Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉበህዳሴው ግድብ የአሜሪካ አሸማጋይነት ከዓለም አቀፍ ሕግ አንፃር ያለው አንድምታና ትንተናዊ ምክረ...

በህዳሴው ግድብ የአሜሪካ አሸማጋይነት ከዓለም አቀፍ ሕግ አንፃር ያለው አንድምታና ትንተናዊ ምክረ ሐሳብ (የመጨረሻ ክፍል)

ቀን:

በዘርዓይ ይህደጎ (ፕሮፌሰር)

የአሜሪካኖቹ በድርድሩ ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ ማሳደር ወይስ ሽምግልና? ከዓለም አቀፍ ሕግ አንፃር ሲፈተሽ

ይህ የመጨረሻ ክፍል በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ጥያቄ በማንሳት የሚያተኩር ሲሆን፣ ይህም አንደኛ ዋነኞቹ የምሥራቅ ዓባይ ተፋሰስ አገሮች በጥቁር ዓባይ ግድብ ድርድር ላይ የነበራቸው ትብብር፣ ፉክክርና የኃይል ሚዛን አሜሪካኖቹ ወደ መድረኩ ከተቀላቀሉ በኋላ ተፅዕኖ አሳድረውበታልን? እንዲሁም ሁለተኛ ይህ የአሜሪካኖች ጣልቃ ገብነት (ከግብፃዊያን ጋር በማበር) ከሕግ አንፃር እንዴት ይታያል?  የሚሉ ጉዳዩችን በማንሳት ለመመርመር ይሞክራል፡፡

- Advertisement -

የአሜሪካኖቹ በጉዳዩ እጃቸውን የማስገባት ጉዳይ

እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2019 የህዳሴው ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር አጣብቂኝ ውስጥ መግባትን ተከትሎ፣ አሜሪካ ከግብፅ በቀረበላት አጣዳፊ ጥሪ የድርድር መድረኮችን ለማመቻቸትና በእንጥልጥል ላይ ያሉ አወዛጋቢ ጉዳዮችን ለመፍታት ተዋናይ ሆና ብቅ አለች፡፡ ይህ ሁኔታ በግብፃዊያኑ ዘንድ ቀደም ካሉት ጊዜያትም ጀምሮ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን በጉዳዩ ላይ የማሳተፍ የጎላ ፍላጎት ቅጥ ያጣ እንደነበር መገመት የሚቻል ሲሆን፣ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ችግሩ በሦስቱ ወገኖች መፈታት ካልቻለ በቤዝኑ (በተፋሰሱ) ሥር የሚገኙ አካላትን በማሳተፍ ጉዳዩ እልባት የሚያገኝበት ዝንባሌ ማሳየቷ የሚታወቅ ነው፡፡

ይህም ሆኖ ኢትዮጵያና ሱዳን በጉዳዩ ላይ የጎላ ተቃውሞ ሳያሰሙ መድረኩን መቀላቀላቸውን ተከትሎ፣ የትራምፕ አስተዳደርና የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በኅዳር 2019 የታላቁ ህዳሴ ግድብ የድርድር አካል ሆነው ተገኙ፡፡ በዚህም መሠረት የአሜሪካ መንግሥት እነዚህን መሰል ጉዳዮች ለመከታተል የባለሙያም ሆነ የዓለም አቀፍ ድንበር ዘለል ወንዞች ተመክሮ ያላቸውን የውጭ ጉዳይ ወይም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ሳይሆን፣ የትሬዥሪ ሴክረተሪው አገሮቹን የማደራደር ኃላፊነት እንዲይዙ አደረጉ፡፡ ጅምሩ ጥሩ ውጤት ያሳያል ተብሎ የተጠበቀው የአገሮቹ ድርድር እ.ኤ.አ. በየካቲት 2020 የሰፋ ልዩነት በመካከላቸው ተፈጥሮ የተከፋፈለ አቋም እንዲይዙ አደረገ፡፡ የዚህ ልዩነት መንስዔም በትሬዥሪ ዲፓርትመንት ተረቅቆና የዓለም ባንክን ይሁንታ ያገኘውን ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ኢትዮጵያ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳትሆን በመቅረቷ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ተካፋይ ባልሆነችበት መድረክ ግብፅንና ሱዳንን ብቻ አካትቶ ስብሰባ በማካሄድ በመጨረሻ በወጣው መግለጫ አንደኛ ኢትዮጵያ ስምምነቱን እንድትቀበል፣ ሁለተኛ ወደ አንድ ስምምነት ከመደረሱ በፊት የግድቡን ሙሌት ከመፈጸም እንድትታቀብ፣ እንዲሁም ኃይል ለማመንጨት የኤሌክትሪክ መስመሩ ላይ ማናቸውንም የሙከራና ፍተሻ ተግባራት እንዳትፈጽም የሚያስጠነቅቅ ነበር፡፡

