Monday, April 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኮቪድ-19፡ ተገማቹ የግብርና እና የገበያ ሰንሰለት ቀውስ

በሶፎንያስ ዳርጌ

በህንድ ቤንጋል ግዛት እ.ኤ.አ. በ1943 ከሁለት እስከ ሦስት ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ለሕልፈት ተዳርገዋል። የዚህ አስከፊ ረሃብ መንስኤ በተፈጥሮ አደጋ የተከሰተ ረሃብ የፈጠረው የምግብ እጥረት አልነበረም። ይህ ሁሉ እልቂት የደረሰው ምግብ ሳይታጣ ሰውሰራሽ በሆነ የምግብ አቅርቦት ሰንሰለት መጓደል ምክንያት ነበር። በተመሳሳይ በመላው ዓለም በ1911 ዓ.ም. በአገራችን የተከሰተው የኅዳር በሽታ እየተባለ በተለምዶ የሚጠራው ስፓኒሽ ፍሉ ድንበር ተሻጋሪ ወረርሽኝ አንድ ሦስተኛውን የዓለም ሕዝብ የሞት ሲሳይ አድርጓል። በተለይ ኑሮውን በግብርና ላይ ለመሰረተው የአፍሪካ ሕዝብም ወረርሽኙን ተከትሎ የተከሰተው ረሃብ ከወረረሽኙ መሳ ለመሳ ገዳይ ነበር።

በተለያየ ጊዜ በአገራችን የተከሰቱት የረሃብ አደጋዎች ምክንያት በምግብ እጥረት ሳይሆን የአቅርቦት ችግርና ጦርነት ዋና ምክንያት እንደሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። በክረምት ዝናብ ላይ ተስፋውን ላደረገ፣ ከእጅ ወደ አፍ የግብርና ታሪኩን እንደቅርስ ለጠበቀ፣ የአንድ ክረምት ዝናብ መቅረት ህልውናውን ለሚፈታተነው ሕዝብ፣ ኮቪድ-19 ከባድ ሥጋት ደቅኗል።

በኢትዮጵያ የመጀመርያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ከታወቀበት ከመጋቢት 13 በኋላ መዛመቱን ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ  አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ  ጀምሮ በግብርና፣ የምግብ ዋስትና እና የግብይት ሥርዓቱ ላይ የከፋ ተፅዕኖ እንዳሳደረ በቅርብ ያለፈው የትንሣዔ በዓል ምስክር ነው።  

በጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ሥራው ድንቅ ፍቅረ ኢየሱስ እና ባልደረቦቹ “COVID-19 Probable Impacts on Ethiopian Agriculture and Potential Mitigation and Adaptation Measures: No Food-No Health-No Life” በሚል ርዕስ በ2020 በሠሩት ጥናት ላይ በኮቪድ-19 ምክንያት የእንቅስቃሴ መገደብ በግብርና ግብአቶች ላይ በጊዜ መድረስና መሠራጨት ላይ፣ በመስኖ በሚለሙ ሰብሎች ላይ በሚፈጠር የአያያዝና ገበያ እጦት ምክንያት እየተበላሹ እንደሆነና በግብርና ሥራ በሚበዛባቸው ወቅቶች በደቦና በኅብረት መሥራት ለለመደው አርሶ አደርም እንቅፋት እንደፈጠረ ያስረዳሉ። በተጨማሪም በገበያ እጥረት ምክንያት ምርታማነታቸው የቀነሱት እንደ የአበባ ኢንዳስትሪ ዓይነት ዘርፎች ሠራተኞች እንዲቀንሱ ምክንያት እንደሆነ በጥናቱ ተገልጿል። ብዙ ኢ-መደበኛ ሠራተኛ ለበዛባት አገር ይሄ ሌላ ትልቅ ኪሳራ ነው።

ደግዬ ጎሹ እና ባልደረቦቹ “Economic and welfare effects of COVID-19 and responses in Ethiopia: Initial insights” በሚል ርዕስ ዘንድሮ በሠሩት ጥናት የግብርናው ዘርፍ 68 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ የሥራ መስክ የሚሸፍን ሲሆን፣  ለጂዲፒም 33.3 በመቶ ድርሻ እንዳለው ይጠቅሳሉ። ወረርሽኙ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ከሆነ በግብርና ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከሌሎች ዘርፎች አንፃር ትንሽ እንደሆነ ይገልጹና፣ ወረርሽኙ እየተባባሰ የሚሄድ ከሆነ ግን በተለይም በመጭው ክረምት የምርት ዘመን ላይ ከባድ ጉዳት እንደሚያደርስ ያሰምሩበታል። በተለይም በመስኖ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ በርበሬና የመሳሰሉት ፍራፍሬዎች የሚያመርቱ ገበሬዎችና የኅብረት ሥራ ማኅበራት በእንቅስቃሴ መገደብ ምክንያት ክፉኛ ይጎዳሉ። ለምሳሌ በቅርቡ የፋሲካ በዓል ሳምንት እንኳ በትግራይ ክልል በራያ ዓዘቦና ራያ አላማጣ ወረዳዎች ገበሬዎች ያመረቱት ቲማቲም ወደ ገበያ ለማቅረብ እንደተቸገሩ የሚገልጸው ዜና የማኅበራዊ ሚዲያ መወያያ ርዕስ ነበር። የሰመረ የግብይት  ሥርዓት በሌለበትና ከአካባቢ ገበያ ወደ ሆድ በሆነ እሴት ሰንሰለት ለሚኖር አርሶ አደር ይሄ ትልቅ ጉዳት ነው፤ ለመንግሥትም ሌላ ሸክም።

“በእንቅርት ላይ…” እንደሚባለው የአንበጣ መንጋ እስካሁን 200,000 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሰብል አውድሟል፡፡ በዚህም ከ3.5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የማሽላ፣ በቆሎና ስንዴ ምርት ወድሟል። አሁንም ይህ ሥጋት እንዳለ ነው።  ሌላው በኮቪድ-19  ቫይረስ ምክንያት የተገደበው እንቅስቃሴ በብዙ ከተሞች በግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ መናር አስከትሏል። ለምሳሌም በፋሲካ በዓል ጊዜ ዶሮ እስከ 1,000 ብር እና ፍየልና በግ እስከ 10,000 ብር ተሽጧል። ይህም በተመሳሳይ ወቅት ዓምና ከነበረው ዋጋ ከእጥፍ በላይ ነው። 

በግብርናው ላይ ተገማች ጉዳት

የተለያዩ ጥናቶች እስካሁን በኮቪድ-19 የደረሰውን ጉዳት መሠረት በማድረግ በምግብ ዋስትና፣ በድህነት መጠን፣ በግብይት ሰንሰለት፣ ወደ ውጭ አገር በሚላኩ የግብርና ውጤቶች፣ በሥራ አጥ ቁጥር፣ በግብርና ምርት በአጠቃላይ በአገሪቱ የጂዲፒ ያለውን ተፅዕኖ በተለያዩ ተቋማትና ተመራማሪዎች ሊያደርስ የሚችለው አደጋና የአጭርና የረጅም ጊዜ  መፍትሔዎችና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን አመላክተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፣ በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ምክንያት አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ  የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እስከ 30 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል የተናገሩት በቅርቡ ነው። በተመሳሳይ ከግብርና ዘርፍ ሊሰበሰብ ከታቀደው ቀረጥ ውስጥ በኮቪድ-19  ምክንያት እስከ 838 ሚሊዮን ዶላር አገሪቱ እንደምታጣ የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን አስታውቋል።

ዓለማየሁ ገዳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ “The Macroeconomic and Social Impact of COVID-19 in Ethiopia and Suggested Direction for Policy Response” በሚል በሚያዝያ 2012 የሠሩት ጥናት ላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በ2020/21 የበጀት ዓመት የአገሪቱ ጂዲፒ በ11.1 በመቶ እንደሚቀንስ ይገልጹና ግብርና ደግሞ ለጂዲፒ ከሚያደርገው አስተዋፅኦ በ1.6 በመቶ እንደሚቀንስና ወደ ውጭ በሚላኩ የግብርና ውጤቶች ላይም ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ወረርሽኙ የሚቀጥል ከሆነ የተፅዕኖው መጠንም እስከ ሦስት በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ነው የተገመተው። 

