Wednesday, June 12, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የመዝጋት ምክረ ሐሳብ በኮሮና ወረርሽኝ ከበባ ሥር ላለችው ኢትዮጵያ

በዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ

ኢትዮጵያ ሰውና ተፈጥሮ አመጣሽ አደጋዎችን ለመቋቋም የሚረዳ ተቋማዊ አቅም በመገንባት ረገድ ፈር ቀዳጅ ነች፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ በርካታ አገሮች ተላላፊ በሽታዎችንና ወረርሽኞችን ጨምሮ የተለያዩ አደጋዎችን የመቋቋም አቅማቸውን ለማደራጀት ኢትዮጵያን እንደ አርዓያ ይወስዱ ነበር፡፡ ይህ አቅም በቅድሚያ የተደራጀው በ1966 ዓ.ም. የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን (ዕማማኮ) ነበር፡፡ እናም፣ ከእዚያ በኋላ በተከታታይ በተደረጉ ለውጦች ሥር አልፋ ኢትዮጵያ፣ ሰፊና በጣም ውስብስብ የሆኑትን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተራድኦ ሥራዎችን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለመምራት ችላ ነበር፡፡ መላው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን እንደስኬታማ ታሪክ ቆጥሮ ሲያነሳሳው ነበር፡፡ ስለዚህም ሥራ በርካታ መጻሕፍት ተጽፈዋል፡፡ ምሥራቁንና ምዕራቡን፣ እንዲሁም ቀሪውን ዓለም በጋራ ያቀራረበ ዓለም አቀፍ ጥረት ተደርጓል፡፡

በወቅቱ ዓለም በከባድ ድርቅ፣ በማያባራ ጦርነትና የምግብና የመሠረተ ልማት እጥረት ወደ ተጠቃችው ኢትዮጵያ ትኩረት ያደረገበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ ለዓለም የማንቂያ ደወል ያቃጨለበትም ጊዜ ነበር፡፡ አውሮፓና አሜሪካ የራሳቸው የአደጋ ቁጥጥር ሥርዓት ያላቸው ቢሆንም፣ በዚያ ልክ ከድንበራቸው ውጭ ለተከሰተ ሰብዓዊ ቀውስ የሰጡት ምላሽ በደካማ ዝግጁነት የታጠረ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ፣ ከዚህ አሳዛኝ ሁኔታና ሌሎች ልምዶች ብቻ በመማር የዓለም አቀፍ የምላሽ አሰጣጥ አቅማቸውን እንደ አዲስ በማዋቀር ጉልህ ለውጦችን አድርገዋል፡፡ ይህ አጋጣሚ የአደጋ ሥራ አመራር ትምህርት ወደ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ካሪኩለም እንዲካተት አስደርጓል፡፡ የአደጋ ሥራ አመራር ትምህርት እስከ 1986 ድረስ በትምህርት ቤቶች አይሰጥም ነበር፡፡ እኔው ራሴ በቀጥታ ስለሥጋትና አደጋ የሥራ አመራር በርካታ የአፍሪካ አገሮችም አማክሬአለሁ፣ በአንዳንድ አጋጣሚዎችም ለሰብዓዊ ቀውሶች ምላሽ በመስጠቱ ጥረት ውስጥም እንዲሁ ተሳትፌአለሁ፡፡

ፖለቲካው እንዳለ ሆኖ፣ ኢትዮጵያ እንደ (ኮቪድ-19) ያለ ግዙፍ ቀውስ  ምንም እንኳ የተለየና በሁሉም አካባቢ የተከሰተ ቢሆንም ለመቆጣጠር ተቋሙ፣ ልምዱና ዕውቀቱ ነበራት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ተቋም ፖለቲካዊ ፍረጃ ተደርጎበት፣ ዕማማኮን መደገፍና ማወደስ የመንግሥቱን አስተዳደር እንደማመሥገን ተደርጎ ሲቆጠር ነበር፣ ኮሚሽኑ ከመንግሥት ገለልተኛ በሆነ አኳኋን ሲመራ ቢቆይም፡፡ እንዲህ እንዲመራ የተደረገው ባሉ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታዎችና በቀውሱ ዓለም አቀፋዊነት ምክንያት ነበር (በእኔ የተደረሰውን ‹‹የደም ዕንባ›› መጽሐፍ፣ በተለይም ስለዚህ ሥራ የሚተርከውን ክፍል ይመለከቷል)፡፡ ቆይቶ ሥልጣን የያዘው መንግሥት (ሕወሓት) የዚህን ተቋም ስኬት አንስቶ ለማመስገን ባለመፈለግ፣ በርካታ አገሮች በአርዓያነት ወስደው የተጠቀሙበትን ተቋም ወደ ማፍረሱ አዝማሚያ አምርቷል፡፡

ከዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን (ዕማማኮ) ጋር በቅርበት ሲሠራ የነበረው፣ የአሜሪካ የፌዴራል የአደጋ ሥራ አመራር ኤጀንሲ ልክ እንደ አሁኑ የኮሮና ቀውስ ጊዜ ያሉ የቀውስ ወቅቶች በሚያጋጥሙ ጊዜ የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡ የእኛው ኮሚሽን የተቋቋመው ለዚሁ ዓላማ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሰልጥነው በታሪካችን ውስጥ በነበሩ አስቸጋሪ ወቅቶች በፊት መስመር ተሠልፈው እንደነበር ያለፈ ታሪካቸው ያረጋግጣል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ውስጥ በአያሌው ተጋላጭ ከሆኑ አገሮች መካከል አንዷ ነች፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደ ድርቅ፣ ግጭት፣ ስደት፣ የአገር ውስጥ መፈናቀል፣ ጎርፎች፣ የሰብል በተባይ መጠቃት፣ ተላላፊ በሽታዎችና የአካባቢ ሥነ ምኅዳር መሸርሸር የመሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን አስተናግዳለች፡፡ የኢትዮጵያ የአደጋ ሁናቴ ከድህነት፣ ከተጎዳ የአካባቢ ሥነ ምኅዳርና በአፍሪካ ቀንድ ላለፉት 30 እና 50 ዓመታት ከተደረጉ ጦርነቶችና ግጭቶች የመነጨ ነው፡፡ የሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ድምር ውጤት ሕዝባችንን በእጅጉ እንዲቸገር አድርጓል፡፡

እንደ ተላላፊ በሽታዎችና ወረርሽኞች ያሉ ቀውሶች ራሳቸውን ችለው አደጋ አይፈጥሩም፡፡ አደጋዎችን የሚፈጥረው ዋናው ምክንያት ሕዝቦችና መንግሥታት ለተጋላጭነቱ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት አለመቻላቸው ነው፡፡ የአደጋዎችና ተጋላጭነት ጥምርታ በማንኛውም የሥጋት ‹‹ቢሆን›› እንደቀረበው፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ በጊዜ ሒደት የሚፈጠር ነው፡፡ የአደጋን ሥጋት ቅርፅ የሚወስኑት ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና መንግሥታት ናቸው፡፡ የእነርሱ ዕርምጃዎችና ግንኙነቶች የቀውሱን የጉዳት ልክና የአደጋውን ሥጋት ጭማሪ ለማወቅ ይረዳል፡፡

ሕዝቦችና መንግሥታት ምንጊዜም ስለግላቸው አበርክቶ የተገኙ ውጤቶችን ከተመለከቱ በኋላ መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሌም እንዲህ እላለሁ፣ ‹‹መሪዎች ብሔራዊ ቀውስን ለመቆጣጠር በአግባቡና በሰዓቱ ምላሽ መስጠት መቻል አለባቸው፡፡ አሁን ባለው መዋቅርና ሥርዓት መረጃ በሚያቀብላቸው ሕዝብ ላይ በቂ ትምምን ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህም ማለት በደንብ የተደራጀ፣ የታጠቀ ቅንጁ መዋቅር በአመራር እርከን ውስጥ ካለ ከበቂ የአማራጮች ክምችትና የገንዘብና ቁሳቁሶች ጋር የሚሠራ፣ የአስተዳደራዊ አካሄዱ በአግባቡና በልክ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መሆን አለበት፡፡››

በዚህ ጊዜ፣ ኢትዮጵያና በእርግጥም ዓለም በቅርቡ የዓለም ታሪክ ካጋጠሙ እጅግ ከባድ ወረርሽኞች በአንዱ እየተፈተኑ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና አጀንዳ ፖሊሲዎችን መቅረፅና ሰዋዊና ተቋማዊ አቅም ለመገንባት፣ እንዲሁም ለማቀድና የተጠናከረ ምላሽ ለመስጠት የሚረዱ አግባብነት ያላቸው ጥረቶች በሰፊው ማድረግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዚህ ምላሽ ለመዘጋጀት ወሳኝ ጊዜ አላት፡፡ ጊዜ በራሱ ዛቢያ ላይ ቢኖርም፣ ነገር ግን ሌላ ጭማሪ የለውም፡፡ አሁን ጊዜው እያለቀ፣ ምናልባትም ለሚሊዮኖች ለመድረስ ዘግይተንም ሊሆን ይችላል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ስለቀውሱ ለመጀመርያ ጊዜ ባስታወቀበት ወቅት፣ መንግሥት ስላደረገው ዝግጅት በበቂ መልኩ አይታወቅም፡፡ መጋቢት 1 ቀን የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መሆኑን ባወጀበት ጊዜ፣ በመላው ዓለም በሚገኙ 110 አገሮችና ግዛቶች ከ118,000 በላይ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች የተመዘገቡበት፣ ከዚህ በበለጠ በዓለም ላይ የመዛመት ዘለቄታዊ ሥጋት ያሳደረ በሽታ ሆኗል፡፡

ዝግጁነት ማለት በቅድሚያ የሚከወን የማቀድና አቅም የመገንባት ሒደት ነው፡፡ በርከት ያሉ እንቅስቃሴዎች በውስጡ ይካተቱበታል፡፡ ዋነኞቹ ግብዓቶች፣

  • ተቋማዊና ፖሊሲያዊ አውታር
  • ቅድመ ማስጠንቀቂያ
  • የመረጃና የተግባቦት (ኮሙዩኒኬሽን) መዋቅር
  • የሀብት ክምችት
  • የምላሽ አሰጣጥ ሥነ ዘዴ

ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ሦስቱ ግብዓቶች አሏት፡፡ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ በሚያጋጥሙ የተለዩ ፈተናዎች የሚታወቁ ሲሆን፣ ነገር ግን የማስተባበሪያና የምላሽ አሰጣጥ መዋቅሮች ከ1966 ዓ.ም. አንስቶ የነበሩ ናቸው፡፡ በዚህ ሰዓት፣ እንደ ዕርዳታና የመልሶ ማቋቋም ኮሚሽን ያለ፣ ነፃ ለማንም ያልወገነ ድርጅት በደንብ ከተጠኑ ተፈጻሚ የሚሆኑ አማራጮች፣ መዘጋትን ካካተተ ጋር መንግሥትን ሊወክል ይገባል፡፡ ይህንን ሚና የሚጫወት ተቋም ከሌለ ደግሞ፣ ጎምቱና ችሎታ ያላቸው ሰዎች (ፖለቲከኞችን አይደለም) ያቀፈ፣ ባለሙያዎችንም እንዲሁ የያዘ ብሔራዊ ግብረ ኃይል መቋቋም አለበት፡፡

አፍሪካ በቅድሚያ የተገመተውን ያህል አልተጠቃችም፡፡ ከቅድመ ትንበያዎቹ በራቀና በተቃረነ መጠን፣ የታማሚዎቹና የሟቾቹ የቁጥር ማዕበል እስካሁን አልገጠመም፡፡ ‹‹ትንሽ ለየት ያለ ሁኔታ ነው፡፡ ያስፈራል፡፡ ማንም ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት እርግጠኛ አይደለም፤›› ይላሉ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ የሚኖሩ የተላላፊ በሽታዎች ስፔሻሊስት ኤቫን ሾውል (ዶ/ር) ፡፡ በመላ አኅጉሪቱ የሚገኙ በርካታ ዶክተሮች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ ‹‹በርካታ ሰዎችን በመረመርን ቁጥር፣ እውነት አለመሆኑንና መሆኑን በደንብ ልናረጋግጥ እንችላለን. . . ብዬ አስባለሁ፡፡ ቁጥሮቹ ግን የሉም፡፡››

በአፍሪካ ሁኔታ ላይ አትኩረው፣ ከዓለም ጤና ድርጅት ፕሪሺየስ ማቶትስ ይናገራሉ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ስላለው የቫይረሱ ሥርጭት ጠቅላላ ድምዳሜ የሚሰጥበት ኃላፊነት የጎደለው ያልተገባ አካሄድ አለ፡፡ ሰዎች በተገደበው የቀደመ መረጃ ተንተርሰው መዘናጋት የለባቸውም፡፡ ሁላችንም መጠንቀቅና ሊደረግ የሚገባውንም ነገር ማድረግ አለብን፡፡

መዘጋት

መዘጋት ማለት የድንገተኛ አደጋ ሥነ ሥርዓት ሲሆን፣ ሰዎች ከቤታቸውና መኖሪያ ሥፍራቸው ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ ይከለክላል፡፡ ሙሉ በሙሉ መዘጋት ባሉበት እንዲቀመጡና ከሕንፃ ወይም ሌላ ቦታ እንዳይወጡ ወይም እንዳይገቡ ሊያስገድድ ይችላል፡፡ በዓለም ጤና ድርጅትና በበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል መረጃ ላይ ብንመረኮዝ፣ እንደኢትዮጵያ ላሉ አገሮች የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመግታት ከመዘጋት የተሻለ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ግለሰቦች ጤነኛ ሆነው እንዲዘልቁና የሥርጭት ሰንሰለቱ እንዲበጠስ፣ ከፅኑ አካላዊ መራራቅ የተሻለ መንገድ የለም፡፡ በጣም ተጋላጭ የሆኑ ሕዝቦች ይህንን ወረርሽኝ ተቋቁመው እንዲያልፉት በደንብ ያግዛል፡፡

መንግሥት መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

ነገር ግን እንዴት መዘጋቱ በትክክለኛ ሁኔታ ሊሠራ ይችላል? ለምን ወጣትና ጤናማ ለሆኑ ሰዎች፣ ያውም በጠና ለበሽታው የመጋለጣቸው መጠን አናሳ ሆኖ ሳለ፣ በቻሉት መጠን ቤታቸው መቀመጣቸው አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ? ዛሬ ኃላፊነት የሚሰማቸው መሪዎች ሊያነቧቸው የሚገቡ፣ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተጻፉ በርካታ ጽሑፎች አሉ!!! ለመሪዎች አለማወቅ ስርየት የሌለው ጥፋት ሲሆን፣ በእውነትም የወንጀል ባህሪ የሚንፀባረቅበት ባህሪ ነው፡፡ የመዘጋት ግብ ማለዘብና ጫና መጨመር ነው፡፡

መዘጋትን በተገበሩ አገሮችና የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ፣ ምንም እንኳ መዘጋቱ ጎጂ ቢሆንም፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሚገኙ በሚሊዮናት ለሚቆጠሩ ዜጎች በሚገባ ሠርቷል፡፡ ከማንኛውም መዘጋትና አካላዊ ርቀት ልናገኘው የምንችለው ከፍተኛ የታማሚና የሟች ቁጥር ብቻ ነው፡፡ በርካታ አገሮች ደካማ የጤና ሥርዓትና የመኖሪያ ቤት አልቦ የሆኑ ሥራ አጥ ዜጎች ለሚገኙባት አፍሪካ፣ (የኮቪድ-19) የዘገየ አመጣጥ ለዝግጁነት በርካታ አስፈላጊ ጊዜን አምጥቷል፡፡ በዓለም ጤና ድርጅትና የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ትብብር፣ አሁን ኢትዮጵያ የመረሩ፣ ግን አስፈላጊ የሆኑ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ እያሰበች ነው፡፡ ጊዜ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ እናም፣ በሽታውን ለመከላከል አጣዳፊ ዕርምጃ መውሰድ ወሳኝ ዓላማ መሆን ይኖርበታል፡፡

በይፋ በሚገኘው መረጃ ብንመሠረት እንኳ፣ አገሪቱ ውስጥ ባሉ ከተሞች ላይ ትኩረት ተደርጎ፣ የቫይረሱን ሥርጭት ለግለሰብና የሚያመጣውንም ጉዳት ለመከላከል ሳምንታትን የሚያስቆጥር መዘጋትን ከመተግበር በስተቀር አማራጭ የለም፡፡ ይህም ማለት በማኅበረ ፖለቲካና ፀጥታ ችግሮች ምክንያት የበርካታ ሚሊዮናትን ሕይወት ልናጣ እንችላለን፡፡ ወደ መዘጋቱ ውስጥ ለመግባት በዋናነት ሁለት ዕርከኖች አሉ፡፡

ዕርከን አንድ፡-

ከኢትዮጵያና ዳያስፖራው ማኅበረሰብ የተውጣጡ በበርካታ ዘርፎች ልምድ ያላቸው ሰዎችና ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ፣ መንግሥትን በማማከር ኢትዮጵያ ውስጥ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ መዘጋት ጋር የተያያዘ የአዋጭነት ጥናት ያድርግ፣ እንዲሁም እንዴት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ይጠይቅ ዘንድ መቋቋም አለበት፡፡ ምክረ ሐሳቡ ለመንግሥት ይቀርባል፡፡ መንግሥትም በበኩሉ ዕርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ በፊት ተግባራዊ አድርጎት ሊሆን ቢችልም፣ ተግባራዊ ካላደረገው ግን ወዲያውኑ መተግበር አለበት፡፡ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” ተብሎ የሚጠራው፣ ሚያዝያ 11 ቀም 2012 ዓ.ም. ላይ የታወጀው አዋጅ ድንጋጤ የሰፈነበት ምላሽ ሲሆን፣ (ኮቪድ-19) የሚያመጣቸውን ችግሮች አንዱንም የሚቀርፍ አይደለም፡፡ እዚህ አዋጅ ላይ አስተያየት መስጠት ትርጉም የለውም፡፡

ዕርከን ሁለት፡-

ይህ የአሠራር ሁኔታ የፈጠራ ሐሳቦች ያስፈልጉታል፡፡ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ የተሰጠው ምክረ ሐሳብ እንደተጠናቀቀ፣ በምዕራፍ የተከፈለ መዘጋት ተቀባይነትን ያገኛል፡፡ መንግሥት በሕግ መሠረት፣ ወታደርን፣ ፖሊስን፣ የክልል ሚሊሺያዎችን፣ የማኅበረሰብ ጤና መኮንኖችን፣ የተዛማች በሽታዎች ባለሙያዎችን፣ የአደጋና ሥጋት ሥራ አመራር ባለሙያዎችን፣ የሎጅስቲክስ ባለሙያዎችን፣ የአቅርቦት ሰንሰለት ሥራ አመራር ባለሙያዎች፣ የማኅበራዊ ሥራ ባለሙያዎች፣ የሥነ ምግብ ባለሙያዎችና ከንቲባዎች፣ ሲቪል ኢንጂነሮች፣ እንዲሁም በየክልሉና የብሔር ጎራዎች የሚገኙ፣ የተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ያሉ ሰዎች የተካተቱበት፣ በሙሉ ኃላፊነትና ሥልጣን አፈጻጸሙን የሚከታተል ብሔራዊ ግብረ ኃይል ማቋቋም ይጠበቅበታል፡፡ ዕቅዱ ከከባዶቹ ሥራዎች መካከል አንዱን፣ ሁሉንም ሰዎች ከዚህ በታች በቀረቡ ሦስት ጎራዎች ለይቶ መመዝገብን ያካተተ ሲሆን፣ ክፍት ቦታዎችን ለድንኳንና መጠለያዎች መለየት ትምህርት ቤቶችን፣ ባዶ ወይም ሥራ ያልጀመሩ ሕንፃዎችን መለየት፣ መጠለያዎችን መሥራት፣ ወደ መጠለያዎቹ ለተዘዋወሩ ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማቅረብ፣ ለምሳሌ ብርድ ልብሶችን፣ ምንጣፎችን፣ የሕክምና አገልግሎቶችን፣ የውኃ ታንከሮችን፣ የምግብ ማብሰያዎች፣ ለዚህ ሥራ የሚያገለግሉ ሠራተኞች፣ ሰዎችን ማጓጓዝና ለቁሳቁስና ምግብ አቅርቦቶች ዓለም አቀፍ የድጋፍ ጥሪ ማድረግ. . . ወዘተ. ደግሞ የተቀሩት ሥራዎች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የመዘጋቱ ዋነኛ አትኩሮት ማረፍ ያለበት እዚህ የሕዝቡ ክፋይ በተለይም የከተማ አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ ላይ መሆን አለበት፡፡ ገቢዎች ያሏቸውና መጠለያዎች ሰዎች በመንግሥት የፀደቁትንና ተግባራዊ የተደረጉትን የመዘጋት ግዴታዎችን የሚጥሱ ከሆነ፣ በጣም አስቸጋሪው ግዴታ፣ እናም የግብረ ኃይሉ ሙሉ ትኩረት ማረፍ ያለበት፣ በሦስት ጎራዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች ላይ ሊሆን ይገባል፡፡

