በአማረ ተግባሩ (ዶ/ር)
ይህ ጽሑፍ የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና ፖለቲካል ሥርዓት ላይ ጥገኛ በሆኑ፣ እንደ ኢትዮጵያ በመሳስሉት የምግብ ዋስትናን፣ ጤናንና ሰላምን ለሕዝባቸው ማረጋገጥ ባልቻሉ አገሮች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ጉዳት ለመዳሰስ ይሞክራል። ይህ ወረርሽኝ ካለፈ በኋላ ዓለም አቀፋዊ (Globalized) የሆነው የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ግንኙነት እንዴት ሊቀጥል እንደሚችልና ለእኛ የሚያተርፍልን ተጨማሪ መከራ ይሁን ዕድል ምን ሊሆን እንደሚችል በትክክል ለመተንበይ እንደሚያስቸግር ያስገነዝባል። ይህ ወረርሽኝ አገርና መንግሥት፣ ኃያል ይሁን ደካማ፣ ሀብታም ይሁን ደሃ፣ ጥቁር ይሁን ነጭ ወይም ቢጫ ሳይለይና ሳይዘጋጅበት ሁሉንም እኩል ያዳሸቀና ጉዳቱም ሆነ ምስቅልቅሉ በታሪክ አቻ የማይገኝለት መሆኑን እስካሁን የቀረቡት በርካታ ጥናቶች ይናገራሉ። ይህ በራሱ አዲስ ዓይነት ዓለም አቀፋዊ የአስተሳሰብና አቀራረብ (Paradigm Shift) ለውጥ ያስከትል አያስከትል እንደሆነ አሁንም በትክክል መገመት ባይቻልም። አንደኛው ዓይነት የአመለካከት ለውጥ ሀብታም አገሮች ይበልጥ ነጣይና የእኔ ብቻ የሚል (Isolationist and Protectionst) ፖሊሲ ምርጫ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው አዲስ ዓይነት ዓለም አቀፍ ትብብርን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊነቱን የተቀበለ ዓለም አቀፍ ደንብና ሥርዓት (Global Order) ሊሆን ይችላል። ምን እንደሚከሰት መገመት ባይታወቅም፣ የምርምር አቅምና ብቃት ያላቸው ወገኖች በዚህ ጉዳይ ላይ መረባረብ ለመጀመራቸው ምልክቶች እየታዩ ነው።
እኛን በሚመለከት አገራችን ለሕዝቦቿ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለመቅረፍና በተቻለም የውስጥ ሰላም በማረጋገጥና የአካባቢ መረጋጋት በማስፈን ሕዝቦቿን ወደ መካከለኛ ገቢ ለማሸጋገር ያልቻለች መሆኗ ሲታሰብ ይህ ወረርሽኝ ካለፈ በኋላ የሚከሰተው ዓለም አቀፍ ሁኔታ ማሳሰቡ አይቀርም። ለእኛም ቢሆን ጉዳቱ በድኅረ ኮሮና ዘመን ጭምር የሚከተለን መሆኑ ሲታሰብና ሌላም ዓይነት ተመሳሳይ ወረርሽኝ ወይም ተፈጥሯዊና ተፈጥሯዊ ያልሆነ መቅሰፍት በድጋሚ ሊከሰት እንደሚችል ሲገመት በምግብ ራስን ከመቻል አልፎ በግብርና ላይ የተመረኮዘ ብልፅግናን እንዴት መጎናፀፍ እንደሚቻል ከአሁኑ መታሰብ ይኖርበታል።
አማራጩም በውል የተመከረበት የረጅም ዘመን መርሐ፟ ግብር በአስቸኳይ መቅረፅ ነው። ይህም አማራጭ ችግር የማይፈታው፣ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ፣ ተመፅዋችነትንና የምግብ ዕርዳታ ተቀባይነትን የሚያስቀር፣ አገር በቀል የግብርና ምግብ ሥርዓትና ዘላቂ የሆነ የአቅርቦት ሰንሰለት (Resilientdomestic Agri-Food System and Sutainable Supply Chain) መገንባት ነው። ይህንንም አማራጭ በየጊዜው ለውጥ ሊደረግበትና ሊስተካከል እንደሚችል አድርጎ አድርጎ መቅረፅ ይቻላል። በዚህ በኩል ሃቀኛ ፍላጎት ካለ ስትራቴጂውም ዕውቀቱም በአገራችን እንደሚኖርና እንዳለም አልጠራጠርም። በአጭርና በመካከለኛ ዘመን በኤች አይ ቪ ኤድስ ዘመን የነበረውን ልምድ መልሶ በማሰስ፣ በሌሎች አገሮች በእዚሁ ኤች አይ ቪ ኤድስና ኢቦላ ወረርሽኝ ዘመን የምግብ ዋስትናን ከጤናው ዘርፍ ጋር በማቀናጀት ከተገኘው የተሳካ ውጤት ትምህርት መቅሰም እንደሚቻል አምናለሁ። ይህም ትምህርት ምን ሊሆን እንደሚችል በአንድ ግብረ ኃይል በፍጥነት ለውጤት መብቃት (Fast Track) ቢችል ጠቃሚ እንደሚሆን በመጠቆም ጽሑፉን እደመድማለሁ።
የኮሮና ወረርሽኝና ከጤና ችግር ባሻገር ሊያስከትል የሚችለው መዘዝ
የኮሮና ወረርሽኝ ለማንም ይቅርታ የለሽ ዓለም አቀፍ (Global) መቅሰፍት እንደሆነ ምንም ተጨማሪ ማረጋገጫ የማያሻው ነው። ይህም በመሆኑ በዓለም ሕዝቦች ጤና ላይ ያስከተለው ሰቆቃ ከዚህ በፊት በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅትና መንግሥታትም ከዳር እስከ ዳር ተስማምተውበታል። መዘዙ ዓለም አቀፍ (Global) ኢኮኖሚውንና ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ሁሉ ያመሳቀለና ያስከተለውም ድቀት ገና በድኅረ ኮሮና ዘመን ጭምር እንደሚዘልቅ ሳይንሳዊ ጥናቶችና ትንበያዎች (Forecast) እየቀረቡ ነው።
ለምሳሌ ያህል እንደ (William A. Kerr (2020) እና (B. James Deaton et al (2020) የመሳሰሉ ታዋቂ ኢኮኖሚስቶች ባቀረቡት ጥናት ይህ ወረርሽኝ በዓለም (Global) ኢኮኖሚው ላይ ያደረሰው ምስቅልቅል በ2007 እና በ2008 ከደረሰው ግሎባል የፋይናንስ ቀውስና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ቀደም ብሎ ከተከሰተው የ1930 ታላቅ የኢኮኖሚ ዝቅጠት (Great Depression) የከፋ ነው ብለውታል። እነዚሁ ሳይንቲስቶች ከዚህ ቀውስና ኢኮኖሚ ድቀት በኋላ ሊከሰት የሚችለው ዓለም አቀፍ ሁኔታ ምን ሊሆን እንደሚችል በትክክል ለመገመት እንደሚያስቸግር በቅርቡ ባሳተሟቸው ጥናቶች ገልጸውታል።
ይህ ቀውስና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተከተለው መሸበር እጅግ ፈጣን፣ ሥር የሰደደና ቀውሱም ገና ያላከተመ በመሆኑ መቼ ከዚህ ቀውስ ለመውጣት እንደሚችልና የገበያውም እንቅስቃሴ መልሶ ነፍስ በመዝራት መቼ መስተካከል እንደሚያሳይ ለመተንበይ ጊዜ የሚጠይቅ እንደሆነ ጥናታቸው ያመለክታል። የእነዚህ ሳይንቲስቶች ጥናት በተለይም የግብርና ምርትና ንግድ የህልውናቸው መሠረት ላደረጉ አገሮች የምግብ ዋስትናን ለሕዝባቸው ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ጥረት ላይ ትልቅ ፈተና እንደሚሆንባቸው ግምት ውስጥ እንድናስገባ በቂ መንደርደሪያ ይሰጣል። ከዚህ በታች የማቀርባቸው ምልከታዎቼ በእነዚህና ሌሎችም ጥናቶች ላይ መሠረት ያድረገ ሲሆኑ ችግሩ ከጤና ችግር ዘልቆ የሚሄድ መሆኑን አስረግጣለሁ። ይህ ወረርሽኝ በተናጠል የማይታይ፣ ግዙፍና ውስብስብ (Compounded) ከሆነው የምግብ ዋስትና ችግር ጋር የተገናኘ በመሆኑ በግብርና ምርምርና ልማት ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን የአገራችንን ኢኮኖሚስቶችን፣ የሥነ መንግሥት፣ ሥርዓት ፆታና ፖሊሲ አማካሪዎችን፣ የምግብ ሳይንስ ቴክኖሎጂና የምርትና ድኅረ ምርት ባለሙያዎችን (Food Science Technology & Postharvest Specialists) ዕገዛ ይጠይቃል። ስለዚህም በዚህ ውይይት ውስጥ በመሳተፍ ያቅማቸውን ያበረክታሉ ብዮ ተስፋ አደርጋለሁ።
የኮሮኖ ወረረሽኝ በድንገት የተከሰተ መቅሰፍት መሆኑ እንዳለ ሆኖ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ የምግብ ዋስትናን ሊያረጋግጡ ያልቻሉና የውጭ ምንዛሪያቸውን የምግብ ሸቀጦችን ወደ አገር በማስገባት በዓለም አቀፍ የእርሻ ንግድና የምግብ አቅርቦት ሰንሰለታዊ ሥርዓት ላይ ጥገኛ (Agriculture Trade and Food Supply Chain Depenedent) የሆኑ አገሮች ላይ ባጭርና ረጅም ጊዜ የሚያስከትልባቸው ጉዳትና ምስቅልቅል ቀላል አይሆንም። ከዚህ የተነሳ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ አገሮች ከውጭ በግዥ መልክ የግብርናና ምግብ ነክ ሸቀጦችን ለሚያስገቡ አገሮች ለተጨማሪ ችግር በማጋለጥ ይብሱን ወደ ፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ሰላም መደፍረስና ግጭት ሊጋብዝባቸው ይቻላል። ዘርዘር አድርገን እንመልከተው ያልን እንደሆነ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያና ሥርጭቱንም ለመግታት አገሮች በሰዎችና የሸቀጦች ዝውውርና የንግድ ልውውጥ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥርና ማዕቀብ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የራሷ የባህር በር የሌላት አገር አብዛኛውን የውጭ ንግዷን በአየር የምታጓጉዝ እንደ ኢትዮጵያ የመሰለችን አገር ከውጭ ንግድ ይገኝ የነበረውን ገቢ እጅግ አድርጎ ማዳከሙ የማይቀር ነው። በዚህ ሳያበቃ እስከ ዛሬ የእኛን የግብርና ምርት ሲቀበሉ የነበሩ አገሮች የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት በሚል እጅግ የተወሳሰበና ለሟሟላት የሚከብድ የቁጥጥር መመዘኛ እንድናሟላ ሊያስገድዱን ይችላሉ።
አልፎ ተርፎም የምግብ ጥራትንና ደኅንነትን (Quality and Safety) የሚመለከቱ አዳዲስ የቁጥጥር ሥርዓቶችን በማውጣት የውስጥ ገበያቸውን በእኛ ላይ ለመዝጋት አይመለሱ ይሆናል። ወደ ውጭ የምንልካቸው አብዛኞቹ የግብርና ምርቶቻችን ጥራትና ደረጃን በመጠበቅ በኩል የተዋጣልን እንዳልሆነ የታወቀ ነው። በዓለም ገበያም ተፎካካሪ በመሆን ብቃት የጎደላቸው በመሆኑ በገቢ ደረጃ የማሽቆልቆል ችግር እንዳለብን የአደባባይ ሚስጥር ነው። እኛም በበኩላችን የውጭ ምንዛሪ እየተከፈለባቸው ወደ አገራችን በሚገቡት የምግብ ምርቶች፣ ስንዴም ይሁን በቆሎ፣ አኩሪ አተርም ይሁን የምግብ ዘይት ወይም የቆሮቆሮና የታሸጉ አትክልትና ፍራፍሬዎች በተመሳሳይ መንገድ ጥራታቸውን (Standaradized Food Safety Regulation and Product Sepcification) በመመርመር አስተማማኝ ባልሆኑት ላይ ዕገዳ እናድርግ ብንል እነዚሁ ምግብ ነክ ምርቶቻቸውን ማራገፊያ ያደረጉን አገሮች ሊበቀሉን ይችላሉ።
ሌሎች የእኛ የግብርና ምርት ተፎካካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባትም ሆነ በአገር ውስጥ ለማምረት የሚችሉበትን ታሳቢ ቢያደርጉ በዓለም አቀፍ የእርሻ ንግድና የምግብ አቅርቦት ሰንሰለታዊ ሥርዓት (Global Agricultre Trade and Food Supply Chain) ላይ ያለን ጥገኝነት (Dependency) ያመጣብን መዘዝ ነውና ጥገኛነታችንን ሳንወድ በግድ ተቀብለን እንድንቀጥል ልንገደድ እንችላለን። ይህ ብቻ ሳይሆን በፖሊሲ ደረጃ ወዳገር እንዳይገቡ የታገዱት የዘር ውርስ ይዘታቸው የተለወጡ አዝርዕት (GEMO Crops) በእጅ አዙር በታሸጉ ምግቦች በኩል ወደ አገራችን ከመግባት የሚቆጣጠርና የሚያግድ ምንም ጉልበት ባለመኖሩ ሌሎችም የዘር ውርስ ይዘታቸውን እንደ ልብ ለማድረግ የተለወጡ (Gene Manipulated) እንደ ዝንጅብል፣ ቀይና ነጭ ሽንክርት፣ ስንዴ፣ በቆሎና አኩሪ አተር በገበያው በሰፊው ለመገኘታቸው ወይም ላለመገኘታቸው የግብርና ምርምር ባለሥልጣኖች ለማረጋገጥም ለማስተባበልም እንዳይችሉ ሊገደዱ ይችላሉ።
አማራጫችን ችግር የማይፈታው (Resilient) የሆነ አገር በቀል የምግብ አቅርቦት ሰንሰለታዊ ሥርዓት (Domestic agri-food System and Sutainable Supply Chain) መገንባት ነው በሚለው መስማማት ችግር የለውም። ይህንን ለማድረግ ግን የግድ ከኮሮና በአገራችን ከመከሰቱ በፊት የምግብ ዋስትናን በተመለከተ የምንገኝበትን ሁኔታ በሚገባ መረዳት ይኖርብናል። አለበለዚያ የአጭርና መካከለኛ ዘመን የመፍትሔ ሐሳቦች የሚባሉትን ለማቅረብና ከረጅሙ ስትራትጂ አካል ጋር አገናዝቦ ያሰቡት ግብ ለመድረስ ያስቸግራል።
በአገራችን የምግብ ዋስትና ምን ላይ ይገኝ ይሆን?
የምግብ ዋስትናን በሚመለከት የምንገኝበት ሁኔታ ምን ይመስላል ወደሚለው ጉዳይ ከማለፌ በፊት ኢትዮጵያ ከውጭ በምታስገባው የምግብ ምርት ምን ያህል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደምታጠፋ ማውሳት ያስፈልጋል። ይህንንም በማስላት አገራችን ከውጭ በሚገቡ የምግብ ሸቀጦች ላይ ምን ያህል ጥገኛ እንደሆነች መገንዘብ ያስችላል። ይህም ጥገኝነት የሕዝቧ ቁጥር በአደገ መጠን እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ለመሄዱ ምንም ምልክት እንደማይታይ ጥናቶች አጣቅሶ ማለፍ ያስፈልጋል። በ2015 ብቻ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን ከዚህም መካከል አብዛኛውን ድርሻ የያዙት የስንዴና በቆሎ፣ የምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ እንደ ፓስታና ማኮርኒ የመሳሰሉ የስንዴ ምርት ውጤቶች፣ አኩሪ አተርና፣ አተር። ይገኙበታል። በ2016 ደግሞ ከአገሪቱ ባጀት 8.4 በመቶ የውጭ ምግብ ለመግዛት ወጭ ተደርጓል (www.kneoma.com) በ2019 አተር ከውጭ ለመግዛት 53 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሆኗል። ይህ አንግዲህ አገሪቱ በየ ዓመቱ ከምታገኘው 20 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ተጨማሪ የምግብ ዕርዳታን ሳይጨመር ነው። የዚህ ጥናት አቀናባሪዎች ወደ ፊትም አገሪቱ ከውጭ ለምታስገባው የምግብ ሸቀጥ በውጭ ምንዛሪ የምታወጣው ክፍያ እየጨመረና የውጭ ምንዛሪዋን እያራቆተና ይበልጡን ዕዳ ውስጥ እየጨመራት እንደሚሄድ ያትታሉ። ከዚህም የተነሳ አገራችን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዋጋ ግሽበትን ለመግታት አስቸጋሪ እንደሚሆንባትና ይህ ደግሞ ‹‹በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ በመሆን›› ወደ ከፋ የፖለቲካ ትርምስና ግጭት ሊያስገባት እንደሚችል መረዳት አያስቸግርም።
በያዝነው እ.ኤ.አ. 2020 ማለትም የኮሮና ወረርሽኝ በአገራችን ከመግባቱ ቀደም ብሎ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅት አንድ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። በዚህ ሪፖርት መሠረት በ2019 ከዓለም እጅግ የከፋ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ተብለው ከተዘረዘሩት አሥር አገሮች መካከል አገራችን ኢትዮጵያ አንዷ ሆና ተመዝግባለች። ከአፍሪካ ደግሞ ከደቡብ ሱዳንና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር በተርታ ተቀምጣለች (2020:93-96)። በዚሁ ሪፖርት (WFP 2020) እንደተገለጸው ምንም አንኳን ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ ዓመታት በኢኮኖሚው መስክ ዕድገት ያሳየችና ይህም ልማቷን ለማፋጠን አጋዥ ይሆናል ተብሎ ቢገመትም አሁንም ከሕዝቡ 27 በመቶ ማለትም 30.2 ሚሊዮን ሕዝብ ከድህነት ወለል (አንድ ዶላር በቀን) በታች ይገኛል። ከ70 በመቶ በላይ በገጠር የሚኖረው ሕዝብ ለበርካታ ዓይነት የድህነት መለኪያዎች (Multidimensional Poverty Index) የተጋለጠ ሲሆን በተደጋጋሚ በሚከሰት ድርቅ ለዘር ያስቀመጠውን በልቶ የጨረሰ፣ አርሶም ሆነ አርብቶ ለማደር የቋጠረው ቅርስ የወደመበትና የተሻለ አየር ንብረት ለውጥ እንኳን ቢያጋጥም ከተረጂነት ተላቆና አገግሞ በቶሎ አምራች ለመሆን የማይችል እንደሆነ በሌላም ተጨማሪ ጥናት ተዘክሯል (See OPHI, September 2019)።
የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅት (WFP, January 2020) ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ፣ የሥራ አጥ (በተለይም የወጣት ሥራ አጥ ቁጥር) ሊቀረፍ ባለመቻሉ በየክልሉ፣ ወረዳ፣ ዞንና መንደር የሚታየው የእርስ በርስ ግጭት ሊያባብስ ይችላል። በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ዕርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅት (United Nations Office for the Coordination of Humanitarina Affairs) ባወጣው ሪፖርት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ በነፃ የሚንቀሳቀሱ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ለአዳዲስ መፈናቀሎች ምክንያት በመሆናቸው በሰው ሕይወት ላይ ከሚደርሰው ሰቆቃ ባሻገር፣ ከግብርናው ዘርፍ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ምርት ጨርሶ እንዲያሽቆልቁልና የገበያው ሥርዓት የባሰ ቀውስ ውስጥ በማስገባት የምግብ ዋስትናው ላይ ከባድ ጫና በመፍጠር ለመንግሥት ተጨማሪ ችግር እንደሆነበት ያትታል (OCHA, 2020)። በዚሁ ድርጅት ሪፖርት ከ1.6 ሚልዮን በላይ ከሚሆነው ተፈናቃይ መካከል ከሁለት እስከ ሦስት የሚሆነው የተፈናቀለው በብሔርና ብሔረሰብ መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ሲሆን ይህን የመሰለው መፈናቀል ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ከጥር እስከ መጋቢት ወር 2019 ድረስ ያለውን ቁጥር ይዘን በድርቅና አየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከተፈናቀለው ጋር ስናዳምረው ከ3.2 ሚልዮን ይደርሳል (OCHA, 2020)። በዚህ ኮሮና ወረርሽኝ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት ዕርዳታ መተባበሪያ ድርጅትም ሆነ ሌሎች ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንቅስቃሴያቸው በተገታበትና ምናልባትም ባጀታቸውን ወደ ጤናው ዘርፍ ለማዞር በሚገደዱበት ሰዓት ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ሕዝብ ለተደራራቢ የምግብ ዋስትናና ለተወሳሰበ የጤና ችግር እንደሚጋለጥ አያጠራጥርም።
በያዝነው 2012 ዓ.ም. (በፈረንጅ 2020) ከጥር እስከ መጋቢት ወር ባለው ብቻ የበቆሎ ዋጋ በ30 እስከ 65 በመቶ መጨመሩን የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅት ሪፖርት ይናገራል (FAO-GIEWS, December 2019)። በጥቅምት ወር ብቻ በተለይ በአዲስ አበባና በሌሎችም የክልል ከተሞች የጥራ ጥሬ እህል በተለይም የጤፍ፣ ስንዴና ማሽላ የመሳሰሉት ዋጋቸው ከ40 በመቶ በላይ መጨመሩን ጥናቱ ያሳያል (FAO-GIEWS, December 2019)። ይህ የዋጋ ግሽበት በተለይም በአዲስ አበባና በሌሎችም የክልል ከተሞች መታየቱ የብርን የመግዛት አቅም ዝቅ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በተለይም እንደ ነዳጅ፣ ለግብርና የሚያስፈልጉት ግብዓቶችና ትራንስፖርት ወዘተ. ላይ የታየው ትልቅ የዋጋ ጭማሪ ሥጋትንና መፍጠሩ እንደማይቀር ጥናቱ ይጠቁማል።
መንግሥት የአገር ውስጥና የውጭ የግል ባለሀብቶች በግብርናው ዘርፍ በመሠማራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ ሁኔታዎችን አመቻችቶ እንደነበር በሰፊው ስናገር እንደነበር እናስታውሳለን። ደን እየተመነጠረና ሕዝብ በማፈናቀል ለውጭ ባለሀብቶች ሰፋፊ እርሻ ማስፋፊያ ተችሮ ነበር። ውጤቱ ግን ያ የተመነጠረውና ለሰፋፊ የግል እርሻ የተዘጋጀው መሬት አገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን ምግብ ለመቀነስና የምታመርተውንና ወደ ውጭ የምትልከውን በጥራትና በብዛት በማምረት የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት ላይ ያተኮረ እንዳልነበረ ይታወቃል።
እነዚህ የውጭ ባለ ሀብቶች ያመረቱትና ለማምረትም የተጣደፉበት የውጭ ገበያ የሚፈልገውንና ላፈሰሱት መዋዕለ ንዋይ በዓለም ገበያ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ትርፍ አግኝተው፣ ደናችንን ጨፍጭፈው፣ ለሕዝብ መፈናቀል ምክንያት ሆነው፣ የመሬታችንን ምርታማነት አውድመው፣ የውኃ ሀብታችንን መርዘውና በእነዚህ ከፍተኛ እርሻዎች ላይ ተቀጥረው በሚሠሩ ወንድና ሴት የዘመናዊ እርሻ ሠራተኞች ላይ የጤና ቀውስ ፈጥረው፣ ከግብር ነፃ ላስገቡት ንብረት ማንም ሳይጠይቃቸው ከአገር መልቀቃቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። በምግብ ዋስትና ላይ እንኳን የምርት እንቅስቃሴ የነበራቸውም ቢኖሩም ለምን ያህል ጊዜ እንዳመረቱ መረጃው የለም።
እነዚህም ባለሀብቶች ይዘውት ወደ አገራችን የገቡት ‘ምርጥ ዘር’ ምን ያህል በበቂ የተመረመረና ለአገራችንና ለአካባቢው ሥነ ምኅዳር (Agroecological System) የሚስማማ ወይም የማይስማማ መሆኑ ምንም መረጃ ሳይቀርብበት የተቸረው መሬት እንዳለ ምድረ በዳ ሆኖ ቀርቷል። ይህን ስናይ በመንግሥት በኩል የምግብ ዋስትናን ለማረገጋጥና ከምግብ አስመጭነትና ተመፅዋችነት ለመገላልገል በሚል የሚጀመረው ሁሉ ዳር ሳይደርስ ተሰናክሎ የሚቀርበት ምክንያት እጅግ የበዛ መሆኑን ያመለክታል። ከዚህ የተነሳ ዘላቂና የአርሶ አደሩን ጥያቄ የምታሟላ መርሐ ግብር ተቀርፆ አርሶ አደሩ ያለበት ድረስ ሄዶ ተግባራዊ ማድረግም መከታተሉም ቀላል አይሆንም።
አገራዊ መቆርቆር፣ ሀቀኝነቱ፣ ግልጽነቱና የሚያስፈልገው ግብዓት ተስተካክሎና ተቀናብሮ ከቀረበ፣ ብቃቱና ልምዱ ባላቸው የአገራችን ሙያተኞችና አዋቂዎች ከተመራ በግብርናው መስክ ወደፊት የሚሠማሩ የውጭ ባለሀብቶች በምግብ ዋስትና ላይ ያተኮረ፣ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ላይ ያተኮረ ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም። የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅት ሪፖርት የሚለውን ተከትለን በአገራችን የሚጠበቀው ምርት በአየር ንብረት መለወጥም ሆነ በተባይና አንበጣ መንጋ ምንም ጉዳት ሳያገኘው ይሰበሰባል እንኳን ብንል የኮሮና ወረርሽኙን ሥርጭት ለመከላከል ሲባል የሰዎችንም ሆነ ምርትን ከቦታ ቦታ የማመላለስ ዕገዳ ለአጭር ጊዜ ቢሆን መኖሩ በምግብ አቅርቦትና ዋስትና ላይ ትልቅ ጫና መፈጠሩ አይቀርም። ምርት በጊዜው ወደ ገበያ በመውጣት ለሸማቹ ሕዝብ ሳይደርስ ከቀረ በቀላሉ ሊበሰብስና ሊበላሽ እንደሚችል ሲታወቅ በዚህ በኩል ይበልጥ ተጎጂ የምርት ዓይነቶች መካከል እንደ አትክልትና ፍራፍሬ ይገኙበታል። ይህ ደግሞ ሸማቹን ብቻ ሳይሆን በተለይም አማራጭ የሌለውን አምራች ገበሬ እጅግ አድርጎ ይጎዳል። ይህ ሁሉ ከምግብ አቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ ገበያውን የሚያሸብር ሁኔታ ስለሚያስከትል የሽሚያ ሸመታን ሊያባብስና የዋጋ ግሽበትን ሊያግዝ አልፎ ተርፎም ለግጭትና አመፅ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ስለዚህም የኮሮና ወረርሽኝን ተፅዕኖ ከምግብ ዋስትና ምንነትና በርካታ ገጽታዎች እንዲሁም ከሰላምና ግጭት ጋር ያለውን ተያያዥነት አበክሮ መመልከት ይጠይቃል።
ትኩረታችን ምንና ማን ላይ መሆን እንዳለበት መወያያ ይሆን ዘንድ
በዚህ በኮሮና ወረርሽኝና በድኅረ ኮሮና ዘመንም ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገባ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? ይበልጥ ተጠቂና ተጋላጮቹስ እነማን ናቸው? እነዚህን ጥያቄዎች ማብላላትና ሐሳብ መስጠት ተገቢ ነው። ከፍ ብዬ እንዳመለከትኩት ይህ ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስና የፈጠረው መሸበር ገና አላከተመም። ስለሆነም በአጠቃላይ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሕይወታችን ላይ እስካሁን ያደረሰውንና ወደፊትም ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመገመት ያስቸግራል። ይህም ሆኖ ከችግሩ እንደምንም አገግሞ ለመውጣት በየጊዜው ጥናትና ክትትል ይጠይቃል። ለዚህም አጠቃላይ ሁኔታውን በመገምገም አቅጣጫ ሊጠቁምና በየጊዜው ሊከለስ የሚችል ስትራቴጂ ወይም አንደ ዓይነት ፍኖተ ካርታ ማሰብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
እስካሁን የኮሮና ወረርሽኝን በተመለከተ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል የሚሰጠው ገለጻ ችግሩን ከጤና አንፃር ብቻ የሚመለከት ነው። ስንት ሰው የቫይረሱ ተጠቂ እንደሆነ፣ ስንቱ ከጥቃቱ እንዳገገመና ጨርሶ እንደተሻለውና ስንት ሰው ሕይወቱ እንዳለፈ በማሳወቅ ላይ ያተኮረ በመሆኑ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ የተሰጠውን የኃላፊነት ድርሻ ለመወጣት በመድከም ላይ እንደሚገኝ ያስረዳል። ይህ እንዳለ ሆኖ በአገራችን 57 በመቶ ወይም ደግሞ ከ110 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል 62.7 በመቶ ሚሊዮኑ ብቻ ንፅህናውን ለመጠበቅና ለመፀዳዳት Access (IFRC, July 2019) እንዳለው በጥናት የተደረሰበት ሃቅ ነው። ባለፈው መጋቢት እስከ ታኅሳስ 2019 (April – December 2019) የኮሌራ በሽታ በአገራችን ጥቃት ማድረሱ ይታወሳል። የመኖርያ ቤት እጥረትና መተፋፈግ ብዙም መሻሻል ባላሳየበት አገር አካላዊ ርቀትን ጠብቆ ለመኖርም ሆነ ይህንን አዲስ ማኅበራዊና ባህላዊ የአኗኗር ዘይቤ ተቀብሎና ተከላክሎ ውጤት ማስመዝገብ ፈታኝ እንደሆነ መቀበል የግድ ነው።
በአንድ በኩል የዜጎችን በዚህ ወረርሽኝ ከጥቃትና ሞት ለመጠበቅና በሌላ በኩል ደግሞ ከምግብ አቅርቦት እጥረትና ዋጋ ሽቅበት ጋር ተያይዞ በከተማና በገጠር ሊከሰት የሚችለውን ረሃብ ለመከላከል መንግሥት ሚዛን ጠብቆ ያለውን ጥሪት (Resource) ለጤናውም ለምግብ አቅርቦትም ለማዳረስ እጅግ ከባድ እንደሚሆንበት መገንዘብ ተገቢ ነው። በዚህ ድንገተኛና አስቸጋሪ ወቅት መንግሥትና ዜጎች ተደማምጠውና ተቀናጅተው በጋራ በመሠለፍ ለዚህ አገራዊ ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት ይኖርባቸዋል። የምግብ ዋስትና ማለት በርካታ ገጽታዎች (Multiple Indicators) ያሉት መሆኑን በመረዳት እንደ በአገር ደረጃ የተቀናጀ ከኢኮኖሚስት፣ ሥነ መንግሥትና ፖሊሲ፣ የግብርና ምርምርና ኤክስቴንሽን፣ ከሥርዓተ ፆታ ወጣቶች ጉዳይ እስከ ምግብ ጥናት ምርምርና ዝግጅት (Nutrition and Food Science Tecknologists) ድረስ ያሉትን የዕውቀት ዘርፎች (Multidisciplinary) ያቀናጀ፣ ለሁሉም እኩል ዕድል የሚሰጥና የሚያዳምጥ፣ ለሕዝብ መድረስ ያለበትንም መልዕክት በሕዝብ ቋንቋ ለማድረስ የሚችል መድረክ መፈጠር ይኖርበታል።
ይህ የተቀናጀ ክህሎት (Expert Capacity) በአገራችን የወረርሽኙ ሙሉ ምን ሊሆን እንደሚችል በትክክል ማወቅ እንኳን ባይችል አቅጣጫ ሊጠቁም የሚችል ፍኖተ ካርታ መቅረፅ ይችላል። ከዚያም ባሻገር የፕሮጄክት ንድፈ ሐሳብ ለማቅረብና ለዚህም የሚሆን ግብዓትና ሀብት ማሰባሰብ እንዲቻል (Resource Mobilization) አመራር መስጠት ይችላል። በዚህ ወረርሽኝ ሁሉም የአገራችን የኅብረተሰብ ክፍሎች አንድ ወጥ በሆነ መንገድም ባይሆን በሰፊው እንደተጠቁ አያጠራጥርም። ለምሳሌ ያህል መካከለኛ ገቢ ያለውንና የምግብ ዋስትና ችግር የሌለበትን የኅብረተሰብ ክፍል የወሰድን እንደሆነ ይህም ክፍል ቢሆን ምናልባት ለጥቂት ወራት ወይም ዓመት ጉዳቱ ላይ ሰማው ይችል ይሆናል። ምግብ ነክ ባልሆኑና ከቅንጦት ጋር በተያያዙ ሸቀጦች ላይ ያወጣ የነበረውን ወደ ምግብ በማዞርና ገቢውን በማብቃቃት ይበልጥ ተጠቂና ተጋላጭነቱን ሊቀንስና ይህ ክፉ ጊዜ እስኪያልፍ እንደምንም አገግሞ ለመውጣት ዕድል ይኖረው ይሆናል። የዚያኑ ያህል ደግሞ በተለያየ ንግድ፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ ትራንስፖርት፣ ጅምላና ችርቻሮ፣ የግምባታና ጥገና፣ ባህልና ኪነት ነክ ሙያ ላይ የተሠማሩትን ወደ ኪሳራና ሥራ አጥነት ሊከታቸው እንደሚችል መገመት ይቻላል።
በትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎችም አካባቢ የምግብ እጥረት መኖሩ አይቀርም። በተለይ እናትና አባት የሌላቸውንና የአካልም ሆነ የአዕምሮ ዝግመት ያለባቸውን ልጆች በነፃ ሰብስበው በሚያሳድጉና በሚያስተምሩ፣ ለአቅመ ደካማና ሰብሳቢ ለሌላቸው ወገኖች የዕለት ጉርስና መጠጊያ ያቀርቡ የነበሩ ከትንሽ እስከ ትልቅ የሚደርሱ ተቋማት የዚህ ወረርሽኝ ተጋላጭና በኃላፊነት የተረከቧቸውን ለመንከባከብ የማይችሉበት ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይቻላል። በተለይ የአገር ውስጥና የውጭ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ለመንቀሳቀስም ሆነ ዕርዳታ ለማድረስ የሚገቱ መሆናቸውና ባጀታቸውንም ወደ ጤናው መስክ በማዞር ወረርሽኙ እንዳይዛመት ለመከላከል መጠቀማቸው እንደማይቀር መገመት አያዳግትም።
ከዚህ የተነሳ ይህ ትልቅ ሰብዓዊና ማኅብራዊ ኃላፊነት የወሰደው ተቋምና ተጠቃሚዎቹ የአገራችን ዜጎች እጅ አድርገው እንደሚጎዱና ምናልባትም ተቋማቱን በመዝጋት እነዚህ ቀድሞውንም የተገፉ ዜጎች የጎዳና ተዳዳሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰብ አያስቸግርም። በእኔ አስተያየትና እምነት የመንግሥት ትኩርት መሆን አለበት ብዬ የምለው ከዚህ በላይ ያነሳኋቸውን የኅበረተሰብ ክፍል ጨምሮ በተለይ በከተማም በገጠርም የተረሱ፣ የተገፉና የተፈናቀሉ፣ የምግብ ዕጦት በሚያስከትለው የጤና እክል በቀላሉ ለሚተላለፍና ክሮኒክ ለሆነ ተላላፊ በሽታና የተመጣጠነ ምግብ ዕጦት (Malnutrition) የተጋለጡት ላይ ነው።
እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸውን ዜጎች ከመጀመርያውም የረጅም ዘመን ረሃብተኞች ናቸው። ቀደምም ሲል ከፍተኛ የአልሚ ንጥረ ነገሮች እጥረት የተጋለጡ በመሆናቸው ከኮሮና ወረርሽኝም ዘመን በፊት ወደ ጤና ጣቢያዎች በመሄድ አስፈላጊውን ክትትል ለማግኘት ዕድል ያላገኙ ናቸው። በዚህ በኮሮናና በድኅረ ኮርና ዘመን ወንዶችም ሴቶችም እኩል ተጠቂ ቢሆኑም ለተደራረበ ጥቃት የሚጋለጡት ሴቶች፣ ሕፃናት፣ በእርግዝና ላይ ያሉ ወይም የሚያጠቡ ደሃ እናቶችና አቅመ ደካማ አዛውንት ስለሆኑ መንግሥትና ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት እነዚህ ዜጎች ላይ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል። ከፍ ብዬ ባመለከትኳቸው ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍል አባላት ላይ ትኩረት መስጠት ሌሎች ዜጎችን መዘንጋት ማለት አይደለም።
ከኮሮና ወረርሽን ቀደም ብሎ ከድህነት ወለል በላይ (Above the Poverty Line) የሚገኘውም ቢሆን የወረርሽኙ መዘዝ ሥር እየሰደደና ጠቅላላ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ መልሶ ነፍስ ለመዝራትና ለማንሰራራት የተራዘም ጊዜ በወሰደ ቁጥር ይህ ከፍ ብዬ የጠቀስኩትም የኅብረተሰብ ክፍል ወደ ድህነት አዘቅት መውረዱ በምግብና ጤና ዋስትናም ክፉኛ የተጎዳውን ክፍል መቀላቀሉ አይቀርም። በሌላ አነጋገር በቀጥታ አምራች ባይሆኑም በምርት አካባቢ የሚገኙ፣ በጅምላም ሆነ ችርቻሮ ንግድ ላይ የተሠማሩ፣ ተቀጥረውም ሆነ ለራሳቸው ሥራ ፈጥረው የሚኖሩ፣ ከኑሮ ውድነት የተነሳ ከእጅ ወዳፍ ካልሆነ በስተቀር ምንም የማይተርፋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የኮሮና ወረርሽኝ ባስከተለው ጉዳት በቀላሉ ወደ ድህነትና ጉስቁልና ሊወርዱ ይችላሉ።
ከሕዝቡ ቁጥር ወደ 60 በመቶ የሚጠጋውንና በሥራ ፈጠራ ዕድል ተጠቅሞ አምራች ዜጋ ለመሆን ዕድል ያላገኘውን ወጣት ጉዳይ በተለይም በዚህ በኮሮና ወረርሽኝ ዘመን በሚገባ መጤን አለበት። ማስታገሻው ሊገኝለት ካልቻለም በማንኛውም ጊዜ እንደሚፈነዳ የተጠመደ ቦምብ ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለሆነም አንዳንድ አገሮች ለወጣቱ ሥራ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ወጣቱ ራሱ የራሱ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆን ለማስቻል የሄዱበትን ጎዳና በመመርመር ለአገራችን እንዲመች አድርጎ መቅረፅ ይጠይቃል። የግብርናው መስክ ብቻውን የወጣቱን ሥራ አጥነት ሊያቃልል ይችላል የሚለው ግምት (Assumption) በሚገባ መመርመርና በጥናት ላይ የተመሠረተ ምኞትን ሳይሆን ዕድሉን ያካተተ መረጃ ሊቀርብበት ይገባል።
አካላዊ ርቀት የሚጠብቅ አርሶ አደርነትና አርብቶ አደርነት እንዴት ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ በበኩሌ ያስቸግራል። ተራርቀው በሚኖሩ፣ የቤተሰብ ቁጥራቸውም እጅግ አነስተኛና ዘርዛራ አሰፋፈር ባላቸው (Sparsly Populated)፣ ተለይተው በሚኖሩ ማህብረሰቦች (Isolated communities) ላይ ያተኮረ፣ “ለክፉ ቀን” (“Survival Crops”) ተብለው በተለዩ አዝርዕት፣ ብዙ የሰው ጉልበት ማሰባሰብ የማይጠይቅ የግብርና ቴክኖሎጂም ለዚሁ የሚስማማና ለዚያው አካባቢ ውስን ገበያ አቅርቦትን ሊያስታግስ የሚችል የተሰባጠረ አስተራረስን የሚያግዙ (Mixed Farming Technologies) የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ያዋሉ ማኅበረሰቦች ላይ ያተኮረ ጥናት እንዳለ አውቃላሁ (IDRC)። ይህ ግን ምን ያህል ተገምግሞ አሁን ላለንበት የኮሮናና ድኅረ ኮሮና ዘመን ሊረዳ እንደሚችል ማወቅ ያዳግታል።
በቅድሚያ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት አርሶ አደሩን በተመለከተ የእርሻ መሬትን አዘጋጅቶ ለማረስ፣ ለመዝራት፣ ለማጨድና ለመከመር ሊያውክ የሚችል የጤና ችግር ለማጋጠሙ አሰሳ በማካሄድ መረጃ መሰብሰብ ይጠይቃል። አሁን ለጊዜው ለመገመት የሚቻለው ችግር የተዘራውን ለመሰብሰብ፣ ወደ ገበያ ለማድረስ የሚያስፈልገው የሰው ጉልበትና ትራንስፖርት እጥረት ይመስለኛል። ወደፊት ግን በኤች አይ ቪና ኢቦላ ወረርሽኝ ዘመን እንደሆነው ወረርሽኙ ወደገጠሩ የተዛመተ እንደሆነ ሊቀሰም የሚችለው ትምህርት ምን ሊሆን እንደሚገባ መወያየት ይቻላል።
በኤች አይ ቪና ኢቦላ ወረርሽኝ ዘመን የተሠራው ስኬታማ ሥራ ለገጠሩም ለከተማውም ትምህርት ሊሆን ይችላል። ኤች አይ ቪና ኢቦላ ወረርሽኝ በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር አምራች ኃይል እንደቀሰፈ ይታወሳል። ከነዚህም መካከል እጅግ አድርገው የተጎዱት ሴቶች፣ ሕፃናት፣ በእርግዝና ላይ ያሉ ወይም የሚያጠቡ ደሃ እናቶችና አቅመ ደካማ አዛውንት፣ አልፎ ተርፎም የግብርናና ጤና ሙያተኞች ይገኙበታል። የኤች አይ ቪና ኢቦላ ወረርሽኝ ከፍተኛ ጥቃት ባደረሱባቸው የምዕራብ፣ ምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የግብርና ምርምር ከጤናው ዘርፍ ጋር በመቀናጀት የተገኘውን ውጤቱ ለአገራችን መልሶ ሊጠቅም በሚችል መንገድ መመርመር ይቻላል።
ለምሳሌ ያህል የፕሮቲን፣ (Iron: Zinc Vitamin A & B) ሌሎችንም (Micornutirents) እንደበቆሎ፣ ድንች፣ አኩሪ አተር (Soyabean)፣ ስኳር ድንች፣ ካሳቫና ሙዝና (Banana Planatin) በመሳሰሉት ላይ (Biofortify) በማድረግና ከግብርናና ጤና (Extension Services) ጋር እንደ አንደ ዘርፈ ብዙ ክህሎቶችን ያቀፈ ቡድን (Multidisciplinary Team) አብሮ በመሥራት የተገፉ፣ የተረሱ፣ የምግብም የጤናም ዋስትና ያልነበራቸውን ሰዎች ሕይወት መለወጥ ተችሏል። እነዚህ በእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድካምና ብርታት ላይ ያተኮሩት የግብርና ምርት ዝርያዎች ተዘርተው በቶሎ የሚደርሱ ተባይን፣ ውርጭና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ፣ በምግብ የማዘጋጀቱ ሒደት ከፍተኛ የማገዶ ፍላጎት የማይጠይቁና በምግብ ዝግጅቱም ሒደት የአልሚ ንጥረ ነገሮች (Micornutirent) ይዘትና ጠቀሜታ የማይባክንበት ዘዴ ማረጋገጫ የተገኝቶላቸው ነበሩ።
ሥርዓተ ፆታን፣ ድህነትና (Social Inclusiveness) ላይ (Focused)፣ (Sensitive) ያደረገ የፕሮጀክት ሥራ የሆነው የግብርና ቴክኖሎጂ ያስገኘው ውጤት ገና ለረጅም ዘመን ክትትል የሚጠይቅ ነው። ቢሆንም በተለይም የተጠቃሚዎቹ የጤና ሁኔታ እየተገመገመና አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሱ እየተረጋገጠ ወደ አምራችነት በማሸጋገር፣ ራሳቸው በሚያመርቱት ላይ ተጨማሪ ዕሴት በማከል የገበያ ተፎካካሪነትና አትራፊነትን ያስገኘላቸው ነበር። በኤች አይ ቪና ኢቦላ ወረርሽኝ ዘመን ዘመን የጠፋባቸውን (Livelihood Assets) መልሰው ለመገንባት፣ ለልጆቻቸው አስተማማኝ ትምህርትና ጤና ለማብቃትና ተቀማጫቸውን በማሳደግ (Small Scale Agroprocessing Centers) በግልም በጋራም ባለቤት እስከ መሆን ደርሰዋል።
የተገኘው ልምድ በዋና ዋና ከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ እየከፋ የሄደውን የከተማ ድህነት ለመቀነስ ይረዳል። የከተማ ግብርና (Urban Agriculture)፣ (Promote) ከማድረግ ጋር ተያይዞ የዚህ የከተማ ግብርና ተጠቃሚዎች በምግብ ዕጦት ለረጅም ዘመን ረሃብ የተጋለጡትና ከፍተኛ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች እጥረት ያጋጠማቸውን ወገኖች ላይ በማተኮር ተመሳሳይ ውጤት ማግኘት ይቻላል።
መደምደሚያ
ይህ የኮሮና ወርርሽኝ ያደረሰው ጉዳይ በታሪክ አቻ የማይገኝለት በመሆኑ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚው ላይ እስካሁን ያስከተለው ጉዳት ገና በትክክለኛ ሥሌትም አመርቂ ትንተናም (Quantified and Qualified) አልቀረበበትም። ቢሆንም ጉዳቱና መዘዙ በቀላሉ እንደማይገመት አገሮችንና መንግሥታትን ከዳር እስከ ዳር ያስማማ ጉዳይ ሆኗል። ይበልጥ ተጎጂና ተጋላጭ የሆኑት ከኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ቀደምም ብሎ ለሕዝባቸው የምግብ፣ የጤናና የሰላም ዋስትና ማቅረብ ያልቻሉት እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች ናቸው። በተለይም አገራችን ከድርቅና አየር ንብረት ለውጥ ጋር በተገናኘ ከሚደርስባት ተደጋጋሚ ጉዳት እንዳለ ሆኖ የሰላምና መረጋጋት ችግር ከኮሮና ወረርሽን መዘዝ ጋር ሲዳመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፈተናዋ የበዛ እንደሚሆን አያጠራጥርም (See Global Report on Food Crises 2020)።
ከዚህ ወረርሽኝ ሁሉም አገሮች ሀብታም ይሁኑ ደሃ ምናልባት የሚቀስሙት ትምህርት ነጣይና የእኔ ብቻ የሚል (Isolationist and Protectionst) ፖሊሲ ምርጫ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው አዲስ ዓይነት ዓለም አቀፍ ትብብርን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊነቱን የተቀበለ፣ ማንኛችንም ከሌላው ተነጥለን ራስችንን ልንጠብቅና ልናድን እንደማንችል የሚገነዘብ፣ ዓለም አቀፍ ደንብና ሥርዓት (Global Order) ሊሆን ይችላል። የመጀመርያው ሁሉንም አገሮች በተለይም አገራችንን የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም እንደማይሆን የሚያከራክር አይመስለኝም። ሁለተኛው ማለትም አዲስ ዓይነት ዓለም አቀፍ ትብብር የምንመኘው አማራጭ ማለት ይቻላል።
ይህን የመሰለ ዓለም አቀፍ/ግሎባል ትብብር ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሁሉንም የሚያስተናግድ ከሆነ ወደፊት ተመሳሳይ ወረርሽኝም ይሆን ሌላም ዓይነት ዓለም አቀፍ መቅሰፍት ቢከስት የተሻለ ቅንጅት በመፍጠር ችግሩን በጋራ ማቃለልና መፍትሔውንም በተሻለ ለሁሉም ማዳረስ ያስችላል። ጥያቄው ግን እውነት ይህን ዓይነት አዲስ የአመለካከት ለውጥ ማለትም ሚዛኑን የጠበቀና ዓለም አቀፍ (Global) ግዴታን ያገነዘበ አዲስ ዓይነት ግንኙነት እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ አገሮችና ሕዝቦች ምን ዕድል ያስገኝላቸዋል የሚለው ነው። ይህ በራሱ ትልቅ ምርምር የሚጠይቅ ስለሆነና የምርምሩም ውጤት መቼ ተጥናቆ ለውይይት እንደሚቀርብ ለማሰብም እጅግ ሩቅ ስለሚሆን ለጊዜው ወደ ጎን ማድረግ ይቻላል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ተፅዕኖ የማሳደር አቅሟ እጅግ ውሱን ነው። እንኳንስ በተናጠል እንደ አኅጉር በአፍሪካ ኅብረት በክሉ በጋራ ለመደራደርና ዓለም አቀፉም የንግድ ስምምነት ለአኅጉሩ ምርት ፍትሐዊ (Terms of International Trade Agreement Favourable to the Continents Products) ለማድረግ በርካት ድርድሮች ቢደረጉም ውጤቱ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይታወቃል። አሁንም ይህ ቀውስ ካለፈ በኋላም ቢሆን የአፍሪካ አኅጉር በጋርም ሆነ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች ዓለም አቀፍ የምግብ አቅርቦት ሰንሰለታዊ ሥርዓት (Globalsources of Food Supply Chain) ላይ ጥገኝነቱን በመቅረፍ፣ በምግብ ራስን በራስ መቻል ላይ ትኩረት እስካልሰጡ ድረስ ነገም ተነገ ወዲያም ለተመሳሳይና ለከፋ ችግር እንደተጋለጡ መቆየታቸው አይቀርም።
በአገራችን የወረርሽኙ ተፅዕኖ ምን ሊሆን እንደሚችል ገና በትክክል አይታወቅም። ይህ እንዳለ ሆኖ እንደ አገር በተቀናጀ መልክ ጉዳቱንና መዳሰስ ያስፈልጋል። ይህ ዳሰሳ አቅጣጫ ሊጠቁም የሚችልና ለድኅረ ኮሮና ዘመንና ከዚያም በኋላ የሚዘልቅ ስትራትጂ ወይም ፍኖተ ካርታ ለመንደፍ ይረዳል። ይህንን የመሰለው ስትራቴጂ ወይም ፍኖተ ካርታ የቅርብ፣ የመካከለኛ ዘመንና የረጅም ዘመኑን ዓላማን ግብ ያቆራኘ ሲሆን በመጨረሻው ይህ ስትራቴጂ ወይም ፍኖተ ካርታ ሊያደርስ የሚገባው ለችግር ደራሽና ዘለቄታ ያለው የምግብ ምርትና አቅርቦት ሥርዓት (Resilient and Sustainable Food System) ግንባታ ላይ ነው።
በአገራችን የኤች አይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝ በከፋበት ዘመን በግብርና ምርምርና ልማት በኩል ሥርዓተ ፆታን፣ ወጣቶችን፣ አዛውንቶችን ያካተተና በእነርሱ ፍላጎትና ጥቅም ላይ ትኩረት ያደረገ ምን ሥራ እንደተሠራ ዕውቀቱም መረጃውም የለኝም። ይህም ሆኖ በአገራችን የተሠራ ወይም የተሞከረና ውጤት ያሳየ ሥራ የለም ማለት አልችልም። ይህ እንዳለ ሆኖ በሌሎች አገሮች በዚሁ ኤች አይ ቪ ኤድስና ኤቦላ ወረርሽኝ ዘመን የምግብ ዋስትናን ከጤናው ዘርፍ ጋር በማቀናጀት ለገጠሩም ለከተማውም የሚበጅ ሥራ መሠራቱን በመገንዘብ፣ ይህም ልምድ በበቂ የተመዘገበ በመሆኑ ከዚያ ልምድ በመቅሰም የበለጠ ውጤታማ ሥራ በአገራችንም መሥራት የማይቻልበት ምክንያት አይታየኝም።
ይህ ልምድ በአንድ ግብረ ኃይል በኩል ፈጥኖ ሥራ ላይ ማዋል ቢችል ጠቃሚ መሆኑን ስለማምን ይህ ሥራ በቶሎ አንዲሠራ ካስፈለገ አመራር መስጠት ያለበት የግብርና ምርምር ወይም ለዚህ የምርምር ተቋም አጋዥ መሆን የሚችሉ ባለድርሻ አካላት ይመስለኛል።
የአገራችን ግብርና ምርምር ከአስፈላጊ ድርጅቶችና አካሎች ጋር አብሮ በመሥራት በዚህ የኮሮና ወረርሽኝ ዘመንና ከዚያም በድኅረ ኮሮና ዘመን የራሱን ድርሻ ማረጋገጥ ይኖርበታል። በርካታ የምግብ ዋስትናን የተመለከቱ ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በመምከር የገጠሩንም የከተማውም ድህነት ለመቅረፍ የሚያስችል መሪ ሐሳብ ይዞ መውጣት ይጠበቅበታል። የአገራችንን የግብርና ሥርዓትና የአስተራረስ ባህል ከሥር መሠረቱ ለመለወጥ (Revolutionize and Transform) መታሰብ ያለባቸው ጉዳዮች እጅግ በርካታና ርዕስ በርሳቸው የተሳሰሩ ናቸው። በዚህ በኩል አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚችል የሠለጠነ፣ አገር በቀል ክህሎትን ከዓለም አቀፍ ልምድና ክህሎት ጋር ያዋደደ የሰው ኃይል ችግር በአገራችን የለብንም። ከአስተራረስ ዘዴው እስከ አመጋገብ ባህሉ ድረስ የሚደርሰውን ችግር ለመቅረፍ ካልቻልን የአገራችን ግብርና ከችግር ሊወጣና የምግብ ዋስትናን ሊያረጋግጥልን አይችልም።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሲኒየር ሶሻል ሳይንቲስት ደረጃ የቀድሞ ዓለም አቀፍ ግብርናና ልማት ድርጅት ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለከካት ብቻ የሚንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