Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የብድር ወለድ ቅናሽ ያደረጉ ሦስት ባንኮች ቱሪዝምና ሆቴሎችን ቃኝተዋል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮሮና ቫይረስ መከሰት በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ እያደረሰ ያለው ተፅዕኖ ተጠቃሽ ነው፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዘርፉ ሰፊ ኃላፊነት እንዲሸከም እየተገደደ ነው፡፡ የቢዝነስ እንቅስቃሴ መዳከምና የኢኮኖሚው መዋዥቅ የገንዘብ ፍሰቱንም አዳክሞታል፡፡

ይህ በመሆኑ ከባንክ ብድር ጋር የተያያዙ የንግድ እንቅስቃሴዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ተመላሽ መደረግ በነበረባቸው ጊዜ ውስጥ ለመሰብሰብ አዳጋች በመሆናቸው፣ ተቀማጭ ገንዘብ አከማችተው ተጨማሪ ብድር የማቅረብ አቅማቸውን እየፈተነው ይገኛል፡፡

ይህም ሆኖ ችግሩና ጫናው እንዳለ ተበዳሪዎችን ለማገዝ፣ ባንኮች የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ የብድር ወለድ ማስከፈያ ቅናሽ፣ የብድር ወለድ ስረዛ ማድረግን ጨምሮ የአገልግሎት ዋጋ ማሻሻያኛ ሌሎችም ገቢያቸውን ሊቀንሱ የሚችሉ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ማግኘት የነበረባቸውን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመተው አጋዥ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ ነው፡፡

አዋሽ ባንክ ከ12.5 እስከ 15.7 በመቶ የብድር ወለድ ያስከፍልባቸው የነበሩ የአበባ እርሻ፣ የሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም የአስጎብኝ ድርጅቶች ቅናሽ ተደርጎላቸው በሰባት በመቶ ወለድ ብቻ ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ወስኗል፡፡ ይህ ቅናሽ የሚቆየው  ለመጪዎቹ ሦስት ወራት ነው፡፡

ከአዋሽ ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በእነዚህ የንግድ ዘርፎች ላይ እስከ 15 በመቶ የሚደርስ ወለድ ይጠየቅበት የነበረ ብድር ላይ ቅናሽ በማድረግ፣  ለቁጠባ በሚፈከል ወለድ ምጣኔ ልክ ብቻ የብድር ወለድ እንዲከፍሉ ተደርጓል፡፡ ይህም ባንኩ በሦስት ወራት ውስጥ ከእነዚህ ዘርፎች ያገኝ የነበረውን ትርፍ በመልቀቅ የኮሮና ቫይረስ ያደረሰውን ጫና ለመጋራት የወሰደው ዕርምጃ እንደሆነ ባንኩ አስታውቋል፡፡

ኅብረት ባንክ በበኩሉ በኮሮና ቫይረስ መሠረት ሥርጭት በተለየ ከፍተኛ ተፅዕኖ ላረፈባቸው ማለትም ለአበባ እርሻዎች እንዲሁም ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች ባንኩ የ25 በመቶ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ ማድረጉን ገልጿል፡፡ ለሌሎች ዘርፎችም የአምስት በመቶ ቅናሽ ያደረገ ሲሆን፣ ይህ ግን ቀደም ሲል ልዩ የወለድ ቅናሽ ወይም የተሰጣቸውን ዘርፎች አይመለከትም፡፡ ለሦስት ወራት በሚቆየው በዚህ ቅናሽ ከአምስት በመቶ እስከ 25 በመቶ የሚደርሰው የወለድ ቅናሽ  ኅብረት ባንክን 50 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሚያሳጣው ይጠበቃል፡፡ አዋሽ ባንክ ያደረገው የብድር ወለድ ቅናሽ የ60 ሚሊዮን ብር ገቢ ያሳጣዋል ተብሏል፡፡

ሌላኛው የብድር ወለድ ማስከፈያ ቅናሽ ያደረገው ዘመን ባንክ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እንደየዘርፉ ሁኔታ የብድር ወለድ ስረዛና የብድር መክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ መፍቀዱ ይታወሳል፡፡ በወረርሽኙ ለጉዳት ከተጋለጡ ቀዳሚ ዘርፎች አንዱ የሆልቲካልቸር ሲሆን፣ ለዚህ ዘርፍ ደንበኞቹ ባንኩ የሦስት ወር የብድር ወለድ ስረዛ ማድረጉ ተዘግቧል፡፡ ይህ ዕርምጃ ተበዳሪዎች በየወሩ ይከፍሉ የነበረውን ወለድ በመሰረዙ በልዩነት እንደሚታይ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ባንኩ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መረጃም ወረርሽኙ ጉዳት ካደረሰባቸው ዘርፎች የሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎችም አስተያየት ተደርጎላቸዋል፡፡ የእነዚህ ዘርፍች ተበዳሪዎች ከ0.5 እስከ ሦስት በመቶ የሚደርስ የወለድ ቅናሽ እንደሚያገኙ ባንኩ አስታውቋል፡፡

የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ዘነበ እንደገለጹት፣ ባንኩ ካሁን በፊት ቃል በገባው መሠረት ለሆቴል፣ ለቱሪዝምና ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የብድር ወለድ ቅናሽ አድርጓል፡፡ ወረርሽኙ በሌሎች የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባትና ከባለድርሻ አካላት የሚመጡ ጥያቄዎችን መሠረት በማድረግ ጉዳት እየደረሰባቸው ከሚገኙ ዘርፎች መካከል በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ እንዲሁም በአምራች የኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ደንበኞቹ ለሁለት ወራት የሚቆይ ወለድ ምጣኔ ማስተካከያ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የወለድ ማስከፈያ ማስተካከያ የተደረገላቸው የኢኮኖሚ ዘርፎችም የባንኩን 42 በመቶ የብድር ድርሻ እንደያዙ ተጠቅሷል፡፡ የድጋፍ ዕርምጃቸው የባንኩን ጤናማነት ባረጋገጠ መንገድ የተወሰደ በመሆኑ ለሁሉም አካላት አጋዥ ነው ብለዋል፡፡ እነዚህ መስኮች በርካታ ሠራተኞች ቀጥረው ከማሠራት ባሻገር፣ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና የተለያዩ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሾች በመሆናቸው ሌሎችም አካላት ድጋፍ ሊሰጧቸው እንደሚገባ አቶ ደረጀ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የባንኩ የወለድ ምጣኔ ማስተካከያ ለተበዳሪዎች የሚሰጣቸው የክፍያ ጊዜ ዕፎይታ በመሆኑ፣ የብድር አመላለስ ሒደቱን የተሻለ እንደሚያደርገው አቶ ደረጀ አመልክተው፣ ተመላሽ የሚደረገው ጤናማ ብድርም መልሶ ለሌላ ልማት እንዲውል ያግዛል ብለዋል፡፡

እንዲህ ካሉ ድጋፎቹ በተጨማሪ ዘመን ባንክ፣ በመጋቢት ወር የአምስት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ለመንግሥት በመስጠት፣ ተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ብር ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳበረከተ አስታውሶ፣ ለጤና ባለሙያዎች ድጋፍ የሚውል ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ አሁንም እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ዘመን ባንክ የብድር ወለድ ቅናሽ ያደረግንባቸው ዘርፎች አራት ቢሊዮን ብር ብድር ያገኙ ናቸው፡፡ ይህም የባንኩን 42 በመቶ የብድር ድርሻ የሚሸፍን ነው፡፡ ይህም ከፍተኛ መጠን ያለው የብድር ዕዳ ላይ ማስተካከያ መደረጉን አመላካች ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ግማሽ ቢሊዮን ብር ለተበደሩ ዘርፎች የሦስት ወር የብድር ወለድ ስረዛ በመደረጉ እስካሁን 4.5 ቢሊዮን ብር በሚሸፍን የብድር ዕዳ ላይ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡

ዘመን ባንክም ሆነ ሌሎች ባንኮች የሚወስዷቸው እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎች ባንኮችን በሚሊዮን የሚቆጠር ወጪ እንደሚያስወጣቸው ቢታወቅም፣ ይህንን ማድረግ ተገቢና ኃላፊነትን መወጣት እንደመሆነ የጠቀሱት አቶ ደረጀ፣ ግዴታ ጭምር እንደሆነ ያምናሉ፡፡

‹‹ይህ ዕርምጃ ባንኩን በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ ያሳጣዋል፡፡ ነገር ግን የባንካችን ህልውና ደንበኞቻችን በመሆናቸው ይህ ለእኛ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን፣ የብድር አመላለስ ሥርዓቱ ጤናማ እንዲሆን በማድረግ ከኅብረተሰቡ የሰበሰብነውን ገንዘብ ሌላ ልማት ላይ እንዲውል ስለሚያግዝ ደንበኞችን በዚህ መልኩ ማገዝ ተገቢ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዘመን ባንክ የኮሮና ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ለሠራተኞቹ፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለደንበኞቹ ደኅንነት ሲባል በሁሉም የሥራ ዘርፍ ላይ የነበረውን የሰዎች መቀራረብን ንክኪ በማስቀረት፣ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ጭምር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ በኢንተርኔት ባንኪንግ ደንበኞች የሚፈልጉትን ያህል የገንዘብ መጠን ማንቀሳቀስ እንዲችሉ፣ በኤቲኤም እስከ 12,000 ብር ያለምንም ክፍያ ማውጣት እንዲችሉ መደረጉ፣ ባንኩ በተለያዩ መገበያያ ቦታዎች ባስቀመጣቸው የግብይት መፈጸሚያ ማሽኖች የገንዘብ ልውውጥ ማድረግ እንደሚችሉም አስታውሰዋል፡፡

ኮሮና በባንኮች ላይ የሚያሳርፈውንና እያሳረፈ ያለውን ተፅዕኖ ለመገመትና ለመተንተን ተጨማሪ መረጃዎች እንደሚያስፈልጉ፣ በወረርሽኙ እየተጎዱ ከሚገኙት አንዱ የባንክ ኢንዱስትሪው እንደሆነ አቶ ደረጀ ገልጸው፣ ጉዳቱ የሚታየው ወደፊት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች