Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአረጋውያንን ከኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል ለውሳኔ ሰጪ አካላት ምክረ ሐሳቦች ቀረቡ

አረጋውያንን ከኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል ለውሳኔ ሰጪ አካላት ምክረ ሐሳቦች ቀረቡ

ቀን:

ሔልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት፣ ለውሳኔ ሰጪ አካላት ወሳኝና ቁልፍ ያላቸውን ባለስድስት ነጥብ ምክረ ሐሳቦች አቀረበ፡፡ በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙ በአረጋውያን ላይ ያልተነገሩ ከፍተኛ ፍርኃትና ጉዳቶች በዓለም ዙሪያ እያደረሰ መሆኑን አስታውቆ፣ የብዙዎችን ሕይወት ከመቅጠፉም በላይ ከ80 ዓመት በላይ የሆኑትን እንደ በረታባቸው ገልጿል፡፡

ከምክረ ሐሳቦቹ አንደኛው እኩልነትና አለማግለል ነው፡፡ አረጋውያን እንደ ማንኛውም ዜጋ ጤና ነክ መረጃዎችን፣ እንክብካቤና ሕክምና በእኩልነት የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑን፣ አረጋውያንን ጨምሮ ከፍተኛ ሥጋት ያለባቸው ሰዎች ማግኘት ከሚገባቸው የሕክምና አገልግሎቶች የማግለል እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል ብሏል፡፡

ሁለተኛው ዝግጁነትና ማቀድ ሲሆን፣ ሁሉም የዓለም አገሮች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስቀመጣቸውን የዝግጁነትና የዕቅድ ተግባራዊ መንገዶችን፣ እንዲሁም የተቀመጡ ዝርዝር ነጥቦችን በመከተል ለአረጋውያን ተገቢ ምክሮችንና አስፈላጊ ዕገዛዎችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲል አሳስቧል፡፡

ለሕዝብ የሚደርሱ መረጃዎችን ለአረጋውያኑ ማድረስ ሦስተኛው ነጥብ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከኅብረተሰቡና ሥጋት ወይም ሕመም ላይ ካሉ አረጋውያን ጋር የሚደረጉ መደበኛ ግንኙነቶች ወይም የመልዕክት ልውውጦች፣ በሽታዎችን በመከላከልና ሕይወትን በመታደግ ረገድ በጣም የጎላ ጠቀሜታ እንዳላቸው፣ በተለይም አረጋውያኑ የሚጋፈጧቸውን እንቅፋቶች ለምሳሌ የማንበብና የመጻፍ ችግር፣ የቋንቋ ችግሮችና አካላዊ ጉዳቶች (ውስንነቶች) ለመቅረፍ ያመች ዘንድ ተገቢና ጠቃሚ መረጃዎችን በተለያዩ መንገዶችና አረጋውያኑ በሚገባቸው ወይም በሚረዱት ቋንቋ ማስተላለፍ እንደሚገባ ጠይቋል፡፡

አቅርቦትና ድጋፍን በተመለከተ ባቀረበው አራተኛ ነጥብ በበሽታዎች ወረርሽኝ ወቅት አረጋውያንን ለመደገፍና ለመንከባከብ ልዩ ልዩ ዕርምጃዎች ሊወሰዱና ሊተገበሩ እንደሚገባ፣ ለምሳሌ የውኃ አቅርቦት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የአልኮልና የፀረ ተህዋሲያን ኬሚካሎችን ማቅረብ፣ እንዲሁም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉና ራሳቸውን ለይተው ለሚገኙ አረጋውያን ሁሉ ማኅበራዊ ድጋፍና አቅርቦቶችን ለአረጋውያኑ ማቅረብ ያስፈልጋል በማለት አሳስቧል፡፡

ግጭትና መፈናቀልን በሚመለከት በአምስተኛ ነጥብነት ያነሳው በጎ አድራጊ ተቋማትና መንግሥት በዕቅድ የያዟቸውን የአደጋ ጊዜ የመጠባበቂያ ወጪዎች፣ በተለይም ከፍተኛ ሥጋት ላለባቸው በመጠለያዎች ውስጥ ላሉ አረጋውያንና ለተፈናቀሉ ሰዎች ማድረስና በአገር አቀፍ ደረጃ በሚገኙ የጤና ተቋማትና ሆስፒታሎች ተገቢውን የጤና ሕክምናና እንክብካቤ ሕጉ በሚፈቅድላቸው መሠረት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊነትን አካቷል፡፡

በስድስተኛው ነጥብ የበጎ አድራጎት ተቋማት ድጋፍና ልማት አረጋውያን በልማታዊና የበጎ አድራጎት የገንዘብ ድጋፍ እንቅስቃሴዎች ላይ በብዛት ሲዘነጉ እንደሚስተዋሉና ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ተጋላጭ የሆኑ አረጋውያንን ግልጽ በሆነ መንገድ በመለየት፣ በየትኛውም ሁኔታ ላይ ያሉ አረጋውያን በልማታዊ ተግባራትና ከበጎ አድራጊዎች በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሊወሰንና ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሔልፕኤጅ ኢንተርናሽናል የዓለም የጤና ድርጅት ሁሉም አገሮች አስፈላጊውን ዝግጅት ካደረጉና ተግባራዊ ምላሽ ከሰጡ በቀላሉ ሊቆጣጠሩት የሚችሉት ወረርሽኝ እንደሆነ መግለጹን አስታውሶ፣ ይህ ቫይረስ በተለይም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው፣ ያልተሟላ (ዝቅተኛ) የጤና እንክብካቤ ለሚያደርጉና ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ በርካታ ዜጎችን በመጠለያዎች ለያዙ አገሮች ፈታኝና አደገኛም መሆኑን ገልጿል፡፡

ኮሮና ቫይረስ በተለይ አረጋውያንን የሚያሠጋ አዲስ በሽታ መሆኑን፣ በቻይና ከ44 ሺሕ በላይ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ላይ የተሠራው መነሻ ጥናት ከአጠቃላይ ሕዝቡ 2.3 በመቶ የነበረው የሞት መጠን ዕድሜያቸው ከ70 እስከ 79 ዓመት ባሉት አረጋውያን ላይ ስምንት በመቶ፣ እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ የሆኑት ላይ ደግሞ የሞት መጠኑ ወደ 15 በመቶ እንደጨመረ ማሳየቱን በማስታወስ የአረጋውያን ጉዳይ ይታሰብበት ሲል ምክረ ሐሳቦቹን አጠቃሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...