ለኮቪድ 19 የሚደረገው ርብርብ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኤድስ እንዲሞቱ ሊያደርግ እንደሚችል ዩኤን ኤድስና የዓለም ጤና ድርጅት በሰጡት መግለጫ አሳሰቡ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የጤና ሥርዓቱን በአጠቃላይ በማስተጓጎሉና የአገሮች ትኩረትም ወረርሽኙን በመከላከሉ ላይ በማተኮሩ፣ ለኤችአይቪ ኤድስ የሚሰጠውን አገልግሎት ላይ መስተጓጎል ፈጥሯል፡፡
ድርጅቶቹ እንደሚሉት በችግሩ ይበልጥ ተጎጂ የሚሆኑት ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ሲሆኑ፣ በቀጣዩ ዓመት ማብቂያ ላይም ከኤድስ ጋር በተያያዘ 673,000 ተጨማሪ ሞት ሊመዘገብ ይችላል፡፡
ከዚህ ቀደም በኤችአይቪና በቲቢ ምክንያት ይመዘገብ ከነበረው አማካይ ሞት በማከል፣ በቀጣናው 673,000 ተጨማሪ ሞት ይመዘገባል የሚል ሒሳባዊ ቀመር ጠቅሰው ድርጅቶቹ ያስታወቁት፣ አሁን ላይ የጤና ሥርዓቱ በአጠቃላይ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ትኩረት በመስጠቱ ነው፡፡ በ2018 በኤችአይቪ ኤድስ ምክንያት የሞቱት 470,000 ነበሩ፡፡ በቀጣዩ ዓመት ማብቂያ ላይ የሚመዘገበው ሞት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ያደርገዋል፡፡
ኤችአይቪንና ከዚህ ጋር የተያያዙ ሞትን ለመከላከል ይደረጉ የነበሩ የኮንዶም ሥርጭት፣ የወንድ ልጅ ግርዛት፣ የኤችአይቪና የቫይረሱን መጠን (ሲዲ4) ለማወቅ የሚደረግ ምርመራ ለኮቪድ 19 በተሰጠው ትኩረት ምክንያት እየቀነሰ ነው፡፡ ሆኖም የዩኤን ኤድስ ዋና ዳይሬክተር ዋይኒ ቢኒያማ ኤድስ ላይ ይደረግ የነበረው ኢንቨስትመንት ወደ ኮቪድ 19 ማድላቱ ዋጋ ያስከፍላል ብለዋል፡፡
በዚህም ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ኤችአይቪ መጠን ብቻ በ104 በመቶ ይጨምራል፡፡ በ2018 በተሠራ ዳሰሳ፣ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች 25.7 ሚሊዮን ሕዝቦች ከኤችአይቪ ኤድስ ጋር ሲኖር ከእነዚህ 16.4 ሚሊዮን (64 በመቶ) ብቻ ናቸው መድኃኒት የሚወስዱ፡፡
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በኤድስና በቲቢ ሕክምናም ሆነ መድኃኒት አቅርቦት ላይ መስተጓጎል ብቻ ሳይሆን ሰዎችም ወደ ሕክምና ተቋም ብንሄድ በኮቪድ 19 ልንያዝ እንችላለን ብለው በመሥጋት ክትትላቸውን እያቋረጡ ነው፡፡
በኢትዮጵያም ይህ እያጋጠመ በመሆኑ የኤችአይቪ ኤድስ፣ የቲቢና ሌሎች ክትትል መቋረጥ በሌለባቸው በሽታዎች የተጠቁ ሰዎች ክትትላቸውንም ሆነ መድኃኒታቸውን እንዳያቋርጡ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሳሙኤል ዘመንፈስ ቅዱስ (ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል፡፡