የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በመስከረም 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ለማከናወን አቅዶት የነበረው 70ኛ ጉባዔውን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በቪዲዮ ኮንፈረስ ለማካሄድ መወሰኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡
ፊፋ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማክሰኞ ሚያዝያ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ ወረርሽኙ በሁሉም የዓለም አገሮች በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ፣ በሰው ሕይወትና በዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲሁም ኪሳራ እያደረሰ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ ከሦስት ሺሕ በላይ ታዳሚዎች የሚስተናገዱበት ጉባዔ በአዲስ አበባ ማድረግ የሚቻል አይደለም፡፡
“ጉባዔውን የምታስተናግደው ኢትዮጵያ አዲስ አበባን ጨምሮ የዓለም አገሮች የወረርሽኙን ሥርጭት ለመከላከል የተለያዩ መፍትሔዎችን እየወሰዱ እንደሚገኙ እናውቃለን፤” የሚለው የፊፋ ደብዳቤ ከእነዚህ ዕርምጃዎች መካከል በርካቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ማድረጋቸው ለአብነት ይጠቅሳል፡፡
ዕርምጃው በዋናነት የአባል አገሮቹ አመራሮችና ለስብሰባው ታዳሚዎች ደኅንነት ሲባል የስብሰባው ታዳሚዎች በርቀት ሆነው ባሉበት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ስብሰባው እንዲካሄድ የብዙ አገሮች ፍላጎት ነውም ብሏል፡፡ ፊፋም በዚሁ ተስማምቶ በአዲስ አበባ ሊያደርግ ያቀደውን ጉባዔ በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት መከናወን ይችል ዘንድ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ፣ ለስብሰባው አስፈላጊ የሆኑ መልዕክቶችን በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚልክ መግለጹን ጭምር ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
የፊፋ ዋና ጸሐፊ ፋጡማ ሳሞራ ተቋሙ 70ኛ ጉባዔውን በአዲስ አበባ ለማድረግ ሲያቅድ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም ብሔራዊ አዘጋጅ ኮሚቴው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምሥጋናቸውን ማቅረባቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በመግለጫው አካቷል፡፡