Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሥራ ማስኬጃ ብድር ፈቀደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰበት የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ባንኮች ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ብድር በአምስት በመቶ ወለድ እንዲሰጥ፣ ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮቹ የአንድ ዓመት ብድር በአምስት በመቶ ወለድ እንደሚያቀርብ ገልጿል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ማክሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ለባንኮቹ በሙሉ በደብዳቤ እንዳስታወቀው፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ ደንበኞቻቸው ለሥራ ማስኬጃ የሚውል ገንዘብ የሚደለደለው ባንኮቹ በሰጡት የብድር መጠን እየተሰላ ነው፡፡

ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚለቀቀው ገንዘብ አጠቃላይ መጠኑ ባይገለጽም፣ ባንኮቹ ግን የሚለቀቅላቸው የገንዘብ መጠን ተጠቅሶ እንዲያውቁት ተደርጓል፡፡ ሪፖርተር ባገኘው መረጃ መሠረት እስካሁን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 850 ሚሊዮን ብር፣ ዘመን ባንክ 172.46 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም እናት ባንክ 12 ሚሊዮን ብር የሚለቀቅላቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች በጻፈው ደብዳቤ የተመደበላቸውን ገንዘብ ለደንበኞች የሚያበድሩት፣ ከአምስት በመቶ ባልበለጠ ወለድ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ባንኮች ከሚለቀቅላቸው ገንዘብ ለሆቴል ተበዳሪዎች 89 በመቶ፣ ለአስጎብኚዎች ደግሞ 11 በመቶ እንደሆነ ብሔራዊ ባንክ በደብዳቤው አስታውቋል፡፡

መንግሥት አሁን ባለው ጉዳት መሠረት የስድስት ወራት የማገገሚያ ጊዜን እንደ መነሻ በመውሰድ፣ ባንኮች ከግንቦት 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ለሆቴልና ለቱሪዝም ዘርፍ ተበዳሪዎች ብድሩን ማቅረብ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

ብሔራዊ ባንክ በደብዳቤው እንደገለጸው፣ ይህንን ብድር ለማግኘት ባንኮች በቅድሚያ ጠቅላላ የብድር ስምምነት (Master Loan Agreement) ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመፈራረም የዋስትና ሰነድ እንዲያሲዙ ይጠየቃሉ፡፡

ገንዘቡ የሚለቀቀው ግን ባንኮች ለተጠቀሱት ተበዳሪዎቻቸው ብድሩን ከሰጡ በኋላ አስፈላጊውን ሰነድ በማያያዝ፣ ብሔራዊ ባንክን ሲጠይቁ እንደሆነ በደብዳቤው ተመልክቷል፡፡

ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርብ የይከፈለኝ ጥያቄ ለኮርፖሬት ፋይናንስ ዳይሬክቶሬት የሚቀርብ ሆኖ ብድሩ ለመሰጠቱ ከማረጋገጫ ጋር አብሮ ሲቀርብ፣ ዳይሬክቶሬቱ አስፈላጊውን የብድር ሒሳብ በመክፈት ገንዘቡን ወደ ተበዳሪው ባንክ ሒሳብ ገቢ እንደሚያደርግና ዝርዝር ማብራሪያ ከተፈለገ የገንዘብና የፋይናንስ ትንተና ዳይሬክቶሬትን ማነጋገር እንደሚቻል ብሔራዊ ባንክ በደብዳቤው አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች