የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢኮኖሚው ላይ እያሳደረ ያለው ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በተለያዩ አቅጣጫዎች እየታየ ነው፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት ጫና ከሚያርፍባቸው ዘርፎች ውስጥ የኮንስትራክሽን መስኩ ይጠቀሳል፡፡ ተፅዕኖው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ይገለጻል፡፡ የመንገድ ግንባታ ሥራም ሰለባ መሆኑ አልቀረም፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ወረርሽኙ ከመንገድ ግንባታና ተያያዥ ጉዳዮች አንፃር ግልጽ ተፅዕኖ የሚያርፍበት በመሆኑ፣ ጉዳቱ ምን ያህል እንደሚሆን ጥናት እየተደረገበት እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ባለፉት ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት ውስጥ ከመንገድ ግንባታ አንፃር ያጋጠሙ ችግሮች በዕቅድ የተቀመጠው ሥራ ስኬታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ እንዲሁም በወረርሽኙ ሳቢያ ፈታኝ ሁኔታዎች እንደሚባባሱ ይታሰባል፡፡ በተለይ ዘንድሮ 21 የመንገድ ፕሮጀክቶች በድጋሚ ለጨረታ እንዲቀርቡ መደረጋቸውም በዘርፉ እየታየ ላለው ተግዳሮት ማሳያ ናቸው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እንዲህ ያሉ ችግሮችን ጨምሮ በርካታ መሰናክሎችን ለመሻገር የሚያግዙ አዳዲስ አሠራሮች ሊተገበር እንደሆነ፣ ክልሎችም በዚህ ሥራ ላይ መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው እየተጠቀሰ ነው፡፡ ተቋሙ ስለሚያስባቸው አዳዲስ አሠራሮች፣ ስለ ኮሮና ተፅዕኖና ሌሎችም ጉዳዮች ዳዊት ታዬ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ያሳደረው ተፅዕኖው እንዴት ይታያል?
አቶ ሀብታሙ፡- ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ትራንስፖርትና ኮንስትራክሽን ላይ ከፍተኛ የሆነ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ እኛም ተፅዕኖውን በጥልቀት እየገመገምን ነው፡፡ ጥርጥር በሌለው ሁኔታ እየታየ እንዳለው በርካታ ሥጋቶች አሉ፡፡ የመንቀሳቀስና በጋራ የመሥራት ሥጋቶች አሉ፡፡ ከዋጋ አንፃር ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖ ይኖራል፡፡ ብዙ ነገር ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡ በኢኮኖሚው ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር መገመት ይቻላል፡፡ ከእንቅስቃሴ አኳያ ፍሰቱ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ በአጠቃላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ በመገመት ሊያስከትል የሚችለውን ችግር እየገመገምን ነው፡፡ ምን ያህል ይሆናል የሚለው እየተሠራ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ እንደገለጻችሁት በዚህ ዓመት የ21 መንገዶችን የግንባታ ጨረታ ሰርዛችሁ በድጋሚ እንዲወጣ አድርጋችኋል፡፡ በሌላ በኩል የተቋራጮች አቅም እየተዳከመ ነው የሚል አስተያየት ይሰነዘራል፡፡
አቶ ሀብታሙ፡- ይኼ ከኮሮና ቫይረስ ሥጋት ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ከኮሮና ጋር የተያያዘው ቀደም ብዬ የጠቀስኩልህ ሥጋት ነው፡፡ ይኼ ግን ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ በአጠቃላይ በተፈጠረው የፀጥታና የወሰን ማስከበር ችግር እንዲሁም ከውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከመሳሰሉት ችግሮች ጋር ሊያያዝ የሚችል ነው፡፡ በለተይ የአገር ውስጥ ተቋራጩ የራሱ ችግር እንዳለበት ይታወቃል፡፡ በሌላው አካባቢ ብዙ ዕውቀት፣ ቴክኖሎጂና ልምድ ብዙም ሀብት የሚያንቀሳቀስ ዘርፍ ቢሆንም፣ የእኛ ግን የሃያ ዓመት ልምድና ተሞክሮ ያለው በመሆኑ አሁን ያለው ችግር ሳይመጣም ጀምሮ ውስንነት ያለበት ዘርፍ ነው፡፡ ሌሎች ከወሰን ማስከበር፣ ከግንባታ ጥሬ ዕቃ አለማግኘት ጋር የተያያዙ ችግሮች የግንባታ ሥራው ላይ ተፅዕኖ አሳርፈዋል፡፡ በዋጋ ግሽበት ምክንያት የግንባታ የዋጋ ጭማሪዎች ለረዥም ዓመታት ታይተዋል፡፡ ሥራውን ባሰብከው ጊዜ ውስጥ እጨርሳለሁ ብለህ በማሰብ ነው ሥጋቱን አስበህ የምትገባው፡፡ ነገር ግን በሦስት ዓመታት ማለቅ የነበረበት ሥራ አምስትና ስድስት ዓመታት እየቆየ ሲሄድ ተቋራጮቹን እየጎዳ ይመጣል፡፡ ይኼ ቀላል ተፅዕኖ አይደለም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ወይ እኛ የምንፈልገውን መሥፈርት የሚያሟላ ተጫራች የለም፣ አለበለዚያ በጣም የተጋነነ ዋጋ ይዞ በመምጣት ምክንያት ጨረታዎች እየተሰረዙ ነው ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም የነበሩ ልምዶች በመንገድ ግንባታ ጨረታዎች የሚሳተፉ ተቋራጮች አይታጡም ነበር፡፡ አሁን ግን ይህንን ያህል ፕሮጀክት ተሳታፊ ጠፍቶ ጨረታ ሲሰረዝና ድጋሚ ሲወጣ ማየት ያልተለመደ ነው፡፡ ምን ተፈጥሮ ነው?
አቶ ሀብታሙ፡- ከዚህ በፊት የተሰረዙ ጨረታዎች ይህን ያህል አልነበሩም፡፡ ይኼ ግን በጣም ትልቅ ቁጥር ነው፡፡ ሥራው ሲለጠጥ ሌሎች ነገሮችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን ወጫዊ ተፅዕኖዎችን መቀነስ መቻል አንዱ መፍትሔ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ውጫዊ ተፅዕኖዎቹ ምንድን ናቸው?
አቶ ሀብታሙ፡- ውጫዊ ተፅዕኖዎች ከሚባሉት መካከል ቀደም ብዬ የጠቀስኩልህ የወሰን ማስከበር ችግር አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ ወጣቶችን በማደራጀት፣ ሌሎች አካላትን በማደራጀት የሚፈጸሙ ችግሮችም አሉ፡፡ ወሰን ማስከበር ቶሎ አይተገበርም፡፡ መነሳት ያለባቸው ግንባታዎች በተፈለገው ጊዜ አይነሱም፡፡ የቆሻሻ መድፊያ ቦታ ለማግኘት ችግር ነው፡፡ አስፓልትና ሌሎች መለዋወጫዎችን ለማስመጣት የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ እነዚህ ችግሮች መቀነስ አለባቸው፡፡ ለልማታችንና ለራሳችን ዕጣ ፈንታ ስንል ከኅብረተሰቡና ከክልሎች ዕገዛ መደረግ አለበት፡፡ ከዚያ በተረፈ የአቅም ግንባታ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ የግዥ ሕጉም የተወሰነ ማስተካከያ ያስፈልገዋል፡፡ እንደ አገር ተገቢ ማስተካከያዎችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሥራው በጣም በዝቶ እንጂ በአንድ ጊዜ 90 ፕሮጀክቶች መቼ ተፈርመው ያውቃሉ? ይህ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ በሥራም በቁጥርም ያህንን የሚመጥን የአገር ውስጥ ተቋራጭ ያስፈልጋል፡፡ ለውጦች አሉ፡፡ ብዙ ለውጥ እያሳዩ፣ ድጋፍ እያደረጉ ያሉ ክልሎች አሉ፡፡ ፍላጎት ላይ ለውጥ አለ፡፡ መሻሻሎች አሉ፡፡ በቂ ግን አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ መንገድ የሌላት አገር ነች፡፡ መንገድ ግን በጣም ወሳኝ መሠረተ ልማት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ብልፅግና ለማምጣት መንገድ ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከመንገድ ግንባታዎች ላይ የሚታዩ ችግሮች በጅምር ሥራዎች ላይም ተፅዕኖ ይኖራቸዋልና እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን እንዴት ይዛችኋችዋል? የብዙ መንገዶች ግንባታ ተጓትቷል፡፡ ከተቋራጮች ጋር የሚታሰረውን ውል እንዴት እየመራችሁት ነው?
አቶ ሀብታሙ፡- መገምገም ያስፈልጋል፡፡ ሁሉንም ሥጋት በወቅቱ መገምገም ያስፈልጋል፡፡ በግምገማ ችግሩ ምን እንደሆነ ይለያል፡፡ ሥጋቱ የተቋራጮቹ ከሆነ ተጠያቂነት መኖር አለት፡፡ ተጠያቂነቱ ሌላ ቦታ ከሆነም ፕሮጀክቶችን እስከ ማጠፍ መሄድ ነው፡፡ ችግሩ ሌላ ቦታ ከሆነ ተቋራጩ ብቻ ተጠያቂ መሆን የለበትም፡፡ የሥጋት ምንጮቹ የአሠሪዎችም ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሥጋት ነው፡፡ መንግሥትን ወክሎ እስከተፈራረመ ድረስ የሚመጣው ሥጋት የእሱም ነው፡፡ ተቋራጩ በራሱ ችግር ምክንያት ያመጣው ከሆነ ግን ውሎች የግድ መቋረጥ አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ዕርምጃ ወስዳችኋል?
አቶ ሀብታሙ፡- ስምንት ውሎች አቋርጠናል፡፡ በተቋራጮች ችግር ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት ግንባታቸው የተጓተቱ የስምንት ፕሮጀክቶች ኮንትራት ተቋርጧል፡፡ ሌሎችም ሊቋረጡ የሚችሉ ኮንትራቶች በሒደት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ መልኩ ነው ዕርምጃ የሚወሰደው፡፡ በውሉ መሠረት ነው ፕሮጀክቱ የሚተዳደረው፡፡ ዝም ብለህ የምትወስደው ውሳኔ የለም፡፡ የእኛ ተቋራጮች ዓለም አቀፍ ተቋራጮች ናቸው፡፡ ለዚህ ተብሎ የተለየና የታወቀ የኮንትራክት ስታንዳርድ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ በዚያ መሠረት ነው ወደ ዕርምጃ የምትሄደው፡፡
ሪፖርተር፡- በኮንትራት ውል መሠረት ባለመሠራቱ ውሎች መቋረጣቸው ተገቢ ቢሆንም በአንፃሩ ውል ማቋረጥ የመንገድ ፕሮጀክቶቹን ወጪ እንደሚያንር ይታወቃልና ይህንንስ እንዴት እየተወጣችሁት ነው?
አቶ ሀብታሙ፡- እንግዲህ ምንም ማድረግ አትችልም፡፡ ወሰንና ገደብ የሌለው ቻይነት ወይም ሆደ ሰፊነት የለም፡፡ በአምስት ዓመታት የሚገባ ፕሮጀክት ሰጥተህ አሥር ዓመታት መቆየት የለበትም፡፡ ይህ አስተዳደራዊ ጉዳይ ወደ መሆን ይሄዳል፡፡ የሕዝብ አመኔታን ይሸረሽራል፡፡ ሕዝብ ይጠብቃል፡፡ ተቋራጩ ብቻ የሚያመጣው ገንዘብ ላይ የተመሠረተ ከሆነ ዓለም አቀፍ አሠራር ነው፡፡ እንዲህ ማድረጉ ተፅዕኖ እንዳለው እናውቃለን፡፡ ግን ምን ታደርጋለህ? ዕድሜ ልክ ፕሮጀክቱ ላይ እንዲተኛበት አትፈቅድም፡፡ ይኼ መሆን አይችልም፡፡ የመንግሥትን አመኔታ ያሳጣል፡፡ ሕዝቡንም ይጎዳል፡፡ ነው፡፡ ስለዚህ እያየህ የምትወስው ዕርምጃ ነው፡፡ እያወቅኸውም ቢሆን ዕርምጃ መውሰድ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ምንም ብታደርግ ለውጥ የማያመጣ ነገር የኮንትራት ውላችን ስለማይፈቅድ በዚህ አግባብ መታየት አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- የ21 ፕሮጀክት ጨረታ መሰረዝና ድጋሚ መውጣት ጊዜ ይወስዳል፡፡ ለእነዚህ መንገዶች የተያዘው በጀት እንዲታጠፍ አያደርግባችሁም?
አቶ ሀብታሙ፡- ከ21ዱ የመንገድ ፕሮጀክቶች 17ቱ በድጋሚ ለጨረታ የወጡ ናቸው፡፡ አራቱ በቅርቡ ጨረታቸው ይወጣል፡፡ እንዲህ መሆኑ ለመንገዶች የተያዘውን በጀት እንዲታጠፍ አያደርግም፡፡ ምክንያቱም እስካሁን ባለው ልምድ በገንዘብ ሚኒስቴር ከተያዘ ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ በጀቱ የሚመደብ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ አይታጠፍም፡፡ መንግሥት ቋት ውስጥ ከገባ አይታጠፍም፡፡ ግን ደግሞ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ታች ያሉት የአስተዳደር አካላት በአካባቢያቸው ያለውን ግንባታ የሚያግዙበት ሁኔታ ውስን ከሆነ፣ በአንድ አካባቢ የነበረውን ፕሮጀክት አጥፎ ወደ ሌላ አካባቢ ማስኬድ የሚቻልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ፍላጎቱና ድጋፉ ከሌለ ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የባለሥልጣኑ ሥራ በርካታ በመሆኑ ሥራዎችን የመጋራት ሁኔታ መፈጠር አለበት የሚል ሐሳብ እየተነሳ ነው፡፡ ብዙ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ይህ ጫና ፈጥሯል እየተባለ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ምን ታስቧል?
አቶ ሀብታሙ፡- ባለፉት 20 ዓመታት በርካታ ምዕራፎች አልፈናል፡፡ መጀመርያ በነበረው አሠራር ሁሉንም ነገር ባለሥልጣኑ ይሠራ ነበር፡፡ አየር ኃይል፣ ወደብና ሌሎችንም ጨምሮ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ይገነባ ነበር፡፡ እዚሁ ባለሥልጣን ውስጥ የገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን የሚባል መጣ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የገጠር መንገዶች በመዋቅር ወደ ክልሎች ሄደ፡፡ ወደ ክልሎቹ ሄዶ ግን እዚያው ነው የቆመው፡፡ በእነሱ ደረጃ ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎችን ኮንትራት አስተዳድረው ማሠራት አለባቸው፡፡ ይኼ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በጣም የተለጠጠ ነው፡፡ ፕሮጀክቶችን ይዞ ይሠራል፡፡ ጥገና ስትጨምርበት ሱፐርቪዥንና የማማከር ሥራ ጨረታ ስትጨምርበት፣ የዲዛይን ጨረታ ስታክልበት የእያንዳንዱን ባለሙያ ሥራ ስትደርብበት ከ400 በላይ ይሆናል፡፡ ይህ ከግዥና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዞ ሲሆን፣ በመስኩ ያሉ ከ160 በላይ ውሎች አሉ፡፡ በጣም ሰፊ ሥራ የያዘ ተቋም እንደሆነ ያሳይሃል፡፡ በዓለም ላይ እንዲህ ያለ አሠራር ያለ አይመስለኝም፡፡ በአፍሪካ የምታስበው ነገር አይደለም፡፡ በአንድ ዓመት 91 ፕሮጀክቶችን መሥራት የምታስበው አይደለም፡፡ ወደ ኋላ የቀረ የብዙ ዓመታት ሥራ አለብን፡፡ ብዙ ያልተሠራ ሥራ አለ፡፡ አገሪቱ ትልቅ ነች፡፡ ሕዝቡ አሁንም በመንገድ ዕጦት እየተሰቃየ ነው፡፡ የዳበረና የረዥም ጊዜ ልምድና ታሪክ ስለሌለን በቶሎ ከችግራችን ለመውጣት የሚደረግ ጥረት አካል ነው፡፡ ወደ መካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ ተርታ ለመግባት መጀመርያ መሠረተ ልማት መቅደም አለበት፡፡ በተለይ መንገድ ካልቀደመ ሌላው አይከተልም፡፡ ቴሌ፣ መብራትና መስኖ ልማት የለም፡፡ ከሁሉም ነገር መንገድን አስቀድመህ ስታመጣ ነው ሌላውን መሠረተ ልማት የምትዘረጋው፡፡ መንገድን ቀድመህ ስታመጣ ነው አጠቃላይ ኢኮኖሚው የሚሳለጠው፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን በሰፊው ዕቅድ የተያዘውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማሳካት ብዙ ነገሮች እየሠራን ነው፡፡ ተደራራቢ ሥራዎችን ይዘን መሄድ ግድ ነው፡፡ ክልሎች ግን የተወሰነውን ሥራ መውሰድ አለባቸው፡፡ የአቅም ግንባታ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ግንባር ቀደም ሚናውን ወስዶ ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ ብድር የምንሠራው የአቅም ግንባታ ሥራ አለ፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ እንደገፋለን፡፡ ክልሎች ለዚህ መዘጋጀት አለባቸው፡፡ የመንገድ ሥራ ክፍፍሎች አሉት፡፡ ከተወሰነ ደረጃ በታች ያሉትን ለመሥራት ክልሎች መግባት አለባቸው፡፡ የመንገድ ሥራው በተወሰነ ደረጃ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መቀነስ አለበት፡፡ አለበለዚያ ሁሉንም ሥራ እንዲህ ይዘህ ጥራት ላይ ተፅዕኖ ይመጣል፡፡ አቅርቦትና ቁጥጥር ላይ ተፅዕኖ አለው፡፡ ከተማ ውስጥ ያለ አንድ ፕሮጀክት መጨረስ ቀላል አይደለም፡፡ ስለመንገድ ነው የምናወራው፡፡ ስለቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ነው የምናስበው፡፡ ይህንን በዘርፉ ውስጥ ካሉ ውስንነቶች ጭምር እያየን ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሌላ ደረጃም መሄድና መሻገር ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ለምሳሌ እንዴት ያለ?
አቶ ሀብታሙ፡- ከእነዚህ ባሻገር ተጨማሪ ምዕራፍ መሄድ ያስፈልጋል ስንል ወደ ተሻለ ሥራ የሚወስደንን አሠራር መከተል ማለት ነው፡፡ አሁን በሐሳብ ደረጃ ያለና እየተሠራበት ያለ ነገር አለ፡፡ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ በአዋጅ የሚቀርብ ሐሳብ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የአገር ውስጥ ተቋራጮች አሁን ካለባቸው ችግር አንፃር የጨረታ መሥፈርቶችን ቀንሰንላቸዋል ብላችኋል፡፡ ከዚህ ባሻገር እነሱን ለመደገፍ ምን ይደረጋል? አቅም ከሌላቸው ምን ታስቦላቸዋል?
አቶ ሀብታሙ፡- በአጠቃላይ ዘርፉን የመደገፍ ብሎም ለሪፎርም የሚያግዝ ሥራ በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ በትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ እንደኛ ባሉ ተቋማትና በሌሎችም አካላት ትብብር በጋራ ተነሳሽነት መቀረፅ አለበት፡፡ በእኛ ደረጃ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት ነው የምናስከብረው፡፡ ሌላ የምታደርገው ነገር የለም፡፡ ተቋማት ያላቸውንና የሚንቀሳቅሱትን ሀብት መጠን፣ ያላቸውን ልምድና የመሳሰሉት ሁሉ የሚመለከተው በመንግሥት የግዥ ሥርዓት ነው የሚሄደው፡፡ ከእኛ ተቋም አኳያ የምናደርገው ነገር የለም፡፡ እኛ የተወሰነ ነገር ልናይ እንችላለን፡፡ ከብቃት አኳያ፣ አንድ ተጫራች አንድ ሥራ ወስዶ ዳግም ሲመጣ፣ ምን ያህል በመቶ ሥራ ሲሠራ ነው እንደገና በጨረታ መሳተፍ የሚችለው? በሚሉት ላይ ከቦርዱ ጋር በመነጋገር ማየት የምንችለው ይኖራል እንጂ በዘርፉ ደረጃ ከፍ ብሎ መወሰን ያለበት በአገር ደረጃ በሚደረጉ ማሻሻያዎች ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ የወሰን ማስከበር ችግር ይነሳል፡፡ ይህ እንዴት ይፈታል? የመንገድ ግንባታዎችን በአግባቡ ለማስኬድ ምን መደረግ አለበት?
