በዳዊት ታዬ
የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመታደግ ባንኮች ድጋፋቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እናት ባንክም ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ደንበኞቹ የሦስት ወራት የብድር ወለድ መሰረዙን አስታውቋል፡፡ በሌሎች አገልግሎቶች ላይ የሚታሰቡ ክፍያዎችንም አንስቷል፡፡
እናት ባንክ የወለድ ዕዳ የሰረዘበት የብድር መጠን 100 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የዕዳ ስረዛ በማድረጉ ምክንያት ከ6.5 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ገቢ እንደሚያጣ አስታውቋል፡፡
ባንኩ ግንቦት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳስታወቀው፣ ከወረርሽኙ መከሰት ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ ጉዳቶች ድጋፍ ለማድረግ፣ በተለይም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ደንበኞቹ ያጋጠማቸውን ጫና በመመልከት፣ ለሦስት ተከታታይ ወራት እንዲከፈል ይጠበቅ በነበረ የብድር ዕዳ ላይ ወለዱን እንደሰረዘላቸው አስታውቋል፡፡
የብድር ዕዳቸው መክፈል ከሚጠበቅባቸው ጊዜ አስቀድመው በሚከፍሉ ደንበኞች ላይ ይጣል የነበረውን ቅጣትም ሙሉ በሙሉ እንደሰረዘው የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ተሾመ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር፣ ባንኩ ለተለያዩ አገልግሎቶች ያስከፍል የነበረውን ክፍያ እንደሰረዘ ገልጸዋል፡፡ በባንኩ መረጃ መሠረት፣ የብድር ማራዘሚያ ላይ ይከፈል የነበረው የአገልግሎት ክፍያ ሙሉ በሙሉ የተሰረዘ ሲሆን፣ የኦቨር ድራፍት አገልግሎት ይታሰብ የነበረው ክፍያም መነሳቱ ታውቋል፡፡
ውዝፍ የብድር ዕዳቸውን አዘግይተው በሚከፍሉ ተበዳሪዎች ላይ ይጣል የነበረው ቅጣትም እንዲሁ መነሳቱን አቶ ወንድወሰን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተቀመጠው የብድር አከፋፈል ሥርዓት ብድራቸውን በኮሮና ቫይረስ ጫና ምክንያት በአግባቡ መክፈል ያልቻሉ ደንበኞችም አስተያየት ተደርጎላቸዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት መስክ፣ አስመጪዎች ዕቃ ወደ አገር ለማስገባት ለከፈቱት ሌተር ኦፍ ክሬዲት (L/C) በዓለም በተፈጠረው የኮሮና ቀውስ ምክንያት፣ አስቀድመው ለማራዘሚያ ይጠየቁ የነበሩ የአገልግሎት ክፍያዎች ሙሉ ለሙሉ እንዲቀሩ ተደርጓል፡፡ ኮሮናን ለመከላከል የሚውሉና ተዛማጅነት ያላቸውን ዕቃዎች ለሚያስመጡም ባንኩ የ50 በመቶ የአገልግሎትና የኮሚሽን ክፍያ ቀንሷል፡፡
የማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ እናት ባንክ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶችን በመደገፍ ለብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሁለት ሚሊዮን ብር አበርክቷል፡፡
የባንኩ ሠራተኞችም ራሳቸውን ከተጋላጭነት ለመጠበቅ እንዲያስችላቸው በሁሉም ቅርንጫፎቹና በዋናው ቢሮ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ፣ የእጅ ጓንት፣ የንፅህና መጠበቂያ ሳኒቲሳይዘር፣ አልኮልና ፈሳሽ ሳሙና እያቀረበ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በሁሉም ቅርንጫፎች የእጅ መታጠቢያ ውኃና ሳሙና በማቅረብ ደንበኞች ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲስተናገዱ የሚያስችል የአሠራር ሒደት ዘርግቷል፡፡ በተጨማሪም በዋናው ቢሮና በሁሉም ቅርንጫፎች ያሉ ሠራተኞች የባንኩን ሥራ በማይጎዳ መልኩ በፈረቃ እንዲሠሩ፣ ሁሉም ነፍሰ ጡር ሴቶች ቤታቸው እንዲቆዩ በማድረግ ንክኪዎችን በማስቀረት የበሽታውን ሥርጭት በመቀነስ ሥራ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡
ስለ ኮሮና ቫይረስ የግንዛቤ ማሰጨበጫ ሥራዎችን ለማጎልበት በባንኩ ቅርንጫፎች ቪዲዮዎች ተዘጋጅተው ደንበኞች ሊመለከቱት በሚያመች መልኩ በመተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ንክኪዎችን ለመቀነስ ደንበኞች ከኤቲኤም ማሽኖች በክፍያ ካርድ በአንድ ቀን እስከ አሥር ሺሕ ብር ድረስ ወጪ ማድረግ እንዲችሉ ተደርጓል፡፡
በአጠቃላይ እናት ባንክ እንደ ስምምነት ባህርያትን በመላበስ ይህን ፈታኝ ወቅት ከደንበኞቹ፣ ከማኅበረሰቡ ብሎም ከመንግሥት ጋር በመደጋገፍ መታለፍ እንዳለበት በመገንዘብ ወደፊትም የተደረጉትን ማሻሻያዎች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል፡፡ ‹‹ኢኮኖሚው ሲጎዳ የእኛም ባንክ መጎዳቱ አይቀርም ያሉት አቶ ወንድወሰን፣ ‹‹የህልውና ጉዳይ ስለሆነ፣ የወቅቱን ችግር በመመልከት ዕቅዳችንን ከልሰን እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ባንኩ እንዲህ ያለውን ዕርምጃዎች የወሰደው ወረርሽኙ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ከግምት በማስገባትና በደንበኞቹ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ በወሰነው ውሳኔ መሠረት ነው፡፡