Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ሰውየው ነው አሉ በመጥረቢያው የአገር እንጨት ከምሮ ሲፈልጥ ሳለ አንዱ ጀርጃራ ቆም ብሎ፣ ‹‹ጃል ምን እየሠራህ ነው?›› ይለዋል፡፡ በጥያቄው የተናደደው ሰው ከግንባሩ ላይ ላቡን እየጠረገ፣ ‹‹ትሞታታለህ እንጂ አልነግርህም፤›› አለው፡፡ እኔ እንዲህ ዓይነት ገጥሞኝ ያውቃል፡፡ አንዱ ቤቴ ይመጣና ምን እየሠራሁ እንደሆነ ይጠይቀኛል፡፡ ልብ በሉ እሱ ሲደርስ እኔ ልብሶቼን እየተኮስኩ ነበር፡፡ በእጄ ካውያ ይዤ እያየኝ፣ ‹‹ምን እየሠራህ ነው?›› ብሎ ሲጠይቀኝ መልሴ ቢሆን ጥሩ ነው? ‹‹ተኝቻለሁ!›› ነው ያልኩት፡፡ እያንቀላፋ ወይም እየቃዥ ካልሆነ በስተቀር የምሠራውን እያየ፣ ‹‹ምን እየሠራህ ነው?›› ብሎ መጠየቅ የለበትም፡፡ ከጠየቀ ደግሞ የሚያናድድ መልስ ነው ማግኘት ያለበት፡፡ በአገራችን በፖለቲካውም ሆነ በተለያዩ መስኮች ብዙ ተመሳሳይ ነገሮች ይገጥሙናል፡፡ እኔ አሁን ወደ ሌላ የሚያናድድ ጉዳይ ልውሰዳችሁ፡፡

ዘወትር ጠዋት በመገኛኛ በኩል አልፋለሁ፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ አስፈሪ በሆነበት በዚህ ጊዜ፣ መንገድ ለማቋረጥ የሚታየውን ትርምስ ለማወቅ እዚያ መገኘት ብቻ በቂ ነው፡፡ በመንገድ ትራንስፖርት ሠራተኞች አስተናጋጅነት ከአንዱ ጥግ ወደ ሌላው ጥግ ለመሸጋገር በሚደረግ ጥረት በርካታ አሳዛኝ ነገሮች ይታያሉ፡፡ አስተናጋጆቹ ተሽከርካሪዎችን እያስቆሙ በሥርዓት ሲያሻግሩ ሥርዓቱን ጠብቀው የሚስተናገዱ እንዳሉ ሁሉ፣ ተሽከርካሪዎች ተፈቅደውላቸው በተራቸው ሲተላለፉ ግር ብለው ጥልቅ እያሉ ራሳቸውንና ሌላውን ለአደጋ የሚያጋልጡ ደግሞ አሉ፡፡ በሥርዓት መሸጋገር የሚሰጠውን ጠቀሜታ የተረዱ ሲታገሱ፣ ሥርዓት አልበኝነት የተጠናወታቸው ደግሞ ዘለው እየገቡ ግጭት እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ አንድ ቀን አንዲት አዛውንት እናት ቆም ብለው ተራቸውን ሲጠብቁ፣ በእነዚህ ሁከተኞች ተገፍተው የመኪና ቁርስ ከመሆን የተረፉት ለጥቂት ነው፡፡ ልብ በሉ ነፍሰ ጡሮች፣ ሕፃናት ያዘሉ ወይም የተሸከሙ፣ አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች በሥርዓት ለመስተናገድ ሲጠብቁ፣ በእነዚህ ኃላፊነት የማይሰማቸው ግለሰቦች በግድ ተገፍተው ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ ሁሌም ይህ ትዕይንት ያሳቅቀኛል፡፡

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ማለዳ ላይ እንደ ተለመደው መገናኛ ደርሼ የገርጂ ታክሲ ለመሳፈር ሳዘግም መንገዶቹን ማቋረጥ ነበረብኝ፡፡ ጥግ ላይ በጥንቃቄ ቆሜ የአስተናጋጆቹን ትዕዘዝ ስጠባበቅ ሁለት ጎረምሶች ሁለት ሰዎችን ገፍትረው መንገድ ውስጥ ይዘዋቸው ይገባሉ፡፡ በመተላለፍ ላይ የነበሩ ሁለት ተሽከርካሪዎች በድንጋጤ ሲያቆሙ፣ ከኋላቸው በሌሎች ተሽከርካሪዎች ይገጫሉ፡፡ ጎረምሶቹ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ተሹለክልከው አልፈው ይሻገራሉ፡፡ በግጭቱ ምክንያት ተሽከርካሪዎቹ መንገድ ዘግተው በመቆማቸው፣ እኛም ተፈቅዶልን እንሻገራለን፡፡ ጥቂት ራመድ ስንል ብዛት ያላቸው ሰዎች ዙሪያ ክብ ሠርተው ቆመዋል፡፡ መተላለፊያ በመዝጋታቸው በጠባብ መስመር ላይ እየተጋፋን ስንሄድ፣ እነዚያ አደጋ እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ጎረምሶች እጃቸውን አጣምረው ቆመው አየኋቸው፡፡ በጣም ተናድጄባቸው ስለነበር እንደ ምንም ብዬ ከትርምሱ መሀል ተሹለክልኬ አጠገባቸው ስደርስ በመመሰጥ ቆመው የሆነ ነገር ይመለከታሉ፡፡ ወደሚያዩበት አቅጣጫ ዓይኖቼን ስወረውር ባየሁት ነገር ደነገጥኩ፡፡ የበለጠ ደሜ ፈላ፡፡