አቶ ሀብታሙ፡- ብዙ ጊዜ እንደምለው ለውጫዊ ችግሩ መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ዘርፉ ቅድሚያ የሚያገኝበት መንገድ ይፈለጋል፡፡ ሁሉም የየራሱን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል፡፡ ተቋራጩ ሙያዊ ሰብዕናውን፣ አቅሙንና ሀቀኝነቱን ጠብቆ መሄድ ይኖርበታል፡፡ መንገድ ሲባል ቀድሞ የሚታሰበው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ነው፡፡ የመንገድ ሥራ ብዙ ተዋንያን አሉት፡፡ ተቋራጭ፣ አማካሪ፣ ሕዝቡ የአስተዳድር አካላት፣ ባለሥልጣኑና ሌሎችም ተዋንያኖች አሉበት፡፡ ስለዚህ እነዚህ አካላት ተባብረው መሥራት አለባቸው፡፡ አንድ አካል ላይ ብቻ የሚወድቅ አይደለም፡፡ እንደኛ ያለው መሥሪያ ቤት ሊወስድ የሚችለው ከኮንትራንት ጋር የተያያዘ ዕርምጃ ብቻ ነው፡፡ ሁሉንም የአገር ውስጥ ተቋራጭ የውል ስምምነት ደካማ ሆኖ ቢገኝ የሁሉንም ኮንትራት አቋርጠህ አትጨርስም፡፡ ሁሉንም ታባርረዋለህ ወይ? ከዚያስ ምንድነው የሚመጣው? ስለዚህ በሁሉም አቅጣጫ ዘርፉ መደገፍ አለበት፡፡ ገና መንገድ አልሠራንም እኮ፡፡ በሌላው ዓለም የምናያቸው ትልልቅ መንገዶችና ድልድዮች አልተሠሩም፡፡ ገና እየጀመርን ነው፡፡ ስለዚህ ለትልቁ ነገር ማሻሻያ አድርጎ ለትልቅ ሥራ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ 120 ሺሕ ኪሎ ሜትር መንገድ አለ ይባላል፡፡ ይኼ ኢትዮጵያን ለሚያህል አገር ኢምንት ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ኪሎ ሜትር መንገድ ያላቸው ትንንሽ አገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ መንገድ ወሳኝ ነው፡፡ ለልማቱ ወሳኝ ነው፡፡ አሁንም ሁሉ አቀፍ ዕድገት ስለሆነ የሚፈለገው መንገዱ ያስፈልጋል፡፡ ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርናው፣ ማዕድንና ቱሪዝም ልማቶች ሁሉ መንገድ ይፈልጋሉ፡፡ ለዚያ ሁሉ መሳለጥ መንገድ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ዕድገት ገና እየመጣ ነው፡፡ የእስካሁኑ ሙከራ ነው ማለት ትችላለህ፡፡ ስለዚህ ነገሮችን በትልቅ ስኬት ማየት ያስፈልጋል፡፡ አንድ አካል ላይ የሚጫን ሥራ አይደለም፡፡ በተለይ የሕዝቡን ጉጉት፣ መቸገርና መሰቃየትን በቅርብ የሚከታተለው ከታች ያለው አመራር፣ ክልልና ሕዝቡ ራሱ ለዚህ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡ ባለን አቅም ድጋፍ እንሰጣለን፡፡ ባለን አቅም የጥራት ደረጃውን ከማስጠበቅና መሰል ሥራዎችን ከመሥራት አኳያ ጠንክረን እንሠራለን፡፡ ሁሉም መበርታት አለበት፡፡ በዲዛይን በሱፐርቪዥንና በመሳሰሉት ላይ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም አሁን ሁሉም ከዚህ ወጥቶ ተባብሮ አዲስ ነገር ውስጥ መገባት አለበት፡፡ ሌላ ምዕራፍ ውስጥ መግባት አለብኝ ተብሎ መሠራት አለበት፡፡ እኛም ወደዚሁ የሚወስደን መንገድ ተከትለን እየሠራን ነው፡፡