ይህ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በግላጭ ለተጋፋው የትሬዥሪ ዲፓርትመንት መግለጫ እ.ኤ.አ. መጋቢት 1 ቀን 2020 የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምላሽ የሰጠ ሲሆን፣ በዚህም የኢትዮጵያን ጥቅም የሚፃረርና ሉዓላዊነቷን የሚጋፋ ማናቸውም ስምምነት ለመቀበል እንደምትቸገር የሚያሳውቅ ነበር፡፡ ግብፅ በበኩሏ ኢትዮጵያ ከ2015 የመርሆች መግለጫ ስምምነት መንፈስ ውጪ እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ በማመልከት መግለጫ ከማውጣቷም በተጨማሪ ጉዳዩን በዓረብ ሊግ ፊት በማቅረብ የግብፅ ታሪካዊ መብት እንዲከበር ሊጉ ድጋፍ እንዲሰጥ እስከ ማድረግ የዘለቀ ዕርምጃ ወሰደች፡፡

በአንፃሩ ሱዳን በትሬዥሪዲ ፓርትመንት ተዘጋጅቶ በቀረበው ሰነድ ላይ ፊርማዋን ለማኖር ከመታቀቧም በተጨማሪ የዓረብ ሊግ ያወጣው መግለጫን በመቃወም የውሳኔው አካል መሆን እንደማትሻ አቋሟን በማሳወቅ በልዩነት አስመዝግባ ወጣች፡፡ ኢትዮጵያ የሱዳንን አቋም ከማወደስ በተጨማሪ የዓረብ ሊግ ያመጣው መግለጫን በማወገዝ አቋሟን አሳወቀች፡፡

ይህ የኢትዮጵያና ግብፅ የተካረረ እሰጣ እገባና የቃላት ጦርነት ተፋፍሞ ባለበት ሁኔታ ሱዳን አገሮቹ ወደ ድርድር ጠረጴዛ ተመልሰው በመምጣት ድርድሩ እንዲቀጥል ሐሳብ ስታቀርብ፣ የአሜሪካኖቹ አሸማጋይነት ውድቀት እንደገጠመው የተገነዘቡ ተመራማሪዎች (የዘርፉ ባለሙያዎች) እየተካረረ የመጣውን የአገሮችን ግንኙነት ከውጥረት የሚያወጣ ሚዛናዊ የሆነ ሐሳቦችን በጽሑፎቻቸው በማንሸራሸር ልዩነቱን ለማጥበብ ሙከራዎች ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ይህ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የተፈጠረ ውዝግብ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ሆኖ በመውጣት የተለያዩ ኃይሎች መካከል የሐሳብ ልዩነት ከመፍጠሩም በላይ በአፍሪካና በዓረብ፣ መካከል የተፈጠረ ልዩነት እስኪመስል ድረስ የተለያዩ ድምፆች የተሰሙበት ሁኔታ ተስተውሎ ነበር፡፡

ሒደቱ በዝርዝር ሲፈተሽ

የአሜሪካኖቹ ተግባር ከዓለም አቀፍ የግጭት አፈታት ሥርዓትና ደንብ ያፈነገጠ ነበርን? እዚህ ይህን ጉዳይ ማንሳት ያስፈለገበት ምክንያት አሜሪካኖቹ በዓለም አቀፍ ድንበር ዘለል ወንዝ አስተዳደር ድርድር ዙሪያ የተጫወቷቸው ሚናዎችን ከሕጋዊነትና ከተቀባይነት አንፃር በጥልቀት ወይም በጥንቃቄ በመመርመር፣ በክፍል ሁለት ሥር የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች በድጋሚ እዚህም በማቅረብ ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡ በዚህም መሠረት አንደኛ የአሜሪካኖች ሚና ከታዛቢነት ደረጃ ባለፈ የተፈጸመ አልነበረምን? ሁለተኛ አሜሪካ እንደ አሸማጋይነቷ ኢትዮጵያ ባልተሳተፈችበት ከግብፅና ከሱዳን ጋር በተናጠል በሒደቱ መቀጠሏ አግባብነት ነበረውን? ሦስተኛ ኢትዮጵያ መጨረሻ ላይ በድርድር ሒደቱ መሳተፍ ማቋረጧን ገልጻ ባለበት ሁኔታ፣ አሜሪካ በብቸኝነት ረቂቅ የስምምነት ሰነድ አዘጋጅታ ለሦስቱ አገሮች ፊርማ ማቅረቧ ተቀባይነት ያለው አካሄድ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላልን? በመጨረሻም ኢትዮጵያ በዚህ ረቂቅ ሰነድ ላይ ፊርማዋን ሳታስቀምጥ፣ የግድቡን ውኃ ሙሌት ማካሄድም ሆነ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሩ ላይ የፍተሻ ተግባር መፈጸም እንደማትችል የሚገልጽ መግለጫ መውጣቱ የሕግ መሠረትና ተቀባይነት ያለው ነውን?

ከላይ የቀረቡትን ጥያቄዎች በዝርዝር ከማየታቸችን በፊት የተወሰኑ ነጥቦች ስለግጭት አፈታት የሕግ ሥርዓት አንስተን እንመልከት፡፡ በመጀመርያ ግጭትን ለማስወገድ የመመካከር፣ የመደራደር፣ የማሸማገል፣ የማስታረቅና ምርመራን የማካሄድ ተግባር ከዓለም አቀፍ ሕግ አንፃር የሚፈጸም ቢሆንም ተግባሩ የዳኝነት ሥርዓትን የሚጨምር አይደለም፡፡ እነዚህ የግጭት ማሳወገጃ ሥርዓቶች በሙሉ ከሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች ይሁንታ ካገኙ በኋላ ብቻ የሚፈጸሙ ተግባራት ናቸው፡፡ የማስታረቅና የምርመራ ተግባር ከሆነ ደግሞ ሦስተኛው ወገን የደረሰበትን ግኝት በጽሑፍ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ይህም ተፈጻሚ የሚሆነው ሁለቱ ወገኖች በቀረበው ሐሳብ ላይ ስምምነት ላይ እስኪደርሱ ብቻ ይሆናል፡፡

በተመሳሳይ በማሸማገል ተግባር ላይ የተሰማራ ሦስተኛ ወገን ሁለቱ አካላትን ለማነጋገር ሁኔታውን እንዲያመቻችላቸው ከጠየቁትና የሚደረስበትን ስምምነት በማዘጋጀት እንዲረዳቸው ድጋፍ ከጠየቁ፣ ይህንኑ አዘጋጅቶ የማቅረብ ድርሻ ሊኖረው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ተዘጋጅቶ የሚቀርበው ሰነድ ላይ ሁሉም አካላት መስማማታቸውን እስካልገለጹና የሚቀበሉት መሆናቸውን በይፋ እስካላሳወቁ ድረስ፣ በሦስተኛው ወገን ተዘጋጅቶ የቀረበውን ሰነድ በመልካም ፈቃድና ጥረት ከተፈጸመ በጎ ተግባር ውጪ፣ ሕጋዊ ተፈጻሚነት የሌለው ነጭ ወረቀት ከመሆን የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡

እ.ኤ.አ. በ1997 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ኮንቬንሽን ከላይ ከቀረበው ጋር ተመሳሳይ አካሄድን የሚከተል መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ለዚህም ማስፈጸሚያ ዝርዝር መመርያ በማዘጋጀት በተፋሰስ አገሮች መካከል ግጭቶች ሲከሰቱ እውነታ አፈላላጊ አካል ወደ መሰየም እንዲያመሩ ያስገነዝባል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 ሦስቱ አገሮች ኢትዮጵያ፣ ግብፅና፣ ሱዳን የተፈራረሙት የመርሆች መግለጫ በመባል የሚታወቀው ሰነድ አንቀጽ አሥር የመመካከርና የድርድር አቅጣጫን አገሮቹ እንዲከተሉ የሚጠቅስ ስለሆነ፣ ይህም የማይሠራ ሆኖ ሲገኝ ጉዳዩ ወደ ሦስቱ አገሮች ርዕሰ ብሔሮች እንደሚያመራ ተስማምተዋል፡፡

ከዚህ በላይ የቀረበው የዓለም አቀፍ ሕግ ደንብና ሥርዓት ላይ በመንደርደር አንደኛና ሁለተኛ ጥያቄዎችን በአንድነት አጣምረን ማየት የምንችል ሲሆን፣ ሒደቱን በጥልቀት ለመመርመር ያህል የአሜሪካና የዓለም ባንክ የአሸማጋይነት ሚና ሦስቱም አገሮች ተስማምተው በይፋና በጋራ የመረጡ መሆናቸውን የሚያመላክት ማስረጃ ማግኝት ያልተቻለ ሲሆን፣ አሜሪካ አገሮቹን ለማነጋገርና ለማቀራረብ ፈቃደኝነቷን በመግለጽ ጥሪ ማቅረቧን ለዚህም ሦስቱ አገሮች አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ መሆናቸውን ግን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህም ሆኖ በምን ዓይነት ሁኔታና ለምን ዓላማ ፈቃደኝነታቸውን እንደገለጽ የሚያመላክት ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ከመጀመርያው አንስቶ ኢትዮጵያ ሁለቱ አሸማጋይ ወገኖች በታዛቢነት ደረጃ ብቻ እንዲሳተፉ ያሳወቀች ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የሦስተኛ ወገኖች ሚና ከታዛቢነት የዘለለ አለመሆኑን በመግለጻቸው በመጀመርያዎች የድርድር መድረኮች የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ ተወካዮች ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነትና ተሳትፎ ሳያሳዩ የታዛቢነት ሚናቸውን መፈጸማቸው ታይቷል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የአሜሪካ መንግሥት ተሳትፎ የሕግ ረቂቅ እስከ ማዘጋጀት የሚዘልቅ ኃላፊነት እንዲኖረው መፍቀድ ቀርቶ፣ በቀጥታ የአደራዳሪነትና ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ እንዲወጣ ፍላጎት እንዳላሳየች መገንዘብ ይቻላል፡፡

ይሁን እንጂ አሜሪካኖቹ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የሚታየውን የተራራቀ አቋም ለማጥበብ፣ ከስብሰባ አዳራሾች ውጪና በድርድሩም መሀል አስታራቂ ሐሳቦች በማቅረብ ድጋፍ ለመስጠት መሞከራቸው እውነት ነው፡፡      በአንፃሩ ግብፅ የሦስተኛ ወገን በአሸማጋይነት እንጂ በታዛቢነት ደረጃ ብቻ ታጥረው እንዲቀመጡ ፍላጎት እንዳልነበራት በግልጽ ታይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በተከታታይ ከድርድር መድረኮች መጨረሻ የሚወጡ መግለጫዎች በትሬዥሪ ዲፓርትመንት ድረ ገጽ ላይ የተለጠፉ ሰነዶች፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. የካቲት 13 ቀን 2020 የወጣው መግለጫ ላይ በግልጽ እንዳሰፈሩት የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ የነበራቸው ሚና በታዛቢነት ደረጃ ብቻ የሚገለጽ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም ከዚህ መንፈስ ውጪ የተካሄደ የድርድር ሒደት ከዓለም አቀፍ ሕግ ያፈነገጠ ሦስቱ አገሮች ስምምነት ከደረሱበት የመርሆች መግለጫን የሚፃረር በመሆኑ፣ በሕግ ፊት ተቀባይነት የሌለው እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቁጥር ሁለት ላይ ለሰፈረው ጥያቄ ምላሽ የሚሆን ድምዳሜ ደግሞ አሜሪካ እንደ አንድ ታዛቢ ኢትዮጵያ ባልተካፈለችበት፣ ሱዳንና ግብፅን ብቻ የሚያካትት የተናጠል ስብሰባ የማመቻቸትና ድርድሩን የማስቀጠል ተግባር መፈጸሟ ኃላፊነት ወይም ተቀባይነት የሌላት መሆኗን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፣ ለድርድሩ መጨናገፍ ምክንያት እንድትሆን አድርጓል፡፡

ገለልተኝነትና ጣልቃ ያለ መግባት ሕግ በጥብቅ መከበር ያለበት ስለመሆኑ

ሦስተኛውን ጥያቄ ለመመለስ መንደርደሪያ የሚሆኑ ጉዳዩችን ጠቃቅሶ ማለፍ ሒደቱን ለመረዳት ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል፡፡ በዚህም መሠረት ለአሜሪካ ረቂቅ የሕግ ሰነድ አዘጋጅታ ማቅረብ መነሻ የሆኑ ምክንያቶች መኖራቸውን ከየካቲት 13 የጋራ መግለጫን በማየት መረዳት የሚቻል ሲሆን፣ መግለጫውም ላይ እንደ ሰፈረው አሜሪካ የመጨረሻውን የስምምነት ሰነድ አዘጋጅታ ለማቅረብ ሁኔታዎችን እንደምታመቻች ተደራዳሪዎቹ ዕውቅና የሰጡበትን ሁኔታ ተጠቅሷል፡፡ ይህን ጉዳይ ከኢትዮጵያ አንፃር ስንመዝነው የትሬዥሪ ዲፓርትመንቱ ቀደም ባለው ጊዜ ረቂቅ ሕግ የማዘጋጀት ኃላፊነት እንዳለው ምልክት የሚሰጡ መግለጫዎችን በሚያወጣበት ወቅት የተቃውሞ ድምፅ ሳታሰማ ያለፈችበት ሁኔታ፣ ለጉዳዩ በተዘዋዋሪ ዕውቅና የመስጠት አዝማሚያ የተከተለች አስመስሎባታል፡፡

ይሁን እንጂ ረቂቅ ሕግ አዘጋጅቶ ለማቅረብ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ኃላፊነት መስጠት ማለት ደግሞ፣ አገሮቹን ሳያማክሩና ሐሳባቸውን ሳያዳምጡ ያለቀለት ሰነድ አሰናድቶ ማቅረብ ከሚለው ኃላፊነት ጋር የሚጣጣም አለመሆኑ የአሜሪካኖቹን ገለልተኛነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተደራዳሪዎቹ በዋሸንግተንም ሆነ በዚሁ የአፍሪካ ክፍል ባካሄዷቸው የድርድር መድረኮች ለአሜሪካ በተናጠልም ሆነ ወይም ከግብፅ ጋር በጋራ ረቂቅ የሕግ ሰነድ አስናድተው እንዲያቀርቡ ውክልና ያልተሰጣቸው መሆኑ፣ ተግባራቸው ነፃና ገለልተኛ አካል የሚፈጸመው እንዳይሆን አድርጎታል፡፡

ኢትዮጵያ ተረቅቆ የቀረበውን የስምምነት ሰነድ ውድቅ ካደረገችባቸው ምክንያቶች አንዱ በሰነዱ የተካተቱት አንዳንድ ሐሳቦች በድርድር ሒደት ያላለፉ ወይም በቴክኒክም ሆነ በሕግ ንዑሳን ቡድኖች ዘንድ ቀርበው ያልተተቹ፣ የግብፅ ፍላጎትን ለማሟላት በግል ተነሳሽነት የሰነዱ አካል እንዲሆኑ የተደረጉ ናቸው በሚል ነበር፡፡ ይህ የአሜሪካኖቹን ገለልተኛ አለመሆን በርካታ ወገኖች እንዲያነሱ ያደረገ ሲሆን፣ ከእነዚህም የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ምሁራን የቀድሞ ዲፕሎማቶችና ሌሎችንም የሚጨምር ነበር፡፡

በመሆኑም የአሜሪካ የስምምነት ረቂቅ ሰነድ ዝግጅት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያላሳተፈ መሆኑ፣ ከዲፕሎማሲያዊም ሆነ ከሕግ አንፃር በስህተት የተሞላና ደካማ ተግባር ተደርጎ እንዲወሰድ ያደርገዋል፡፡ ይህ አሜሪካ የሕግ ረቂቅ አዘጋጅታ ወደ ማቅረብ መሸጋገሯ በቀጥታ ለአራተኛው ጥያቄ ምላሽ መስጠት እንድንችል የሚመራን ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት በተሰናዳው ሰነድ ላይ አገሮቹ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ አሜሪካ ያደረገችላቸው ጥሪን ተከትሎ ሦስት ዓይነት ምላሾችን ይዞ የመጣ ሲሆን፣ በዚህም ግብፅ ጥቅሟን እንደሚያስከብርላት በማመን በበጎ መንፈስ መቀበሏን ከሁሉም ቀድማ በማሳወቅ ሰነዱን ስትቀበል፣ ሱዳን በሰነዱ ላይ ፊርማዋን ከማኖርም ሆነ ሰነዱን መቀበሏን ከማሳወቅ ተቆጥባ ግልጽ አቋም ሳታሳይ ሁኔታውን በገለልተኛነት መንገድ መያዝ የፈለገች መስላ ታየች፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ በስምምነቱ ላይ ፊርማዋን እንድታኖር የተለያዩ ጫናዎች ቢደርስባትም፣ ሁኔታውን ተቋቁማ ስምምነቱን የማትቀበል መሆኗን ተቃውሞዋን አሰምታለች፡፡

በአንድ የአደራዳሪ አካል ተዘጋጅቶ የቀረበ የስምምነት ሰነድ መቀበል በራሱ ችግር ያለበት ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም፡፡ እንዲሁም ሕጋዊነት የሌለው ተደርጎ ሊቀርብም አይችልም፡፡ ነገር ግን ይህ ዓይነት ሰነድ ሲዘጋጅ በቀና መንፈስ ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀ ከሆነ ዝግጅቱና የሰነዱ አቀራረፅ ያገባናል ባዮችን እያማከረና እያሳተፈ እስከ ተፈጸመ ድረስ፣ የገለልተኝነት መሥፈርትን ያሟላና ቅቡልነት ያለው ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የአሜሪካ ትሬዥሪ ዲፓርትመንት የተከተለው መንገድ ግን ፈጽሞ ከወገንተኛነት የፀዳ ባለመሆኑ ሕጋዊ ነው ብሎ ማስቀመጥ ያስችግራል፡፡ ይህ ተግባር ከዓለም አቀፍ ሕግ አንፃር በአንድ ሉዓላዊ አገር የውጭ ግንኙነትና ጉዳይ ውስጥ የጣልቃ ገብነት ተግባር መፈጸሙንም ያመለክታል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የድርድሩ ሒደትና የተቀረፀው ረቀቅ ስምምነት የተሟላና ሕጋዊነት የተላበሰ እንኳን ቢሆን፣ ኢትዮጵያም ሆነች ማናቸውም አካል የህዳሴው ግድብ ላይ ያለውን ጥቅም አያስከብርልኝም ብሎ እስካመነ ድረስ የቀረበለትን የስምምነት ሰነድ ያለመቀበል፣ እንዲሁም ያለመፈረም ሙሉ መብት ያለው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

የትሬዥሪ ዲፓርትመንት ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት ሥራ እንዳትጀምር እንዲሁም የኃይል ማመንጫ የሥራ ክፍሎች ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የሙከራና የፍተሻ ተግባር እንዳትፈጽም ያሳለፈው የየካቲት 13 መግለጫ በእውነታ ላይ የተመሠረተና በቂ ምክንያት ያለው አስመስሎ ለማቅረብ ሙከራዎች ቢያደረግም፣ እውነቱ ግን ከዚህ በተፃራሪው ሊታይ የሚገባ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የአሜሪካ መንግሥት ለወሰዳቸው አቋሞች ምክንያት ያደረጋቸው አንደኛ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች የውኃ ደኅንነት (Water Security) ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመከላከል ከማሰብ የመነጨ ተደርጎ ሊታይ እንደሚችል ሲገልጽ፣ በተመሳሳይ የግድቡ የግንባታ አስተማማኝነት ላይ ካደረ ሥጋት በሚመነጭ ለጥንቃቄ የተወሰደ አቋም አድርጎም ለማቅረብ ሞክሯል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት በአገሮቹ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ወደ ውጥረት አምርቶ የደኅንነት ቀውስ በማስከተል፣ በሁለቱም የአሜሪካ ሸሪኮች መካከል ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ቀድሞ ከመገንዘብ የመነጨ የአርቆ አስተዋይነት ተግባር አድርጎ ለማሳየትም ሞክሯል፡፡ ይሁን እንጂ በቀጣናው ሊከሰቱ የሚችሉ የደኅንነት ሥጋቶችም ሆነ የውኃ ደኅንነት ችግሮች በሚል የቀረቡ መላምቶችን በቅርበት ለመረመራቸው የፈጠራ ድርሰቶች በመደርደር ቀልብ ለመሳብና ለማስመሰል የቀረቡ መሆናቸውን፣ ሦስት ዋና ዋና ነጥቦች አንስቶ ማሳየት ይቻላል፡፡ አንደኛ የትሬዥሪ ዲፓርትመንት ቀደም ብሎ ካወጣቸው የጋራ መግለጫዎች በአንዱም የደኅንነት ሥጋቶች የሚያመለክት ችግር አንስቶ አለማወቁ ሲሆን፣ ሁለተኛው እጅግ ከመጠን ያለፈ ለታችኛው ተፋሰስ አገሮች ልዩ የመጠቀም መብት የሚሰጥ የውኃ ይዞታቸው ላይ በጥንቃቄ ጥበቃና ከለላ መስጠቱ በመግለጫዎቹ ውስጥ የሚንፀባረቁ መሆናቸው ነው፡፡

ሦስተኛው ትሬዥሪ ዲፓርትመንት ካወጣቸው ተከታታይ መግለጫዎች በአንዱም የመርሆች መግለጫ ስምምነቱንና የእሱም ዋነኛ መግለጫ የሆኑት ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀምና ጉልህ ጉዳት በሌላው ላይ አለማድረስ የሚሉትን ሲጠቀስ አለመስተዋሉ የሚሉት፣ በአጠቃላይ የአደራዳሪነት ኃላፊነትን የወሰዱት አካላት ነፃ ያልሆኑና ገለልተኝነት የማይታይባቸው እንደነበረ ያሳያል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌትም ሆነ የተርባይኖች ፍተሻ እንዳታካሂድ የተጣለባት ማዕቀብ ከዚሁ ወገንተኝነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ከዚህ በላይ የቀረቡትን ሐሳቦች በማየት አሜሪካ በዚህ ጉዳይ ውስጥ እንድትገባ ገፊ ምክንያት የሆናት በአገሮቹ መካከል የተከሰተው የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የሚያጋጥም ችግርን ለመፍታት በማሰብና በቀጣናው ላይ ሊከሰት የሚችል የደኅንነት ቀውስን ከማስወገድ አንፃር መፍትሔ ለማፈላለግ ሳይሆን፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ባለው ጂኦ ፖለቲካ ላይ አጋር ለማግኘት ካላት ፍላጎት የታላቁ ህዳሴ ግብፅን የዚህ ዓላማ ማስፈጸሚያ ለማድረግ አቅዳ የተንቀሳቀሰችበትን ሁኔታ በዋነኛ ገፊ ምክንያትነት መውሰድ እንደሚገባ፣ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ተመራማሪዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ይደመጣል፡፡

በእነዚህ ወገኖች እምነት ይህን ውስብስብ የሆነ የድንበር ዘለል ወንዞች አጠቃቀም ችግር ከአሜሪካ የውጪ ፖሊስ ጥቅም ጋር አስተሳስሮ ለመፍታት መሞከር፣ ቀውሱን ከፍ ወዳለ ደረጃ በማሸጋገር ዘለቄታዊ መፍትሔ ማሳጣት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ሲጠቃለል በኢትዮጵያ፣ በግብፅና፣ በሱዳን መካከል የተካሄደው ድርድር ላይ የአሜሪካ መንግሥት ተግባር የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን በመጣስ በጥቅሟና መብቶቿን አስመልክቶ ባደረገቻቸው ድርድሮች ላይ ጋሬጣ ከመሆን በተጨማሪ፣ በረቂቅ ስምምነቶች ቅርፅና ይዘት ላይ ይሁንታዋ ሳይጠየቅ በተፅዕኖ ፊርማ እንድታኖር ጫና ከማሳደር ጀምሮ የህዳሴ ግድብ ውጤት ፍሬ እንዳያፈራ የግንባታው ሒደት ላይ ማዕቀብ በማሳረፍና እንቅፋት በመፍጠር ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡

ከእነዚህ ተግባራት በመነሳት በተለያየ ጊዜያት የወጡ የጋራ መግለጫዎች ከተደራዳሪ ወገኖች ከዕውቅና ውጪ የተፈጸሙ በመሆናቸው በሕግ ፊት ተቀባይነት የማይኖራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ ሕግ በሉዓላዊ አገሮች የውስጥና የውጭ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የሚለውን ደንብ የሚጥስ ነው፡፡ አሜሪካ በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ ጣልቃ ገብነት በመፈጸም ላደረገችው ተግባር አግባብ በሆነ የዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ተጠያቂ መሆን ይኖርባታል፡፡

ማጠቃለያ

በመጀመርያ እነዚህ ሦስት ቀደምት ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር የነበራቸው አገሮች እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ በመደጋገፍና በመተባበር በህዳሴው ግድብ ላይ ያላቸውን ልዩነትና ችግር በጋራ ለመፍታት ጠንክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም በተቻለ መጠን የሦስተኛ ወገን አደራዳሪ ኃይል ሳያስፈልጋቸው ቢፈጽሙት ይመረጣል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ቴክኒካዊና መሰል ድጋፎች ካስፈላጋቸውም የሦስተኛ ወገን ተሳትፎ የሚገድብ መሆን አይኖርበትም፡፡ ይህ ተሳትፎ ግን በምንም ዓይነት ምክንያት በተደራዳሪዎቹ ላይ ጫና የማሳደር ሥልጣን ወይም ማናቸውንም ተደራዳሪ አካል ላይ የማስገደድና ከፍላጎቱ ውጪ የማይቀበለው ሐሳብ ሊጫንበት አይገባም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሦስተኛው ወገን ተግባር ሁሉ የተደራዳሪ አገሮችን ዕውቅና እያገኘ እነሱ ብቻ ፈቃደኛነታቸውን በሚገልጹበት ላይ ተመሥርቶ የሚፈጸም መሆን ይኖርበታል፡፡

ይህም የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ የምሥራቃዊው ናይል ተፋሰስ አገሮችን ለማሸማገል በሚል ገብተው ከፈጠሩት ችግር በቂ ትምህርትና ተሞክሮ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ ሁለተኛ ሦስቱ የምሥራቅ ናይል ተፋሰስ አገሮች ለችግሮቻቸው ፍትሐዊና ምክንያታዊ መፍትሔ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረትና የታላቁ ህዳሴ ግድብ አሞላልና አስተዳደርን በተመለከተ ያላቸውን ልዩነት በወንድማማችነት መንፈስ ለማጥበብ፣ የመርሆች መግለጫ በመባል የሚታወቀው የስምምነት ሰነድና የዓለም አቀፍ ሕጎችን ላይ ተመሥርተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሦስተኛ አገሮቹ የሚያካሂዱት ስምምነት ማተኮር የሚኖርበት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ብቻ የተወሰነ ሆኖ፣ ሌሎች ጉዳዮች ከዚህ በተለየ መድረክ ሁሉንም የተፋሰሱ አገሮች በሚያቅፍ መንገድ የሚታይ መሆን ይኖርበታል፡፡

ከዚህ ውጪ የናይል ወንዝ የውኃ ክፍፍልን በህዳሴው ግድብ ሙሌትና አስተዳደር ስም አደባልቆ ለመፈጸም መሞከር፣ እንዲሁም በድርቅና በተራዘመ ድርቅ ወቅቶች የሚከሰቱ ሁኔታዎችን እያነሱ ተደራዳሪ ወገኖችን በበርካታ አጀንዳዎች የማጨናነቅ ተግባር ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ የአንድን አገር ሉዓላዊነት ከመጋፋት ጋር የሚያያዝ ተግባር ነው፡፡ በመጨረሻም ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና ሚዛኑን የጠበቀ መፍትሔ ለማግኘት መወሰድ ካለባቸው ጉዳዮች መካከል 65 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን የኤሌክትሪክ ኃይል የማግኘት መብት፣ እጅግ የከፋ የድህነት ኑሮ በመግፋት ሕይወታቸውን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሚሠፈር የዕርዳታ ስንዴ ላይ ጥገኛ ሆነው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ወገን እያሰብን መሆን ሲኖርበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሱዳንና የግብፅ ሕዝቦች በናይል ወንዝ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ከግንዛቤ በማስገባት መሆን ይኖርበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በስኮትላንድ ዩኒቨርሲቲ አፍ አብርዲን የሕግ ፕሮፌሰርና በአሁኑ ወቅት በዚሁ ዩኒቨርሲቲ በማስተማርና በምርምር ሥራ የተሰማሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚገልጽ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...