Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንግሥት አበረ ተባበረ  

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚያስከትለውና እያስከተለ ካለው ማኅበራዊና ሰብዓዊ ቀውስ ባሻገር በኢኮኖሚያዊ ቀውሱም አገሮችን እያንበረከካቸው ነው፡፡ እስካሁን ከተስተናገደውም የላቀ ቀውስ ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ከፍተኛ ሥጋት አሳድሯል፡፡

አፍሪካ ቀጣይዋ የወረርሽኙ መናኸሪያ የመሆኗ ሥጋት ሲነገር፣ አስደንጋጭ ትንበያዎችም ሲወጡ ከርመዋል፡፡ የሰዎች ቸልተኝነትና ጥንቃቄ አለማድረግ ቀውሱን አስከፊ ሊያደርገው እንደሚችል ይታመናል፡፡ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ አባባሽ ግርግር ሲታከልበት፣ የበሽታውን ሥርጭት የመቋቋም ሒደት አሳሳቢና አደገኛ ሊያደርገው ይችላል፡፡

መንግሥት በኢኮኖሚው መዳከም ምክንያት የሚጎዱትን ዘርፎችን የሚደግፉ  ውሳኔዎች በማሳለፍ ለትግበራ ላይ ታች እያለ ነው፡፡ በውሳኔዎቹም የበሽታው ሰለባ የሆኑና እየሆኑ ያሉትን በመለየት ለድጋፍ ምቹ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር አስታውቋል፡፡ ለታክስ ከፋይ ድርጅቶች ምሕረትና ዕፎይታ ሰጥቷል፡፡ አፈጻጸሙን በተመለከተ የገቢዎች ሚኒስቴር ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብድር አመቻችቶ፣ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ላኪዎችና ሌሎችም ድጋፍ የሚሹትን በመለየት እንደሚያግዝ ገልጿል፡፡ የወረርሽኙን አደጋ ለመቀነስ፣ ኅብረተሰቡንም ከተጋላጭነትና ከጉዳት ይታደጋሉ የተባሉ ዕርምጃዎች እንደሁኔታው እንደሚተገበሩ መንግሥት አስታውቋል፡፡

ብዙኃኑን እንደሚመለከት የሚታመንበት አከራይና ተከራይን የሚመለከተው  ውሳኔ ሌላው ሲሆን፣ የግል ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችም አነስተኛ የንግድ ድርጅቶች በሚከፍሉት የቤት ኪራይ ላይ የተደረጉ የድጋፍ ዕርምጃዎችም ወሳኝ ናቸው፡፡ በመንግሥት ውሳኔ መሠረት ከኪራይ ገቢ የሚገኘውን ታክስ በመቀነስ፣ በድርጅቶቹ የተቀጠሩ ሠራተኞች ከሥራ እንዳይቀነሱ፣ ቀጣሪዎችም የሚከፍሉት ደመወዝ ሳያጡ እንዲያቆዩ የሚያግዝ ዕርምጃ ነው፡፡  

የዜጎችን የወጪ ጫና ለመጋራት የታሰበበት ነው ተብሏል፡፡ በጎ አድራጊ ግለሰቦች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ያጋጠማቸውን የኢኮኖሚ ጫና ለማገዝ ድጋፍ ማድረጋቸውንና የሕዝቡን ተነሳሽነት በማወደስ በመንግሥት በኩልም ይህንኑ የሚያበረታታ ድጋፍ መደረጉ ተገልጿል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቤት አከራዮች ለተከራዮች የሁለትም የሦስት ወርም ክፍያ በማንሳት ነፃ የሚያደርጉበት ድጋፍ መንግሥትም አነሳስቶ ድርሻውን እንዲወጣ እንዳነሳሳው የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ከሥራ እንዳይፈናቀሉ፣ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ለመክፈል ተቸግረው ጎዳና እንዳይወጡ ዕገዛ ማድረግ ተገቢ በመሆኑ ለመኖሪያና ለትምህርት እንዲሁም ለአነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች አገልግሎት የሚውሉ ቤቶችን በማከራየት ከሚገኝ ገቢ የሚከፈለውን ግብር ማንሳቱ በእርግጥም በአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ ከፍተኛ ጫና የሆነውን የቤት ኪራይ ወጪ በተወሰነ ደረጃ ሊያግዝ እንደሚችል ይታመናል፡፡  

ከመንግሥት ውሳኔ መረዳት እንደሚቻለው፣ የቤት ኪራይ ወጪን ሙሉ በሙሉ ባይሸፍንም፣ ይህንን ወጪ መጋራቱ፣ የቤት አከራዮች ከቤት ኪራይ ከሚያገኙት ገቢ ላይ ሊከፍሉ የሚገባውን በአማካይ 30 በመቶ የገቢ ግብር በማስቀረት ያደረገው ድጋፍ ግን አይናቅም፡፡ ይህ የሚመለከታቸው ከ10,000 ብር በታች ለሚያከራዩ እንጂ ከፍተኛ አከራዮችን አይደለም፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት፣ በወር በ10,000 ብር ያከራይ የነበረ አከራይ፣ በዓመት ይጠበቅበት የነበረውን 36 ሺሕ ብር፣ የሁለት ወራት የኪራይ ገቢ ለተከራዮች ምሕረት በማድረጉ የሚያገኘው ዕፎይታ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ ዝርዝር ጉዳዮች ቢኖሩትም ባጭሩ የቤት ኪራይ ለቀነሱና ለሰረዙ አከራዮች በዚህ አግባብ የግብር ቅናሽ ይደርግላቸዋል፡፡ ለትምህርት አገልግሎት የዋሉ የኪራይ ቤቶችና   የመኖሪያ ቤቶች አከራዮች ማስረጃ ሲያቀርቡ በዓመቱ መጨረሻ መክፈል የሚጠበቅባቸው የቤት ኪራይ ገቢ ግብር ነፃ ይደረግላቸዋል፡፡

ይህ ውሳኔ ለሁለት ወራት ከተማሪዎቻቸው የትምህርት አገልግሎት ክፍያ የማይጠይቁትን ተቋማት ብቻ የሚመለከት በመሆኑ፣ ልጆቻቸውን በክፍያ በሚያስተምሩ ወላጆች ላይ የሚኖረውን ጫና በማቃለል ጭምር ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተመልክቷል፡፡

እንዲህ ያሉት የመንግሥት ውሳኔዎች ዘላቂ መፍትሔ ማምጣታቸው በጥያቄ ይቀመጥና፣ ውሳኔዎቹ በአግባቡ እንዲተገበሩ ማድረግ ግን ወሳኝነት አለው፡፡ አከራዮች መንግሥት የሰጣቸውን ዕድል ተጠቅመው መተባበር አለባቸው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ አከራዮች ውሳኔው ከመተላለፉ ቀድመው ሲያደርጉ የቆዩት ትብብርና መልካም ተግባር የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ በመንግሥት ውሳኔ መሠረት ሌሎችም እንዲሁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ መንግሥት የሚያወጣቸው እንዲህ ያሉ ውሳኔዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠትና አተገባበሩን ማስረዳት ይጠይቃል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ዜጎችና ተቋማትን ለመታደግ በማሰብ የሚተላለፉ ውሳኔዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ማድረግና ያስገኙትን ውጤት የሚገመግም አሠራር መዘርጋት ይስፈልጋል፡፡

ከመንግሥት ውሳኔዎች በፊትም በመልካም የሚያስነሳቸውና የሚያስመሰግናቸውን ተግባር እየተወጡ ያሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ እንዲህ ያለ የመንግሥት ድጋፍ እየተደመጠም ጆሮ ዳባ ያሉ አይታጡም፡፡ ከቤት አከራዮች ባሻገር ትምህርት ቤቶች አካባቢ ይህ ይታያልና እንዲህ ባለው ጊዜ ልባቸውን አራርተው ሌሎችን ለማገዝ ቢተባበሩ የነገ እንጀራቸውን ያሰፋሉ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት