Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኮሮና መስፋፋት የዘፈቀደ ግምት ከጥቅሙ ጉዳቱ በእጅጉ ያመዝናል!

የኮሮና መስፋፋት የዘፈቀደ ግምት ከጥቅሙ ጉዳቱ በእጅጉ ያመዝናል!

ቀን:

በታደሰ በርሄ (ብርጋዴር ጄኔራል)

እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 13 ቀን 2020 ‹‹በኢትዮጵያን ኢንሳይደር›› ለአንባቢያን የቀረበ በኢትዮጵያ ስለሚኖረው የኮሮና ቫይረስ መስፋፋት የሚያትት፣ በባለሙያዎች የተደረገ ጥናታዊ ግምት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ በዚህ ከቀጠለ በሰኔ ወር መጨረሻ 33 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በቫይረሱ እንደሚጠቁ፣ በመጪው ግንቦት ወር ብቻ 1.94 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ እንደሚለከፉ፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ንክኪ በግማሽ መቀነስ ከተቻለ ወደ 15 ሚሊዮን ገደማ በበሽታው እንዳይያዙ መታደግ እንደሚቻል፣ የቫይረሱ ሥርጭት ወደ ወረርሽኝ በሚያድግበት ወቅት ከአዲስ አበባ ሕዝብ ውስጥ 50 በመቶ ያህሉ ለቫይረሱ ሊጋለጥ እንደሚችል፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ በሚያዝያ ወር በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች 250 ሺሕ ሊደርስ እንደሚችል፣ በቀጣይ ወር (ግንቦት) ቁጥሩ ወደ 1.4 ሚሊዮን ሊያሻቅብ እንደሚችል ጥናታዊ ግምቱን ገልጾ፣ የኅብረተሰቡ ንክኪ በግማሽ ከቀነሰ ግን 872,243 ሰዎች ከመጠቃት ሊድኑ እንደሚችሉ ያስቀምጣል (እዚህ ላይ የግምታዊ አኃዙ ሥሌታዊ እርግጠኝነት ግርምት ይፈጥራል)፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ የጤና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፈው መጋቢት ወር የወጣ ሌላ ሰነድ 28 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ሊያዙ እንደሚችሉ፣ ሆኖም የጎንደርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ሐሳብ ተጨምሮበት ይኼንን አኃዝ በአምስት ሚሊዮን ጭማሪ ሊያሳይ እንደሚችል፣ እንዲሁም ከከተማ ነዋሪዎች አጠቃላይ የሕዝብ ብዛት ውስጥ 21 በመቶ በኮሮና የመጠቃት አደጋ እንዳለውና ይህም በቁጥር ሲገመት 23 ሚሊዮን እንደሆነ ተገልጿል፡፡

አሁን በቅርቡ በጤና ሚኒስቴር የጤና ነክ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ያዕቆብ ሰማን ለኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥርና የከፋ ጉዳት ሊደርስ የሚችለው ሰኔ መጨረሻና ሐምሌ መጀመሪያ ቀናት መሆኑን ገልጸው፣ በገር አቀፍ ደረጃ አሁን የምናደርገውን ጥንቃቄ ባናደርግ ከ27 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ኮሮና ያጠቃ እንደነበር፣ በደንብ ከተጠነቀቅን ደግሞ የዚህ ቁጥር 60 በመቶ ወይንም 16 ሚሊዮን መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

እርግጥ ነው በመንግሥት የሚወጡ መመርያዎችና በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክሮች ኅብረተሰባችን ተቀብሎ በጥንቃቄ ካልተገበረ፣ በኮሮና ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ስለሆነም የቫይረሱን መስፋፋት ለመከላከል በመንግሥት የሚወጡ መመርያዎች ለተፈጻሚነታቸው መንግሥት ቁጥጥሩን ማጥበቅ፣ ሕዝቡም በመንግሥት የሚወጡ መመርያዎችንና በሕክምና ባለሙያዎች በመሰጠት ላይ ያሉት ምክሮችን ፀንቶ የማክበርና የመፈጸም ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ መፈጸም ይኖርበታል፡፡

በሕዝቡ ዘንድ አሁን ባለው በቫይረሱ የሚያዝ አነስተኛ የሰው ቁጥር ምክንያት የሚታየው መዘናጋትና ቸልተኝነት የሚኖር ከሆነ ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጥ ይሆናል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ‹‹በጥናታዊ›› ግምቱ ላይ መነሳት የሚችሉ በርካታ ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ፣

  • በቁጥር ተደግፎ የቀረበው ጥናታዊ ግምት እንደ መነሻ የወሰደው ምንድነው?
  • የጥናቱ ዓላማስ ምንድነው? የሚሉ ጥያቄዎች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በባለሙያ የሚደረግ ግምት (Estimation) በተራ ሰው በዘፈቀደ ከሚደረግ ግምት (Intuitive Guess) የሚለየው፣ በባለሙያ የሚደረግ ግምት ምክንያታዊነት ባለው አግባብ ተሂዶ የሚደረስ ድምዳሜ በመሆኑ፣ በተቻለ መጠን ወደ እውነታው (Reality) የተጠጋና ተገቢነት ያለው ግምት ይሆናል፡፡

በአንፃሩ በዘፈቀደ የሚደረግ ግምት በአመዛኙ በግብታዊነት (Spontaneous) የሚመረኮዝ በመሆኑ፣ ከእውነታው ጋር ተቀራራቢነት የሌለውና በእጅጉ የሚራራቅ በመሆኑ ጠቃሚነቱ እስከዚህም ነው፡፡ በተጨማሪ በእሱ ላይ ተመርኩዞ የሚካሄድ ተግባር የሚኖር ከሆነ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ይሆናል፡፡ በዚህ መነጽር የተነሳውን የመጀመርያ ጥያቄ ስናይ ለቫይረሱ ጥቃት ይጋለጣል በሚል የቀረቡት አኃዞች፣ በየትኛው የምክንያታዊነት መንገድ ተሂዶ የተደረሰ ድምዳሜ ወይም ጥናታዊ ግምት መሆኑን ለመረዳት እጅግ ያስቸግራል፡፡ የቫይረሱ የመስፋፋት ባህሪ፣ የኅብረተሰባችን አኗኗር ዘይቤ፣ እንዲሁም ግንዛቤና አስቀድሞ ቫይረሱ በተሠራጨባቸው አገሮችም ሆነ በዓለም ደረጃ ከታየው የተጠቂ ሰው ብዛት ጋር አነፃፅሮ ያንን የተጋነነ አኃዝ ማሰቀመጥ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በዚህ ላይ አኃዙ የተምታታ ነገር አለበት፡፡

ይህም ከከተማ ነዋሪዎች አጠቃላይ የሕዝብ ብዛት ውስጥ 21 በመቶ በቫይረሱ የመጠቃት አደጋ እንዳለው ገልጾ፣ ይህ በቁጥር ሲገመት 23 ሚሊዮን እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ በከተማ የሚኖረው ሕዝብ 21 በመቶው 23 ሚሊዮን የሚሆነ ከሆነ በእጅጉ የሚበልጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚኖረው በገጠር ሳይሆን፣ በከተማ እንደሆነ ያስመስላል፡፡ ሁለተኛው ጥያቄ “የጥናታዊ” ግምቱ ዓላማ ምንድነው? የሚል ነው፡፡ ከላይ በአጭሩ እንደተገለጸው በምክንያታዊነት ተመሥርቶ የሚደረግ ግምት ቀጥሎ ለሚከሰት አሉታዊም ሆነ በጎ ሁኔታ በቅድሚያ ለእውነታው የሚቀራረብ ግምት በማስቀመጥ፣ ከዚህ አንፃር መደረግ ያለበት በቂ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግና በድንገተኛነት ከሚሠራ የተዝረከረከ የእሳት ማጥፋት ዓይነት እንቅስቃሴ ከሚያደርሰው ጉዳት ራስንም ሆነ ሌላውን አካል ለመታደግ ነው፡፡

በስሜት ወይም በግብታዊነት የሚደረግ ግምት ከሆነ ግን የተጠቀሰውን ዓይነት ጥቅም የሚሰጥ አይሆንም፡፡ እንዲያውም ጉዳት ነው የሚኖረው፡፡ በዘፈቀደ የሚደረግ ግምት ወደ እውነታው ተቀራራቢ የማይሆነው በሁለት መንገድ ነው፡፡ ግምቱ በጣም በማጋነን ወይም በጣም በማሳነስ ሊገለጽ ይችላል፡፡ በሁለቱም መንገድ  ጉዳቱ ያው ነው፡፡ ይህንን ከውጊያ ጋር በተያያዘ አብነት ወስዶ ማየት ይቻላል፡፡

አንድ ተዋጊ ኃይል በአንድ ቦታ ላይ የተቀመጠ የጠላት ኃይል ለማጥቃት ፈለገ እንበል፡፡ ማጥቃቱን ለመፈጸም የጠላት የውጊያ አቅም (ትጥቅ፣ የሰው ብዛት፣ የውጊያ ልምድና ብቃት፣ የመዋጋት ሞራል፣ የያዘው ቦታ ሁኔታና አሰፋፈሩ. . .) ዝርዝር ጥናት ማድረግ ይገባዋል፡፡ ስለጠላት የተሰበሰበውን መረጃ በመተነተን ከራስ ወገን የውጊያ አቅም ጋር በማስተያየት፣ በጣም ሳያጋንን ወይም ሳያሳንስ ትክክለኛ ድምዳሜ በማስቀመጥ ውሳኔ ላይ መድረስ ይኖርበታል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የጠላት ኃይል ከተጨባጭ አቅሙ በላይ ካጋነነው ግን፣ አቅሜ አይፈቅድም በሚል አጥቅቶ ሊያገኝ ይችል የነበረው ድል ያመልጠዋል፡፡ ወይም ደግሞ ከሚያስፈልግ በላይ የወገን ኃይል በማጥቃቱ በማሠለፍ፣ ለአላስፈላጊ ኪሳራና የኃይል ብክነት ራሱን በማጋለጥ ለጉዳት ይዳረጋል፡፡ በአንፃሩ የጠላትን ኃይል አሳንሶ መዝኖ ከሆነም በጠላት ተበልጦ ለሽንፈት ይዳረጋል፡፡ ስለሆነም ወደ እውነታው ተቀራራቢነት የሌለው ግምት በሁለቱም መንገድ በማጋነንም ሆነ በማሳነስ ጉዳት እንጂ ጥቅም አይኖረውም፡፡

በተለያየ ወቅት የቀረበው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሊጠቃ የሚችል “ጥናታዊ” ግምት በእኔ ዕይታ በጣም የተጋነነና ለእውነታው ተቀራራቢነት የሌለው ነው፡፡ አገሪቱ፣ መንግሥትና የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በጥናታዊ ግምቶቹ የተጠቀሰው አኃዝ ይቅርና የአኃዙ አንድ ሃያኛ የሚሆን ታማሚ ለማከም ሆነ ለመንከባከብ የሚያስችል አቅም የለንም፡፡ ሰለዚህ ድንጋጤ ፈጥሮ ወደ ተስፋ መቁረጥ የሚገፋ ነው፡፡ ገማቾቹ ባለሙያዎችም  ቢሆኑ የአቅማችን ሁኔታ ጠፍቷቸው አይሆንም፡፡ ከማንም በርቀት ሆኖ ከሚታዘብ ሰው በላይ ዝርዝር ዕውቀት ይኖራቸዋል፡፡

ጥያቄ የሚያስነሳው ለምን እንደዚያ እንደሆነ ነው፡፡ መንግሥትም እንዲህ ያለ በጣም የተጋነነ ግምት ተደጋግሞ ወደ ሕዝብ እየተሠራጨ ለምን ዝም እንዳለ ግልጽ አይደለም፡፡ ምናልባት የተገመተውን አኃዝ ያህል ያልገጠመው፣ ልዩና ከፍተኛ ጥረት ስለተደረገ ነው በሚል ቆይቶ ለሚከተል ፕሮፖጋንዳ ታሳቢ ተደርጎ ከሆነም የጤንነት አይሆንም፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ የቀረቡ “ጥናታዊ” ግምቶች ምርጫ ቦርድ ምርጫ ለማካሄድ አልችልም የሚል ውሳኔ ላይ ለመድረስ ምን ጫና አሳድረው ይሆን? መነሳት የሚችል አግባብነት ያለው ጥያቄ ነው፡፡

ቸር ይግጠመን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ የአመራር ቦታ ካገለገሉ በኋላ በጡረታ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...