Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉሻሞ! “274”

ሻሞ! “274”

ቀን:

የሽግግር መንግሥት ጥያቄ ወቅታዊ፣ ጠቃሚና ምትክ የለሽ መሆኑን የሚያሳይ የቅድመ ምርጫ ግምትና ትንተና

(ክፍል አንድ)

በልደቱ አያሌው

- Advertisement -

የኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን ከመግባቱ በፊት የዘንድሮ ምርጫ እንዲራዘምና አንድ ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ስንጠይቅ እንደነበር ይታወቃል። በእኛ ጥረትና ትግል ሳይሆን በኮሮና ቫይረስ አስገዳጅነት፣ አገራችን ምናልባትም ህልውናዋን ሊፈታተን ይችል ከነበረው ከምርጫ 2012 ግርግር ለጊዜውም ቢሆን አምልጣለች ማለት ይቻላል። የኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን መግባት ምርጫውን እንዲራዘም ከማድረጉ በተጨማሪ፣ የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ጥያቄያችንን የበለጠ አስፈላጊና ጥያቄውን ወደ ተግባር የመለወጡንም ዕድል ከቀድሞ በተሻለ ቀላል አድርጎታል። ይህንን የምንለውም በሚከተሉት ሁለት ምክንያቶች ነው።

የመጀመሪያው ምክንያት እንደሚታወቀው ቀደም ሲል ምርጫው እንዲራዘምና የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ስንጠይቅ የነበረው በዋናነት አገሪቱ ከምትገኝበት የፖለቲካ ውጥረት አኳያና “የለውጥ ሒደቱ” ስኬታማ ባልሆነበት ሁኔታ፣ የምናካሂደው ምርጫ በአንፃራዊነት ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ የመሆን ዕድል አይኖረውም በሚል ነው። እንዲያውም ሰላምና የሕግ የበላይነት ባልሰፈነበት ሁኔታ የምናካሂደው ምርጫ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ውጤት ሊያስከትል ይችላል ከሚል ሥጋትም ጭምር ነው። ይህ የቀደመ ሥጋታችን አሁንም መቀጠሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት አገራችን በአሁኑ ወቅት ከኅብረተሰብ የጤና ችግር በተጨማሪ በሐሳብ ለመገመት በማይቻል መጠን ለከፍተኛና ለተራዘመ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ተጋላጭ ሆናለች። ይህንን ከባድና ፈርጀ ብዙ የሆነ አገራዊ ችግር እንኳንስ ከፋፋይ ወደ ሆነና የፖለቲካ ቀውስ ወደ የሚያስከትል ምርጫ ውስጥ ገብተን ቀርቶ፣ በሙሉ ትኩረትና ትብብር አንድ ላይ ቆመን ብንሠራም በቀላሉ ልንወጣው የምንችለው አይደለም። ስለዚህ በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ጥያቄያችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለአገራችን የፖለቲካ ችግር አስፈላጊና ምትክ የለሽ መፍትሔ መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል።

ሁለተኛው ምክንያት የምርጫውን መራዘምና የሽግግር መንግሥት መቋቋምን ቀደም ሲል ይቃወሙ የነበሩ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች ያቀርቡት የነበረው ብቸኛ መከራከሪያ፣ “በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የምርጫ ጊዜ ማራዘም የሚቻልበት ዕድል የለም” የሚል እንደነበር ይታወሳል። ይህ የክርክር ነጥብ ከፖለቲካ አንፃር ቀድሞውንም ተገቢ ያልነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በኮሮና ቫይረስ መምጣት ምክንያት ክርክሩ እንዳይመለስ ሆኖ ተዘግቷል። ከእንግዲህ በአሁኑ ወቅት እየታየ እንዳለው ዓይን ባወጣ ድርቅና ካልሆነ በስተቀር፣ የሕግ አንቀጽና ትርጓሜን ጠቅሶ “ምርጫውን ማራዘም አይቻልም” ብሎ መከራከር የሚቻልበት ዕድል የለም።

በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት የሥልጣን ዘመኑ መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ስለሚጠናቀቅና የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ለአንድም ቀን ለማራዘም የሚያስችል ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የሌለ በመሆኑ፣ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ከመደበኛው የሕግ አሠራር ውጪ ‘Extra-Constitutional’ በሆነ የፖለቲካ ድርድር አገሪቱን እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ሊያስተዳድር የሚችል አንድ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም፣ ከፊታችን ያለ ምትክ የሌለው አማራጭ ሆኗል። ‘አገሪቱ የአንድ ገዥ ፓርቲ የግል ንብረት ናት’ ካልተባለ በስተቀር፣ እንዲህ ዓይነቱ የፖለቲካ ውሳኔ ላይ ሊደረስ የሚገባው በገዥው ፓርቲ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን ሁሉን አቀፍና አሳታፊ በሆነ አገራዊ የምክክር ሒደት ‘National Dialogue’ ነው። ስለሆነም የኮሮና ቫይረስ መከሰት ምርጫውን ለማራዘም የነበረውን የሕግ እንቅፋት በማስወገድ የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ጥያቄን በቀላሉ የሚቻል አድርጎታል። ከእንግዲህ የአገርን ጉዳይ ለማስቀደም፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች እንደተለመደው ቅንነትና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ካላጣን በስተቀር፣ የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ጥያቄን ላለመቀበል ሰበብ ወይም እንቅፋት የሚሆን የሕግ ድንጋጌ የለም።  

ነገር ግን ብልፅግና ፓርቲ በአሁኑ ወቅት እያሳየው ካለው የአገርን ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ፣ ለራስ የፖለቲካ ሥልጣን የበለጠ ቀናዒ ከሆነው ባህሪው አንፅር፣ በሕገወጥ መንገድ ሥልጣኑን ሊያራዝምና ምርጫውን ራሱ በፈለገው ጊዜና ሁኔታ እንዲካሄድ ሊወስን ይችላል። ገዥው ፓርቲም ወደዚህ ዓይነቱ ያልተገባ አቅጣጫ በመሄድ፣ (ምናልባትም የኮሮና ቫይረስ ችግር በቀጣዩ ጥቂት ወራት ከተወገደ)፣ ምርጫውን እስከ 2013 ዓ.ም. አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ የማካሄድ ፍላጎት እንዳለው ከውስጥ አዋቂ ምንጮች እየሰማን ነው። ይህ መረጃ እውነትነት ኖሮት ወደ ተግባር ከተለወጠ፣ ይህ የገዥው ፓርቲ ውሳኔ በአገራችን ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል ታሪካዊ ስህተትና ክስተት ይሆናል። ምክንያቱም የአገራችን የወቅቱ የፖለቲካ ችግር በእውነተኛ የውይይትና የድርድር ሒደት እንጂ፣ ከእንግዲህ ወዲያ በተለመደው ዓይነት የይስሙላ ምርጫ የሚፈታ አይደለም። ውጤታማ በሆነና መዋቅራዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት በሚያስችል የሽግግር ሒደት ባላለፍንበት ሁኔታ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድም አይቻልም። የሆነ ሆኖ ገዥው ፓርቲ ወደዚህ ዓይነቱ የተሳሳተና ሕገወጥ ውሳኔ ሊገባ የሚችልበት ሰፊ ዕድል መኖሩን በመገንዘብና ለሕዝብ ግንኙነት ተብለው በገዥው ፓርቲ በሚካሄዱ የታይታ ውይይቶች ሳይዘናጉ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁለት ፈርጅ ያለው ትግል ማካሄድ ይኖርባቸዋል።

የመጀመሪያው በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ በሕገወጥ መንገድ በሥልጣን ላይ እንዳይቀጥል፣ ምርጫው የሚካሄድበትን ጊዜ ብቻውንና የራሱን መፃዒ ሥልጣን በሚያረጋግጥ መንገድ እንዳይወስን የሚያደርግ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ማድረግ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም በተጭበረበረ ምርጫና በአፈና ድርጊት ለ29 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው ገዥው ፓርቲ ከእንግዲህ በሌላ ማናቸውም አሳማኝ ያልሆነ ሰበብና ምክንያት በሥልጣን ላይ እንዲቀጥል ሊፈቀድለት አይገባም። ገዥው ፓርቲ በአሁኑ ወቅት ሥልጣኑን በኃይል ለማስቀጠል እያሳየው ያለው አስፈሪ አዝማሚያ ከወዲሁ አደብ እንዲገዛ ካልተደረገ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደለየለት አምባገነናዊና ጨፍጫፊ ኃይል ሊቀየር እንደሚችል አጠራጣሪ አይሆንም፡፡ ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዲሉ አደጋውን ከወዲሁ ለመቀልበስ መሞከር፣ ለአገሪቱ ህልውና እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ዕርምጃ ይሆናል፡፡

በእንዲህ ዓይነቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ወደ አገራዊ ምርጫ የምንገባ ከሆነም፣ በምርጫው ግብፅን የመሰሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ካልሆኑ በስተቀር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ የትኛውም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ኃይል አሸናፊ ወይም ተጠቃሚ ሊሆን እንደማይችል በመገንዘብ፣ እንዲህ ዓይነቱ አገራዊ አደጋ እንዳይከሰት ተቃዋሚው ጎራ ሕዝቡን በማስተባበር ጠንካራ ትግል ማድረግ ይጠበቅበታል። ገዥው ፓርቲ ራሱን ከውይይትና ከድርድር ሒደት አርቆ ሥልጣኑን በጉልበት የማራዘሙን ድርጊት የሚገፋበት ከሆነ፣ ተቃዋሚ ጎራ በአንድ ላይ መቆም ከቻለና ይህንን የገዥውን ፓርቲ ሕገወጥነት ለሕዝቡ በበቂ መጠን ማሳመን ከቻለ የተቃዋሚው ጎራ በራሱ ተነሳሽነትና መንገድ የሽግግር መንግሥት እስከ ማቋቋም የሚደርስ ትግል ማድረግ ይኖርበታል። ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ከገዥው ፓርቲ የተለየ ግብዣና መፍትሔ መጠበቅ ሙሉ በሙሉ መቆም ይኖርበታል።

ሁለተኛው ተገቢውና ትክክለኛው መፍትሔ ከዚህ በላይ የተጠቀሰ ቢሆንም፣ መንግሥት በተለመደ አምባገነናዊ ባህሪው በሕገወጥ መንገድ የራሱን ሥልጣን ማራዘም ከቻለና ምርጫው በአጭር ጊዜ እንዲካሄድ የሚወስን ከሆነ (የሚወስን ስለመሆኑ በእኔ በኩል ብዙም አልጠራጠርም) ተቃዋሚው ጎራ በምርጫው ማግኘት የሚችለውን ከፍተኛ ውጤት አሟጦ ለማግኘት የሚያስችለውን ጥረትና ዝግጅት ከወዲሁ ማድረግ ይጠበቅበታል። ገዥው ፓርቲ የወቅቱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽፋን አድርጎና መንግሥታዊ መዋቅሩን ተጠቅሞ (ከላይ ለስድስት ወራት ሥልጣኑን በማራዘም ዕቅዱ ላይ የሰማነውን ፍንጭ ታሳቢ በማድረግ) ውስጥ ውስጡን የራሱን የምርጫ ዝግጅት እያደረገ ነው። ተቃዋሚው ጎራ ይህንን ተገንዝቦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማይፃረር አግባብ የራሱን የምርጫ ዝግጅት ከወዲሁ ማድረግ ይኖርበታል። ይህንን ማድረግ ካልቻለና የኮሮና ችግር በተፈታ ማግሥት ምርጫው እንዲካሄድ በገዥው ፓርቲ የሚወሰን ከሆነ ግን፣ ተቃዋሚው ጎራ “ሠርገኛ መጣ” ዓይነት ችግር ውስጥ እንዳይገባ ከወዲሁ መዘጋጀት አለበት።

ከዚህ ግንዛቤ ጋር በተያያዘ በአንድ በኩል አሁንም ምርጫው በቅርብ ጊዜ እንዲካሄድና የሽግግር መንግሥት የማቋቋሙ ጥያቄ ተቀባይነት እንዳያገኝ ለማድረግ እየጣሩ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ይህንን ለማድረግ ያስገደዳቸው ጠባብ የግልና የቡድን ፍላጎት ለአገር ብቻ ሳይሆን ለራሳቸውም ፍላጎት የማይጠቅም መሆኑን ለማሳየት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍ ሲል ለመጥቀስ በተሞከረው ምክንያት ምርጫው በቅርብ ጊዜ መካሄዱ የማይቀር ከሆነ ተቃዋሚው ጎራ በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ የኃይል አሠላለፍ በአግባቡ ተገንዝቦ የራሱን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ እንዲችል፣ የቅድመ ምርጫ ውጤት ግምት ትንተና ከወዲሁ ማቅረብ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ። ቀደም ሲል ስለ ‹‹የሽግግር መንግሥት መቋቋም አስፈላጊነት›› ባቀረብኩት ጽሑፍ ላይ እንደገለጽኩት፣ አሁን በምንገኝበት ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ በአንፃራዊነት ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የማካሄድ ዕድላችን አንድ አምስተኛ ወይም ከ20 በመቶ ያነሰ ነው። ይህ ዕድል በኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን መግባት ምክንያት የበለጠ ጠባብና ምናልባትም ወደ ዜሮ የተጠጋ ሆኗል። ይህ ግምት ከቅርቡ የዶ/ር ዓብይ የከረረ የማስጠንቀቂያ ንግግርመግለጫ በኋላ የበለጠ ተጠናክሯል።

ነገር ግን ምርጫው መካሄዱ የማይቀር ከሆነና በሆነ ተዓምራዊ ምክንያት  በአንፃራዊነት ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ መሆን ቢችል በአሁኑ ወቅት በአገራችን ካለው የፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ አኳያ ምርጫውን የትኛው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ጎራ ሊያሸንፍ ይችላል? ለሚለው ጥያቄ ‹‹የቅድመ ምርጫ ውጤት ግምትና ትንተና›› መስጠት ጠቃሚ ይሆናል። ጠቃሚነቱም በሚከተሉት አምስት ዋና ዋና ምክንያቶች ላይ የተመሠረተ ይሆናል።

 1. ምርጫው በቅርብ ጊዜ ከተካሄደ “እኛ የተሻለ የማሸነፍ ዕድል አለን” ብለው በማመን ምርጫው በቅርብ ጊዜ እንዲካሄድ ግፊት እያደረጉ የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች የሠሩት ሒሳብ፣ ምን ያህል ጥቅማቸውን የማያስጠብቅና ከእውነት የራቀ ግምት እንደሆነ ቆም ብለው ማሰብ እንዲችሉ፤
 2. የቅድመ ምርጫ ግምቱንም ሆነ በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ የኃይል አሠላለፍ በአግባቡ መረዳትም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ዜጎች በተለያዩ ጉዳዮች ለሚይዟቸው አቋሞች እጅግ ጠቃሚ ግብዓት ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ በመሆናቸው፤
 3. ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ የኃይል አሠላለፍ ሚዛን በአግባቡ ተገንዝበው፣ በተናጠልም ሆነ በትብብር ማድረግ የሚገባቸውን ዝግጅት ከወዲሁ ለማድረግ እንዲችሉ፣
 4. አንዳንድ ወገኖች እንደሚያስቡት መጪው ምርጫ በሆነ ተዓምራዊ ምክንያት ነፃና ፍትሐዊ ለመሆን ቢበቃ እንኳን፣ የምርጫው ውጤት በቀላሉ የሕዝብ መንግሥት ለማግኘት የሚያስችለን ሳይሆን፣ በእስካሁኑ የፖለቲካ ታሪካችን ዓይተነው የማናውቅና በበቂ ሁኔታ ያልተዘጋጀንበት አዲስ ዓይነት ውጤት ሊሆን እንደሚችል እንዲገነዘቡት ለማድረግ፣
 5. እነዚህን ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ግንዛቤዎች በአግባቡ በመፍጠርም ሕዝቡ ከምርጫው በፊት አገራችን በቂ የዝግጅት ጊዜና የፖለቲካ ሒደት እንደሚያስፈልጋት፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ የዕርቅና የአንድነት የሽግግር መንግሥት ማቋቋምም ምን ያህል ወቅታዊ፣ አስፈላጊና ሊታለፍ የማይገባው ጥያቄ እንደሆነ የሚኖረውን ግንዛቤ የበለጠ ለማጠናከር ነው።

በአጠቃላይ እንዲህ ዓይነቱን የምርጫ ውጤት ቅድመ ግምትና ትንተና ማቅረቤ፣ ሀገራችን በድኅረ ምርጫ 97 ወቅት የገጠማት ዓይነት ወይም ከዚያ የባሰ የህልውና ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ የማገዝ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል በሚል እምነት ነው። በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱን ‹‹የምርጫ ውጤት የቅድመ ግምትና ትንተና›› ከፓርቲ ጥቅም አኳያ ካየነው፣ ለአንድ ፓርቲ ውስጣዊ ሥራ እንጂ ለሕዝብ በይፋ መቅረብ የሚገባው አልነበረም። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ ግምገማ ከምርጫ ስትራቴጂ ዝግጅት አንፃር ሌሎች ፓርቲዎች ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት መረጃ ሆኖ ሊያገለግል ይችላልና። ነገር ግን ጉዳዩ ከአገር ደኅንነት ጋር የተያያዘና እንዲህ ዓይነቱን የሕዝብ ጉዳይም በውስጠ ፓርቲ መዋቅር ብቻ ገድቦ መወያየቱ፣ ኋላ ላይ ምን ያህል ያልተፈለገ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ከተገኘው ልምድ በመነሳት ይህንን ሰነድ በዚህ መልክ ለሕዝብ ውይይት ይፋ ማድረጉ፣ በቀና አመለካከት ላይ የተመሠረተ ተመራጭ መንገድ ነው ብዬ አምናለሁ።

በዚህ ጽሑፍ ላይ የተገለጸውን የምርጫ ውጤት ግምት ለመስጠት የተሞከረውም፣ እንዲሁ ከአንድ ግለሰብ ወይም ፓርቲ አመለካከት ጋር ከተያያዘ ጠባብ ግምገማ በመነጨ አይደለም። ይህ ግምገማ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከተሰበሰበ ናሙና የመነጨ ባይሆንም፣ በአንዳንድ ክልሎች እስከ ወረዳ፣ በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ ቢያንስ እስከ ዞን መዋቅር ድረስ ከሚገኙ የአገሪቱ አካባቢዎችና ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ፣ በአገሪቱ ውስጥ የተለያየ አመለካከት ካላቸው የፖለቲካ ድርጅት አመራሮችና አባላት መደበኛ ባልሆነ መንገድ የተሰበሰበ መረጃን መሠረት አድርጎ የቀረበ ግምትና ግምገማ ነው። ይህ የሆነውም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በፖለቲካ ዙሪያ የሚካሄድ ጥናት ግልጽና መደበኛ ከሆነ የጥናት አሠራር ይልቅ፣ መደበኛ ባልሆነ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴ ቢሠራ የተሻለ ውጤታማ እንደሚሆን በማመን ነው። ይህ የቅድመ ምርጫ ውጤት ግምትና ትንተና የተሰጠውም አሁን የምንገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት እስከ ምርጫው ዕለት ድረስ በሚኖረው ጊዜ፣ በተለይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ወራት የሚካሄዱ የምርጫ ዘመቻዎችና የምረጡኝ ክርክር መድረኮች ሊያመጡ የሚችሉትን ከፍተኛ የኃይል አሠላለፍ ለውጥ ጭምር ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። በመጨረሻም የ1997 ዓ.ም. ምርጫን አስመልክቶ በወቅቱ በቅንጅት ውስጥ አቅርቤው የነበረው ተመሳሳይ ‹‹የቅድመ ምርጫ ውጤት ግምትና ትንተና››፣ ኋላ ላይ በምርጫው ከመጣው ውጤት ብዙም ርቀት ያልነበረው እንደነበር እዚህ ላይ አስታውሶ ማለፉ ጠቃሚ ይሆናል።

 1. ምርጫውን ማን ሊያሸንፍ ይችላል?

በምርጫ ሊመጣ የሚችለውን ውጤት ወይም በምርጫው ማን አሸናፊ ሊሆን እንደሚችል ግምት ከመስጠቴ በፊት፣ የወቅቱ የአገራችን የፖለቲካ የኃይል አሠላለፍ ምን እንደሚመስል ጠቅለል ባለ መልኩ ለማሳየት እሞክራለሁ። ከፖለቲካ አጀንዳ የኃይል አሰላለፍ አንፃር በአሁኑ ወቅት በአገራችን ያሉ ተፎካካሪ አስተሳሰቦች ወይም ቅራኔዎች በዋናነት ሁለት ናቸው። እነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች በሌሎች አገሮች እንደሚታየው፣ ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም ወይም ደግሞ ከሕዝቡ ተጨባጭ የዕለት ተዕለት ሕይወትና ኑሮ ጋር የተያያዙ አጀንዳዎች ሳይሆኑ፣ ‹‹በዋናነት ከብሔር ተኮርና ከአገር አንድነት ተኮር አስተሳሰብ›› ወይም በሌላ አገላለጽ፣ ‹‹ብሔር ተኮር ከሆነው የአገሪቱ ሕገ መንግሥትና አገራዊ አደረጃጀት እንዳለ እንዲቀጥል ከመፈለግና ካለመፈለግ አስተሳሰብ›› ጋር በተያያዘ የሚንፀባረቁ ቅራኔዎች ናቸው።

ከአጀንዳ አንፃር ዋናዎቹ ተፎካካሪዎች እነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች ቢሆኑም፣ ከፓርቲዎች የኃይል አሠላለፍ አንፃር ግን በአሁኑ ወቅት በአገራችን ሦስት ዋና ዋና የፖለቲካ ጎራዎች አሉ ማለት ይቻላል።

እነዚህም ጎራዎ፣

 1. ብሔር ተኮር የፖለቲካ ኃይሎች ጎራ (ኮንፌዴራሊስት)
 2. አገራዊ አንድነት ተኮር የፖለቲካ ኃይሎች ጎራ (ፌዴራሊስት)
 3. ብልፅግና ተኮር የፖለቲካ ኃይሎች ጎራ (አቋም አለመያዝን የመረጠ) በማለት ልንከፍላቸው እንችላለን።

‹‹እነዚህ ጎራዎች ስማቸውና ግብራቸው አብሮ ይሄዳል ወይ?›› የሚለውን ጥያቄ፣ በተለይም ‹‹የብልፅግናው ጎራ በእውነትም የብልፅግና ኃይል ነው ወይ?›› የሚለውን ጥያቄ ለጊዜው ወደ ጎን ትተን የኃይል አሠላለፉን በአግባቡ ለመገንዘብ እንዲረዳን ብቻ፣ የጎራዎቹን ስያሜ በዚሁ መልክ እየተጠቀምንበት ብንቀጥል የተሻለ ይሆናል።

“ብሔር ተኮር” ባልነው ፈርጅ ውስጥ በአብዛኛው ራሳቸውን በብሔር ስም ያደራጁና ኦነግን፣ ኦፌኮን፣ ሕወሓትን፣ ኦብነግን የመሳሰሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ተካተውበት እናገኛለን። ነገር ግን አንዳንድ በደቡብ፣ በአፋር፣ በአማራና በትግራይ ክልል ወዘተ… በብሔር ስም ተደራጅተው ሳለ የኢትዮጵያን ህልውናና አንድነት ጥያቄ ውስጥ የማያስገቡ የፖለቲካ ድርጅቶችን ከብሔር ተኮር ይልቅ፣ የአንድነት ጎራው ውስጥ ልንመድባቸው እንችላለን። ለምሳሌ አረናን፣ አብንን፣ አሕፓን፣ ጌሕዴድንና ቤጉዴግን የመሳሰሉትን ፓርቲዎች የአንድነት ተኮር ጎራው አካል አድርገን ልንቆጥራቸው እንችላለን።

“አንድነት ተኮር” ባልነው ጎራ ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ ራሳቸውን በኢትዮጵያዊነት ስም ያደራጁ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎችንና ከፍ ሲል የጠቀስናቸው ዓይነት የኢትዮጵያን አንድነትና ህልውናን ጥያቄ ውስጥ የማያስገቡ፣ በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች ጭምር ተካተው ይገኙበታል።

“ብልፅግና ተኮር” ባልነው ጎራ ውስጥ ደግሞ በዋናነት የሚካተተው የቀድሞው ኢሕአዴግ ማለትም የአሁኑ ብልፅግና ፓርቲ ሲሆን፣ ነገር ግን በተቃዋሚ ፓርቲነት የተደራጁና በአቋም ደረጃ የብልፅግና ፓርቲ ደጋፊ የሆኑ፣ በዋናነት ኢዜማን የመሰሉ አንዳንድ ፓርቲዎች ጭምር ተካተው ይገኙበታል። ይህንን “የብልፅግና ተኮር” ጎራ ከሌሎቹ ሁለት ጎራዎች የተለየ የሚያደርገው በአገሪቱ ካሉት ሁለት የፖለቲካ አስተሳሰብ ጎራዎች ውስጥ፣ ማለትም ከብሔር ተኮር ወይም ከአንድነት ተኮር አስተሳሰቦች ውስጥ ለየትኛው ታማኝ እንደሆነ የማይታወቅና ሆን ብሎም እውነተኛ አቋሙን ለመደበቅ የሚፈልግ “አቋም የለሽ” ጎራ በመሆኑ ነው። ይህ ጎራ “አቋም የለሽ” ለመሆን የወሰደው አቋም ምን ዓይነት ዋጋ ሊያስከፍለው እንደሚችል፣ ከዚህ በታች በተተነተነው  የምርጫ ውጤት ግምታችን ላይ የምናየው ይሆናል። ብልፅግና ፓርቲ ከአገሪቱ ሁለት መሠረታዊ የፖለቲካ ቅራኔዎች አንፃር በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት ማኅበራዊ መሠረት የሌለው ፓርቲ ነው። አስተሳሰባዊ ቅራኔ መሠረት ባደረገ የኃይል አሠላለፍ ደረጃም ቢሆን፣ እንደ አንድ የፖለቲካ ጎራ ሊቆጠር የሚችል አይደለም። እንደዚያም ሆኖ ግን የመንግሥትን መዋቅሮች የተቆጣጠረ፣ ሥራ ቀጣሪ የሆነ፣ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስና ኪራይ አከፋፋይ መንግሥታዊ ኃይል ‘Incumbent’ ከመሆኑ አኳያ፣ የግድ እንደ አንድ ተፎካካሪ ጎራ ሊታይ የሚገባው ኃይል ነው።

በሚመጣው ምርጫ ዋናው ፉክክር በእነዚህ ሦስት የፖለቲካ ጎራዎች መካከል ቢሆንም፣ ነገር ግን ሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእነዚህ ሦስት ጎራዎች ገና ያልተሰባሰቡ በመሆናቸው ምክንያት፣ የመጪው ምርጫ ውጤት ከሦስት በላይ በሆኑ፣ በእኛ እምነት ከአሥር በማያንሱ ዋና ዋና ፓርቲዎች ወይም ጥምረቶች የሚከፋፈል ይሆናል። ሆኖም በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ሲሆን እንደታየው፣ እነዚህ ፓርቲዎች ቢያንስ የምርጫው ዕለት ሲቃረብ ወይም ከምርጫው ውጤት መገለጽ በኋላ ያገኙትን የምርጫ ድምፅ በሦስት ዋና ዋና ጎራዎች ለማጣመር የሚገደዱበትና የጥምር መንግሥት ለማቋቋም የሚሞክሩበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ታሳቢ በማድረግ፣ የምርጫ ውጤት ግምታችንን በሦስቱ ጎራዎች አካተን ለማቅረብ እንሞክራለን። ግምታችንን በቅድሚያ በክልሎች ደረጃ ጀምረን፣ በክልሎች ከሚኖረው የውጤት ግምት ድምር በመነሳት ደግሞ በፌደራል ደረጃ አሸናፊ ሊሆን የሚችለውን ጎራ ለመገመት እንሞክራለን። ለተሻለ አረዳድ ይረዳን ዘንድም ውጤቱን በቀላሉ ለመገመት ከምንችልባቸው ክልሎች ጀምረን፣ በቅደም ተከተል ለመገመት አስቸጋሪ የሆኑትን ክልሎች በማስከተል ለማየት እንሞክራለን።

  1. ክልሎችን ማን ያሸንፋል?
   1. ትግራይ ክልል (38 የምርጫ ወረዳ)

ከሁሉም ክልሎች በመጪው ምርጫ የሚመጣውን ውጤት ወደ እርግጠኝነት በተጠጋ መጠን አስቀድሞ መገመት የሚቻለው በትግራይ ክልል ይሆናል። በመጪው ምርጫ በትግራይ ክልል ዋናው (ምናልባትም ብቸኛው) የምርጫ አጀንዳ የትግራይ ክልል ሉዓላዊነትና የሕወሓት ህልውና መቀጠል ጉዳይ ይሆናል። ይህንን አጀንዳ ከሕወሓት በተሻለ መጠን በአሁኑ ወቅት ሊያሳካ የሚችል ድርጅት አለ ተብሎ በአብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ዘንድ ስለማይታሰብ፣ ሕወሓት ምርጫውን መቶ በመቶ ሊያሸንፍ ይችላል። ከትግራይ ሕዝብ ውስጥ ሕወሓትን በተለያየ ምክንያት መምረጥ የማይፈልግ ከአሥር እስከ 15 በመቶ የሚደርስ ሕዝብ ሊኖር እንደሚችል መገመት ቢቻልም፣ “የአብላጫ ድምፅ” በሚባለው የአገራችን የምርጫ ሥርዓት ምክንያት፣ የዚህ ሕዝብ ድምፅ ወደ መቀመጫ አሸናፊነት የሚቀየርበት ዕድል ግን አይኖርም። ለምሳሌ በእያንዳንዱ የትግራይ ወረዳ ከአሥር እስከ 15 በመቶ የሆነው ብቻ ሳይሆን፣ 49 በመቶ የሆነው ሕዝብ የሕወሓት ተቃዋሚ ሆኖ ቢገኝ እንኳ ሕወሓት በአገራችን የምርጫ ሕግ መሠረት በ51 በመቶ የየወረዳው የሕዝብ ድጋፍ ብቻ ምርጫውን መቶ በመቶ የማሸነፍ ዕድል ሊኖረው ይችላል። በሌላ አገላለጽም የ49 በመቶ ሕዝብ ድምፅ በአንድም ወንበር ሳይወከል ከንቱ ይቀራል ማለት ነው።

የአገራችን ሕገ መንግሥት ተመጣጣኝ የውክልና ሥርዓትን ባገናዘበ ሁኔታ መሻሻል አለበት እያልን የምንጮኸው፣ እንዲህ ዓይነቱ ኢፍትሐዊ አሠራር እንዲቀየር ስለምንፈልግ ጭምር ነው። ስለዚህ ከዚህ የምርጫ ውጤት ግምታችን አኳያ በዘንድሮው ምርጫ ሕወሓት የክልሉን ምክር ቤት በአሸናፊነት ይዞ ይቀጥላል፡፡ በፌዴራሉ ፓርላማ ደግሞ 38 ወንበሮች ያሸንፋል። በነገራችን ላይ ከዚህ የእኛ ግምት በተቃራኒ አንዳንድ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በመጪው ምርጫ ብልፅግና ፓርቲ ትግራይ ላይ እንደሚያሸንፍ በእርግጠኝነት ሲናገሩ እየሰማን ነው። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ንግግር ብልፅግና ፓርቲ ምን ያህል የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ለመረዳት በማያስችልና በማይጨበጥ ቅዠት ውስጥ እንደሚገኝ ከማሳየት ያለፈ ትርጉም የለውም። በአጠቃላይ በትግራይ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ የምርጫ ውጤት፣ የመሀል አገር ፖለቲከኞች ሕወሓትንና የትግራይን ሕዝብ በተመለከተ የምንጠቀምበት የፕሮፓጋንዳ ሥልት ትርጉም ባለው መጠን እስካልተቀየረ ድረስ ወደፊትም የሚቀጥል ይሆናል። ይህ ሁኔታ ሲቀየር ግን የአንድነት ፖለቲካና አካባቢያዊ (አውራጃዊ) ስሜት ዋናው የትግራይ ብሔርተኞች ፈተና ይሆናል።

    1. ኦሮሚያ ክልል (178 የምርጫ ወረዳ)

ከትግራይ ክልል ቀጥሎ የምርጫውን ውጤት ወደ እርግጠኝነት በሚጠጋ መጠን ለመገመት የሚቻለው በኦሮሚያ ክልል ነው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እየተሰማ ካለው መረጃ እንደምንገነዘበው ከዚህ ክልል ውስጥ በአነስተኛ ግምት 50 በሚሆኑ የምርጫ ወረዳዎች ውስጥ በፀጥታ ምክንያት ምርጫው ሊደረግ የሚችልበት ዕድል ስለሌለ፣ የውጤት ግምታችን 128 የምርጫ ወረዳዎችን ብቻ መሠረት የሚያደርግ ይሆናል። ቢያንስ በዘንድሮው ምርጫ በኦሮሚያ ክልል አብዛኛው ሕዝብ ድምፅ የሚሰጠው ለፖለቲካና ለኢኮኖሚ አጀንዳዎች ሳይሆን በዋናነት “ለነፃ አውጭነት ትግል” ውለታ መክፈያነት ይሆናል የሚል ጠንካራ ግምት አለ። በዚህ መመዘኛ መሠረት ላለፉት 40 ዓመታት “የነፃ አውጭነት” ትግል ያካሄደው ኦነግና ከኦነግ ጋር ተባብረው ወደ ምርጫው ለመግባት የወሰኑት እነ ኦፌኮ፣ ከ75 በመቶ ያላነሰ መቀመጫ በማሸነፍ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤትንና በፌዴራሉ ፓርላማ 96 መቀመጫዎችን ሊያሸንፉ ይችላሉ። ቀሪውን 20 በመቶ ወይም 26 መቀመጫዎች ደግሞ ብልፅግና ተኮር ጎራው፣ ቀሪውን አምስት በመቶ ወይም ስድስት መቀመጫዎች ደግሞ የአንድነት ተኮር ጎራው (በተለይም የሕዝብ ስብጥር ባላቸው ትልልቅ ከተሞችና አካባቢዎች) ሊያሸንፉ ይችላሉ። ብልፅግና ፓርቲ እስከ 20 በመቶ የሚደርስ መቀመጫ ሊያሸንፍ የሚችለው በዋናነት በፓርቲው አመራርነት ያሉ አብዛኞቹ የኦሮሞ ተወላጆች ካላቸው አካባቢያዊ ማንነት ጋር በተያያዘ በሚወዳደሩባቸው ወረዳዎች ላይ ምርጫውን የማሸነፍ የተሻለ ዕድል ስለሚኖራቸው ነው። ብልፅግና ፓርቲ በአብዛኞቹ የኦሮሚያ ምርጫ ወረዳዎች በአማካይ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን የሕዝብ ድጋፍ ሊያገኝ የሚችል ፓርቲ ቢሆንም፣ ይህ ድጋፍ ግን በምርጫ ሥርዓቱ መሠረት በተሟላ ሁኔታ ወደ መቀመጫ አሸናፊነት የመቀየር ዕድል አይኖረውም።

    1. ሶማሌ ክልል (24 የምርጫ ወረዳ)

እንደ ኦሮሚያ ክልል በሶማሌ ክልልም አብዛኛው ሕዝብ በመጪው ምርጫ ድምፅ የሚሰጠው “ለነፃ አውጭነት ትግል” ውለታ መክፈያነት ይሆናል የሚል ጠንካራ ግምት አለ። ስለሆነም ኦብነግ ከ60 በመቶ ያላነሰ መቀመጫ በማሸነፍ የሶማሌ ክልል ምክር ቤትን የሚረከብ ሲሆን፣ ለፌዴራሉ ፓርላማ ደግሞ 14 መቀመጫዎችን ሊያሸንፍ ይችላል። ቀሪውን 40 በመቶ ወይም አሥር መቀመጫዎች ብልፅግና ፓርቲ ሊያሸንፍ ይችላል። ብልፅግና ፓርቲ ይህንን ያህል ለማሸነፍ የሚበቃውም በክልሉ ውስጥ የጎሳ ወገንተኝነት የራሱ የማይናቅ ሚና ያለው በመሆኑ፣ አንዳንድ ዕጩዎች የየትኛውም ፓርቲ አባል ሆነው ቢቀርቡ በጎሳ ማንነታቸው ብቻ ሊመረጡ የሚችሉበት ዕድል ያለ በመሆኑ ነው። ከብልፅግና ፓርቲ በተጨማሪ በጣም ጥቂት መቀመጫዎችን ሊያሸንፉ የሚችሉ ጎሳ ተኮር ፓርቲዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህ ጎሳ ተኮር ፓርቲዎች አጠቃላይ ውጤቱን የሚያዛባ ሚና ሊኖራቸው ስለማይችል ከግምት ውጪ አድርገን ልናልፋቸው እችላለን። ከዚህ ምርጫ በኋላም የጎሳ ማንነትና የመገንጠል ጥያቄ የክልሉ ዋና ፈተናዎች ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ።

    1. አማራ ክልል (138 የምርጫ ወረዳ)

ከፍ ሲል ከተጠቀሱት ሦስት ክልሎች ቀጥሎ የምርጫውን ውጤት አስቀድሞ ለመገመት ቀለል የሚለው በአማራ ክልል እንደሆነ ቢገመትም፣ ከላይ ከተጠቀሱት ክልሎች በተለየ የአማራን ክልል ግምት ትንሽ የተወሳሰበ የሚያደርጉት ሦስት ምክንያቶች ይኖራሉ።

የመጀመሪያው ምክንያት ከሌሎች ክልሎች በተለየ በዚህ ክልል ሕዝቡ ድምፅ ሊሰጥ የሚችለው ለሦስት አጀንዳዎች ይሆናል። እነሱም (1) ለአማራ ብሔርተኝነት መጠናከር፣ (2) ለኢትዮጵያ ህልውናና አንድነት ዋስትና ማግኘት፣ (3) የሕዝቡን ኑሮ ለሚመለከቱ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አጀንዳዎች ይሆናሉ።

ሁለተኛው ምክንያት ከሌሎች ክልሎች በተለየ በዚህ ክልል ለምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች መሠረታዊ የዓላማ ልዩነት የሌላቸው ቢሆኑም፣ በጋራ ተሰባስበው ለምርጫ የመወዳደር ድክመት ያለባቸው በመሆኑ ነው።

ሦስተኛው ምክንያት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በፖለቲካ ልሂቃኑ ዙሪያ አካባቢያዊ (ክፍለ አገራዊ) ስሜቶች እያቆጠቆጡ በመምጣታቸው ነው።

ነገር ግን በአንድ በኩል ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በክልሉ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነት ያጣበትና ደካማ የሆነበት ሁኔታ ላይ በመሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ ውስጥ ብሔር ተኮር የሆኑ ሌሎች ተቀናቃኝ ኃይሎች የሌሉ በመሆኑ አብንን፣ አብሮነትንና መኢአድን የመሰሉ ፓርቲዎች ቢያንስ እርስ በርስ ላለመፎካከር መስማማት ከቻሉ የአንድነት ተኮር ጎራው በአነስተኛ ግምት ከ90 በመቶ ያላነሰ መቀመጫ በማሸነፍ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤትንና ለፌዴራሉ ፓርላማ 124 መቀመጫዎችን ሊያሸንፉ ይችላሉ። ከቀረው አሥር በመቶ ውስጥ ብልፅግና ፓርቲ 13 መቀመጫ፣ ብሔር ተኮር የሆነው ጎራ (ኦሮሚያ ልዩ ዞን) አንድ መቀመጫ ሊያሸንፉ ይችላሉ። ይህንን ውጤት ለማስጠበቅ ግን ቢያንስ አብንና አብሮነት እርስ በርስ ላለመፎካከር ሊስማሙ ይገባል። ምክንያቱም የክልሉ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት በአዲሱ የአማራ ብሔርተኝነትና በነባሩ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ለሁለት የተከፈለ አመለካከት ያለው በመሆኑ፣ በምርጫው የሕዝቡ ድምፅ በእነዚህ ሁለት አመለካከቶች እንዳይከፋፈል የሚያደርግ የፓርቲዎች ጥምረት መፍጠር የግድ ያስፈልጋል። ቢያንስ አብንና አብሮነት ወደዚህ ዓይነቱ ስምምነት መምጣት ከተሳናቸው የሚያገኙት ውጤት ከ90 ወደ 50 በመቶ አካባቢ ዝቅ ሊል የሚችል ሲሆን፣ በአንፃሩ በክልሉ የሚገኙ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እርስ በርስ ላለመፎካከር መስማማት ከቻሉ ደግሞ፣ ውጤቱ ምናልባትም ከ90 ወደ 95 በመቶ ሊያድግ ይችላል።

ብልፅግና ፓርቲ በአማራ ክልል እስከ 35 በመቶ የሚደርስ የሕዝብ ድጋፍ ሊኖረው ይችላል። የአንድነት ኃይሉ ድምፅ እንዳይከፋፈል የሚያስችል ስምምነት ውስጥ እስከገባ ድረስ ግን፣ ይህ የብልፅግና ፓርቲ ድጋፍ በአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ምክንያት ወደ ወንበር አሸናፊነት የመቀየር ዕድል የለውም። ነገር ግን የአንድነት ኃይሉ ለጋራ ጥቅም በአንድነት መቆም ያለመቻል አሳሳቢ ድክመት ያለበት በመሆኑ፣ ውጤቱ እንዳይበላሽ ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ጉዳዩ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ስለመሆኑ በቅርቡ አብን ከአብሮነት ጋር ለመጣመር ባደረገው ጥረት የገጠመው ችግር በግልጽ አሳይቷል።

    1. አዲስ አበባ ከተማ (23 የምርጫ ወረዳ)

አንዳንድ ሰዎች አቃለው እንደሚገምቱት ሳይሆን አዲስ አበባ ከተማ ከማንኛውም ክልል በላይ፣ ብዙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለምርጫ የሚቀርቡበትና ከፍተኛ የድምፅ መከፋፈል የሚከሰትበት ከተማ ነው። በዚህም ምክንያት በየምርጫ ወረዳው ከ30 እስከ 40 በመቶ ያልበለጠ የሕዝብ ድጋፍ ብቻ ያለው ጎራ ምርጫውን ሊያሸንፍ የሚችልበት ከተማ ነው። ከተማው የአንድነት ኃይሉ ዋና ማኅበራዊ መሠረት ሲሆን፣ በዘንድሮው ምርጫ ሦስት ዋና ዋና አጀንዳዎች መፎካከሪያ ይሆናሉ። የመጀመሪያውና ዋናው “አዲስ አበባ የማን ናት?” የሚለው ጥያቄ፣ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ህልውናና አንድነት መቀጠል፣ ሦስተኛው ከሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር የተያያዙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች (በተለይም ሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት) ናቸው። በከተማዋ የመመረጥ ዕድል የሚኖረው ለእነዚህ ጥያቄዎች አስተማማኝ መልስ መስጠት የሚችል ጎራ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ በከተማው ከፍ ያለ ቁጥር ያለው ብሔር የምርጫውን ውጤት የመወሰን ከፍተኛ ሚና ሊኖረው ይችላል።

ከዚህ አንፃር አብሮነት፣ አብንና ባልደራስን የመሳሰሉ ፓርቲዎች እርስ በርስ ላለመፎካከር ከተስማሙ፣ የአንድነት ጎራው ከ80 በመቶ ያላነሰ መቀመጫ በማሸነፍ የከተማዋን አስተዳደር ሊረከቡና 18 የፌዴራል ፓርላማ መቀመጫ ሊያሸንፉ ይችላሉ። ቀሪው 20 በመቶ ወይም አምስት መቀመጫ ብልፅግና ፓርቲና የእሱ ደጋፊ የሆኑ ፓርቲዎች የማሸነፍ ዕድል ሊኖራቸው ይችላል። ብልፅግና ፓርቲና ኢዜማን የመሰሉ ፓርቲዎች በየወረዳው በድምር 25 በመቶ የሚሆን የሕዝብ ድጋፍ ሊኖራቸው ቢችልም፣ ይህ ድጋፍ በብዙዎቹ ወረዳዎች በምርጫ ሥርዓቱ ምክንያት ወደ ወንበር አሸናፊነት የሚቀየርበት ዕድል በጣም ጠባብ ነው። ይህንን ውጤት ለማስጠበቅም፣ ሲቻል አብዛኛዎቹ የአንድነት ኃይሎች፣ ቢያንስ ግን አብሮነትና አብን እርስ በርስ ላለመፎካከር አስቀድመው መስማማት የግድ ይኖርባቸዋል። የብልፅግና ፓርቲ የገንዘብ ኃይል በአዲስ አበባ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ይኖረዋል። ነገር ግን ብልፅግና ፓርቲ ኦዴፓ በነበረበት ወቅት “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ናት” በማለት የወሰነው ውሳኔና የአዲስ አበባን ሕዝብ ስብጥር ለመቀየር አደረገው የተባለው ሙከራ፣ በምርጫው ሊደርስበት የሚችለውን ሽንፈት በማንኛውም ሌላ ምክንያት የማይቀለበስና አይቀሬ ያደርገዋል። የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በአዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነት ጉዳይ ላይ እያቀረቡት ያለው ጥያቄ እስከቀጠለ ድረስም፣ በአሁኑ ብቻ ሳይሆን በወደፊቶቹ ምርጫዎችም አሸናፊ የመሆን ዕድል አይኖራቸውም።

    1. ደቡብ ክልል (123 የምርጫ ወረዳ)

ከሁሉም ክልሎች የምርጫውን ውጤት አስቀድሞ መገመት አስቸጋሪ የሚሆነው በደቡብ ክልል ነው። በአገራችን ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የሚካሄድ ከሆነ፣ በአሁኑም ሆነ ወደፊት ሊካሄዱ በሚችሉ ምርጫዎች እንደ አሜሪካው ፍሎሪዳ ግዛት የአገራችን የፓርቲዎች የጦር አውድማ (Battle Ground) ወይም ተወዛዋዥ ግዛት (Swing State) ሊሆን የሚችለው ደቡብ ክልል ነው። ይህ የሚሆንበት ምክንያት በአንድ በኩል ደቡብ ክልል የተለያዩ ፍላጎቶች ያሉት ሕዝብና በርካታ ማንነትና ስብጥር የሚገኝበት ክልል በመሆኑ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ክልሉ ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተለየ በአገር አንድነትና በብሔሮች መብት መከበር መካከል ሚዛን የጠበቀ አመለካከት ያለበት በመሆኑ ነው። በዘንድሮው ምርጫ በደቡብ ክልል ዋና ዋና የመፎካከሪያ ነጥብ የሚሆኑት አጀንዳዎች ሦስት ናቸው።

የመጀመሪያውወቅታዊው የዞኖች ክልል የመሆን ጥያቄ፣ ሁለተኛው በኢትዮጵያ አንድነት መቀጠልና በብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር ዙሪያ ሚዛናዊ አቋም መኖር፣ ሦስተኛው ከሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ፣ በተለይም ከመሬት ጥበትና ከወጣቶች ሥራ አጥነት ጋር የተያያዙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ናቸው። ለእነዚህ ጉዳዮች አሳማኝ አማራጭ የሚያቀርብ ጎራ የመመረጥ ዕድሉ ሰፊ ይሆናል። ከሦስቱ የመፎካከሪያ አጀንዳዎች አንፃር ሲታይ አብዛኛው የደቡብ ክልል የአንድነት ተኮር ጎራው (የፌዴራሊስት) ማኅበራዊ መሠረት ነው። ከዚህ አንፃር ሲቻል አብዛኞቹ የአንድነት ኃይሎች፣ ቢያንስ ግን አብሮነትና መድረክ (ኦፌኮን ሳይጨምር) እርስ በርስ ላለመፎካከር ተስማምተው ምርጫ ውስጥ ከገቡ በጣም ባነሰ ግምት 55 በመቶ መቀመጫ አሸንፈው፣ የክልሉን ምክር ቤት ሊረከቡና ለፌደራሉ ፓርላማ 68 መቀመጫዎችን ሊያሸንፉ ይችላሉ። ቀሪውን 30 በመቶ ወይም 37 መቀመጫዎች የብልፅግና ጎራ፣ እንዲሁም 15 በመቶ ወይም 18 መቀመጫ ብሔር ተኮር ጎራው ሊያሸንፍ ይችላል። ይህ ውጤት ዋስትና የሚኖረው ግን ቢያንስ መድረክ በተለይም የእነ ፕሮፌሰር በየነ ኢሶዴፓና አብሮነት እርስ በርስ ላለመፎካከር መስማማት ላይ ከደረሱ ነው። የመድረክ አባል የሆነውና ማኅበራዊ መሠረቱ ኦሮሚያ ብቻ የሆነው ኦፌኮ ከእነ ኦነግ ጋር አብሮ ለመሥራት ስምምነት በደረሰበት ሁኔታ፣ የብሔር ተኮሩ ጎራ አካል እንጂ የአንድነት ተኮር ጎራው አካል ተደርጎ ሊታይ አይችልም።

ፕሮፌሰር መረራም በአጭር ጊዜ ውስጥ የአንድነት ጎራው አካል ተደርገው ከመታየት፣ በአክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ለመረጅ የበቁት በዚሁ ምክንያት ነው። ስለሆነም መድረክ በአጠቃላይም ሆነ በተለይም ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት የሚከተለው ኢሶዴፓ በዚህ ምርጫ ከኦፌኮ ጋር አብሮ በመቅረብ ጉዳት እንጂ ምንም ዓይነት ጥቅም ሊያገኝ አይችልም። መድረክም ሆነ ኢሶዴፓ በደቡብ ክልል የመመረጥ ዕድላቸውን ሊያሰፉ የሚችሉት ራሳቸውን ከኦፌኮ በግልጽ ነጥለው፣ አብሮነትን ከመሰሉ ተመሳሳይ አጀንዳና አደረጃጀት ከሚከተሉ ፓርቲዎች ጋር እርስ በርስ ያለ መፎካከር ስምምነት በመፍጠር ይሆናል። ምክንያቱም አብዛኛው የደቡብ ክልል የኦሮሞ ብሔርተኞችን ጽንፈኛ የፖለቲካ አካሄድ አብዝቶ የሚፈራ እንጂ የሚደግፍ አይደለም። ይህ ስሜት በክልሉ ከቀድሞ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ፖለቲከኞች በአዲስ አበባ ላይ እያነሱ ባሉት የባለቤትነት ጥያቄና ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ የደቡብ ክልል ተወላጆች ከኦሮሚያ ክልል በግፍ በመባረራቸው ምክንያት የበለጠ ተጠናክሯል። እርግጥ ነው አንዳንድ በክልሉ ያሉ ፓርቲዎች ከአንዳንድ የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር የተለየ ግንኙነት አላቸው። ብሔር ተኮር ጎራው የተወሰኑ መቀመጫዎች በዚህ ክልል የማሸነፍ ዕድል የሚኖረውም ለዚህ ነው። እንዲያውም አብዛኛዎቹ የአንድነት ተኮር ኃይሎች እርስ በርስ ላለመፎካከር መስማማት ላይ መድረስ የሚችሉ ከሆነ፣ የአንድነቱ ጎራ ውጤት ከ55 በመቶ ወደ 70 በመቶ የማደግ ዕድል ሊኖረው ይችላል። ከዚህ አንፃር መድረክ በተለይም ኢሶዴፓ የኃይል አሠላለፉን ለማስተካከል የሚወስደው አቋም የጨዋታውን ውጤት ቀያሪ (Game Changer) ነው ማለት ይቻላል። ይህንን ውጤት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ እንዲቻል ከኢሶዴፓ በተጨማሪ፣ በየዞኑ ከሚገኙ የብሔር ድርጅቶች ጋር በመባበር ለመሥራት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

    1. አናሳ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ክልሎች (24 የምርጫ ወረዳዎች)

አናሳ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ክልሎች ከአጠቃላይ አገሪቱ በድምር ከአምስት በመቶ ያልበለጡ የምርጫ ወረዳዎችን የሚሸፍኑ ናቸው። ማለትም ቤንሻንጉል ጉምዝ 9፣ አፋር 8፣ ጋምቤላ 3፣ ሐረሪ 2፣ ድሬዳዋ 2 የምርጫ ወረዳዎች አሏቸው። በእነዚህ ክልሎች ጎሳ ተኮር ፖለቲካ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ የሚኖረው ቢሆንም፣ ከሌሎቹ ክልሎች በተለየ ከኢኮኖሚና ከመሠረተ ልማት ጋር የተያያዙ አጀንዳዎች በምርጫው ውጤት ላይ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል። በእነዚህ ክልሎች ሦስቱም ጎራዎች ከሞላ ጎደል ተመጣጣኝ የማሸነፍ ዕድል አላቸው። ለምሳሌ ብልፅግና ፓርቲ በሁሉም ክልሎች ገዥ ፓርቲ በመሆኑ በእነዚህ ክልሎች ቀላል የማይባል መቀመጫ የማሸነፍ ዕድል ይኖረዋል። በርካታ መቀመጫ ባላቸው በአፋርና በቤንሻንጉል ጉምዝ በዘንድሮው ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን የሚችሉት አንዳንዶቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ አደረጃጀታቸው ብሔር ተኮር ቢሆንም፣ ለኢትዮጵያ አንድነት መቀጠል ቀና አመለካከት ያላቸው በመሆኑ ምክንያት እነዚህ ኃይሎች ከብሔር ተኮር ጎራው ይልቅ የአንድነት ተኮር ጎራውን ሊቀላቀሉ የሚችሉበት ዕድል ሊኖር ይችላል። በእነዚህ ክልሎች የሚንቀሳቀሱት አብዛኞቹ ፓርቲዎች ብሔር ተኮር ከመሆናቸው አኳያ ደግሞ፣ የብሔር ተኮር ጎራውም የማይናቅ መቀመጫ የማግኘት ዕድል ሊኖረው ይችላል። ስለዚህ በእነዚህ ክልሎች ሦስቱ ጎራዎች፣ እያንዳንዳቸው በአማካይ ስምንት መቀመጫ ሊያሸንፉ የሚችሉበት ዕድል ሊኖር ይችላል። በዚህ ረገድ ሰፋ ያለ የግምት ስህተት ሊፈጠር ቢችል እንኳን እነዚህ ክልሎች አጠቃላይ ውክልናቸው ከአምስት በመቶ ያልበለጠ በመሆኑ፣ አጠቃላዩን አገራዊ የውጤት ግምት የማዛባት አቅማቸው በጣም ዝቅተኛ ይሆናል።

 1. ምርጫውን በክልልና በፌዴራል ደረጃ ማን ሊያሸንፍ ይችላል?

ከዚህ በላይ ከተራ ቁጥር 2.1.1. እስከ 2.1.7. ድረስ በቀረበው ትንታኔ መሠረት በክልሎች ሦስቱ ጎራዎች በምርጫው ሊያገኙት የሚችሉት አማካይ የውጤት ግምት በሠንጠረዥ ሲቀመጥ የሚከተለውን ይመስላል። በአጠቃላይ የአገሪቱ የምርጫ ወረዳዎች ቁጥር 547 ቢሆንም፣ በፀጥታ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል ምርጫ ሊካሄድ የማይችልባቸውን 50 የምርጫ ወረዳዎች ስንቀንስ፣ በሠንጠረዡ ላይ የሚኖረው የውጤት ግምት ሥሌት 497 የምርጫ ወረዳዎችን ብቻ የሚመለከት ይሆናል።

ሦስቱ የፖለቲካ ጎራዎች ሊያገኙ የሚችሉት ግምታዊ የምርጫ ውጤት

ሻሞ! “274”

ከዚህ የውጤት ግምት እንደምንረዳው ግምቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከፍና ዝቅ የማለት ዕድል ያለው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የክልል ምክር ቤቶችን በማሸነፍ ረገድ የብልፅግና ተኮር ጎራ አናሳ ሕዝብ ከሚኖርባቸው ክልሎች መካከል የተወሰኑትን ሊያሸንፍ የሚችልበት ዕድል ያለ ቢሆንም፣ ከትልልቆቹ ክልሎች ውስጥ ግን አንዱንም የማሸነፍ ግምት አልተሰጠውም። ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ብልፅግና ፓርቲ አገሪቱ ውስጥ ካሉ ሁለት የፖለቲካ የኃይል አሠላለፍ መገለጫ አመለካከቶች ውስጥ አንዱንም የማይወክል፣ ሁለቱንም የአስተሳሰብ ማኅበራዊ መሠረቶች በእወደድ ባይነት ሥልት (Populism) ለማስደሰት ወይም ላለማስከፋት ሲል በወሰደው “አቋም የለሽ” የመሆን ምርጫ፣ ከሁለት ያጣ ወይም ከማኅበራዊ መሠረቱ የተነቀለ የፖለቲካ ጎራ በመሆኑ ምክንያት ነው። ለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት የእነ ዶ/ር ዓብይ አመራር ለብሔር ተኮር ጎራው እንደ አሃዳዊ ኃይል፣ ለአንድነት ተኮር ጎራው ደግሞ እንደ ብሔርተኛ ኃይል ሲቆጠር የምናየው፡፡ ይህ ማለት ግን ብልፅግና ፓርቲ አቋም የለሽ መሆንን ከዕውቀት ማነስ የመረጠው ነው ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ በፖለቲካ አቋም የለሽ መሆን ሆን ተብሎ የሚመረጥ የፖለቲካ ሥልት ነው። ብልፅግና ፓርቲም በዚህ ወቅት ሥልጣኑን ማደላደል እስከሚችል ድረስ አቋም የለሽ መሆንን ተመራጭ ሥልት አድርጎ ስለወሰደው ነው እንጂ፣ ባለማወቅ የያዘው አቋም አይደለም። ነገር ግን አሁን ካለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይል አሠላለፍ አኳያ፣ እንዲህ ያለው ሥልት ዋጋ የሚያስከፍል እንጂ የሚጠቅም አይደለም። ክፍል ሁለት ሳምንት ይቀጥላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...