Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትኮቪድ 19 እና ምርጫ 12

ኮቪድ 19 እና ምርጫ 12

ቀን:

ሌላ ዓድዋዊ ገድል እንሠራለን ወይስ ለዚያ አንሰን እንበላላለን?

በሲሳይ ገላው

ጥቁር ወታደር ከፊት አስቀድሞ በጥቁር ደም ጥቁርን ቅኝ የማስገባት ዘዴ በያዘው የጣሊያን ወራሪ ኃይል ላይ፣ በ1888 ዓ.ም. በቀጥታም በተዘዋዋሪም የተባበሩት ቀደምት ወገኖቻችን ቁስልና መቋሰል የነበራቸው ነበሩ፡፡ ለምለሙ መሬት ለጣሊያን ሰፋሪዎች ሲሰጥበት ያመፀው የባህር ምድር (የኤርትራ) ሕዝብ፣ የጣሊያን ወረራ የዘለቀበት የትግራይ ሕዝብ፣ አገሬ ወገኔ ተነካ ብሎ የዘመቻ ጥሪውን የተቀበለው የኢትዮጵያ ቀሪ ጦረኛና ገበሬ፣ ዘማች ሰንቆ መሸኘትና መንገድ የወጣ ዘማች ሠራዊትን ተቀባብሎ ማሳለፍ ኑሮ አድራቂ መሆኑን የሚያውቀው መላው ሕዝብ፣ በጣሊያን ላይ አንድ ላይ ቆመዋል፡፡ መላው ሕዝብ መተባበር የቻለውም፣ ልዩነትና ቁርሾ የነበራቸው ገዥዎችና የጦር ሰዎች፣ (ምኒልክና ጣይቱ ከእነ አበጋዞቻቸው፣ ዘውድ ይከጅል የነበረው የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ የአባቱን አፄያዊ ዙፋን የመረከብን ዕድል በምኒልክ የተቀማውና ሸፍቶ የነበረው መንገሻ፣ በምኒልክ ከጣሊያን ጋር መመሳጠር በግኖ የቆየው የዶጋሊው ጀግና አሉላ አባነጋ፣ የወሎው ሚካኤል፣ ወዘተ ሁሉ) ተባብረው ስለተንቀሳቀሱ ነበር፡፡ እናም ትንንሽ ቁርሾዎችና ፍላጎቶችን ወደ ሆድ ከትቶ በትልቁ የጋራ ጠላት ላይ መተባበር የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎችን ያስደነገጠና ያሳፈረ፣ ዓለምን ያስደነቀና ጥቁሮችንና አፍሪካውያንን ያኮራ፣ ለዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የተረፈ ድል በቀድሞ አባቶቻንና እናቶቻችን ሊገኝ ችሏል፡፡

ዛሬም የፖለቲካ ቁርሾዎችን፣ የሥልጣን ጥምንና በቀልን ወደ ሆድ ከትቶ በመተባበር የኮሮና ወረርሽኝን በአነስተኛ ኪሳራ ድል መትቶ፣ ያላንዳች ገላጋይና ያላንዳች ጥይት የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በሰላምና በዴሞክራሲ ግንባታ ሞሽሮ በድህነት ላይ በመዝመት፣ ሊፋጁ ነው ብለው የፈሩልንን በማስደነቅ ወይም እንደተፈራልን (አንዳንዶችም እንደተመኙልን) በትንንሽ እልህ ታውሮ በመበላላት ፈተና መሀል እንገኛለን፡፡ ይህን ፈተና በድል ለመወጣት መቻል ለእኛ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ለቀጣናችንና ለአፍሪካ፣ በሌላ ዓድዋዊ ድል መንቆጥቆጥን የሚያህል ታላቅነት አለው፡፡

ለመሆኑ አጣቢቂኝ ውስጥ የገባንበት ዓይነተኛ ችግር ምንድነው?

ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በብልፅግና ፓርቲ ገዥነት የሚመራው መንግሥት የተወሰነ የአመለካከትና የፕሮግራም ለውጥ ከማድረጉ፣ ዴሞክራሲን ለመገንባት ቆርጫለሁ ከማለቱና ለዚያም የሚሆኑ ነገሮች ከመጀማመሩ በቀር፣ በድርጅት ጥንቅሩ የቀድሞ ኢሕአዴግንና አጋሮቹን በአንድ ፓርቲነት ያካተተ ነው፡፡ ከዚያ ውስጥ ሕወሓት ያፈነገጠ ቢሆንም የተወሰኑ የሕወሓት አባላትን ወደ ራሱ ስቦ የትግራይ የብልፅግና ቅርንጫፍን መፍጠር ችሏል፡፡ የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ወደ ውህድ ፓርቲነት ማምራት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ሕወሓትና ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ ከእኛ በላይ ላሳር ይሉ የነበሩ ብሔርተኛ ቡድኖች ሁሉ፣ ‹‹አሀዳዊነት መጣ ሕገ መንግሥቱ ሊቀየር ነው›› የሚል ክስ ይደረድሩ ነበር፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ከተፈጠረም በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ ብልፅግና ፓርቲን የሕገ መንግሥቱ ሰላቢ አድርጎ፣ ራስን ግን እንደ ሕገ መንግሥቱ ጠባቂ የቆጠረ ጩኸት ቀጥሎ ቆይቷል፡፡

