ዓለምን በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ከቶ በሚገኘው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመውጣቱ አጣብቂኝ ውስጥ በገባው መጪው አገራዊ ምርጫ ላይ ስለተጠየቀው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ፣ በዘርፉ የተመረጡ የሕግ ባለሙያዎች ለሕዝብ ይፋ በሆነ መድረክ አስተያየታቸውን ሊያቀርቡ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ በመላው አገሪቱ ተንቀሳቅሶ ለምርጫ የሚያስፈልጉ ዝግጀቶችን ለማከናወንና ምርጫውን ማካሄድ እንደማይቻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማስታወቁ፣ ምክር ቤቱ ሐሳቡን ተቀብሎ ሕገ መንግሥቱ እንዲተረጎም በአብላጫ ድምፅ መወሰኑ ይታወሳል፡፡
የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 82 ድንጋጌ መሠረት በአዋጅ ቁጥር 798/2013 የተቋቋመው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከተወካዮች ምክር ቤት የተላለፈለትን በሕገ መንግሥቱ ላይ ትርጓሜ የመስጠት ውሳኔ አስመልክቶ፣ በዘርፉ ብቃት ያላቸው የሕግ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን እንዲሰጡት ሲጋብዝ መሥፈርቶችንም አስቀምጧል፡፡ ባለሙያዎቹ በአገር ውስጥም ይሁኑ ወይም ከአገር ውጭ ችግር እንደሌለበት ጠቁሞ፣ በሕገ መንግሥት የሕግ ትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪ ወይም ከዚያ በላይ ያላቸው እንዲሆኑና በዘርፉ በመምህርነት፣ በተመራማሪነት፣ በዳኝነትና በተመሳሳይ ደረጃ ባለ ዘርፍ ተሰማርተው ለረዥም ጊዜ ልምድ ያካበቱ መሆን እንዳለባቸው በመግለጽ መሥፈርቱን አስቀምጧል፡፡
የተጋበዙት ባለሙያዎች አስተያየታቸውን የሚያቀርቡት ‹‹. . . ቅድመ ምርጫ ዝግጀቶችን ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰት፣ በዚህ የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን፣ የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው ምክር ቤቶችና አስፈጻሚ አካላት የሥራ ዘመን ምን ይሆናል? ምርጫውስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል?›› በሚለው ላይ መሆኑን ጉባዔው ገልጿል፡፡
በቀረቡላቸው ጥያቄዎች ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጋበዙት ባለሙያዎች የቀረበውን መሥፈርት አሟልተው ከተመረጡ በጉባዔው ፊት ቀርበው ለሕዝብ ይፋ በሆነ መድረክ ግንቦት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ 7 ሰዓት ድረስ፣ እንዲሁም ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ከቀኑ 8 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ድረስ የሙያ አስተያየታቸውን እንደሚሰጡ ጉባዔው አስታውቋል፡፡
የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ስለሕገ መንግሥት በቂ ዕውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች መጋበዙ ትክክለኛ አካሄድና በሕግም የተፈቀደለት መሆኑን የገለጹት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግና አስተዳደር ጥናት ኮሌጅ የፌዴራሊዝም መምህር ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ባለሙያዎች የሚሰጡት የሙያ አስተያየት እንዳለ ተወስዶ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚላክ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል ብለዋል፡፡ ባለሙያዎቹ ባላቸው ብቃትና ልምድ የሚያቀርቡት ሐሳብ ሕዝቡ የተለያዩ አማራጮች መኖራቸውን እንዲገነዘብ እንደሚያደርጉና አጣሪ ጉባዔው ባሉት ብቃት ያላቸው ኤክስፐርቶች የባለሙያዎቹን የሙያ ትንታኔና የራሳቸውን ምርምር በማድረግ ካጣሩ በኋላ፣ የቀረበውን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ውድቅ ሊያደርጉት ወይም ‹‹ትርጉም ያስፈልገዋል›› ብለው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊያሳልፉት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
ባለሙያዎችን ጋብዞ አስተያየታቸውን በነፃነት እንዲሰጡ ማድረግ ግልጽነት እንዲኖር ከማድረጉም በተጨማሪ ሕዝብ የራሱን ጭብጥ ስለሚይዝ፣ የጉባዔው አባላት በራሳቸው ስሜትና መንፈስ እንዲወስኑ እንደሚያደርጋቸውም ሲሳይ (ዶ/ር) አክለዋል፡፡
ምርጫውን በወቅቱ ማካሄድ ባለመቻሉ መንግሥት ካቀረባቸው አራት የመፍትሔ ሐሳቦች ውስጥ፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልና ሕገ መንግሥቱን መተርጎም›› የሚሉት የተሻሉ ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ሕዝብ ተዘዋውሮ በማወያየትና በማነጋገር ውሳኔውን ማሳወቅ የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ እንዲሁም መጪው ክረምት በመሆኑና በኮሮና ምክንያትም መሰብሰብ ስለማይቻል ሐሳቡ ተቀባይነት ሊያገኝ እንደማይችል ሲሳይ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
‹‹ሕገ መንግሥትን መተርጎም›› የሚለው ሐሳብ ግን ከሁሉም የተሻለ መሆኑን ገልጸው፣ የሕገ መንግሥት ጉዳዮችን እንዲተረጉሙ የተመረጡት የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ባለሙያዎች ብቃት ያላቸው መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የቀረበውን የሕገ መንግሥት ትርጉም ተቀባይነት እንዳለውና ‹‹ሊተረጎም ይገባል›› ብለው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከላኩት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የክልል ባለሥልጣናት በመሆናቸው የክልሉን ምክር ቤት እንደሚወክሉና ሕዝቡም ስለሚወከል፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(1) እና አንቀጽ 83 ድንጋጌዎች መሠረት የመተርጎም ሥልጣን እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ግልጽ ያልሆነ ድንጋጌ ሲኖር፣ አሻሚ ትርጉም ሲኖር፣ ትርጉም ያስፈለገበት ሐሳብ፣ ፍላጎትና ዓላማን በተገቢ ሁኔታ ለማስፈጸም የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚሰጥ ሲሳይ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
አንድ ነገር ሲነበብ ግልጽ ቢሆንም ‹‹ንባብ ይገድላል፣ ትርጉም ግን ያድናል፤›› እንዲሉ ግልጽ የሆነበት ምክንያትም መተርጎም እንዳለበት ጠቁመው፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 (1) እና 58 (3) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየአምስት ዓመቱ እንደሚመረጡና የሥራ ዘመናቸው ከማለቁ አንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ እንደሚካሄድ እንጂ ሌላ የሚለው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
በመደበኛና በተቀመጠለት ጊዜ ተብሎ ቢተረጎም፣ ባይመቻችና አሁን እንደ ተፈጠረው ወረርሽኝ ቢፈጠር ምን ማድረግ እንደሚቻል ሕገ መንግሥቱ ያለው ነገር ስለሌለ ለትርጉም የተጋለጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ያሉበትን ክፍተቶች በማሳየት፣ የሚጎሉትን ግልጽነቶች በማመላከትና የተከሰተውንም ችግር ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ትርጓሜ መስጠት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