ከፍ ብሎ በተጠቀሰው የደግዬ ጎሹ እና ባልደረቦቹ ጥናት እንደሚለው፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በግብርናው ዘርፍ ምንም እንኳ በወረርሽኙ ቆይታ የሚወሰን ቢሆንም ከ5 እስከ 12 በመቶ የሥራ እጦት ሊያጋጥም እንደሚችል ይገምታሉ። አያይዘውም ወረርሽኙ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ከሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የድህነት መጠኑ ከነበረበት 22.1 በመቶ ወደ 38.4 በመቶ እንደሚያሻቅብ፤ ይህም ወደ ግማሽ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያጠቃልል ያስረዳሉ። ይህ አኀዝ የሚያመላክተው አገራዊ አማካይ የድህነት መጠንን ነው፡፡ ሆኖም በአንዳንድ ክልሎች የአንበጣ መንጋ ጉዳት ተጨምሮበት የድህነት መጠኑ ከፍ ይላል።

የጀርመን ድምፅ ሬድዮ የዓለም የምግብ መርሐ ግብርን ጠቅሶ ባለፈው ሚያዝያ የኮሮና ቫይረስ በምሥራቅ አፍሪቃ የሚገኙ ደሃ አገሮች 20 ሚሊዮን ሰዎች ላይ የምግብ ዋስትና  ሥጋት መደቀኑንን ገልጧል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ዋስትና ሥጋት ተደቅኖባቸዋል ካላቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን የምግብ ዋስትና እጦቱ በሦስት ወራት ብቻም በእጥፍ ሊያድግ እንደሚችልና በሽታው ከተባባሰ ግን የምግብ ዋስትና እጦቱ እስከ 43 ሚሊዮን እንደሚደርስ ያስጠነቅቃል። ይህን ለመቅረፍም ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ አስቸኳይ ርዳታ ያሻል ይላል ዘገባው

እንደ መፍትሔ

አስቸኳይ ጊዜ  አዋጆችና ክልከላዎች ሲወጡ በተገቢው መልኩ የአፈጻጸም ሒደቱና መካታት ያለባቸው ነገሮች ለሁሉም የሥራ ዘርፎች በባለሙያዎች ጥናት መሠረት  መሆን እንዳለበት ከላይ የተዘረዘሩት የባለሙያ ጥናቶች አስረጂ ናቸው። የአገራችን ግብርና ምንም እንኳ በስፋት በክረምት ዝናብ ላይ የተንጠለጠለ ይሁን እንጂ ቀላል የማይባል መሬት በመስኖ ስለሚለማ የመፍትሔ ሐሳቦቹ የአጭርና የረጅም ጊዜ  የወረርሽኙን ጉዳት መሠረት  ያደረጉ ሊሆን ይገባል። ይበልጥ ትኩረት ያሻቸዋል ያልኳቸውን ነጥቦች ከፍ ብሎ በተጠቀሰው በሥራው ድንቅ ፍቅረ ኢየሱስ እና ባልደረቦቹ፣ ደግዬ ጎሹ እና ባልደረቦቹ፣ እና ዓለማየሁ ገዳ በሠሯቸው ጥናቶችና ተግባራዊ/የመስክ ትዝብቴን መሠረት በማድረግ የሚከተሉትን የመፍትሔ ሐሳቦች አስቀምጣለሁ።

1. ከገበሬዎች ማሳ እስከ ሜካናይዝድ እርሻዎች ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብ በመጀመርያ የመረጃ እጥረት/ አለመኖር ዓብይ ምክንያት ነው። በእርሻ የሚተዳደረው ሕዝባችንን እንዴት ተደራሽ በሆነ መልኩ በዚህ ጊዜ ማስኬድ ይቻላል? በሬዲዮ የገበያ ሥርዓት ለመጠየቅ በፋና ሬድዮ የሚተላለፍ ፕሮግራም ዓይነት በሁሉም መገናኛ ብዙኃን በመጠቀም ችግሩን ማቅለል ይቻላል። በዚህም ስለገበያ ውሎ ብቻ ሳይሆን አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ በኮሮና ጊዜ ማድረግ ስለሚገባው ጥንቃቄም ጭምር እንደ አገር ከሚነገረው በተለየ መልኩ መሠራት አለበት። የገበያን መረጃ መሠረት በማድረግ ገበያ የት እንደሚገኝና በኅብረት ሥራ ማኅበሮችና ማኅበራት ተደራሽ ማድረግ ይገባቸዋል።

