Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርምርጫን በፍጥጫ?

ምርጫን በፍጥጫ?

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ከመነሻው ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በተደራጀ በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ‘መንግሥት’ የምንለው አገር አካታች የፖለቲካ ውቅር፣ የሕዝብ ሉዓላዊነት ለተወሰነ ጊዜ በወር ተራ እየተላለፈ የሚያዝበትና ገቢራዊ የሚደረግበት ተቋም ነው፡፡ ምልዓተ ሕዝቡ በተፈጥሮ ያገኘውና በሕገ መንግሥት ደረጃ የተረጋገጠው ሥልጣን በእየ እርከኑ የመንግሥት አስተዳደር አካላት በይፋ የሚተላለፈው ታዲያ፣ በየጊዜው በሚካሄድ ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊና ትክክለኛ በሆነ ምርጫ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ነው ምርጫ በጠባዩ ከፍተኛ የሕዝባዊ ጉዳዮች ኩነት ‘The Conduct of Public Affairs’ ነው እየተባለ ሲበዛ የሚንቆለጳጰሰው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን እንደምትከተል በሕገ መንግሥት ደረጃ ታውጇል፡፡ ይህ በእርግጥ እስኪያቅረን ድረስ ዘወትር ሲለፈፍ የምናዳምጠው ባዶ ቱማታ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እስከ ዛሬ ድረስ ዓለም አቀፋዊ መሥፈርቶችን የሚያሟላ ምርጫ ለማካሄድ አልታደልንም፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የእስካሁኑ ምርጫ ከንቱ ማላገጫ ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡ ምናልባት በ1997 ዓ.ምሦ ተካሂዶ የነበረው ሶስተኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ ብቻ በመጠኑም ቢሆን ለእውነታው የቀረበ እንደነበር ይታወስ ይሆናል፡፡

ሆኖም ይህንን ግዙፍ እውነታ ህሊናው እየተረዳ በአምስተኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ በመቶ ፐርሰንት ተመርጫለሁ በማለት ያለ ኃፍረት ይነግረን የነበረው የቀድሞው የኢሕአዴግ መንግሥት መንበረ ሥልጣኑን በተቆናጠጠና አንድ መንፈቀ ዓመት እንኳ ሳይሞላው፣ ከኅዳር ወር 2008 ዓ.ም አንስቶ ነበር መሬት አንቀጥቅጥ በሆነ ህዝባዊ አመፅ ክፉኛ ሲናጥና ከየአቅጣጫው ሲመታ ባጅቶ ጭራሹን ወደ መፈራረስ ያመራው፡

እነሆ በኢሕአዴግ እግር የተተካው የብልፅግና ፓርቲ በበኩሉ ‘ከማን አንሼ’ በሚመስል አቀራረብ ‘ስድስተኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ ካልተካሄደና አሸናፊነቴ ካልታወጀ በስተቀር በብዙኃኑ ዘንድ ያለኝን አመኔታና ተቀባይነት ላጣ እችላለሁ’ በሚል ዕሳቤ ራሱን በአዲስ መልክ ሲያደራጅ፣ ለካድሬዎቹ ሥልጠና ሲሰጥና በቱባ መሪዎቹ አማካይነት ከሥፍራ ሥፍራ እየተንቀሳቀሰ የሞራል፣ የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያሰባስብ መቆየቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ (ሁሉም ናቸው ባይባል እንኳ) በተቃራኒው ጎራ ከተሠለፉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አንዳንዶቹ ምርጫው የሚካሄድበት ጊዜ እየተቃረበ መምጣቱን ሲረዱ፣ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” በሚል አጓጉል የአቀራረብ ፈሊጥ ገና በይፋ ሳይፈቀድላቸው በምርጫ ቅስቀሳ ስም ወደ አደባባይ እየወጡ አንደኛውን ብሔር ወይም ሕዝብ በሌላው ላይ የማነሳሳትና የጠብ አጫሪነት ተግባር እንዳሻቸው ሲፈጽሙ መከራረማቸውን ለተመለከተ ሰው፣ ከዚያ በፊት በዚህ አገር ከእነሱ አስቀድሞ መንግሥትና የሕግ ሥርዓት ያለ አይመስለውም ነበር፡፡

እነዚህ ልብ አውልቅ ወገኖች ለመራጩ ሕዝብ ደህንነትና በነፃነት የመወሰን ዕድል እምብዛም መጨነቅ ሳያስፈልጋቸው፣ አገራዊው ምርጫ ባልፀዳ አሰራርና መንገድም ቢሆን በአፋጣኝ ተካሂዶላቸውና እነርሱም ተወዳድረውበት የሚያገኙትን የመቀመጫ ወንበር ብዛት ከወዲሁ በምናባቸው እያሰሉ፣ በድልድሉ ለእያንዳንዳቸው የሚደርሰውን መጠን ሲነግሩን ነበር የሰነባበቱት፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ህልውናችን በሺዎች የሚሰሉ ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑ ባይካድም፣ በአገራችን የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት ምርጫ መካሄድ የጀመረው እኮ በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ ፓርላማ ባለሁለት ቤት ሆኖ የተዋቀረ ነበር፡፡ በታችኛው የሕግ መምርያ ውስጥ ዕጩ ተመራጭ ሆኖ ለመቅረብና ለመወዳደር የመሬት ከበርቴ መሆንን ይጠይቃል፡፡ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆኖ ለመመረጥማ ከሁሉም በላይ የንጉሠ ነገሥቱን የመጨረሻ ይሁንታ ማግኘት ያስፈልግ ነበር፡፡

ወታደራዊው የደርግ አገዛዝስ ቢሆን የይስሙላ ምርጫ አካሂዶ አልነበረ እንዴ? ክፋቱ በዕጩነት የቀረበውም ሆነ ከማን ጋር እንደ ተወዳደረ እንኳ አንዳች ፍንጭ ሳይሰጠን ተመረጠ የተባለው አካል ያው ራሱ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) መሆኑ ብቻ ነው፡፡ ብቸኛው የበኩር ልጅ የነበረው ኢሠፓ በያኔው የኢሕዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 6 ድንጋጌ መሠረት ይፋዊ ዕውቅና የተሰጠውና በአገሪቱ የዕድገት አቅጣጫ ቀያሽነት ሙሉ ጥበቃ የተደረገለት መሪ የፖለቲካ ድርጅት ነበር፡፡

ሕገ መንግሥታዊ አቀራረብ

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ ሁለት ሥር ጉልህና ገዥ ሥፍራ ተሰጥቷቸው ከተካተቱት ዓበይት መርሆች አንደኛው በአንቀጽ 8 ሥር ሰፍሮ የምናገኘው የሕዝብ ሉዓላዊነት ነው፡፡ ከተጠቀሰው አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ለመገንዘብ እንደሚቻለው ታዲያ፣ “የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሲሆኑ ሕገ መንግሥቱ ራሱ የዚህ ሉዓላዊነታቸው ዓይነተኛ መግለጫ” እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

ሉዓላዊነታቸው በተግባር የሚገለጸው ደግሞ እነዚሁ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች በዚያው ሕገ መንግሥት መሠረት ወደ አደባባይ ወጥተው፣ “በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ነው” ሲል የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ (2) ይደነግጋል፡፡

እንግዲህ መቸውንም ቢሆን በየትኛውም ደረጃ ይደረግ አንድ ምርጫ ሲካሄድ መራጮች ድምፃቸውን ሊሰጡ የሚችሉት በግለሰብ ደረጃ ስለሆነ፣ ሕገ መንግሥቱ በደምሳሳ አነጋገር እንደሚያስተጋባው ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንደ ቡድን ወጥተው የጅምላ ውሳኔ ሊሰጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ወይም አሠራር የለም፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ የአገሪቱ ሉዓላዊ ሥልጣን እንደሚባለው ከብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይልቅ፣ በባህሪም ሆነ በውጤት ደረጃ ግለሰብ ዜጎች በተፈጥሮ የተጎናፀፉት ሥልጣን ነው ቢባል ፈፅሞ መሳሳት አይሆንም፡፡

በሌላ አነጋገር በየትኛውም የአስተዳደር እርከን የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላትን ወደ አደባባይ ወጥቶ ለመምረጥ ወይም በዕጩነት ተወዳድሮ ለመመረጥ የግድ የብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም የሕዝብ ቡድናዊ ቁመና መላበስን አይጠይቅም፡፡ ይልቁንም የመምረጥና የመመረጥ መብትን በዝርዝር በሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38 ንዑስ አንቀጽ (1) ሥር፣ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር ብሔረሰብ፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ በማናቸውም አመለካከት ወይም አቋም ላይ የተመሠረተ ልዩነት ሳይደረግበት፣ በቀጥታና በነፃነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካይነት በሕዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍና ዕድሜው 18 ዓመት ሲሞላ ደግሞ በሕግ መሠረት የመምረጥ፣ ወይም በማናቸውም የመንግሥት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ ለመወዳደር የሚያበቁ ተጨማሪ መሥፈርቶችን አሟልቶ ሲገኝ የመመረጥ መብቶች” ተብራርተው እንደ ተጠበቁለት እንረዳለን፡፡

እንደዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ተጨማሪ ድንጋጌ ከሆነም በአገሪቱ የሚካሄደው “ምርጫ ሁሉን አቀፍ፣ በሁሉም እኩልነት ላይ የተመሠረተና መራጩ ሕዝብ በሚስጥር የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት ፈቃዱን በነፃነት የሚገልጽበትን ዋስትና የሚሰጥ” መሆን እንዳለበት የተነገረ ሲሆን፣ ይኸውም እንደ አዲስ ተሻሽሎ በወጣው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162 አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ሥር ተጠናክሮ ተገልጿል፡፡

አሁናዊ ዓውድ

ይህ ጸሐፊ እንደሚያስታውሰው ምርጫው ሊካሄድ ገና አምስት ወራት ያህል ሲቀሩት ከፍ ብሎ በተጠቀሰው በአዲሱ አዋጅ ውስጥ፣ ለዳግም ምዝገባ አፈጻጸም የተቀመጡትን ተፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች አሟልተው የተገኙትና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥሪ እየቀረቡ የተመዘገቡት የፖለቲካ ድርጅቶች በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ እንዲያውም ቦርዱ ያን ጊዜ ሰጥቶት ከነበረው ማሳሰቢያ ለመረዳት እንደሚቻለው አዋጁ በሚጠይቀው መሠረት ከአራት ሺሕ የማያንስ የድጋፍ ፊርማዎችን የማሰባሰብ አቅም አግኝተው የቀረቡትና ይፋዊ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል የተባሉት ክልል አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ ሲሆኑ፣ እነሱም በቁጥር ከሦስት የማይበልጡ እንደነበሩ እናስታውሳለን፡፡ ይህንን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው በዕጩነት ለመመዝገብና ወደ ምርጫ ውድድሩ ለመግባት የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ግን መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ፣ ቦርዱ በመገናኛ ብዙኃን ደጋግሞ ሲወተውትም ትዝ ይለን ይሆናል፡፡

ይህ ሁኔታ ራሱ ለወጉ ያህል እንደ ባህር አሸዋ በዝተው የሚታዩትና አብዛኛውን ጊዜ በብሔር ብሔረሰብ ስም እየተቆረቆሩ በአሁኑ ወቅት እንደ አሸን የፈሉት የየመንደሩ ፓርቲዎች የረዥም ጊዜ ግቦችን አልሞ ከሚፈጸም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይልቅ፣ እዚህ ግባ ሊባል የማይችል ባዶ የአጭር ጊዜ ቱሪናፋ ማሰማቱና ማሳየቱ የሚቀናቸው መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ እንዲያም ሆኖ ስድስተኛውን ዙር ብሔራዊ ምርጫ ለማካሄድ ቦርዱ ከአንድም ሁለት ጊዜ ያህል ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት እንዳጠናቀቀ ገልጾልን ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ዝርዝር መርሐ ግብር አዘጋጅቶ፣ ቀን ቆርጦና ይህንኑ ለተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በወቅቱ አሳውቆ ዕለቱን ሲጠባበቅ እንደቆየ መካድ አይቻልም፡፡

ይሁን እንጂ በመላው ዓለም በአስፈሪ ሁኔታ እየተዛመተ የመጣው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአገሪቱ መከሰትና የዚህኑ አደገኛ በሽታ ሥርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በመንግሥት በኩል ለአምስት ወራት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የተባለውን ዝግጅት ሳይታሰብ እንዳስተጓጎለበትና አስቀድሞ ባቀደው መሠረት ምርጫውን ለማካሄድ ከአቅም በላይ እንደሆነበት፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አስታውቀው ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡

በቦርዱ የቀረበለትን ይህንኑ ማሳሰቢያ አግባብ ላለው ኮሚቴ ዝርዝር ዕይታ በቅድሚያ የመራው የአገሪቱ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በበኩሉ ሚያዚያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው አምስተኛ ዙር አምስተኛ የሥራ ዘመን ሦስተኛ ልዩ ስብሰባው ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት አላቸው ያላቸው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች፣ የሕገ መንግሥቱ ባለአደራ ለሆነው ለፌደሬሽን ምክር ቤት ቀርበው እንዲተረጎሙለትና የተፈጠረው ክፍተት በብልኃት ተዘግቶ የምርጫው ጊዜ እንዲራዘም በሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አማካይነት የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ በ25 ተቃውሞ በአብላጫ የድምፅ ድጋፍ ተቀብሎ አፅድቆታል፡፡

እንደሚታወቀው ምርጫ ዘርፈ ብዙ ደረጃዎችን ማለፍ ያለበት ወሳኝ ፖለቲካዊ ኩነት ነው፡፡ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትም ሆነ በድኅረ ምርጫ ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራት ብርቱ ጥንቃቄን ይሻሉ፡፡ የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች አደረጃጀት፣ የአገር ውስጥና የውጭ ታዛቢዎች ምልመላና ሥምሪት፣ የምርጫ ቁሳቁሶች መሰናዶ፣ ሥርጭትና የኮሮጆዎች ደኅንነት ጥበቃ፣ የምርጫ ኦፊሰሮች ሥልጠና፣ የመራጮችና የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ፣ የምርጫ ዘመቻና የምረጡኝ ቅስቀሳ፣ መራጮች በነቂስ ወጥተው ድምፃቸውን የሚሰጡበት ኩነት፣ የድምፅ ቆጠራና ውጤቶችን በይፋ የመግለጽ ሒደት፣ የቅሬታ አቀራረብና አወሳሰን ሥርዓት፣ እንዲሁም በመጨረሻ በምርጫው ያሸነፈውን/ያሸነፉትን  ፓርቲዎች ለይቶ ለሕዝብ የማወጁና የመንግሥታዊ ሥልጣን ርክክቡን በጨዋነት የማስፈጸሙ ተግባር ከብዙዎቹ መካከል በዋነኝነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ይህ ሁሉ ሲታሰብ ታዲያ አገሪቱ አሁን በምትገኝበት የተወሳሰበ ዓውድ ስድስተኛውን ዙር ምርጫ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 38 ሥር ተሟልተው እንዲገኙ በሚጠይቃቸው መሥፈርቶች መሠረት፣ ዜጎች በምርጫው ለመሳተፍና ያላንዳች ፍርኃት ወይም መሸማቀቅ ከተፅዕኖ ነፃ ሆነው በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ እንደራሴዎቻቸውን የሚመርጡበት አስቻይ ሁኔታ እንደማይኖር ዕሙን እየሆነ መጥቷል፡፡ ስለዚህ በሕግ ጠበብት ዓይን ሲታይ በገቢር የሚፈጸምበት መንገድ ለጊዜው የሚያከራክር ቢመስልም፣ አገሪቱ ለገባችበት ቅርቃር ከሌሎች ተወዳዳሪ አማራጮች ይልቅ መጪው ምርጫ የሚካሄድበትን ጊዜ ለማራዘም ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ ይፈለግ ሲል ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምፅ ያሳለፈው ውሳኔ፣ ከበርካታ ክፉዎች መካከል ለጊዜው ተሽሎ የተገኘውን ክፉ የመሸጋገሪያ መንገድ በመምረጥ ላይ አተኩሮ የተላለፈ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ አገር የለውጥ ዕርምጃዎችን መውሰድ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ በማዕከል ከሚወጡ ሕጎችና ከሚተላለፉ ውሳኔዎች ራሱን አብዝቶ የመነጠል ፖሊሲ ሲከተል የምንመለከተው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ከሚያዚያ 23 ቀን እስከ ሚያዚያ 25 ቀን 2012 ዓ.ም፣ ድረስ በመቀሌ ከተማ ሸንጎ ተቀምጦ በህቡዕ ሲንጎዳጎድ ከሰነበተ በኋላ በማግሥቱ ሚያዚያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ “የብልፅግና ፓርቲ በአገር አቀፍ  ደረጃ እንዲፈጸም የታቀደውን ምርጫ ለማካሄድ የሞራል ልዕልናም ሆነ ብቃት የሌለው በመሆኑ፣ እኔ በማስተዳድረው በትግራይ ክልል ውስጥ የራሴን ምርጫ በራሴ ለማከናወን ዝግጅት በማድረግ ላይ ነኝ፤” ሲል ድፍረት የተመላበት አዲስ መግለጫ አውጥቷል፡፡ እንዲያውም ይህንኑ ፈለግ ይከተሉ ዘንድም ወዳጆቼ ናቸው ለሚላቸውና ኅብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ኃይሎች እያለ በቁልምጫ ለሚጠራቸው አካላት፣ በማናለብኝነት የድረሱልኝ አይሉት የደግፉኝ ጥሪውን ጨምሮ አሰምቷል፡፡

ወደ መዲናችን ጎራ ባለ ቁጥር “ስድስተኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ ሁሉን ባሳተፈና ሕገ መንግሥቱ ባስቀመጠው አኳኋን ሊካሄድ እንጂ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሰበብ ሆኖ በአንድ ቀን እንኳ ሊራዘም አይገባም፤” በማለት የነጠረ አቋም ሲያራምድ የባጀው ጉጅሌ ወደ መቀሌ ሲመለስ ግን፣ “ብትወዱም ባትወዱም ምርጫውን በግሌ ለማካሄድ እየተዘጋጀሁ ነው፤” ሲል የበዛ ድንፋታ ዘግይቶ ሲያስተጋባ መደመጡ የተገለባባጭነቱን ልማድ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡ በእርግጥ ይህ ቡድን ሳያስበው ከማዕከላዊ መንግሥቱ መንበረ ሥልጣን ተባሮ መቆየቱ ጤንነቱን ክፉኛ ስላወከው፣ ‘የሁለት ሰባት ፀበል’ እንደሚያስፈልገው ከታወቀ ውሎ አድሯል፡፡

እንግዲህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መቀሌ ላይ በሚጠቀስበት ጊዜ በተለየ ሁኔታ ሲተረጎም የምንሰማለት ያው የፈረደበት ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 102 ንዑስ አንቀጽ (1) ሥር፣ በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ በአንድና በተመሳሳይ ጊዜ የሚካሄዱ ምርጫዎች ሊደራጁና ሊስተናገዱ የሚችሉትና የሚገባቸውም በአንድ ገለልተኛ ተቋም (እሱም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑ ነው)፣ አማካይነት ብቻ እንደሆነ በማያሻማ አኳኋን ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ‘አፈር ድሜ በላ’ ማለት እኮ ነው፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 ንዑስ አንቀጽ 9 (1) እንደሚከተለው ይደነግጋል፡፡ “በፌደራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲያካሂድ ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል”፡፡ በንዑስ አንቀጽ (2) ሥር ደግሞ እንዲህ ተጽፏል፡፡ “የቦርዱ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፤”፡ይላል፡፡

በእርግጥ ቀጪና ተቆጪ አካልና ተጠያቂነትን ያለ አድልዎ በሥራ ላይ የሚያውል ሥርዓት ሥር ሰዶ ባልተተከለበት አገር ይህ ዓይነቱ መረን የለቀቀ ዕርምጃ ገና ከመነሻው ሊታይና መቋጫ ሊበጅለት በተገባ ነበር፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ምንም በጥሬ ንዋይ ደሃ ብትሆንም፣ ትልቅና የባለ ብዙ እሴቶች ሀብት ክምችት ባለቤት የሆነች አገር ናት፡፡ ስለሆነም ይህ ዓይነቱ ከመስመር የወጣ ሥርዓተ አልበኝነት ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የምናደርገውን ርብርብ ማደናቀፍ የለበትም፡፡

ያልተቀደሰው የፖለቲካ ጉድኝት

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገዳቢነት ሳቢያ ብዙዎቹን ሳንታደምባቸው ቀረን እንጂ፣ በክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ወገኖቻችን ዘንድ ገናና ሥፍራ የሚሰጠውን በዓለ ትንሳዔ ተከትሎ ሰሞኑን አያሌ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶችን በየሠፈሩና በየጎራው እየታዘብን ነው፡፡ በወጉ ተዋውቀው ለአብሮነት መተጫጨታቸውን እንኳ ገና በቅጡ ሳንሰማው የቀድሞው የኢዴፓ ሊቀመንበርና ኢትዮጵያዊ ዜግነቱ እንኳ በቅጡ ተጣርቶ ዕልባት ከማግኘቱ በፊት የአገሪቱ ሕግ ከሚፈቅደው አሠራር ውጪ የኦፌኮ ኣባል ሆኖ እንደተ መዘገበ የሚነገርለት ስም አይጠሬው ፖለቲከኛ፣ ወደውና ፈቅደው በፖለቲካ ሕይወት እስከ ወዲያኛው ሊጣመሩ የወሰኑ በሚመስል አቀራረብ የቀለበት ሥነ ሥርዓት እንደፈጸሙ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ አሳየን አይደል?

አንደኛው ወንድማችን በአንድ ወቅት ጤፍ በሚቆላው አንደበቱ የሕዝብ ቀልብ ስቦ  እንቡር እንቡር ሲል ከታየና አያሌ ተከታዮችን ካፈራ በኋላ ድንገት ማርሽ በመቀየሩ ምክንያት፣ ለሕወሓት ከማደሩና የኋሊት ከመንሸራተቱ የተነሳ ለተራዘመ ጊዜ በአልጋ ላይ የዋለ የፖለቲካ መፃጉዕ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በተቋምም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ከሳሽም ሆነ መርማሪ በማጣቱ ብቻ ለግልጽ የዳኝነት ችሎት ቀርቦ ‘ያልተፈረደበት የአደባባይ ወንጀለኛ’ ነው፡፡

እነዚህ ጥንዶች የቀድሞ ባላንጣነታቸው ቀርቶ ሰሞኑን ባልተጠበቀ ሁኔታ ያልተቀደሰ ጉድኝት ፈጥረው፣ “በሥልጣን ላይ ያለው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ መዋዕለ ዘመኑ ስለሚያበቃና ቅቡልነቱን ስለሚያጣ፣ የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊትም ሆነ የፖሊስና የደኅንነት ኃይሎች እንኳ ሊታዘዙለት አይገባም” እያሉ የአገሪቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሳይቀር በአደባባይ ሲያስጠነቅቁና ሲያንጓጥጡ ታይተዋል፣ ተደምጠዋልም፡፡ ‘ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም’ አሉ እማማ ከበቡሽ?

“ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ በዚህ አገር ሁላችንም እኩል ስለምንሆን ጋባዥና ተጋባዥ አይኖርም” ሲል ነበር ያለው አንደኛው ግለሰብ ይህንኑ የተሳከረ አቋማቸውን በተጨማሪ ሲያብራራ፡፡ ተጣማሪው በፊናው፣ “እኛም ዜጎች በመሆናችን በጋራ የመወሰን መብት ያለን ሲሆን፣ ከጀርባችን የምንወክለው ሕዝብም አለ” ሲል በኃይለኛው ተመፃድቋል፡፡ መቼም እነዚህ ሁለት ወንድሞቻችን ያላቸው እብሪት አይጣል ነው ወገኖቼ። ገና መመረጣቸውን እንኳ ሳያውቁ የሚወክሉት ሕዝብ ከጀርባ እንዳለ በልበ ሙሉነት ሲናገሩ በጣሙን ያስገርማል፡፡

በመጨረሻም ለታክቲክ ያህል እንደ ተጣመሩ ሁኔታው በግልጽ የሚያሳብቅባቸው እነዚህ ሁለት ግለሰቦች የተከበረው ሙያ የፖለቲካ ሳይንስ ጠቢባን እንጂ፣ ቢያንስ የሕግ ሙያተኞች እንዳልሆኑ ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ ሆኖም ያለ ሙያቸው ገብተው በመፈትፈት የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች በጥሬው ሊተረጉሙልን ሲቃጣቸው አስተውለናል፡፡

ለምሳሌ አንደኛው ግለሰብ ተጋግሎ ሲካሄድ በነበረው በዚያ የሚዲያ ውይይታቸው መሀል፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ (3) ሥር የሰፈረውንና “በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥትን ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው” የሚለውን ድንጋጌ አዛብቶ ለባልንጀራው ለማብራራት ሲውተረተር መመልከቱ አስተዛዛቢ ነበር፡፡

እርግጥ ነው “በተጭበረበረ ምርጫ ወይም ሕገ መንግሥቱ ከሚደነግገው አሠራር ባፈነገጠ መንገድ የመንግሥትን ሥልጣን መያዝ አይቻልም”፡፡ ይህ ግን በሥራ ላይ ያለው የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የአገልግሎት ዘመን ከመጠናቀቁ አንድ ወር አስቀድሞ ተተኪውን ምክር ቤት ለመምረጥና ሥልጣነ መንግሥቱን ለማስቀጠል የማያስችል፣ እንዲሁም ከአቅም በላይ የሆነ ዕክል መፈጠሩ ሲረጋገጥ የምርጫው ጊዜ የሚራዘምበትን የመፍትሔ ፍለጋ ጥረት ጭምር ሕገወጥና ኢሕገ መንግሥታዊ እስከ ማድረግ ያላግባብ ተለጥጦ የሚተረጎም ድንጋጌ አይደለም፡፡

እንዲያ ሆኖ ሳለ ታዲያ የተጠቀሰው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የሚፈጸምበትን ሽፋን፣ ሰውየው በራሱ ጊዜ ያላግባብ ሲያስፋፋው ወይም ሲቀይረው ‘ለምን’ ብሎ የገሰፀው ተገዳዳሪ በሥፍራው አልነበረም፡፡

አበቃሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋከልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...