ይህንን እንደያዝን የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመን ወደሚያበቃበት ጉዳይ እንምጣ፡፡ ከተቀናቃኝ ፓርቲዎች አካባቢ ለምርጫ ምቹ የሆነ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ አየር ጎድሏልና ያ ከመሟላቱ በፊት (በዚህ ዓመት) ምርጫ ሊካሄድ አይገባውም የሚል አመለካከት ደሞቆ ሲነገር፣ በመንግሥትና በብልፅግና ፓርቲ በኩል ደግሞ ሁኔታዎችን ጊዜው ሲደርስ የማየትን ቀዳዳ ባይዘጋም ምርጫው በጊዜ ገደቡ ውስጥ ይካሄዳል የሚል አቋም ተይዞ ነበር፡፡ ምርጫ ቦርድም ነሐሴን የምርጫ ማካሄጃ ወቅት ያደረገ የጊዜ ሰሌዳና መርሐ ግብር አውጥቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የመራጮችና የዕጩዎች ምዝገባ የውድድር ዘመቻና የምርጫ ሒደት ሲጠበቅ፣ ኮሮና 19 የሚባል ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በመጋቢት 2012 ዓ.ም. ውስጥ መጣብንና የታሰበውን ሁሉ እንዳይሆን አደረገው፡፡ ሰው ሰብስቦ ለምርጫ ተፎካካሪነትና ምርጫ ለማስፈጸም መሰናዳት ይቅርና አንድ ለአንድ መጠጋጋት እንኳ ለወረርሽኝ መዛመት የሚያጋልጥ ሆነ፡፡ አዲሱ በሽታ እንዳይመነጥረን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ግድ ተከተለ፡፡ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር አራትና ከዚያ በላይ ሰውን መሰባሰብ እስከ መከልከል ድረስ የተራመደው የአምስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በገፍ የጤና ምርመራ ለማድረግ ካለብን አቅም ማነስ ጋር ተደምሮ የኮሮናን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የምንችልበትን ጊዜ ለመገመት እንኳ የማይቻል አደረገው፡፡

ይህ ደግሞ የምርጫ ቦርድን የ2013 ዓ.ም. ዋዜማ የታከከ መርሐ ግብር የማይቻል አደረገውና ምርጫ ቦርድ መርሐ ግብሩን ተፈጻሚ ማድረግ እንደማይቻል ገምግሞ አሳወቀ፡፡ ብዙ ፓርቲዎች ቦርዱ እንደ ቃሉ ምነው ድጋሚ ሳያወያየን ከሚል ቅሬታ በቀር የቦርዱን ውሳኔ እንደተቀበሉት ይታወቃል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤትም የቦርዱን ውሳኔ አፅድቋል፡፡ በአጭሩ የኮሮና ወረርሽኝ መምጣት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጎተተ፡፡ የአምስት ወራት ዕድሜ ባለው አስቸኳይ ጊዜ ኮሮናን ለመቆጣጠር የሚደረገው ትግል ደግሞ የነሐሴውን የምርጫ መርሐ ግብር ከሥራ ውጪ አደረገው፡፡ በዚህም ምክንያት በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥልጣን ዕድሜው ከማክተሙ በፊት በሚካሄድ ምርጫ፣ አሸናፊው ፓርቲ/የፓርታዎች ጥምረት ታውቆ ርክክብ የሚካሄድበት መደበኛ ሒደት ተስተጓጎለ ማለት ነው፡፡

ይህ መስተጓጎል እስከ መቼ ሊቆይ እንደሚችል አይታወቅም፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ እስከ 2012 ዓ.ም. ሐምሌና ነሐሴ በቁጥጥር ውስጥ ሊውል የሚችልበት ምናልባት እንዳለ ሁሉ፣ ከመስከረም አልፎ ሊሄድና የአስቸኳይ ጊዜ መራዘምን ሊጠይቅም ይችል ይሆናል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ቢውል በጣም ፈጣን ስኬት ሊባል የሚችል ነው፡፡ ያ ቢሳካ እንኳ ምርጫው የሰመረ ሆኖ እንዲከናወን ከተፈገለ መስከረምን መሻገር አይቀርም፡፡ ከተሻገረ ጊዜው የተላለፈበት ምርጫና የሥልጣን ዘመኑን የጨረሰው መንግሥት እንደምን ይሆናሉ? መደበኛው ሕገ መንግሥታዊ የምርጫና የሥልጣን ርክክብ ክንውን መተላለፍ የደቀነው እነዚህን ‹‹አጣብቂኝ›› ጉዳዮች ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱን ተከትዬ እሄዳለሁ ያለው የዓብይ መንግሥትም ሆነ ሕገ መንግሥቱን ዋልታችን የሚሉት እነ ሕወሓትና ብሔርተኛ ፓርቲዎች፣ ጥያቄና ክርክር ላስነሱት ለእነዚህ ጉዳዮች መልስ መሻት ያለባቸው ከሕገ መንግሥቱ ነው (ሕግን ከማክበር ውጪ የመሆን መብት ባይኖራቸውም፣ ሕገ መንግሥቱን መልስ አምጣ ማለት የማይጠበቅባቸው ሕገ መንግሥቱን ተጋፍተንና የተውጣጣ መንግሥት ፈጥረን ሕገ መንግሥት እንጻፍ የሚሉት ቡድኖች ብቻ ናቸው)፡፡ የዓብይ መንግሥት አስጠንቼ አራት ከአጣብቂኝ መውጪያ ሕገ መንግሥታዊ ቀዳዳዎች አሉ ማለቱ፣ ከሕገ መንግሥቱ መልስ የመፈለግ አንድ ገጽታ ነው፡፡ ‹‹አራት ቀዳዳዎች የተባሉት አንዳቸውም አያስኬዱምና ሕገ መንግሥቱ መልስ የለውም፡፡ ከ2013 ዓ.ም. መስከረም 30 በኋላ በኢትዮጵያ ሕጋዊ መንግሥት አይኖርም›› ባይነትም፣ ወጣም ወረደ ከሕገ መንግሥቱ መልስ የመፈለግና ‹‹መልስ አጣን›› የማለት ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የማያከራክር መልስ በታጣበትና ሰላም እስከ መናጥ ሊሄድ የሚችል አለመግባባት ባለበት ሁኔታ፣ ያልተግባቡ ተከራካሪዎች እነሱ የተረዱትን ትርጉምና መፍትሔ ይዘው ተግባራዊ ለማድረግ ከመሞከር ፈንታ፣ ሕገ መንግሥቱ በውስጠ ታዋቂም ሆነ አንቀጾችን በማሳሳብ የሚሰጠውን መልስ በርብሮ የመፍታት ሥልጣን ወደ ተሰጠው ሕገ መንግሥታዊ አካል ጥያቄን ማቅረብ ነው የሚጠበቅባቸው፡፡ ከዚህ አኳያ የዓብይ መንግሥት ባስጠናቸው ከአጣብቂኝ መውጪያ አራት አማራጮች ውስጥ መጨረሻ ላይ የተቀመጠው የሕገ መንግሥት ትርጉምን መጠየቅ ከሌሎች ጋር እኩል መቀመጥ የማይገባው፣ የአጣብቂኝ መፍትሔ ከሕገ መንግሥቱ ውስጥ አገኘን ላሉትም ሆነ አንዳችም አላገኘንም ላሉት፣ ገላጋይ መልስ የማግኛ አውራ መንገድ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በተለይ ለሕገ መንግሥቱ ጠበቃና ተገን ነን ሲሉ የነበሩ ኃይሎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊ መልስ እንዲሰጣቸው ከመጠየቅ ፈንታ፣ ከሕገ መንግሥቱ ውጪ የሆነ ‹‹ፖለቲካዊ መፍትሔ›› ማለታቸው ሕገ መንግሥታዊነታቸው የቱን ያህል እንደሆነ ትዝብት ውስጥ የጣለ ነው፡፡ ኮሮናን ማሸነፍ የሚጠይቀው የሥልጣን ድርድርን ሳይሆን፣ ትኩረትን አሰባስቦ በሚያዋጣ ሥልትና ዕቅድ መረባረብን ነው፡፡

ኮሮና በቁጥጥር ውስጥ ከገባ በኋላ አለኝ የሚባለው ጉዳይ የተዋጣ ምርጫ ማካሄድ ከሆነም፣ ይህ ጉዳይ ከምርጫ ቦርድና ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦና ትብብር ፈጥሮ ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን መሥራት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በሚያዚያ 2012 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስጠኗቸውን አራት አማራጮች ለፓርቲዎችና ለሲቪል ማኅበራት ሰዎች ባቀረቡ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት ውስጥ አለን የምትሏቸውን ወሳኝ አጀንዳዎች ይዛችሁ ኑና የሚያወያየን ኮሚቴ አቋቁመን አንወያይ በማለት ያቀረቡት ሐሳብ፣ ተወያይቶና ተግባብቶ ወደ ተባበረ ሥራ ለመግባት ጥሩ መነሻ ነውና ፈጥኖ መልክ ማስያዝ ይበጃል፡፡ የምርጫው ጉዳይ ከዚያ ይልቅ ሥልጣንን መጋራት ይሻል የሚል ተከራካሪ ካለ የሚያብከነክነው ጉዳይ ሌላ ነው፡፡

በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከ2013 ዓ.ም. መስከረም 30 በኋላ ሕጋዊነቱን ያጣል? ከምንም ሙግት በላይ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ያለው አካል የሚሰጠው ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም፣ የእኔም የሌሎች ተከራካሪ ቡድኖች የጋራ ገላጋይ መሆን አለበት ባይ አቋሜ እንደተጠበቀ ሆኖ በበኩሌ ሕገ መንግሥቱ መልስ አለው እላለሁ፡፡ በቅድሚያ የተወካዮች ምክር ቤትን በተመለከተ የአንቀጽ 60 (1) ድንጋጌ በማያሻማ ሁኔታ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ…›› ብሎ የሚናገር እንደመሆኑ፣ ከሥልጣን ዘመን ማለቅ በፊት ሊደረግ ላልቻለ የምርጫ ክንዋኔ ሕጋዊ ቀዳዳ ለመሆን የሚያስችል ግንኙነት የለውምና ይህንን አንቀጽ እንደ መውጫ መጥቀስ ልክ አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ የምርጫ ጊዜ ገደቡ ቁልጭ ብለው በተቀመጡ አሳማኝ ምክንያቶች መራዘምን እንዲያዝል አድርጎ ለማሻሻል የሚያስችልም ሕገ መንግሥታዊ መንገድ መኖሩ እውነት ነው፡፡ ይህንን መንገድ በመጠቀም ረገድ ችግር ሊመጣ የሚችለው፣ ማሻሻያ ማድረግ ፖለቲካዊ ሰላምን ይረብሻል ወይስ አይረብሽም ከሚል (ከሕግ ውጪ ከሆነ) ጉዳይ አኳያ ነው፡፡ ማሻሻያው ለገዥው ፓርቲ ማምለጫ ከመሆን ባሻገር የሕዝብ ተቀባይነት ስለማግኘቱ መተማመን ከተቻለ፣ የፓርቲና የመንግሥት ካድሬ ባልገባበት አካኋን ሕዝብ ተወያይቶ ፍላጎቱን እንዲገልጽ በማድረግ፣ የማሻሻያውን ሕዝባዊነት መለካትና ከዚያ በኋላ ሌሎችን ሒደቶች ማስከተል ይቻላል፡፡ የሕዝብ ተቀባይነት ጉዳይን በዚህ ዓይነት መንገድ ተወጥቶ ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽን ማሻሻል አግባብነትን ሊቀዳጅ የሚችለው ግን ኮሮና ወረርሽኝን መቆጣጠር ተችሎና መደበኛው የምርጫ ጊዜ ከማብቃቱ በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነስቶ የሚገኘው የጊዜ ክፍተት፣ ምርጫ ለማካሄድ የሚያንስ የሕዝብን ፍላጎት ተመርኩዞ አንቀጽ ለማሻሻል ግን የሚበቃ ከሆነ ነው፡፡ ይህም ሲደረግ ከፖለቲከኞች ጋር መግባባት ላይ የመድረሱ ጥረት የማይዘነጋ ነው፡፡

የሕገ መንግሥት አንቀጽ ማሻሻል ውስጥ መግባት ሳያስፈልግም የጊዜ ገደቡን የተላለፈ ምርጫና የፌደራል መንግሥት ሕጋዊነቱን ላያጣ የሚችልበት ሕገ መንግሥታዊ ቀዳዳም አለ፡፡ የምርጫ መርሐ ግብር መጣበብ ገጥሞት ምርጫውን ከጊዜ ገደቡ ለማዘለል ሲባል የአስቸኳይ ጊዜ ላውጅ ቢባል ኢሕገ መንግሥታዊ መሆን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ በቂ የሚሆኑትን ምክንያቶች በማያሻማ ሁኔታ አንቀጽ 93 (ሀ) ላይ አስቀምጧል፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱ የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ነው፡፡ ኮሮና 19 ወረርሽኝ የሕዝብን ጤና ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ወረርሽኝ ስለሆነ በዚህ ምክንያት በፌዴራል መንግሥት የታወጀውና ዛሬም ሥራ ላይ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ ለአዋጁ መነሾ የሆነው ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር የሚደረገው ትግል እየበረታ ከሄደ ወይም በቁጥጥር ውስጥ የማስገባቱ ትግል አስቸኳይ ጊዜውን ለማንሳት የማይበቃ ከሆነ፣ የተወካዮች ምክር ቤት ገምግሞ በየአራት ወራት በ2/3 ድምፅ ሊያራዝመው ይችላል (93/3)፡፡ እዚህ ላይ የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመኑን ጨርሶ ያልተተካው ተወካዮች ምክር ቤት ነው አራዛሚው? የሚል ጥያቄ ይመጣ ይሆናል፡፡ ኮሮናን በቁጥጥር ውስጥ የማዋሉ ነገር ከመስከረም ወር 2013 ዓ.ም. ቢሻገር፣ ከዚያ ወዲያ ያለውን ጊዜ ለማስተዳደርና በተገቢ ምክንያት የተላለፈውን ምርጫ ለማካሄድ ጊዜው ያለፈበት ነባሩ ፌዴራላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው ወይ ብሎ መጠየቅም አግባብ ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ በቂ ይሆናሉ ካላቸው ምክንያቶች አንዱ፣ ተሟልቶ የታወጀውና በተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ መንግሥታዊነቱ የማያከራክር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በውስጠ ታዋቂ መልስ ይሰጣል፡፡ በአንቀጽ 93(4ሐ) የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚው ምክር ቤት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር በሚያወጣቸው ድንጋጌዎችና በሚወስዳቸው ዕርምጃዎች፣ በምንም ዓይነት አኳኋን የማይደፈሩት ተለይተው ተቀምጠዋል፡፡ እነሱም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 1፣ አንቀጽ 18፣ አንቀጽ 25፣ አንቀጽ 39(1 እና) ናቸው፡፡ ለእነዚህ ጠንካራ ጥበቃ የተደረገላቸው፣ ከእነዚህ ውጪ ያሉት ድንጋጌዎች በሁኔታዎች አስገዳጅነት ሊገደቡ/ሊተጓጎሉ እንደሚችሉ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ የሚገባን፣ አንቀጽ አንድ የሕገ መንግሥቱን ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ አወቃቀርን ከእነ ስሙ እንዳይነካ መጠንቀቁን ስናስተውል ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግድ ሆኖበት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር በሚደነግጋቸው ድንጋጌዎችና በሚወስዳቸው ዕርምጃዎች አማካይነት ከተጠቀሱት አንቀጾች ውጪ ሌሎቹን ለማስተጓጎል ተፈቅዶለታል ማለት ነው፡፡ የሚኒስተሮች ምክር ቤት ለተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ እንደ መሆኑ (አንቀጽ 76/3)፣ ለሚኒስትሮች ምከር ቤት የተፈቀደው በተዘዋዋሪ ለተዋካዮች ምክር ቤትም የተፈቀደ መሆኑ ነው፡፡ በአጭር አነጋገር ሕገ መንግሥታዊ በሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ተሁኖና የማይመለጥ ሆኖ የምርጫ ጊዜ ቢስተጓጎልና ጊዜ ገደቡ ቢተላለፍ፣ መደበኛ ጊዜውን የጨረሰው የተወካዮች ምክር ቤትና ሥራ አስፈጻሚው ከአምስት ዓመት ዕድሜ ቢዘል ኢሕገ መንግሥታዊ አይሆንም ማለት ነው፡፡

የምርጫን መካሄድ ያስተጓጎለውና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ግድ ያለው አደጋ ተቃሎ ምርጫን ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ እስኪመጣ ድረስ፣ ነባሩ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊነቱን አያጣም፡፡ የእኔ አረዳድ ይህንን ፍቺ ነው የሚሰጠኝ፡፡ ሌላው ሕገ መንግሥታዊ አማራጭ ነው ያለውን እኔ ስህተት ነው እንዳልኩ ሁሉ፣ ሌላውም የእኔን አገነዛዘብ ስህተት ሊል ይችላል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለእኔ የገባኝ ዓይነት አንድምታዊ ትርጉም እንዳለው የሚረዱ ከእኔ ውጪ እንደሚኖሩ ግን አልጠራጠርም፡፡ ይህንን ሙግቴን እንደ ምንም የዓብይን መንግሥት ዕላፊ የሥልጣን ቆይታ ሕጋዊ ለማድረግ መፍጨርጨር አድርገው ሊያቃልሉና ለዓብይ መንግሥት ያላቸውን ቅዋሜ ሊሸነግሉ የሚሞክሩ አይታጡም፡፡ ክርክሬ ግን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ከመደገፍና ሕገ መንግሥታዊ አናቅጾችን እንደ ምንም ቆልምሞ ለመንግሥት እንዲመቹ ከማድረግ ጋር አንዳችም ግንኙነት የለውም፡፡ ክርክሬ ሕገ መንግሥቱን በመረዳት ጥረት ላይ ብቻ ያነጣጠረ ነው፡፡

የቢሆን ምሳሌ ወስጄ ጭማሪ ላስረዳ፡፡ አያድርገውና ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ብትገባ፣ ወይም የወራሪ ጦርነት ቢከፈትባና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያለ የሌለ አቅምን ማንቀሳቀስ ውስጥ ቢገባ፣ በዚያ የጭንቅና የጥድፊያ ሁኔታ ውስጥ የመንግሥት የሥልጣን ዘመን የሚያልቅበትና ምርጫ የሚካሄድበት የጊዜ ገደብ ደግሞ ላከትም ነው ብሎ ቢያፈጥ፣ መንግሥት ሕጋዊነቱን እንዳያጣ በማለት የጦርነት ግብግብን አቋርጦ ወይም አትኩሮትን ሁለት ቦታ ከፍሎ የምርጫ ሥራ ውስጥ መነከር፣ በመንግሥትም በኅብረተሰብም ሆነ በፖለቲከኞች ዘንድ የጤና ሥራ አይሆንም፡፡ ‹‹በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን የምርጫ ጊዜን ማለፍ አይፈቀደም›› የሚል ድንጋጌ ኖሮ ቢሆን እንኳ፣ የጤና ሥራ የሚሆነው ያንን ገደብ ጥሶ ጦርነቱ ላይ ማተኮር ነው፡፡ የኢፌዴሪ አካል የሆነ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር አካባቢ፣ ምርጫን ለማስፈጸም ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን በሰጠው አካል አማካይነት ሌሎችን ሳይጠብቅ ምርጫ ቢያካሂድ የሕገ መንግሥት ጥሰት አይፈጸምም፡፡ የራሳችንን ምርጫ አስፈጸሚ ቦርድ/ኮሚሽን እንፍጠር የሚል ዳር ዳርታ ግን የሕገ መንግሥት ጥሰትን መታከክ ነው፡፡ አገር የጦርነት ትግትግ ውስጥ እያለች አቅምን አስተባብሮ እዚያ ላይ በመረባረብ ፈንታ፣ የአገሪቱ አካል የሆነ አካባቢያዊ መስተዳደር ጦርነቱ እኔ ዘንድ ስላልደረሰ በፌዴራሉ ምርጫ ቦርድ አማካይነት በአካባቢዬ ውስጥ ምርጫ አደርጋሁ ቢልም፣ ፍላጎቱ የጤና አስተሳሰብ አይሆንም፡፡ ጦርነት እየጦፈ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ፖለቲከኞችም ተነስተው፣ ‹‹የመንግሥት ዘመኑ አብቅቷል! ጦርነቱን መምራት አይችልም! የሽግግር መንግሥት/የባለሙያዎች መንግሥት፣ ወዘተ ይቋቋም!…›› እያሉ ከጮሁም ድርጊታቸው ያው ከጤና ማጣት አይተናነስም፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌው ለእንዲህ ያለው ጤና ቢስ አጣብቂኝ ነው መፍትሔ የሰጠው፡፡

በምሳሌዬ ላይ ተመሥርተው የጦርነት ሁኔታ ውስጥ ከተገባማ እውነት ነው ብዙ ነገሮች ሊታገዱና ሊዘለሉ ይችላሉ፡፡ ምርጫን መዝለል (ማስተላለፍ) እንዲያውም ቀላሉ ነገር ነው የሚሉ እንደማላጣ እገምታሁ፡፡ ወደዚህ ዓይነት አመለካከት መምጣት አንድ ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ እዚህ አመለካከት ውስጥ ከተገባ አንደኛ ሕገ መንግሥቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ግድ የሚሉ አደጋዎች በመጡበት ሁኔታ ውስጥ የምርጫ ጊዜ ሊስተጓጎልና በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት የአምስት ዓመት ገደብ ሳይወድ ተገዶ እንዲጥስ የሚፈቀድበት ሕገ መንግሥታዊ ቀዳዳ እንዳለ ለመገንዘብ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ሁለተኛ እዚህ ላይ መግባባት ከተቻለ የአሁኑን የኮሮና ወረርሽኝ ከጦርነት አሳንሶ ዓይቶ፣ ‹‹ወረርሽኙ በዓለም ደረጃ እንጂ በኢትዮጵያ ገና ወረርሽኝ አልሆነምና ምርጫ ማካሄድ ይቻላል…›› ባይነት ሌላ ጤና ማጣት እንደሆነ ማሳየት ቀላል ነው፡፡

‹‹ምርጫ ማካሄድ ይቻላል›› የሚሉ ፖለቲከኞች በይፋ በመገኛኛ ብዙኃን ወጥተው፣ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳና እንቅስቃሴዎች ወደ ወትሯቸው ይመለሱ፣ የምርጫ መሰናዶዎች፣ የአዳራሽና የአደባባዮች ስብሰባዎች ሁሉ ይጀመሩ…›› ብለው ሲከራከሩ እስቲ እንያቸው!! ‹‹በእኛ አገር በሽታው ይህን ያህል አልተሠረጫጨም›› መባሉስ ምን ተይዞ ነው? የመርመር አቅማችን ሰፍቶ በየቀኑ አሥር ሺሕ ሰው መመርመር ብንችል ከመርመር በመለስ፣ በአገሪቱ ዋና ከተሞችና ተጋላጭ ተብለው በተለዩ የጠረፍ አካባቢዎች ውስጥ በየአምስት ቀኑ የሰውነት ሙቀት ፍተሻ የማድረግ ዘመቻ ብናካሂድ፣ ዛሬ ካለን መረጃ የራቀ መረጃ ማግኘታችን ብዙ ያጠራጥራል? በአሁኑ ደረጃ በበሽታው የተያዘው ሰው ቁጥር አነስተኛ ቢሆን እንኳ በምናችን ተማምነን ነው፣ ‹‹የወረርሽኝ ደረጃ ላይ አልደረስንም›› ለማለት የምንበቃው? አንድ የተያዘ ሰው የበሽታውን ምልክቶች ሳያሳይ ከአንድ አምስት ሰዎች ጋር (በጣም በአነስተኛ የቁጥር መጠን) ቢቀራርብ ብለን ብንገምት ከ25 ወደ 125፣ ከ125 ወደ 500 የሚምዘገዘግ ንክኪ ይፈጠራል ማለታችን ነው፡፡ የአንድን ያልታወቀ ታማሚ የሰዎች ንክኪ በቀን ውስጥ አሥር አካባቢ አድርሰን ከገመትነው ደግሞ የበሽታው ተዛመችነት የትና የት ይሆናል፡፡ ይህንን ፈጣን ተዛማችነት እኛ አገር ካለ የሰዎች ቸልታ፣ ድህነት አመጣሽ የትፍግፍግ ኑሮ፣ ተሰባስቦ ጫት ከመቃም ልማድ ጋር አገናኝተን ካየነው ደግሞ ፊታችን ገና ብዙ ፈተና እንዳለብን መረዳት አያዳግትም፡፡ አዲስ አበባ፣ አፋር፣ ድሬዳዋ፣ ሐረርን፣ ሶማሌና ጋምቤላን ይዞ ያለብን በሽታውን የመቆጣጠር ትግል ብቻውን እንኳ ሁለንተናዊ ርብርብን የሚያራውጥ ነው፡፡ አጀብ እኮ ነው! ኮሮና በመላው ዓለም በድንበር አልገደብም ብሎ ዓለምን ሲያንቶሰቱስ እያታየ በእኛ አገር ውስጥ በጎጤ ተቆጣጥሬዋለሁ ሊባል ነው?

በጦርነት ጊዜ በአየር፣ በየብስ፣ በባህርና በሳይበር የሚመጣ የጠላት ጥቃትን ነቅቶ መበጠበቅና መመከት ይቻላል፣ ቅድመ መሰናዶው ካለ፡፡ በወታደራዊ ጦርነት ውስጥ በሰርጎ ገብ ከሚመጣው አሠላለፍ ይልቅ ፊት ለፊት የሚመጣው አብዛኛውን ጊዜ ይበልጣል፡፡ የኮሮና ዓይነቱን በትንፋሽና በንክኪ ያውም ምልክት ሳያሳይ ሊዛመት የሚችል ጠላትን መዋጋት ግን ሳይታይና ሳይታወቅ የሚያጠቃ ጠላትን የማሳደድና የማምከን ግብግብ ነው፡፡ የኮሮናን ክፉነት እዚህ ጋ ተወት ላድርግ የማይባልበት ሁሉን ኅብረተሰብ ያካለለና ያነቃነቀ እንቅስቃሴንና ጥንቁቅነትን የሚጠይቅ የሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ይህን ከባድ ጦርነት አቅሎ ማየት ለሞት ድግስ ራስንና ወገንን ከማጋለጥ አይተናነስም፡፡ በተለያየ አቅጣጫ ተዘናግተን ፍትልክልኩ ከወጣብን፣ በእኛ ድህነት ምኑን ከምኑ እናደርገዋለን? አሜሪካን በሚያህል አገር ውስጥ በየቀኑ እስከ ሃያ አምስት ሺሕ የሚደርስ ሰው በወረርሽኑ እየተያዘ ነው ያለው፡፡ በእኛ አገር አንድና ሁለት ሺሕ ሰዎች በየቀኑ የሚያዙበት ሁኔታ ቢፈጠር እንኳ በየትኛው ሥልጣኔ፣ በየትኛው የኑሮ አቅምና የመሠረተ ልማት አቅም ነው ወረርሽኙ ጎርፍ እንዳይሆን የምናግደው? ኮሮናን ድል ለመምታት ከፈለግን የእኛ ዋና ትንንቅ መካሄድ ያለበት በሽታው ሳይስፋፋ አሁን በቶሎ እንጂ በሽታው ካጠለቀን በኋላ አይደለም፡፡

ከፖለቲከኞቻችን የሚጠበቀው ኃላፊነት የተሞላው ተግባር ምንድነው?

 ሕገ መንግሥትን አክባሪ የሆነና እንቅስቃሴውን ሁሉ ሕገ መንግሥታዊ ለማድረግ የሚጣጣር ፓርቲ/ቡድን ወይም ግለሰብ ፖለቲከኛ፣ በሆነ ጉዳይ ላይ ሕገ መንግሥቱ ክፍተት ቢኖርበት እንኳ ወደ ኢሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ አይሮጥም፡፡ ቀጥተኛ አንቀጽ ባይኖርህም እንኳ ምንም ምንም አድርገህ ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ ውለድ ብሎ ያንኑ ሕገ መንግሥት ወጥሮ ነው መያዝ ያለበት፡፡ አሁን በገጠመን ችግር ሕገ መንግሥቱ ያን ያህል መላ የጠበበው እንዳልሆነ አምናለሁ፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን ለመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው አማካይነት በደንብ የተብራራና የደረጃ የትርጓሜና የመፍትሔ ሐተታ እንደሚያቀርብልንም ተስፋ አለኝ፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ክፍተት እንዳላጋጠመን እያመንኩና ይህንኑ አፍታቶ የሚያሳይ የሕገ መንግሥት ትርጓሜን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚሰጠን እየተማመንኩ ሳለሁ፣ ዝምብዬ ከሕጋዊው አካል ትርጓሜ እስኪመጣ አርፌ ያለ መቀመጤ ምክንያት ብዙም ግራ የሚያጋባ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ርዕስ ላይ እንድጽፍ ያነሳሳኝ፣ በኮሮና ወረርሽኝና ወረርሽኙን ግድ ባለው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር በሚካሄድ የወረርሽኝ ውጊያ ምክንያት፣ ምርጫው ከ2013 ዓ.ም. መስከረም አልፎ ቢሄድ የሕጋዊ መንግሥት ክፍተት ስላለመፈጠሩ በፖለቲከኞቻችን ዘንድ መግባባት እንዲፈጠር የማገዝ ዓላማ ነው፡፡ ሌላውም በቅንነትና በሀቀኝነት ያለውን ያዋጣል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ይንን በዚሁ ላብቃና ጎልተው የሚሰሙኝን ነጥቦች እንደሚከተለው እየደረደርኩ ላጠቃልል፡፡

አንድ፡- በኮሮና ወረርሽኝና በዚሁ ምክንያት በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተስተጓጎለው የቡድኖች የተውጣጣ ሥልጣን ሳይሆን፣ የተገባደደ የሕገ መንግሥት የሥልጣን ዘመንን በሌላ አዲስ የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመን የሚተካው ምርጫ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹የሽግግር ሕገ መንግሥት››፣ ‹‹የባሙያዎች መንግሥት››፣ ‹‹የፖለቲካ መፍትሔ›› የሚባለው ሁሉ ከተንጠለጠለው ጉዳይ ውጪ ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በቁጥጥር ውስጥ ውሎና የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ግብግቡ (አዋጁ) እንደ አበቃ በቀጥታ የሚከፈተው አጀንዳ፣ በእንጥልጥል የቀረውን የምርጫ ክንዋኔ ማካሄድ ነው መሆን ያለበት፡፡

ሁለት፡- ፓርቲዎች በምርጫው አሸናፊ ሆኖ መውጣት ከፈለጉ ድርጅታዊ ሽርክና ከመፍጠርና የሕዝብ ድምፅን ሳያፍስብን አይቀርም ብለው የፈሩትን ፓርቲ ስም ከማጠልሸት ይልቅ፣ ትርፋማ ሊያደርጋቸው የሚችለውን ሚስጥር መጨበጥ ከፈለጉ ቀላል ነው፡፡ ቀጣፊ ፕሮፓጋንዳን፣ ስም ልጠፋን፣ ያፈነገጡ ቡድናዊ ፍላጎቶችንና ቁርሾዎችን ጥሎ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚፈልጉት ምንድነው ብሎ ወደ ሕዝብ ቀልብን መመለስና የሕዝቦችን ፍላጎቶችና የአገሪቱን ዕውነታ በሀቅ አንጥሮ ማንፀባረቅ ነው፡፡ ይህ ማስገንዘቢያ በቁጣና በዕብሪት የተሞሉ አንዳንድ ቡድኖችና ፖለቲከኞች በለጡን ብለው ነው መሰል፣ አፍ እንዳመጣ ስድብ መለጠፍ አይሉት ደባን አጋላጭ ክስ አይሉት ድፍን ቅል ዘለፋ የጀማመሩትን የብልፅግና ፓርቲ ሰዎችንም ይመለከታል፡፡

ሦስት፡- ‹‹የፖለቲካ መፍትሔ›› ምናምን የሚል ነገር ከተቀናቃኝ ፓርቲዎች አካባቢ የሚነፍስበት እውነተኛ ምክንያት መንግሥቱን የሚመራው የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ማጭበርበር ሊፈጽም ይችላል የሚል ሥጋት ከሆነ፣ ለዚህ ሥጋት ኢሕገ መንግሥታዊ የሆነ መንግሥት ማዋቀር ወይም የሥራ አስፈጻሚውን ወንበሮች መቃረጥ መፍትሔ አይሆንም፡፡ መፍትሔ የሚሆነው፡-

  • ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ከአጣብቂኝ መውጫ ሕገ መንግሥታዊ አማራጮችን በተመለከተ ከፓርቲዎች ጋር በተወያዩ ጊዜ፣ የሰነዘሩትን አወያይ ኮሚቴ አቋቁመን አሉን በምትሏቸው አበይት ጉዳዮች ላይ እንምከር የሚል ሐሳብ ጠበቅ አድርጎ መያዝ፣
  • ጊዜ ሳያጓትቱ መግባባት የሚደረሰበት ብልህና ብስል ውይይት አድርጎና (የርብርብ ተልዕኮ ነድፎ) ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተጀመረውን ምክክር ቋሚ ባደረገ አኳኋን አብሮ መሥራት፣
  • የርብርብ ተግባሩ የይስሙላ እንዳይሆን ለማድረግ፣ የፖለቲካውንና የፀጥታውን ጉዳይ ወደ ጎን ብሎ በጤናው አደጋ ላይ መተባበር እየተባለ በአንዳንድ የፖለቲካ ቡድን መሪዎች ሲነገር የተሰማውን አስቂኝ ሐሳብ ቦታ ሳይሰጡ፣ በኮሮና ላይ የሚደረገውን ትግልና የኅብረተሰቡን ሰላም የሚረብሹ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርቅ ለሰላማዊ መፍትሔ ከመንግሥት ጋር ተገግዞ እያካሄዱ ኮሮናን ከመቆጣጠር ውጤት ጋር ለሕዝብ፣ ለማኅበራትና ለፓርቲዎች ሰፊ እንቅስቃሴ የሚስማማ ነፃና ሰላማዊ ድባብ ከትግራይ እስከ ሞያሌ፣ ከድሬዳዋ እስከ ምዕራብ ወለጋና ቴፒ ድረስ እንዲሟላ በርትቶ መሥራት፣ (ይህንን ማድረግ መቻል በሌላ መልክ ያለአማላጅ ዕርቅን መጨበጥም ነው)፣
  • ኮሮናን መቆጣጠር ተችሎ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁ እንደተነሳ፣ አምባጓሮና ግርግር አልባ የሆኑ የብዙኃን ነፃ ማኅበራት እንቅስቃሴዎችን በየቦታው ማበረታት፣ አንዱን ፓርቲ የመጥቀምና ሌላውን የማሳጣት ተልካሻ ዓላማ ያላነገቡ በአገሪቱ ሁነኛ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩና የሚከራከሩ የፓርቲዎችና የምሁራን ውይይቶች በየቦታው (በዩኒቨርሲቲዎች፣ በየመድረኮችና በየሚዲያዎች) እንዲንቦገቦጉ ማድረግ፣
  • በዚሁ ሒደት ውስጥ የምንደግፈውንም ፓርቲ ቢሆን በድብስብስ ምርጫ አሸናፊ ከማድረግ ተልካሻነት ይልቅ (ማንም ያሸንፍ ማን)፣ በኢአድላዊነቱና ባለመዘረፉ በሕዝብ ለመታመን የበቃ ምርጫ የማካሄድ ምዕራፍ መከፈቱ፣ ለሁላችንም የሚበልጥብን የዴሞክራሲ ጥቅም መሆኑ ፈክቶ ልብ እንዲባል መሥራት፣ እናም ከዚህ ፍካት በሚገኝ ከቡድን ይልቅ ዴሞክራሲን ባስበለጠ የአስተሳሰብ ሙሽት የምርጫ አስፈጻሚነትንና የነፃ ታዛቢነቱን ሥምሪት መገንባት ነው፣

አራት፡- በዚህ ዓይነት የሰመረ አካሄድ የዴሞክራሲን ምዕራፍ የሚከፍት ምርጫ አካሂዶ መሬትን ከሕዝብ አብልጦ ከመናጠቅ ይልቅ፣ መሬቱ ላይ ያለውን ሕዝብና መብቶቹን አብልጦ የማክበር መሠረትን በመጣል፣ እንዲሁም በፌዴራል በአካባቢዎች ደረጃም ሕዝባዊ የሥልጣን ልዕልና እንዲያብብ በማድረግ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የማስደሰት ወርቃማ ዕድልን (ከዓመት ዓመት በመላ አገሪቱ ሊዘከር ከሚችል ሞገስ ጋር) ለዛሬ ወጣቶች ታሪክ ደቅናለች፡፡ የዛሬ ወጣቶች ሰክነውና በኃላፊነት ተሞልተው ይህን የታሪክ አደራ ዕውን ማድረግ ከቻሉ ለእኔና እኔን ለመሰሉ ጎፋፋ ፖለቲከኞች፣ እኛ በወጣትነታችን ልናሳካ ያልቻልነውን የትናንት ቁጭታችንና የዛሬ ኑዛዜያችንን በልጆቻችን ሲሟላ ማየት ከመታደልም መታደል ነው፡፡ ገድላቸው አሮጌ ትውልድን ከማስደሰትም የትናየት ይልቃል፡፡ ይህንን ለማሳካት መቻል ቀደም ብሎ እንደተነገረው፣ የዳግማዊ ዓድዋ ባለገድል ሆኖ ማብራትም ነው፡፡ ሊፋጁ ነው ሲባል የዴሞክራሲ፣ የሰላምና የኢኮኖሚ የማንሰራራት ዕጣችንን በሠለጠነ የማስተዋል መዶሻና ፍም ስንገራ የሚያየንን ዓለም ማስደመማችንም አይቀሬ ነው፡፡

ወጣት ፖለቲከኞቻችን ባሩድና ትርምስ አይጠፋሽ በሚባለው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ውስጥ ይህንን የመሰለ የድል ታሪክ ይሠሩ ይሆን? ወይስ ጥላቻ፣ ቂምና በቀል ህሊና ነስቷቸው በጎረቤቶቻችን ያየነውን ዓይነት በሕዝቦች ደምና ዋይታ የተሞላ መፈራረስን ያስከትላሉ? ከዚህ ዕብደት እንዲርቁ በፅኑ እንማፀናለን፡፡ ይህ ተማፅኖ እኔን የመሳሰሉ ግለሰቦች ተማፅኖ ብቻ ሳይሆን፣ የመላ ሕዝቦቻችንን ተማፅኖ የሚያስተጋባም ይመስለኛል፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...