  1. ለጊዜው በአሠሪዎቻቸው የደመወዝ ክፍያቸው ያልተቋረጠባቸው፣ ነገር ግን በተጨናነቁ የመኖሪያ ቤቶችና ቆሻሻማ አካባቢዎች የሚኖሩ፣
  2. ማንኛውንም የያዙትን ሥራ በማንኛውም ሰዓት ሊያጡ የሚችሉ፣ መኖሪያ ቤት የሌላቸው ወይም በቆሻሻማ አካባቢዎች የሚኖሩ፣ ለአብነት የጎዳና ዳር ነጋዴዎችን መጥቀስ ይቻላል፣
  3. ቤትም ገቢም የሌላቸው ቤት አልቦ ሰዎች ላይ . . . በመጀመርያ ደረጃ፣ በአሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ እስያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ባልተመጣጠነ ሁኔታ በቫይረሱ የሚጠቁትና በዚህም የሚሞቱት ደሃና የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች መሆናቸውን ማመን አለብን፡፡ እነዚህ ሰዎች ቤት ሳይኖራቸው፣ እንዲሁ ጎዳና ላይ ወይም ደሳሳ ድንኳኖቻቸው ውስጥ ወይም ደግሞ በተጨናነቀና በጋርዮሽ አኳኋን እየኖሩ እንዴት ራሳቸውን ሊያገልሉ ይችላሉ?

በርካታ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ኢንተርኔትን ማግኘትና መጠቀም ወይም የኢንተርኔትን አጠቃቀም አሳምረው በማያውቁበት ሁኔታ፣ እንዴት በመካነ ድር ሊማሩ ይችላሉ? ሌላ የመተዳደሪያ አማራጭ ሳይኖራቸው፣ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን መመገብ ሳይችሉ ሰዎች እንዴት ያለሥራ ሊቀመጡ ይችላሉ? በአሜሪካ፣ ለተከታታይ ትውልዶች ሲንከባለሉ የከረሙ፣ የአካባቢ ሥነ ምኅዳር፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ችግሮች በሽታው በጥቁር ማኅበረሰብ ውስጥ በጣም እንዲስፋፋ መንገድ መጥረጋቸውን ከዚህ እንደሚከተለው በአጭሩ መግለጽ ይቻላል፣ ‹‹ጥቁር ሰዎች ሳንባዎቻቸውንና የመከላከል አቅማቸውን በእጅጉ ለሚያዳክሙ ጠንቀኛ በሽታዎች ተጋላጭ ናቸው፣ ለምሳሌ ለአስም፣ ለልብ ሕመም፣ ለደም ግፊትና ለስኳር በሽታ ተጋልጠዋል፡፡ በሚልውኬ ከተማ፣ ጥቁር መሆን ማለት በቀላሉ ነጩ ከሚኖረው የመኖሪያ ዕድሜ በ14 ዓመታት የተቀነሰበት ሰው መሆን ማለት ነው፡፡››

እዚህ ሥራ ውስጥ እንዲህ ባሉ ሰዎች ላይ ያተኮሩ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከታች ጀምሮ፣ በገጠርና ከተማ የተለያዩ ድርጅቶች አሏት፡፡ በከተሞች፣ ቀበሌዎች ዕድሮችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወይም መደበኛ ማኅበራት ይገኛሉ፡፡ እነዚሁ ውጤታማ አጋሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ደግሞ፣ እንዲያውም በጣም የተደራጁ ማኅበራት ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የገዳ ሥርዓት፣ የገበሬ ማኅበራትና በርካታ አገር አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከሕዝቡ ጋር እየሠሩ ነው፡፡ የብሔራዊው ግብረ ኃይል ዋና አካላት መሆን ይችላሉ፡፡

ሙያና ልምድ ካላቸው በርካታ ሰዎች ጋር ውይይት ከተጀመረ፣ ብዙ ሐሳቦች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ሀብት ማሰባሰቡ በጣም ፈታኝ አይሆንም፡፡ የዓለም የምግብ ፕሮግራምን፣ የዓለም ሕፃናት አድን ድርጅትን፣ የዓለም ጤና ድርጅትና ወዳጅ አገሮችን መንግሥት ቢጠይቃቸው፣ የግብረ ኃይሉ አባል መሆን ይችላሉ፡፡ ይህ ዕውን እንዲሆን፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ዳያስፖራው ሙሉና ያልተቋረጠ ድጋፍ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ የምግብና ሌሎች አስፈላጊ ዕርዳታዎችን ለመለገስ ዝግጁ እንደሚሆኑ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቀጥተኛ የገንዘብ ዕገዛ መጠየቅ፣ ሥራው በሙስና እንዲጠረጠር ያደርጋል፡፡ ያላሰለሱ ጥረቶች መደረግ ያለባቸው የሚያስፈልጉንን ሁሉ በዓይነት እንዲገኙ መሆን አለበት፡፡ ፈታኙ ክፍል የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሀብቶችን በማሰባሰብ፣ በውጤታማ አካሄድ በመታገዝ የማከፋፈልና የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችን መስጠት ነው፡፡ ኃላፊነቱ የብሔራዊው ግብረ ኃይል ነው፡፡ ቀላል አይደለም!!! ነገር ግን መከወን ይቻላል፡፡

ማግለልና የግል ንፅህና፡-

የመጠለያና የምገባ ጉዳይ አንዴ ከተነሳ፣ እነዚህ ሰዎችና በአጠቃላይ ሕዝቡ ለመዘጋቱ መመርያዎች ማለትም ለግል ንፅህና፣ አካላዊ ርቀት ተገዥ መሆን አለበት፡፡ እናም፣ ታማሚዎች ተለይተው ሲታወቁ፣ ተገቢው ምርመራ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ በሌላ ቋንቋ፣ የመጠለያው አሠራር ሰዎች እጃቸውን እንዲታጠቡ፣ የግል ንፅህናቸውንም እንዲጠብቁ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ከሌላኛው ሰው ጋር ያላቸውን ርቀት እንዲጠብቁ ማስቻል አለበት፡፡ ይህ ሊፈጸም ካልቻለ፣ የተሠራው ሥራ ሁሉ መና ይቀራል ማለት ነው፡፡ ንፅህናን ለመጠበቅ የተመቻቸ አጋጣሚ ቢኖርም፣ መመርያዎችን የሚጥሱ ሰዎች መኖራቸው ግን አይቀርም፡፡ ስለዚህ የመቆጣጠር ሥራ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ይህ ሐሳብ ከሚቀጥለው ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው፡፡

ሕግና ደንብ፡-

እነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎች መሀል፣ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለተወሰነ ጊዜ የመዘጋት ውሳኔ ቢተላለፍ፣ በርካታ የፀጥታ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ሕገ ወጥ የሆኑ አካላት ዘረፋና የንብረት ውድሚያ በመጀመር፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብሔር አሠላለፍ ሁኔታና ፖለቲካዊ በሆነ ቀውስ ላይ በመጨመር አገሪቱን ሊያምሱ ይችላሉ፡፡ ይህ ብሔራዊ ጉዳይ ስለሆነ፣ ሕዝቡ የፖለቲካ ጨዋታ እንዲጫወት ሊፈቀድ አይገባም፡፡ መንግሥት ወሳኝ ዕርምጃዎችን መውሰድ ግድ ይለዋል፡፡ እንደገናም፣ መንግሥት ከሌሎች አገሮች ልምድ ሊቀስም ይገባል፣ ለምሳሌ ከኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳና ህንድ፡፡ አስፈጻሚዎች የችግሮች አንድ አካል እንዲሆኑ አንመኝም፡፡ ሥልጠናና ተጠያቂነት የዚህ ኃላፊነት ዋና ግብዓቶች ናቸው፡፡ በበርካታ ቁጥር የሚገመቱ ወንጀለኞች ከእስር ስለተለቀቁ፣ የእነርሱን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርና ወደ ድሮ የወንጀል ሥራቸው ስላለመመለሳቸው ማወቅ ስለማይቻል ለእነርሱ ልዩ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡

ነገሩን አቅልዬ ለማሳየት አልሞከርኩም፡፡ ውስብስብና ስሱ ቢሆንም፣ የቫይረሱን ሥርጭትና የሟቾችን ቁጥር ለመቀነስ ከዚህ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ መዘጋቱ በጥንቃቄ የታቀደና ወደ ላይም ወደ ጎንም የተቀናጀ መሆን አለበት፡፡ ለስህተቶች፣ ለስሁት አረዳዶች ወይም ለቅንጅት ጉድለት ቦታ መኖር የለበትም፡፡ የፖለቲካ ካድሬዎችና የአክቲቪስቶች ሥራ አይደለም፡፡ ይህ ሥራ የትጉህ፣ የርኅሩህ፣ የተማረ፣ ልምድ ያለውና የተነቃቃ ሕዝብ ሥራ ነው፡፡ የእያንዳንዱ ተቋምና ግለሰብ ኃላፊነት በግልጽ ተለይቶ መቀመጥና በሥልጣንና በሀብት ሊደግፍ ይገባል፡፡ በማዕከላዊ መንግሥቱ ወይም በክልል ባለሥልጣናት ሥራውን ፖለቲካዊ ልባስ ለማልበስ ጥረቶች ከተደረጉ፣ ሁሉም ነገር ሊደመሰስና ቫይረሱ ከፈጠረው አደጋ በላይ ትልቅ አደጋ ሊፈጠር ይችላል፡፡

መንግሥት በአፋጣኝ ሙሉ በሙሉ ተኩስ ማቆምና ያልተፈለጉ ግጭቶች ውስጥ ከመግባት ራሱን ማቀብ ያስፈልገዋል፡፡ ሁሉም የግጭቱ ተዋንያን ለተወሰነ ጊዜ ተኩስ ለመቆም መስማማት አለባቸው፡፡ ይህ ትልቁ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ በግጭቶች መሀል፣ እነዚህን የመሰሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎችን መሥራት አይቻልምና፡፡ ኢትዮጵያ ሕዝቡን ለጦርነትና ለሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች የማስተባበር ልምድ አላት፡፡ የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሸን (ዕማማኮ) በ1966 ዓ.ም. ከ110 በላይ የምገባ ማዕከላትንና መጠለያዎችን ከሦስት ሚሊዮን ለተሻገረው ሕዝብ ለመስጠት ተቋቋመ፡፡ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደጋፊነት፣ መጠለያ፣ ምግብና የሕክምና አገልግሎቶችን ለሁለት ዓመታት ሊያቀርብ ችሏል፡፡ በ1970 ዓ.ም. በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ወቅት፣ መንግሥት ከ300 በላይ ወጣቶችን ከመላ አገሪቱ በማሰባሰብ ለሦስት ወራት ወታደራዊ ሥልጠና በታጠቅ የጦር ሠፈር ሰጥቶ ለጦርነት አዘጋጅቷቸው ነበር፣ ሁሉንም ነገር በአራት ወራት ውስጥ አጠናቅቆ ማለት ነው፡፡

የአዲስ አበባ ሕዝብ ሥልጠናው በሚካሄድበት ጊዜ፣ ምልምሎችን ምግብ አዘጋጅቶ መግቧል፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ትብብር፣ ወራሪው ኃይል ሊደመሰስ ችሏል፡፡ እንደ ገና በ1974 እና 1977 ዓ.ም. መካከል ወቅት፣ የታወቀውን ረሃብን የማስወገድ ሥራ ዕማማኮ ካልተጠበቀ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትብብር ጋር በመላ ኢትዮጵያ የተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኘውን ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በመመገብና በመንከባከብ አከናውኗል፡፡ ሚሊዮኖች በቤታቸውና በመንደሮቻቸው ተረድተዋል፡፡ እነዚህ ልምዶች የእኛ ሕዝብ በቫይረሱ በጣም ለተጠቁና በመዘጋቱ ለተጎዱ ሰዎች ድጋፍ ለመስጠት ጥንካሬ፣ ልምድና አቅም እንዳለው ያሳያሉ፡፡ ለዚህ የሚያስፈልጉት ደግሞ አስተውሎት የተሞላባቸው ውሳኔዎችና አመራር ናቸው፡፡

መዘጋቶች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ጋር አብረው ይመጣሉ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች በራሳቸው ችግሮችን ሊፈቱ ከቶውኑ አይቻላቸውም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ለድንገተኛ አደጋ ሥራዎች የሚያመቹ አጋጣሚዎችን በመፍጠር፣ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ ያመቻቻል፡፡ ይህም ማለት መንግሥታት አስፈላጊ መፍትሔ የመሰላቸውን ሐሳብ ያለምንም ተጠያቂነት የመፈጸም ትልቅ ጉልበት ይኖራቸዋል፡፡

አምባገነን መሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽን መብት ለመርገጥ፣ የተቃዋሚ መሪዎችን ለማዋከብ፣ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ላይ ገደብ ለማስቀመጥና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ የሚያስገኙ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ለማገድ ይጠቀሙበታል፡፡ ይህ በበርካታ አገሮች የታየ ልምድ ነው፡፡ እንዲህ ባሉ ጊዜያት ሕዝቡ በአምላክ ምሕረት ሥር ሲኖር፣ መሪዎቹ ግን በሽታውን መልሶ ለማጥቃት ቸለልተኛ ይሆናሉ፡፡ መሪዎች ከበዛ ጥበብና ርህራሄ ጋር ሕዝቡን እንደሚመሩ፣ ሥልጣናቸውን አላግባብ ከመጠቀም እንደሚታቀቡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

መዘጋቶች ከምርመራ ጋር እኩል በእኩል መደረግ አለባቸው፣ የመዘጋቶች ውጤት ያለመጠነ ሰፊ ፈጣን ምርመራዎች ይቀንሳል፡፡ ምርመራ ለመከላከልና ቁጥጥር ቁልፍ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ወቅት ሕዝቡ ምርመራን እንደመታሰር እየቆጠረው ነው፡፡ ሕዝቡን ለማስተማር መመርመር መታሰር እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ለሕዝቡ ጥቅም ሲባል በክሊኒኮች ምርመራ እንደሚደረግ መነገር ይኖርበታል፡፡ ሕዝቡ ባልተጠበቁ ቦታዎች ሊታገት እንደሚችል በተሳሳተ መልኩ ስለሚነገረው፣ ከምርመራ ይሸሻል፡፡ ማግለል ሌላው ችግር ነው፡፡ በተወሰኑ የአፍሪካ አገሮች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ወይም የተጠረጠሩ ሰዎችን ማግለል፣ በስድብ መተንኮስና ማሳደድ ይስተዋላል፡፡ መንግሥት በግብረ ኃይሉ በመታገዝ የኮሮና ቫይረስ ሕመም በማንኛውም ሰው ላይ ሊታይ እንደሚችልና የመሠራጫ መንገዶችን በግልጽ በማብራራት ሕዝቡን ማስተማር አለበት፡፡ ሕዝቡ ሳልን እንደሁልጊዜው ሳይሆን ከቫይረሱ ጋር አያይዞ ይመለከተዋል፡፡ አንድ ግለሰብ ከቦትስዋና እንደተናገረው፣ ‹‹በፊት ሳስል ሕዝቡ እንደተለመደ ነገር ያየው ነበር፡፡ አሁን ከበሽታው ነፃ በመሆኔ ተደስቻለሁ፡፡››

ዛሬ አሜሪካ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በርካታ የታማሚና የሟቾች ቁጥር አስመዝግባለች፡፡ [የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ የዘጠኝ ሰዓት መረጃ እንደሚያሳየው፣ አሜሪካ በርካታ ቫይረሱ የተረጋገጠባቸው ሰዎች ቁጥር 1‚390‚764 ሲሆን 84‚136 የሞት መጠን ደግሞ ተመዝግቦባታል፡፡ በዓለም ደረጃ ቫይረሱ የተረጋገጠባቸው ሰዎች ቁጥር 4‚364‚172 ሲደርስ፣ 297‚569 ዜጎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡ አሜሪካ በከፍተኛ ደረጃ ቫይረሱ የተረጋገጠባቸው ታማሚዎች ቁጥር፣ በዓለም የቀዳሚነት ሥፍራውን ይዛለች፡፡]

ዋሽንግተን ፖስት ሚያዝያ 4 ቀን ላይ እንደጻፈው፣ ‹‹በዚህ ሁኔታ በሽታው መከሰት አልነበረበትም፡፡ ምንም እንኳ በደንብ ባትዘጋጅም፣ አሜሪካ በደርዘን ከሚቆጠሩ አገሮች የበለጠ የባለሙያ፣ የሀብት፣ የዕቅድና የተዛማች በሽታዎች ልምድ እያላት ማንኛውንም ዋጋ ከፍላ በሽታውን በአያሌው መመከት ትችል ነበር፡፡››

ጉዳዩ ሁሉ ስለፈጣንና ጉልህ ዕርምጃዎች ነው፡፡ ይህ እንደማንኛውም አደጋ አይደለም፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ሊቆይ ይችላል፡፡ ውሳኔዎች የኢኮኖሚውን ሁኔታ ቢጎዱትም፣ የሕዝቡን ሕይወት ግን ያድናሉ፡፡ መንግሥት የሚገመገመው የሕዝቡን ሕይወት ለማዳን ምን አደረገ?. . . ተብሎ እንጂ፣ ቀድሞውንም የተዳከመውን ኢኮኖሚ ለማዳን ምን ሠራ?. . . ተብሎ አይደለም፡፡ መንግሥትም ይህንን ዕድል የሕዝቡን አንድነት ለማደስና ከዚህ ቀውስ ወጥቶ ስለአንድነት ጥቅም እንዲማር፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚታደስበትን ጥሩ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ አለበት፡፡

ይህ ወቅት ልዩ ወቅት ነው፡፡ ልዩ ውሳኔዎች ያስፈልጉታል፡፡ ነገሩ በአመራር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ቀውሱ በጠነከረ ቁጥር ሁሉም ዓይኖች ወደ መሪዎች ያርፋሉ፡፡ የመሪዎች ፈተና ራሳቸውን ሳይሆን ሕዝቡንና ባለሙያዎችን ማዳመጥ መቻላቸው ላይ ነው፡፡ እስከዚያ ድረስ በቀናነት እንቆይ፣ አንድ እንሁን፡፡

አበቃሁ!

ተርጓሚ፡- ሚኪያስ ጥላሁን

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ፣ በቀድሞው መንግሥት የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን (ዕማማኮ) ኮሚሽነር፣ በመቀጠልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በቦስተን ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናቶች ማዕከል ተጋባዥ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles