Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበጤና ሥርዓት ጠቃሚ ጅምሮቻችን ላይ እየገነባን አለመቀጠላችን ክፉኛ ጎድቶናል

በጤና ሥርዓት ጠቃሚ ጅምሮቻችን ላይ እየገነባን አለመቀጠላችን ክፉኛ ጎድቶናል

ቀን:

በተስፋዬ ቡልቶ (ዶ/ር)

ፉት ሦስት ወይም አራት መንግሥታት ሥር በጤና ሙያ ያገለገልን ሁሉ ወደኋላ መለስ ብለን ስናስብ፣ በዋዛ ያመለጡን በርካታ ዕድሎች የሚያስቆጩ ናቸው፡፡ አሮጌ መንግሥት በአዲስ ሲተካ በሚካሄድ የፖሊሲና የአሠራር ሥልት ክለሳ ተሰፋ የሚሰጡ ጅምሮች ተለይተው ጎልብተው የሚቀጥሉትን ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ፣ በግብታዊ ውሳኔ እንዲቀየሩ ወይም የተለየ ደካማ ቅርፅ እንዲይዙ ሲደረግ በመቆየታችን ወደፊት ከዚህ የአዙሪት ቀለበት የምንወጣበትን ቀን እንጠብቃለን፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጤና ችግር ተላላፊ በሽታዎችና ከሥርዓተ ምግብ መዛባት የተነሳ የሚከሰቱ የጤና መታወክ ሆነው የቆዩ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችም እየተስፋፉ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህን የጤና ችግሮች ለመከላከልና ለማከም የሚያስችል የጤና ሥርዓትና ዝርዝር የአፈጻጸም ሥልቶች ቀደም ሲል በንጉሠ ነገሥቱ አስተዳደር፣ ቀጥሎም በደርግና በኢሕአዴግ ተቀርፆ መተግበሩ አልቀረም፡፡ የዚህን  ጽሑፍ መሠረተ ሐሳብ ለማብራራት በገጠር የሚኖረውን ሕዝባችንን የአገልግሎቱ ተደራሽ ለማድረግ የተሞከሩ ሥልቶችን እንደ ምሳሌ ወስደን ያጋጠሙንን ውጣ ውረዶች እንመለከታለን፡፡

በንጉሡ ዘመን ዋነኛው ትኩረት ተላላፊ በሽታን መቆጣጠር ሆኖ፣ በወቅቱ በተለይም ብዙ ሕይወት ይቀጥፍ የነበረውን የወባ በሽታን ለማጥፋት ጭምር ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋልታ የሆነውን አርሶ አደር የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተዘረጋው የጤና ሥልት፣ በወቅቱ በነበሩት በእያንዳንዱ አውራጃ አንድ ወይም ሁለት ጤና ጣቢያ ማቋቋም ሆኖ አመርቂ የሚባል ውጤት ታይቶ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ጤና ጣቢያን የሚመሩ ባለሙያዎች ማለትም አንድ የጤና መኮንን፣ ሁለት የኅብረተሰብ ነርሶችና አንድ የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያ በጎንደር ጤና ኮሌጅ በቡድን እንዲሠለጥኑ ሲደረግ፣ ተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች (የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት፣ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት ተራድኦ) የንዋይና የቴክኒክ ዕገዛ ይሰጥ ስለነበሩ የሙያተኞቹ ዕውቀትና ክህሎት አመርቂ መሆን ችሎ ነበር፡፡ በኋላም ለትግበራው በጀትን ጨምሮ የመንግሥት ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ፣ የጤና ጣቢያዎች የአገልግሎት ጥራት የሕዝብ አድናቆት የተቸረው ለመሆን በቅቷል፡፡

የ1966 ዓ.ም. አብዮትን ተከትሎ ደርግ አገራችንን በአስተዳደረበት ወቅት ግን የጤና አገልግሎት ጥራት የበለጠ በመሻሻል ፈንታ፣ አንድ ዕርምጃ ወደ ኃላ ተመልሷል ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ዋና ምክንያት የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የውጭ ወረራና ተደጋጋሚ ድርቅን ተከትሎ የሕዝብ መፈናቀል በመከሰቱ መደበኛ የጤና አገልግሎት ወደ ዘመቻ ሥራ ለመለወጥ በመቻሉ ነው፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉም በርካታ የጤና ባለሙያዎች አገር ጥለው የኮበለሉት በዚህ ወቅት ነው፡፡

ሌላው ሊጠቀስ የሚገባው ግብታዊ የደርግ ውሳኔ፣ የጤና መኮንን ሥልጠና እንዲቀር መደረጉ ነው፡፡ ለዚህም የተሰጠው ምክንያት ለጤና መኮንኖች የዕድገት መሰላል አለመኖሩ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የነርሶችን ሙያ ከፋፍሎ በአጭር ጊዜ ሥልጠና በርካታ ዓይነት (ክሊኒካል፣ ፐብሊክ ሄልዝ፣ ሲኒየር፣ ጁኒየር) ነርሶች እንዲፈጠሩ በመደረጉ የአሠራር  መዘበራረቅ ሊከሰት ቻለ፡፡ በዚህ ምክንያት በጤና ጣቢያ በጤና መኮንኖች ይሰጥ የነበረው የማከም አገልግሎት ጥራት ተዳከመ፡፡

ደርግን ተከትሎ ለ27 ዓመታት ኢሕአዴግ አገራችንን ባስተዳደረበት ጊዜ አንፃራዊ መረጋጋት በነበረበት ሁኔታ፣ አዲስ የጤና ፖሊሲ ተቀርፆ ሊተገበር ችሏል፡፡ ከሁሉም በላይ ክልሎች ከሞላ ጎደል ያላማከለ የአስተዳደር ሥርዓት እንዲከተሉ ሲደረግ፣ የክልል ጤና ቢሮዎችና የወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤቶች እንደ አዲስ ሊደራጁ ችለዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ክልሎች በየአምስት ዓመቱ ተከታታይ የጤና ሴክተር ልማት ፕሮግራም በተለያዩ አጋር ድርጅቶች እየታገዙ እንዲተገብሩ በመደረጉ መልካም የሚባል ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ብዙዎችን ያስቆጨው የጤና መኮንኖች ሥልጠናም እንዲካሄድ ተደረገ፡፡ ነገር ግን ባለሙያዎችን በቡድን ማሰልጠኑ ቀርቶ በተናጠል በግል ድርጅቶች ጭምር ጥራት ያልነበረው ቁጥር ማብዛት ላይ ያተኮረ ሥልጠና በመካሄዱ አንድ መልካም ዕድል አምልጦናል፡፡

በተጨማሪ የጤና መኮንኖች የሙያ ዕድገት መሰላል ጉዳይ መልስ ባላገኘበት ሁኔታ የጤና ጣቢያዎችን የሚመሩ ኃላፊዎች በችሎታ ሳይሆን የፖለቲካ ተቯሚዎች እንዲሆኑ በመደረጉ፣ እንዲሁም በሌሎች በርካታ ምክንያቶች በንጉሡ ጊዜ የነበረው ሥርዓትና የአገልግሎት ጥራት ተመልሶ ሊታይ አልቻለም፡፡

በንጉሡና በደርግ ጊዜ የጤና ሥርዓት ክፍተት ሆኖ የቆየው ሌላዉ ጉዳይ በጤና ጣቢዎች ሥር፣ የቀበሌዎችን ብሎም የእያንዳንዱን ቤተሰብ ጤና በሕዝብ ተሳትፎ የማጎልበት ሥልት አለመዘርጋቱ ነበር፡፡ በንጉሡ ጊዜ በጤና ረዳቶች ይሰጥ የነበረ የክሊኒክ አገልግሎት በሽታን የመከላከል ተግባራት ደካማ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በደርግ አስተዳደር ወቅትም የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1978 ያወጀውን መሠረታዊ ጤና ክብካቤ፣ ኢትዮጵያም ተቀብላ በበጎ ፈቃደኞች የቀበሌ ጤና ተጠሪዎች መጠነኛ ሥልጠና ተሰጥቷቸው የንቅናቄውን መርሆ እንዲተገብሩ የተሞከረ ቢሆንም፣ በበጎ ፈቃደኞች ላይ የተመረኮዘ ነፃ አግልግሎት ተቋማዊ መሆን አልቻለም፡፡

የጤና አግልግሎትን ቤተሰብ ድረስ የማድረስ ሥልት ሥራ ላይ ሊውል የቻለው ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን፣ አሱም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የሚል ስያሜ የተሰጠው ነው፡፡ በዚህም መሠረት በጤና ረዳት ሲሰጥ የነበረው የክሊኒክ አገልግሎትት እንዲቀር ሆኖ በጤና ኬላዎች ተተካ፡፡ በአንድ ጤና ኬላ ውስጥ ሁለት ሴት የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ደመወዝ እየተከፈላቸው፣ በየቀበሌው ማለትም በማካኝ ለ1000 የገጠር ቤተሰብ አግልግሎት እንዲሰጡ ተመደቡ፡፡ መጀመሪያ ላይ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞቹ የሚሰጡት አገልግሎት በሽታን መከላከል ብቻ በሚል የጤና ትምህርት መስጠት ብቻ ሆኖ፣ በመድኃኒት የማከም አገልግሎት እንዳይኖረው ተደርጎ ፕሮግራሙ ተጀመረ፡፡

ከሁለት ሦስት ዓመታት በኋላ ሕክምና የማይሰጡ የጤና ባሙያዎች ሕዝብ ባሠራው የጤና ኬላ ውስጥ መቀመጣቸው፣ በሕዝብ ዘንድ ቅሬታን ፈጠረ፡፡ በኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ መርሆም መከላከልና ማከም ሊነጣጠል አይገባም በማለት፣ በሙያ ማኅበራት ስብሰባዎች ላይ ክፉኛ ተተቸ፡፡ በኋላም በአምስት ዓመቱ የጤና ሴክተር ልማት ፕሮግራም ግምገማ ወቅት ይህ ችግር ግንዛቤ አግኝቶ በተሰጠው ግብረ መልስ፣ በተለይ የሕፃናት ገዳይ በሽታዎች ማለትም የሳንባ ምች፣ ወባና ተቅማጥ እንዲያክሙና በተጓዳኝም የክትባትና ቤተሰብ ዕቅድ ፕሮግራሞችን ለቤተሰብ በቀረበ ሁኔታ እንዲተገብሩ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ በዚህ መሠረት የሥራ ላይ ሥልጠና ለእነዚሁ ባሙያዎች ተዘጋጅቶ በአጋር ድርጅቶችና በክልል ጤና ቢሮዎች ርብርብ ተግባራዊ መሆን ቻለ፡፡ የዚህ አሠራር መቃናትም ኢትዮጵያ በምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ዋነኛ የሆነው ከአምስት ዓመት በታች ሕፃናት ሞት በመቀነስ ላስመዘገበችው ስኬት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ በማንም የታመነ ነው፡፡

ለወደፊቱ ለምናደርገው የፖሊሲ ክለሳም ሆነ የወቅቱን ወረርሽኝ ለመግታት በምናደርገው ጥረት ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በአጭሩም ቢሆን ማየቱ አስፈላጊ ነው፡፡

ምንጊዜም ቢሆን ለምንነድፈው ፖሊሲ ትግበራ አስፈላጊው ንዋይ በተቻለ መጠን ከመንግሥት እንዲቀርብ እንጂ፣ የዉጭ ዕርዳታ ታሳቢ ማድረጉ መቅረት ይኖርበታል፡፡ እስካሁን ጤና ለልማት መሠረት ነው እየተባለ የሚመደበው በጀት የማያወላዳ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

ባለሙያ ለጤና አገልግሎት ትግበራ የጀርባ አጥንት መሆኑን ማንም የማይክደው ነው፡፡ ስለዚህ ለሰው ኃይል ሥልጠና በተለይ ምቹ የተግባር ልምምድ ሥፍራዎችን ማዘጋጀት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የቀድሞው ጎንደር ጤና ኮሌጅ (ከ1946 እስከ 1966 ዓ.ም.)፣ እንዲሁም የጅማ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት ጅምሩ ላይ (1977 ዓ.ም.) ይከተሉዋቸው የነበረው በሁሉም ማሠልጠኛዎች ሊተገብሩ ይገባል፡፡

ከሁሉም በላይ የባለሙያዎቸ አስተዳደር ትኩረት የሚያሻው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ቀደም ሲል በየጦር ሜዳው አሁን ደግሞ በወረርሽኝ ወቅት የሕዝብ ሕይወት ለማዳን ያላዳንዳች ማንገራገር በግንባር ቀደምትነት መሠለፋቸው አምነው የገቡበት የሙያ ግዴታ  በመሆኑ ታውቆ፣ በአሁኑ ጊዜ እየተለገሳቸው ያለው ምሥጋናና እየተገለጸ ያለው አስፈላጊ ማበረታቻ ምንጊዜም መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ለጤና መኮንኖችና ሌሎችም የሙያ ዘርፎች የዕድገት መሰላልም አፋጣኝ መልስ ሊያገኝ ይገባል፡፡

ይህ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ጦርነት የገጠምንበት ወቅት የጤና ሥርዓታች ጥንካሬ አስተማማኝ ባልሆነበት የሽግግር ጊዜ ነው፡፡ በተለይም የገጠሩን ኅብረተሰብ ከኮቪድ 19 ዕልቂት ለመታደግ ጤና ጣቢያዎችና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ላይ በአፋጣኝ በቂ ንዋይ አፍስሰን አቅማቸውን መገንባት ያስፈለጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ጤና ጣቢያዎች ውኃና ኤሌክትሪክ ሳይኖራቸው የማዋለድ አገልግሎት እንዲሰጡ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምም በቂ ሥራ ማስኬጃ የለውም፡፡ እስካሁን በአንዳንድ ክልሎችና ወረዳዎች የታየው አመርቂ የኤክስቴንሽን ሥራ በአጋር ድርጅቶች ቀጥተኛ ድጋፍ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ዘላቂ ሊሆን ስለማመይችል የመንግስት ተከታይ ትኩረት ይፈልጋል፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት የሚዘረጉ የመከላከያ ዘዴዎች ባህል አድርገን ልናስቀጥል የሚገቡ ናቸው፡፡ እጅን በሚገባ መታጠብ ከበርካታ ተላላፊ በሽታዎች ሊጠብቀን የሚችል ዘዴ ነው፡፡ ሌሎችም እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች ማለትም ሕሙማንን ፈልጎ ማግለል፣ ከሕሙማን ጋር ንክኪ ያደረጉን ትምህርት ሰጥቶ መከታተል፣ ለሌሎችም ተመሳሳይ ወረርሽኞች መከላከያ ሊተገበሩ ይገባል፡፡ እነዚህን ዕርምጃዎች ለወደፊቱ መተግበር ከቻልን የአሁኑን የመከራ ጊዜ ወደ በጎ ትምህርት ማግኛ ለወጥነው ማለት ነው፡፡ ይህ ወረርሽኝ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ገጠር ባይስፋፋና የጤና ጣቢያዎች ሚና ያን ያህል ሳይሆን ቢቀር እንኳን፣ በዚህ አጋጣሚ መሠረታዊ የጤና ክብካቤ የማጎልበት ሥራ መጀመሪያ ይሆነናል፡፡ ስለዚህ በሰፊው ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ከዚህ ጋር ልናጤን የሚገባን መሠረታዊ ጉዳይ ይህ ወረርሽኝ በሰፊው በመሠራጨቱና የበለፀጉ አገሮችን ዜጎች ሕይወት በከፍተኛ ቁጥር ማጥፋት በመቻሉ እንጂ፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃ አገሮች ክትባትና ፍቱን የሕክምና ዘዴ ያላቸው እንደ ኩፍኝና ኮሌራ ያሉ ወረርሽኝ ሲከሰትና ብርቅዬ ሕፃናትና አምራቹን ገበሬ በብዙ ቁጥር የሚፈጅበት ሁኔታ ሲፈጠር፣ ብዙም ትኩረት እዳልሰጠነው ይታወቃል፡፡ ለወደፊቱ ግን ከኮቪድ 19  በምናገኘው ልምድ  የወገኖቻችንን ሕይወት መታደጉን ችላ ማለት የለብንም፡፡

ከእንግዲህ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ይኖረናል ብለን ተስፋ እናድርግና የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ሥልጣን ለመጨበጥ በሚያደርጉት ውድድር፣ የሕዝብ ጤና ማሻሻያ ለማምጣት ያላቸውን ራዕይ ለመራጩ ሕዝብ መግለጽ ይኖርባቸዋል፡፡ የጤና ባለሙያዎችና ማኅበራትም በዚህ ጉዳይ ላይ ተገቢውን አቅጣጫ ሊያመላክቱ ይገባል፡፡ ወደፊት መልካም ጅምሮች እንዳይስተጓጎሉም በሚመለከተው ሁሉ ጥበቃ ሊደረገላቸው ይገባል፡፡ የሕዝብ ጤና መታወክ የአገር ልማትና የኢኮኖሚ ድቀት የሚያስከትል መሆኑን የኮሮና ወረርሽኝ ግንዛቤ የሰጠን ስለሆነ፣ ከዚህ የመከራ ጊዜ መውጣት ከቻልን አሁን ኮቪድ 19 ለመዋጋት በያዝነው መንገድ ጤና በሁሉም የመንግሥት ሴክተር ትኩረት ይሰጠዋል ብለን ተስፋ እናድርግ፡፡                                                                                       ጤና ለሁሉም!!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ሐኪምና የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...