የዓለም ነርሶች ቀን በየዓመቱ ግንባት 4 ቀን በተለያዩ መሪ ቃሎች የሚከበር ሙያ ተኮር በዓል ነው፡፡ ዘንድሮ መሪ ቃሉ ‹‹ነርሶች ዓለምን ወደ ጤና የሚያደርሱ መሪዎች›› በሚል መሪ ቃል ዓለም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተወጠረችበትና በተጨነቀችበት አጋጣሚ ነርሶች በሥራ ላይ ሆነው አክብረውታል፡፡
በኢትዮጵያ እንደከዚህ ቀደሙ ከቀኑ ባለፈ ‹‹የነርሶች ሳምንት›› በሚል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲከበር እንደነበረው ዘንድሮ ለዚያ አልታደለም፡፡ ይልቁንም ለአስጨናቂውና ለአገርም ሆነ ለዓለም ሥጋት በሆነው ኮቪድ 19 ላይ በማተኮር በሥራ ለወገኖች ሕክምና በመስጠትና በመንከባከብ በማክበር ባለፈ ዕለቱን አስመልክቶ የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ነርሶች ማኅበር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ ነርሶች ሥራ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ነው፡፡
እንደሳቸው አገላለጽ፣ ያለነርሶች የሚታሰብ ምንም ዓይነት የጤና አገልግሎት የለም፡፡ በዚህ ዘመን ኮቪድ 19 ደግሞ ሥራቸውን ከባድ አስተዋጿቸውንም ምትክ የሌለው አድርጎታል፣ በተለያዩ የጤና ተቋማትም የሰውን ሕይወት ለማትረፍ የራሳቸውን ጤናና ሕይወት በመሰዋት እያገለገሉ ይገኛሉ።
ነርሶች ቤተሰቦቻቸውንና ልጆቻቸውን አስቀምጠው የሌሎችን ልጆችና ቤተሰብ ለማከም መስዋዕትነት እንደሚከፍሉም የተናገሩት ሚኒስትሯ ለታካሚዎች ደኅንነትና ጤንነት ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ከ120 ዓመታት በፊት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የነርሶች ምክር ቤትን (አይሲኤን) በ1957 ዓ.ም. የተቀላቀለው የኢትዮጵያ ነርሶች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ታፈሰ በቀለ፣ ነርሶች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በግንባር ቀደምነት ተሰላፊ ባለሙያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ መልዕክት ካስተላለፉት መካከል፣ “ነርሶች በሕሙማን አጠገብ እንደሚቆሙ ቅዱሳን ይቆጠራሉ” ያሉት ፖፕ ፍራንሲስ ይገኙበታል፡፡
የቫቲካን የዜና ምንጭ እንደገለጸው፣ ፖፕ ፍራንሲስ ማክሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በቅድስት ማርታ ቤተ ጸሎት፣ በቅዳሴ ጸሎት መጀመሪያ ላይ ዕለቱ የነርሶች ቀን መሆኑን በማስታወስ፣ የሕክምና አገልግሎትን በማበርከት ላይ የሚገኙ ሴቶችና ወንዶች ነርሶች፣ አገልግሎታቸው ከሞያነት አልፎ ጥሪና ራስን ማቅረብ ነው ብለዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እያስጨነቀ ባለበት ባሁኑ ጊዜ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ፣ በአገልግሎታቸው ወቅት ለሞት የተዳረጉትን በሙሉ እግዚአብሔር እንዲባርካቸው ጸልየው ነርሶችን በሙሉ በጸሎታችን እናስታውሳቸው ብለዋል።
የዓለም ነርሶች ምክር ቤት (አይሲኤን) ቀኑን ማክበር የጀመረው እ.ኤ.አ. ከ1965 ጀምሮ ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀኑ እንዲከበር የተወሰነው ግን ግንቦት 4 ቀን 1966 ዓ.ም. (ሜይ 12 ቀን1974) ነው፡፡ መነሻ ምክንያቱ ደግሞ የዘመናዊ ነርስ ሙያን በተደራጀ መልኩ ሕገ ደንብ በማውጣትና ኃላፊነትንም በመዘርዘር ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት የሚታወቁት ፍሎረንስ ናይትንጌልን የልደት ቀን ለማስታወስ ሲሆን፣ ዘንድሮ 200ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውም ታስቧል፡፡
አይሲኤን የ135 አገሮች ማኅበሮችን በአባልነት ያቀፈ በዓለም ከ20 ሚሊዮን በላይ ነርሶችን የሚወክል ማኅበር መሆኑን በድረ ገጹ ገልጿል፡፡