እነዚያ ሰውን እያተራመሱና እየገፈተሩ ዘለው ባልተፈቀደላቸው ጊዜ ገብተው መኪኖቹን ያጋጩና ሁለት ሰዎችን ለአደጋ ሊዳርጉ የነበሩ ጎረምሶች የሚያስቸኩላቸው ነገር አልነበረም፡፡ ይልቁንም እንደዚያ እየተንደረደሩ መጥተው የቆሙት፣ ሁለት እጆች የሌሉት አካል ጉዳተኛ በእግሮቹ መጋዝና መዶሻ በመያዝ የሚሠራውን የዕደ ጥበብ ውጤት ለማየት ነበር፡፡ እኔ ይኼንን አካል ጉዳተኛ ለረጅም ዓመታት አውቀዋለሁ፡፡ ራሱን ለልመና ሳይዳርግ በአፉ ሚስማር፣ በእግሮቹ የተለያዩ የአናፂ ዕቃዎች በመጠቀም የቡና ረከቦት፣ መቀመጫና ጠረጴዛ የሚሠራ ድንቅ ባለሙያ ነው፡፡ በተለያዩ ሥፍራዎች እሱ ይህንን ሥራውን ሲያከናውን ‹‹ሙሉ አካል አለን›› የሚሉት ግን አፋቸውን ከፍተው ያዩታል፡፡ ለእኔ ይኼ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ እሱ ሥራውን በትጋት ሲያከናውን ሥራ ፈቱ ደግሞ እጁን አጣምሮ ይደመማል፡፡ እነዚያ ከንቱዎችም የእግረኛ መተላለፊያ ላይ በሥርዓት መሻገር ሲገባቸው ቀውስ ፈጥረው፣ እዚህ ደግሞ ጭንቅላታቸውን እያወዛወዙ በአድናቆት ፈዘዋል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ጋር በዚህ ሁኔታ መነጋገሩ ጥቅም እንደሌለው ራሴን አሳምኜ ወደ ጉዳዬ አመራሁ፡፡

በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮቻችንም ውስጥ እንዲህ የሚያበግኑን ሰዎች አሉ፡፡ የሰው ልጅ ከእንስሳት የሚሻለው የሚያስብበት አዕምሮ ስላለው ነው፡፡ ይህንን አዕምሮ በአግባቡ ብንጠቀምበት በሕይወታችን ውስጥ አስገራሚ የሆኑ ለውጦች ይመጣሉ፡፡ እነዚህ ለውጦች ደግሞ ለስኬት ኑሮ ይጠቅማሉ፡፡ አዕምሮአችንን በአግባቡ ካልተጠቀምን ግን አጠገባችን ያለውን ነገር ማየት አንችልም፡፡ በዚህ ደረጃ ስንገኝ ደግሞ እንኳንስ ማስተዋልና ማገናዘብ ሊኖረን ይቅርና ከደመነፍሳዊ አኗኗር ልንወጣ አንችልም፡፡ በደመነፍስ የሚኖር ደግሞ እንስሳ ብቻ ነው፡፡

ይኼ ጉዳይ በጣም የሚያሳስበው ጓደኛዬ ከሥራ ቦታ ጀምሮ እስከ ተለያዩ ሥፍራዎች ድረስ በሚገጥሙት ጉዳዮች ይበሳጫል፡፡ ‹‹አንድ ቀን የመኪና መለዋወጫ ዕቃ ፈልጌ ቄራ እሄዳለሁ፡፡ የተለያዩ መደብሮች ገብቼ ስወጣ የሻጮቹ ቅልጥፍና ለማመን ነው ያዳገተኝ፡፡ እነዚህ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በታች የሚገኙ ሰዎች በጣም የሚገርም ጭንቅላት ነው ያላቸው፡፡ እኔን ለማሳመን የሚያደርጉት ማግባባት ልዩ ነበር፡፡ ይህንን ችሎታቸውን ተጠቅመው ጥሩ ገቢ ስለሚያገኙ ሁሌም ንቁና ብልህ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል እስኪ ወረዳ ወይም ክፍለ ከተማ ሂዱ፡፡ ከኮሌጅ ወይም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ወጣ የሚባል ወይም የምትባል ሠራተኛ አዕምሮን ያናውጡታል፡፡ አንድ ዓይነት ቋንቋ እያወራን አንግባባም፡፡ ሕዝብ በእነዚህ ምክንያት ቢበሳጭ ምን ይገርማል? ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ስንሄድ እኮ በከፈልነው ግብር ሥራ እንዳገኙ አይገባቸውም፡፡ አገልግሎት የማግኘት መብትን ልመና ያደርጉብናል፤›› ያለኝ አይረሳኝም፡፡ እኔም እላችኋለሁ ግራ ገብቷቸው ግራ የሚያጋቡን በዝተዋል፡፡ ከሁሉም የሚገርመኝ ግን የሥራ ዲሲፕሊን የሚያጠፉ የሱስ ዓይነቶች መብዛት ደግሞ ትኩረት አለማግኘታቸው ነው፡፡ በሌላውም መስክ እንዲሁ ነው፡፡ አገር ከማተራመስ እስከ ሕዝብ ማንገላታት ያለው ሽኩቻ ደግሞ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ደግነቱ ሕይወት መቀጠሉ እንጂ የብዙዎቻችን ችግር ከሚታገሱት በላይ እየሆነ ነው፡፡

(ሰለሞን አሰፋ፣ ከጉርድ ሾላ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...