት ከመሆኑም ባሻገር፣  ቀደም ሲል ተግባራዊ ይደረግ በነበረው የአውራ ጎዳና ግንባታ ጽንሰ ሐሳብ እምብዛም ትኩረት ላልተቸረው የእግረኞች መተላለፊያና የፔዳል ሳይክል መስመር ግንባታ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ፣ ከባለሞተር ተሽከርካሪዎች በሚወጣው ጭስ ሳቢያ የሚፈጠር የአየር ብክለትን ለመቀነስ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ ከ100 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች በመገንባት ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የእግረኞችን ምቾት ለመጠበቅና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ ነባርና አዲስ የእግረኛ መንገድ ዕድሳትና ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ለአብነትም በ2010 እና በ2011 ዓ.ም. 26 የእግረኛ መንገድ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው 51.7 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ ተሠርቷል፡፡ በያዝነው ዓመትም 36 የእግረኛ መንገድ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው 55 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ዓመት መልሶ ግንባታ እየተካሄደባቸው በሚገኙ ፕሮጀክቶች ላይ በ62 ማኅበራት የታቀፉ 232 የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ የጥቃቅንና አነስተኛ የማኅበር አባላትና ከ600 በላይ በፕሮጀክቱ የተቀጠሩ ዜጎች በግንባታ ሥራው እየሳተፉ ይገኛሉ፡፡ በ2012 በጀት ዓመት እየተካሄዱ የሚገኙ የእግረኛ መንገድ ፕሮጀክቶች የመንገድ ተጠቃሚ ለሆኑ የከተማችን ነዋሪዎች ከሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ባሻገር፣ በአጠቃላይ ከ800 በላይ ዜጎች ሥራ እንዲያገኙ አስችለዋል፡፡

በያዝነው ዓመት የእግረኛ መንገድ መልሶ ግንባታ እየተካሄደባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች አንዱ የሆነው የመገናኛ-አያት አደባባይ መስመር እንደገና መልሶ እንዲገነባ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ፣ ቀደም ሲል የእግረኛ መንገዱ በሌሎች የመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት በመቆረጡ ምክንያት የተወሰነው የእግረኛ መንገዱ ክፍል መበላሸቱ ነው፡፡

ይህን የእግረኛ መንገድ ባለበት ሁኔታ ጠግኖ ማለፍ ለእግረኞች እንቅስቃሴ ምቾት ስለማይሰጥ፣ ይልቁንም መሥሪያ ቤቱ ካስቀመጠው የዋና ዋና መንገዶች የእግረኛ መንገድ ስታንዳርድ ጋር ተጣጥሞ ሊፈጸም እንደማይችል በመገንዘብ፣ በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የእግረኞች እንቅስቃሴ ሊያስተናግድ በሚችልና ለሁሉም ኅብረተሰብ ተደራሽ በሚያደርግ መልኩ፣ ቀደም ሲል ተነጥፎ የነበረውን ባለ ሦስት ሴንቲ ሜትር ውፍረት ያለውን የሸክላ ንጣፍ በማንሳት በምትኩ ረዥም ጊዜ ሊያገለግል በሚችል፣ ለአካል ጉዳተኞችም ይበልጥ ተደራሽ በሆነ በባለ ስድስት ሴንቲ ሜትር ውፍረት በተሠራ የሸክላ ንጣፍ መልሶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

የእግረኛ መንገዱ የመልሶ ግንባታ ሥራ ላይ የተነሱ ያገለገሉ የእግረኛ መንገድ ንጣፎች ሁሉም ያለጥቅም አይባክኑም፡፡ ተመልሰው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉት ተለይተው ለሌሎች መሰል ተግባራት አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋሉ፡፡  

ይህ በእንዲህ እያለ፣ የመንገድ ሀብታችንን ደኅንነት የሚፈታተኑና ለከፍተኛ የጥገና ወጪ የሚዳርጉ ጥፋቶች በተደጋጋሚ ይፈጸማሉ፡፡ ለምሳሌ በፍሳሽ መስመር ክዳኖችና በሌሎች የመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በአስረጂነት መጠቅሱ በቂ ነው፡፡

በብረት ስርቆትና በተሽከርካሪዎች በሚደረስ ጉዳት ምክንያት የሚሰበሩ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ክዳኖችን የመቀየር (እንደገና ሠርቶ የመክደን) ሥራ በየጊዜው ይከናወናል፡፡ ይህ አንዱ የመንገድ ሀብት አስተዳደር ተግባር ሲሆን፣ በያዝነው ዓመት 1,333 የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር የጉድጉድ ክዳኖችን ለመሸፈን ታቅዶ ነበር፡፡ የሚደርሰው ጉዳት ከተጠበቀው በላይ በመጨመሩ ምክንያት ግን በበጀት ዓመቱ አሥር ወራት ብቻ 1,924 ክዳኖች በተለያዩ የከተማዋ መንገዶች ላይ እንደገና ተሠርተው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

በተጨማሪም በከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች በእግረኛ መንገድና በሌሎች የመንገድ ሀብቶች ብቻ የሚፈጸም ባለመሆኑ፣ ችግሩን ትርጉም ባለው መንገድ ለመቅረፍ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል፡፡ መንገድ የሁላችን የጋራ ሀብት ነውና፡፡ ስለሆነም በመንገድ ሀብታችን ላይ የሚደርሰው ጉዳት፣ በእያንዳንዳችን የግል ንብረት ላይ እንደሚደርስ ጥፋት ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡ የመገናኛ ብዙኃንም ይህን አስተሳሰብ ወደ ኅብረተሰቡ በማስረጽ ጠንካራ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

መላው የከተማችን ነዋሪም፣ የጋራ ሀብቱ በሆነው የመንገድ አውታር ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በመከላከል፣ በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በአግባቡ በመጠቀም ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተገንዝቦ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡

(የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...