የፌደራል፣ ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ፣ እስከ ቀበሌ ያለው መዋቅር በዚህ የወረርሽኝ ጊዜ  እንደሚላላ እሙን ነው። በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ችግሩ የሚፈታበትና የሚቃለልበት መንገድ ሊበጅ ይገባል። በአገራችን አንድ የግብርና የልማት ባለሙያ ለ10,000 ሰዎች /አንድ፡ ለአሥር ሺሕ/ ነው። በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ሰብስቦ መረጃ ከማስተላለፍ ይልቅ ቤተሰብን መሠረት  ያደረገ፣ ከፍ ሲልም ገበሬ ለገበሬ የግብርና ምክክር እንዲያደርጉ ማድረግ። ለግብርና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የተሳካ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር በሞባይል መተግበርያና ሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች መሠረት  ያደረገ እገዛ በማድረግ ሸክማቸውን ማቅለል ይቻላል። አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን መሠረት ያደረገ የሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች አብዝቶ መሥራትና የሥነ ልቦና ቀውስ እንዳያጋጥም በቂ ክትትል ማድረግ ተገቢ ነው።

2. የግብርና ምርቶች የግብይት ሥርዓትና የአቅርቦት ሰንሰለት ተደራሽና ቀላል ለማድረግ መሥራት፣ እንዳይዛባና ጉዳት እንዳያስከትል መከታተል ይገባል። ይህም ማለት ከገበሬዎች ለገበሬዎች፣ የመጀመርያ ደረጃ ግብይት //በገበያ በሮች farmgate//፣ በሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ የግብይት ሥርዓት መዛነፎችና ችግሮች እንዳይኖሩ መሥራት ያስፈልጋል።

3. ለመጭው የክረምት የምርት ዘመን ለግብርና አስፈላጊ የሚባሉ ግብአቶች በተቀላጠፈና በተቀናጀ መልኩ በጊዜ ማቅረብ፡- ይህም ማዳበርያ፣ ምርጥ ዘር፣ የግብርና መሣርያዎች፣ የተባይና የአረም መከላከያ ኬሚካሎችን ያጠቃልላል። እንዲሁም በሁሉም የግብርና ግብአቶች ላይ ድጎማ ማድረግ፣ የአቅርቦት ቦታዎችን ማብዛትና የተራዘመ የብድር አገልግሎት ማመቻቸት ከመንግሥትና ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ነው። በመስኖ የለሙ ሰብሎች በተቻለ ፍጥነት ወደ ገበያ እንዲቀርቡና በጊዜ ወደ ገበያ ባልቀረቡት ላይም ፍራፍሬው እንዳይበላሽ የባለሙያ ምክር መሠረት ያደረገ ሥራ መሥራት ተገቢ ነው።

4. በያዝነው የመስኖ ወቅትና በሚመጣው የክረምት ወቅት ሊፈጠሩ በሚችሉ የሰው ኃይል እጥረቶች ቀደም ተብሎ መታሰብ ከሚገባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው። በተለይም ብዙ ሠራተኞች በሚያሳትፉ በእንደ ሑመራና ጋምቤላ በመሳሰሉ ሰፋፊ እርሻ ባለባቸው አካባቢዎች መንግሥት ለሠራተኞች ተገቢውን ጥንቃቄና እንክብካቤ እንዲያደርጉ ባለሃብቶችን መከታተል ይገባዋል። አረም ለማረም የሚያስፈልገውን የሠራተኛ ብዛት ለመቀነስ ባለሙያን በማማከር የአረም መከላከያ ኬሚካሎችን መጠቀም ጫናውን ይቀንሰዋል። ለማንኛውም የግብርና ሥራ ገበሬዎች በቤተሰብ ብቻ እንዲጠቀሙና የኅብረት/የደቦ ሥራዎችና አካሄዶችን መቀነስ ተገቢ ነው።  እንዲሁም የአርብቶ አደሮች እንቅስቃሴ መገደብ /አስፈላጊ ግብአቶች በቅርብ ርቀት እንዲያገኙ መሥራት ያሻል፡፡/

5. መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዕቅዳቸውን እንዲከልሱና ግብርና እና ገበሬን መሠረት ባደረጉ ጉዳዮች ላይ እንዲያውሉ ማበረታታት፣ የግብርና ምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ከዚህ ቀደም ከነበረው በበለጠ ትኩረት በመስጠት ከግብርና ቢሮ ጋር በተቀናጀ ሁኔታ መሥራት፣ የሀብትና ግብአት ማሰባሰብና ሞቢላይዜሽን ሥራ በመሥራት የምግብ ዋስትና ችግርና የተመጣጠነ ምግብ ክፍተት እንዲሞሉ ማድረግ፤

6. ከወረርሽኙ ጎን ለጎን የተጋረጠውን የአንበጣ መንጋን ለመከላከል በክልልና ፌደራል መንግሥት የተቀናጀ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፤

7. የግብርና ፋይናንስ ተቋማትን ማበረታታት፣ ለኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ዩኒየኖች ድጎማና የግብር ቅነሳ ማድረግ፤

8. የፌደራልም ሆኑ የክልል መንግሥታት ግብርናን መሠረት ያደረገ ጊዜያዊ አዋጆች ሲያወጡ ከኮማንድ ፖስቱ ከፍ ባለመልኩ የግብርና ባለሙያዎችን ማማከር፤

9. በአጠቃላይ የረጅም ጊዜ ተፅዕኖዎች በሚፈታመልኩ ተቋማት መገንባት፣ ግብርናውን በቴክኖሎጂ ማዘመን፣ የገበያ ሰንሰለት ሥርዓቱን ማሻሻል፣ ዘመናዊ መስኖ ውኃ መሠረት  ያደረገ ፖሊሲ መቀየስና ተከታታይነት ያለው የፖሊሲ ክለሳ ወሳኝነት እናዳላቸው ሊታወስ ይገባል፡፡

ማጠቃለያ

ኮቪድ-19 ለአንዳንዶች የአካባቢ ጠበቃ፣ ለሌሎች የጠራ ሰማይ እንዲያዩ ምክንያት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ አቀንቃኞች ሲሳይ፣ በአንዳንዱ አገሮች የፍቺ ጉዳዮች እንዲበዙ ምክንያት፣ በብዙ አገሮች ደግሞ ለኢኮኖሚ መዳከምና ለብዙ ሰዎች ሞት መንስኤ ነው። ለአንዳንዶች የቤት ውስጥ ጥቃት መብዛት ምክንያት፣ ለሌሎችም በታሪክ ያልተጠበቀ ቅናሽ ስላሳየው የነዳጅ ዘይት ዓብይ አጀንዳ ነው፡፡ ፖለቲከኞችም በዚህ የወረርሽኝ ጊዜ ሥልጣናቸውን ስለማስቀጠል ያስባሉ፤ ሌሎች ፖለቲከኞችም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ስለሚኖረው የፖለቲካ አሰላለፍ ያሰላስላሉ። እንደ አፍሪካ ላሉ አኅጉራት ደግሞ ከተጠቀሱት ችግሮች በተጨማሪ የህልውና፣ የሕይወትና ሞት ጉዳይ ነው። ኮቪድ-19 በግብርና፣ በምግብ ዋስትናና የገበያ ሰንሰለት ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የተቀናጀ፣ የረጅምና አጭር ጊዜ  ተግዳሮቶችን በሚፈታ መልኩ በቅንጅት መሥራት ያሻል።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአፈር ሳይንስ የማስተር ኦፍ ሳይንስ ዲግሪ ያላቸውና ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉም የእሳቸውን አመለካከት የሚያንጸባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles