Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሕግ ባለሙያዎች ይኖሯቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብ የሕገ መንግሥት ትርጓሜውን በተመለከተ ሐሳባቸውን ማቅረብ አለባቸው›› አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት

እንደ ሌሎች የዓለማችን አገሮች ኢትዮጵያም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየፈተናት ነው፡፡ በኢኮኖሚው ላይ እያሳደረ ያለው ጫና በግልጽ እየታየ ሲሆን፣ ማኅበራዊ ቀውሱም ቢሆን ከባድ እየሆነ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አንዳንድ አገሮች ደግሞ ከወረርሽኙ ባለፈ ውስጣዊ የፖለቲካ ጉዳያቸው ሌላ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል፡፡ በዚህ ወቅት አገራዊ ምርጫ ይደረግ ስለነበር፣ ይህ ግጥምጥሞሽ ፈተና ሆኗል፡፡ ወረርሽኙን እንዴት እንወጣዋለን የሚለው ብቻ ሳይሆን፣ በወረርሽኙ ምክንያት በተራዘመው ምርጫ ሳቢያ የተነሳውን ጥያቄ የአገሪቱን የፖለቲካ ተዋንያንን እያወዛገበ በተራራቀ የመፍትሔ ሐሳብ የቃላት ጦርነት እስከ መወራወር አድርሷል፡፡ ይህንን ተደራራቢ የአገር ችግር ከመቅረፍ አኳያ እንደ መፍትሔ እየቀረቡ ያሉ አመለካከቶችን በተመለከተ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የራሱ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የሚታመነውን የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎን ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሠማኮና ሌሎች የሲቪክ ማኅበራት በምርጫና በአጠቃላይ በአገር ፖለቲካ ጉዳይ ላይ የሚኖራቸው ሚና ምን ድረስ ነው? በምርጫው መራዘም ላይ ያላችሁስ አቋም ምንድነው?

አቶ ካሳሁን፡- የሲቪክ ማኅበራት ስንል እንደ ማንኛውም ማኅበረሰብ ፖለቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉባቸውና የማይሳተፉባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ አሁን በአገራችን በተፈጠረው ሁኔታ ምርጫው እንዲራዘም የተደረገበት ምክንያት አለ፡፡ ምርጫው ከተራዘመ ደግሞ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከመስከረም 30 በኋላ ምን ይሁን የሚለው ጉዳይ እያከራከረ ነበር፡፡ እንዲህ ባለው ጉዳይ የሲቪክ ማኅበራት የሚያደርጉት የሥነ ዜጋ ትምህርት መስጠት ነው፡፡ ሌላው ተግባራቸው ለተፎካካሪ ፓርቲዎች መድረክ በማዘጋጀት ፕሮግራሞቻቸውን ለሕዝቡና ለደጋፊዎቻቸው እንዲገልጹ ማድረግ ነው፡፡ በምርጫው ወቅትም ምርጫን ይታዘባሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ሥራዎች ምርጫው ቢከናወን ኖሮ ይተገበሩ የነበሩ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ እንደሰማነውና በተግባርም እያየን እንዳለነው፣ ምርጫ ቦርድ በተፈጠረው ችግር ሳቢያ ምርጫ ማካሄድ አልችልም ብሏል፡፡ ቦርዱ ከዚህ ድምዳሜ የደረሰው ይህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በኢትዮጵያም በመከሰቱና ተፅዕኖዎች በግልጽ ስለታዩ፣ ምርጫውን በያዘው የምርጫ ሰሌዳ መሠረት ማከናወን ባለመቻሉ ነው፡፡ በእርግጥ ሰዎች በቤታቸው ሳይቀር እየተያዙና እየሞቱ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ እንደ ሲቪክ ማኅበረሰብ ስናይ ይኼ አሳማኝ ነው አይደለም የሚለውን መመዘን ነው ያለብን፡፡ ከዚህ ተነስተን ሁኔታውን ገምግመናል፡፡

ሪፖርተር፡- የምዘናችሁ ውጤት ምን ሆነ?

አቶ ካሳሁን፡- ይህንን ስንመዝን እውነት ነው ወረርሽኙ የሚተላለፈው በንክኪ፣ በትንፋሽና በመሰል ነገሮች ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት ይሆናሉ፡፡ በሽታውን ለመከላከል ርቀትን መጠበቅና ቤት መቀመጥ እንደ መፍትሔ የተቀመጠ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ያስቸግራል፡፡ ፓርቲዎች ሕዝብ ሰብስበው ለማነጋገር አይችሉም፡፡ ከዚህ አንፃር ምርጫው መራዘሙ ትክክል ነው ብለን እንቀበላለን ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኮሮና ወረርሽኝ ሥጋት በምርጫ ሰሌዳው ምርጫውን ማካሄድ እንደማይችል ከማሳወቁ በፊት፣ እንደ አንድ የሲቪክ ማኅበር በምርጫው ሒደት ለመሳተፍ የሚያስችላችሁን ዝግጅት አድርጋችሁ ነበር? ለምሳሌ ምርጫን ለመታዘብም ሆነ ቀደም ብለው እንደጠቀሱልኝ ፓርቲዎች ፕሮግራሞቻቸውን ሊያስተዋውቁበት የሚችሉ መድረክ አዘጋጅታችሁስ ነበር?

አቶ ካሳሁን፡- በእኛ በኩል ይኼ ችግር ከመከሰቱ በፊት እንደ ኢሠማኮ ከማንም ሲቪክ ማኅበር ቀድመን፣ ለቀጣዩ ‹‹ምርጫ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ሚና›› የሚል ሰነድ ያወጣነው እኛ ነን፡፡ ይኼን ሰነድ አውጥተን ከማፅደቃችን በፊት በሁሉም ክልሎች ሠራተኞች እንዲወያዩ ጭምር አድርገናል፡፡ በወቅቱ ከውጭ ወደ አገር የገቡትን የፖለቲካ ፓርቲዎችና እዚህ ያሉትንም ጨምሮ 130 ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎች ነበሩ፡፡ ይህንን ያህል ፓርቲዎች ያሉበት አገር ውስጥ የእኛ ሚና እንዴት ሊቃኝ ይችላል የሚለውን ሁሉ ያገናዘበ ሰነድ ነበር፡፡ በተጨባጭ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ምን ያድርጉ የሚለው ታይቷል፡፡ ሚናችንን መለየት ስላለብን የሌሎች አገሮችን ተሞክሮዎች ወስደናል፡፡ የተሻለ የምንለውን ከእኛ ጋር አስማምተን እንድንተገብረው ወስንነን ነበር፡፡ ወደፊትም የምንራመደው በዚህ መሠረት ነው፡፡ ለሠራተኛው ጥቅም የሚቆመው ማን ነው ብለን በመለየት ድጋፍ ልንሰጥም እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- የምርጫውን መራዘም እንደግፋለን ካላችሁ እዚህ ድምዳሜ ያደረሳችሁ ምንድነው?

አቶ ካሳሁን፡- ወረርሽኙ መቼ እንደሚቆም አሁንም የሚያረጋግጥ አካል የለም፡፡ መስከረም 30 ቀን በሽታው ይጠፋል ወይ ከተባለውም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ለወራት እንደማይራዘም ማንም ማረጋገጥ አይችልም፡፡ በአጠቃላይ ማረጋገጫ የለም፡፡ ስለዚህ ወረርሽኙ የሚቆምበት ወቅት ካልታወቀ ለመከላከሉ ደግሞ መንግሥት መኖር አለበት፡፡ ከመስከረም 30 ቀን በኋላ መንግሥት መኖር አለበት፡፡ እኛም ከዚህ አንፃር ነው አማራጫችንን የምናየው እንጂ፣ ገዥው ፓርቲ ወይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስላሉ ወይም ሌላ አካል ስላለ አይደለም፡፡ ወይም እነዚህ ወገኖች ያሉት ትክክል ነው ትክክል አይደለም የሚል ክርክር ውስጥ አንገባም፡፡ እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ምን ዓይነት አማራጮች ናቸው ያሉት? ከዚህ ሁኔታ ተነስተን ምንድነው የሚኖረው? የሚለውን ነው የምናየው፡፡ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ያሉ አሉ፡፡ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚለው ግን አስቸጋሪ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያታችሁ ምንድነው?

አቶ ካሳሁን፡- በሕገ መንግሥቱ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚል አንድም አንቀጽ የለም፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ይህ ለውጥ ሲመጣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱ ጉድለት ባይኖረውም ወደፊት ከምርጫ በኋላ እናሻሽላለን፣ ይህንን ሕገ መንግሥት ተቀብለን እንሥራ በሚል ተስማምተው የገቡ ስለመሆናቸው ከዚህ ቀደም  ተጠቅሷል፡፡ እኔም በሚዲያ ይህንን ነገር ተከታትያለሁ፡፡ ይህ ማለት ሕገ መንግሥቱ ላይ ተጻፈው ሁሉ ትክክል ነው ብለው አምነውበት ሳይሆን፣ ጉድለት ቢኖረውም ለገዥውም አማራጭ ስለሌለ በዚህ እየሠራን እንቆይ የሚል መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡ ስለዚህ አሁን ያለውን ሕገ መንግሥት ከተቀበሉ ሁሉም ነገር መደረግ ያለበት በሕገ መንግሥት መሠረት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የምታደርገው ነገር የለም፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚል አንቀጽ ከሌለ ሕገ መንግሥቱን ይዞ መሄድ ተገቢ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ሕገ መንግሥት ይሻሻል የሚለውም ሐሳብ ቢሆን፣ አሁን ባለው ሁኔታ ሕገ መንግሥት ማሻሻል የሚቻልበት ደረጃ ላይ አይደለንም፡፡ ይሻሻሉ ተብለው የሚቀርቡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ደግሞ በርካታ መሆናቸውን እያየን ነው፡፡ አንዱ ፓርቲ ይኼ አንቀጽ ይሻሻል ይላል፣ ሌላው ያኛው ይሻሻል ይላል፡፡ መሻሻል የለባቸውም ብለው የሚሞግቱ አሉ፡፡  የተለያዩ ሐሳቦች እየሰነዘሩ ብዙ አመለካከቶችን በመያዝ ሕገ መንግሥቱ መሻሻል ላይ የሚከራከሩ ስላሉ፣ በዚህ አጭር ጊዜ ይህንን ሐሳብ መተግበር ስለማይቻል ከባድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሽግግር መንግሥት ይመሥረት ቢባልስ ይቻላል? ዕድሉስ አለ?

አቶ ካሳሁን፡- እውነት እንነጋገር ከተባለ አሁን ባለንበት ሁኔታ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ላይ ሆነው ለመሥራት ይቸገራሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይፈቅዳል እንኳን ቢባል በተግባር ሊሆን ይችላል የሚባልበት ነገር የለም፡፡ የሐሳብ ልዩነት እንዳለ ሆኖ የሚታየው ግን በጣም የተራራቀ ነገር ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በጋራ አገራዊ አመራር ይሰጣሉ ወይ የሚለው ጉዳይ ራሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ በተለያየ መንገድ ሲታይ የሽግግር መንግሥት መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ የሕገ መንግሥት  ትርጓሜ የተወሰደው እኮ ከሌላው የተሻለ ይሆናል በሚል ነው፡፡ ሕገ መንግሥት መተርጎም አለበት ሲባል ጥሩ ተመራጭ ነው ተብሎ አይደለም፡፡ እሱም ጠንካራና ደካማ ጎኖች አሉት፡፡ በመንግሥት በኩል ቀርቦ ውይይት ሲደረግበት የነበረው ሁሉም ጠንካራ ጎን አለው፣ ደካማ ጎን አለው፡፡ መንግሥት እንደ መንግሥት እንዲቀጥል ከተፈለገ እነዚህ ያልናቸው ሥራዎች መከናወን አለባቸው? የትኛው አማራጭ ይሻላል? ጠንካራ ጎኑ የትኛው ነው? ትንሽ ከፍ የሚለው የቱ ነው? ተብሎ የተወሰደ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ከቀረቡት አራት አማራጮች የትኛው የተሻለ ነው ተብሎ የተወሰደው?

አቶ ካሳሁን፡- ከእነዚህ የተሻለውን እንምረጥ የሚል እንጂ፣ በጣም ተመራጭ ሆኖ ወይም ምንም እንከን የለበትም ከሚል መነሻ አይደለም፡፡ ስለዚህ እኛ እንደ ሠራተኛ ማኅበር የተረጋጋ ነገር ነው የምንፈልገው፡፡ የአገር ሉዓላዊነት ብቻ ሳይሆን ሠርተን መግባት የምንችለው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ሰላም ሊያሰፍን የሚችል ሐሳብ እንደግፋለን፡፡ ሰላም መኖር አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት መከበር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ወደ ሕገ መንግሥት ትርጓሜ ተገብቷል፡፡ ይህ ውሳኔ እንደተጠበቀ ሆኖ ውሳኔውን ተቀብሎ ወደ ተግባር ለማስገባት ከዚህ በኋላ እናንተ እንደ ሲቪክ ማኅበር ምን ታደርጋላችሁ? አሁን አለ የተባለውን ችግር ለመሻገር መንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

አቶ ካሳሁን፡- የተፈጠረውን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት ተመራጩ መፍትሔ መወያየት ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን እንዲተረጉም ተብሏል፡፡ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረግ አለባቸው፡፡ ሰሞኑን እንደሰማነው የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የሕገ መንግሥቱን ትርጓሜ በተመለከተ ባለሙያዎች ሐሳብ እንዲያቀርቡ ጥሪ ተላልፏል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሕግ ባለሙያዎች ይኖሯቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብ የሕገ መንግሥት ትርጓሜውን በተመለከተ ሐሳባቸውን ማቅረብ አለባቸው፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል ይፈልጋሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያን የማይፈልግ ተፎካካሪ ፓርቲ የለም፡፡ ይህ ከሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት በማድረግ ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችል ዕድል ይኖራል፡፡ መወያየቱ ወደ መፍትሔ ሊመራ ከመቻሉም በላይ የሚያቀራርብ ስለሚሆን፣ ለችግሩ መፍቻ የመጀመርያው አማራጭ መወያየት መሆን አለበት፡፡ የአብላጫውን አመለካከት መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ሲቪክ ማኅበራትም ትክክል ነው ብለው በሚያምኑት ሐሳብ ላይ አስተያየት መስጠት አለባቸው፡፡ ሐሳብ እንዲሰጡ ዕድሉ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ይህንንም ምክንያታዊ በሆነ መርህ የመፍትሔ አካል ሊሆኑ ይገባል፡፡ በምክንያት መደገፍ አለባቸው፡፡ በስሜት ሳይሆን በልኬት መሥራት አለባቸው፡፡ ምክንያታዊ የሆነና ለአገርና  ለሕዝብ የሚጠቅም ሐሳብ በመደገፍ አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው፡፡ እንደምናየው ይህ ሕዝብ ደሃ ነው፡፡ ይኼ ወረርሽኝ መጥቷል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ አንበጣ ረሃብ እየጠራ ነው፡፡ የጎርፍ አደጋም አለ፡፡ ክረምቱም እየመጣ ነውና ምን እንደሚጠብቀን አናውቅም፡፡ ስለዚህ ሕዝባችን በብዙ ነገር ሊቸገር ይችላል፡፡ ፖለቲካችን ይህንን ሕዝብ ታሳቢ ቢያደርግ ይመረጣል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችንና ሌሎች ሥጋቶችን ሊያሻግር የሚችለው ምንድነው የሚለውን መሪ ጉዳይ ይዘን አስተያየቶቻችንን በመስጠት፣ አገርን ለመታደግና ሕዝብንም ለማረጋጋት ይጠቅማል፡፡ የተሻለ አማራጭ ሆኖ የሚቀርበውን ሐሳብ በአግባቡ ለማስፈጸም ሁሉም የበኩሉን ማድረግ አለበት፡፡    

ሪፖርተር፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ኢሠማኮ በተለይ ምን ያደርጋል? በአጠቃላይ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል? እዚህም እዚያም ጫፍ የረገጡ ሐሳቦችን ወደ መሀል በማምጣት የተሻለ ነገር ለመፍጠር ምን መደረግ አለበት?

አቶ ካሳሁን፡- ኢሠማኮ የትኛውንም ፓርቲ እኩል ያያል፡፡ በክልልም፣ በብሔርም፣ በአገር አቀፍ ደረጃም ይደራጁ ለእኛ ሁሉም ፓርቲዎች እኩል ናቸው፡፡ እኛ የምንደግፈውና የምንቃወመው ሐሳብን ነው፡፡ ለአገራችን መልካም ነገር መመኘት ይኖርብናል፡፡ ወቅታዊውን ሁኔታ በተመለከተ በተለየ አቅጣጫ የሚወጡትን ከወቅታዊ ጉዳይ አንፃር፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ውይይት ተሳትፌም ዓይቻለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ስሳተፍ የመጀመርያዬ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ካሉ ምልከታዎች አንፃር እያየን ያለነው ስሜታዊነት መኖሩን ነው፡፡ እኔ ያልኩት ብቻ መሆን አለበት የሚል አመለካከት ይዞ፣ እኔ የያዝኩት ሐሳብ መድኃኒት ነው የሚል ሙግትም ይታያል፡፡ እንዲህ ባለ ስሜት መቀራረብ አንችልም፡፡ ስለዚህ የተሻለ ነገር ለአገር ከታሰበ ከስሜታዊነት መውጣት አለብን፡፡ ሐሳባችን ትክክል ነው ብሎ መከራከር መብት ቢሆንም፣ በውይይት መጨረሻ ላይ ብዙኃኑ የደገፈውን ሐሳብ ግን የመቀበል ባህል ሊኖረን ይገባል፡፡ እኛ አገር ፖለቲካ ውስጥ ማዶ ለማዶ ቆመው ሁሉም በራሱ የእኔ ብቻ ትክክል ነው በማለት፣ ቃላት በመሰንጠቅ መነታረክና የእኛ ቡድን ያሸነፋል ዓይነት የትም አያደርስም፡፡

ኮሮና መጣና ትንሽ ተረጋጋ እንጂ ከኮሮና በፊት የነበርንበት ሁኔታ ጥሩ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው እኛ የማንፈልገውን ሐሳብ ስለተናገረ ሰውዬውን ማሰር አለብን፣ መግደል አለብን ከተባለ መቼም መግባባት አንችልም፡፡ መግደል ያለብን ሰውየውን ሳይሆን፣ ሐሳቡን መሞገት ነው፡፡ ሐሳቡን መምታት ያለብን በሐሳብ ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ሕገወጥ ተግባር ውስጥ የተገኘ አይታሰር ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ያልፈለግነውን ሐሳብ ተናግሯል ብለን ብናስር ሰውዬውን አናስተምረውም፡፡ አስተሳሰቡን  ነው ማሸነፍ ያለብን፡፡ አሁን በተለያዩ ሚዲያዎች አንድ ሐሳብ ያቀረበን ሰው ‹‹መጥፎ›› ተናግሯል ብለን ሐሳቡን ከመሞገትና ከማሸነፍ ይልቅ፣ ሰውዬው ላይ መንጠላጠል እንጂ ሐሳቡን የማሳመን ነገር የለም፡፡ የእኔ ብቻ ነው ትክክል ነው ብሎ ሁሉም እኔ ነኝ ካለ፣ ነገሩ ሁሉ የፉክክር ቤት ስለሚሆን ለመግባባት አይቻልም፡፡ ይህንን ማስቀረት ተገቢ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሊሰርፅብን ይገባል፡፡ ፖለቲከኞቻችን ምንድነው የሚያስተምሩን ብዬ የምጠይቅበት ጊዜ አለ፡፡ ሐሳብን በሰከነ መንገድ መግለጽ፣ ማማመጥና መደማመጥ ሊኖር ይገባል፡፡ የእኔ ብቻ ይደመጥ፣ የእኔ ብቻ ነው ትክልል ብሎ መነሳት ዴሞክራሲያዊነትን አያሳይም፡፡ አሁን ግን ይህንን እያየን ስላልሆነ ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የእኔ ብቻ ይደመጥ የሚለው በአንድ ወገን ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም በሁሉም ወገኖች ላይ ስለሚታይ እርስዎ ይህንን አልታዘቡም?

አቶ ካሳሁን፡- ከሰሞኑ ከተለያዩ ሚዲያዎች መስማት እንደቻልኩት፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ወገን እየታዘብኳቸው ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ ከገዥው ፓርቲም በኩል ያየሁት ነገር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በምሳሌ ይንገሩኝ?

አቶ ካሳሁን፡- ሁሉም ከዚህ አስተሳሰብ ነፃ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ እንዲያውም ግማሹ ሚዲያ ይዞ በቡድን የሆነ ነገር ይላል፡፡ ሌላው በሌላ ሚዲያ የሆነ ነገር ይላል፡፡ ግን በአንድ ቦታ በአንድ መድረክ ሐሳባቸውን እንዲሸጡ ለሁሉም ዕድል መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሆነ የየትኛው ሐሳብ ነው የተሻለው በማለት መዝኖ ውሳኔ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ከተሰሙ ነገሮች አንዱ አሁን ላጋጠመው ችግር አንዱ ምክንያት ሕገ መንግሥቱ ነው የሚል ነው፡፡ በአንፃሩ ሕገ መንግሥቱ ምንም ችግር የለበትም የሚሉ አሉ፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት ላይ የተለያዩ ምልከታዎች አሉ፡፡ ካልተሻሻለ ምንም ማድረግ አይቻልም በማለት የሚሞግቱና ከዚህ ሐሳብ በተቃራኒ የሚቆሙ አሉ፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚነሱበትን የተለያዩ አስተያየቶች እንዴት አቻችሎ ማስኬድ ይቻላል? አጠቃላይ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሚሰሙ አስተያየቶችን በተመለከተ ምን ይላሉ?

አቶ ካሳሁን፡- የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እንዴት ተቀረፀ? በምን ሁኔታ ውስጥ ነው የተቀረፀው? የሚለውን መጀመርያ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ሲቀረፅ እንዴት እንደተቀረፀ ያለን ሰዎች እናውቃለን፡፡ በየብሔሩ ተደራጅተውና ግንባር ፈጥረው ጫካ ውስጥ ቆይተው ሥልጣን በያዙ ቡድኖች የተሰናዳ ነው፡፡ ሕወሓት፣ ሻዕቢያ፣ የኦሮሞ ነፃነት አውጭዎች፣ የኦጋዴን ግንባርና ሌሎችም ሁሉ ጫካ የነበሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ጥያቄያቸው የነበረው በኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ይፈጠር፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ይከበር የሚል ነው፡፡ የተማሪዎች ንቅናቄም ከዚህ ጋር የተያዘና እንዲያውም ይኸው አድጎ ነው ወደ ጫካ የተገባው፡፡ እነዚህ ወገኖች ታግለው ሥልጣን ይዘው የሽግግር መንግሥት መሠረቱ፡፡ ስለዚህ በወቅቱ በየብሔሩ ግንባር ሆነው ተዋግተው የመጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅም ወደ ጫካ ያስገባቸውን ጉዳይ ሕገ መንግሥቱ ላይ እንዲንፀባረቅ አደረጉ፡፡ ስለዚህ  የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄን ለመመለስ የተረቀቀ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ በተለያየ ግንባር በተፈጠሩ የፖለቲካ ድርጅቶች የተረቀቀና የፀደቀ በመሆኑም፣ ራስን በራስ እስከ ማስተዳደርና እስከ መገንጠል የሚሉ አንቀጾች እንዲካተቱ ሆኗል፡፡ በተለይ የሰብዓዊ መብት ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የኢትዮጵያ ሕግ አካል ያደረገ ነው፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርና የመሳሰሉትን ሁሉ ያካተተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን ሕገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት ብለው የሚያምኑ አካላት የዚህ ሕገ መንግሥት አንዱ ችግር፣ በአግባቡ ሕዝብ ተወያይቶበት ያልፀደቀ መሆኑን በግልጽ አሁንም እየሞገቱ ነው፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ አሳታፊ አልነበረም ተብሎ ለሚነሳው ጥያቄ ምክንያት አይሆንም?

አቶ ካሳሁን፡- ሕዝቡ እያንዳንዱ ነገር ላይ ተሳትፎ አይደለም ይህ ሕገ መንግሥት የመጣው፡፡ ቅድም ባልኩህ መንገድ የወጣ ነው፡፡ ስለዚህ የተጻፈው ሕገ መንግሥት ባለፉት ጊዜያት ተግባራዊ ሆኗል ወይ ቢባል፣ በአፈጻጸም ላይ ችግር እንዳለበት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ስለሰብዓዊ መብት ካነሳህ ሳይጻፍ ወይም ድንጋጌዎቹ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሳይኖሩ ቀርተው አይደለም የሰብዓዊ መብት ሲጣስ የነበረው፡፡ ጥሰቱ የነበረው ከአመለካከት ችግርና ባለሥልጣናቱ ሕገ መንግሥቱን እዚህ ጋ ጽፈው እዚያ ጋ ደግሞ ሌላ ነገር ስለሠሩ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን ሰብዓዊ መብቶች የተጠበቁ ናቸው ይላል፡፡ እንዲያውም ልዩ ትኩረት የተደረገባቸው ናቸው፡፡  ማንኛውም ሕግ ሲተረጎም እነዚህን ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መንገድ እንዲተረጎም ሕገ መንግሥቱ አቅጣጫ ይሰጣል፡፡

አሁን አንዱ ይነሳና ይህች የሕገ መንግሥት አንቀጽ ከወጣች ሞቼ እገኛለሁ ይላል፡፡ ሌላው ደግሞ ይህች አንቀጽ ከዚህ ሕገ መንግሥት ካልወጣች ሞቼ አገኛለሁ ይላል፡፡ አንዱ አይነካ ይላል ሌላው መነካት አለበት ይላል፡፡ የሚስተካከሉ አንቀጾች አሉ ብሎ አንቀጾቹን ይቆጥራል፡፡ ሁለት ጫፎች አሉ፡፡ በፌዴራሊዝም ላይ የሚነሳም ጉዳይ አለ፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደርና እስከ መገንጠል የሚሉት ጎልተው የሚታዩ መከራከሪያዎች ናቸው፡፡ አሁን ያለው የክልል አከላለል በብሔር መሆን አለበት የሚለው አጠንክሮ ይከራከራል፡፡ የሕገ መንግሥቱ ችግር ክልሎችን በብሔርና በቋንቋ መከለሉ ነው በማለት፣ መሆን ይገባ የነበረው ፌዴራሊዝሙ እንዳለ ሆኖ አከላለሉ ጂኦግራፊያዊ መሆን እንዳለበት በመጥቀስ ምክንያት ሲያቀርብም እንሰማለን፡፡ በአጠቃላይ እንዲህ ያለ ነገር ችግር ይፈጥራል፣ ይቀየር የሚል ኃይል አለ፡፡ ሌላው ደግሞ በተቃራኒው ሕገ መንግሥቱ እንዲህ መሻሻል አለበት ይላል፡፡ እስከ መገንጠል የሚለው አንቀጽ ወጥቶ ራስን በራስ ማስተዳደር አለበት በሚል መካተት ይኖርበታል የሚለው ሁሉ ከሕገ መንግሥቱ አንፃር የሚነሱ ነጥቦች አሉት፡፡  

ሪፖርተር፡- እነዚህ ተቃራኒ ሐሳቦች ይታወቃሉ፡፡ እንዲህ ያሉት ሐሳቦች እንዴት መፍትሔ ያግኙ የሚለው ጉዳይ እንዴት ተፈትቶ  ሕገ መንግሥቱን እንዴት ማሻሻል ይችላል?

አቶ ካሳሁን፡- እንዲህ ያሉ ሐሳቦች እንዴት መታረቅ አለባቸው የሚለው ነገር ነው ዋናው፡፡ ይህንን ጉዳይ ፖለቲከኞች ብቻ አይደሉም መወሰን ያለባቸው፡፡ ፖለቲከኞች የሚያመጡት ሐሳብ ብቻ አይደለም መወሰድ ያለበት፡፡ ሕዝብ መሳተፍ አለበት፡፡ የሕዝቡ ድምፅ መታየት አለበት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ለዚህ መፍትሔ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እነሱ ይዘው የሚመጡትን ብቻ ለሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ማድረግ አይቻልም፡፡ የሲቪክ ማኅበራት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ሌሎችም የዚህ አካል መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ይኼ ከሆነ በሕዝብ ምርጫ የተሻለ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚቻል አምናለሁ፡፡ ለዚህ ግን ጊዜው አሁን አይደለም፡፡ ከምርጫው በኋላ በተረጋጋ ሁኔታ ሊከናወን የሚችል ነው፡፡ የሕዝቡ ስሜት ምንድነው? ሕዝቡ ተወያይቶ ሊወስን ይገባል፡፡ ሁሉም ሐሳቦች ለእኔ የሚጠሉ አይደሉም፡፡ ነገር ግን በሕዝብ የሚወሰን ጉዳይ በፖለቲከኞች ለምን ይወሰናል ነው፡፡ ለሕዝብ ይቅረብ ነው፡፡ በራሳችን ብቻ ወስነን ይኼ ብቻ ነው የሚሻለው ዝም በል ማለት የለብንም፡፡ ዝም በል የሚባለው በድምፅ ነው፡፡ ሐሳቡ ትክልል መሆኑን አለመሆኑን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንስጠው፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለሕዝቡ ይተው፡፡

ሪፖርተር፡- ከወቅታዊው ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ኢሠማኮ ምን እየሠራ ነው?

አቶ ካሳሁን፡- ወረርሽኙን በተመለከተ ኢሠማኮ በአገር አቀፍ ደረጃ እየሠራ ነው፡፡ የሥራ ቦታ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅና መመርያዎች ወጥተዋል፡፡ እነዚህ በአግባቡ መተግበራቸውን እናያለን፡፡ እዚህም እዚያም ችግር ስላለ አፈጻጸማቸውን እያየን ለሚመለከተው አካል እያቀረብን ነው፡፡ በሥራ በተለይ የንፅህና ዕቃዎች መሰጠታቸው፣ ሠራተኞች ርቀታቸውን ጠብቀው እየሠሩ መሆናቸውን የሠራተኛ ማኅበራት እንዲከታተሉ ይደረጋል፡፡ በፌዴሬሽኖቹም በኩል የዋትስአፕ ግሩፕ አዘጋጅተን መረጃ እንለዋወጣለን፡፡ አሉ የሚባሉ ችግሮችም ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እናቀርባለን፡፡ ከአሠሪዎች ማኅበራት ጋር በመሆን እንወያይባቸዋለን፡፡ እዚህም እዚያም ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ የሥራ ቦታ ፕሮቶኮል ተግባራዊ መሆኑንና አለመሆኑ እያየን መፍትሔ እንዲፈለግ እናደርጋለን፡፡ እንዲህ ያሉ ሥራዎች መደበኛ ሥራችን ሆነዋል፡፡ ከዚህ የበለጠ ሥራ የለም፡፡ በአንድ ወገን ብቻ ተከላክለን የምንችለው ስለማይሆን ሁሉም ወገን መረባረብ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ወረርሽኙ እያስከተለ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጫና በሠራተኛው ላይ እንዳይበረታ ምን እየተደረገ ነው? የሥራ ፕሮቶኮሉስ?

አቶ ካሳሁን፡- ሠራተኛን ማገድ ወይም መቀነስ ከሥራ ማስወጣት እንደማይችል በመመርያ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በቀውሱ የተመቱ ድርጅቶች ሠራተኞችን ይዘው መቀጠል እንዳለባቸው የተቀመጠ ነገር አለ፡፡ አሠሪዎችም የተወሰነ ነገር ከመንግሥት ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ መንግሥት በባንክ በኩል ለተጠቁ ዘርፎች እንዲሰጥ ያደረገውም ሠራተኞች ጭምር እንዳይጎዱ ለማድረግ ነው፡፡ የአሠሪዎችን ጫና ለመቀነስ ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ እየጨመረ ነውና ከዚህ የከፋ ነገር ከመጣ በሚልም የተቀመጡ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ያጋጠሙ ችግሮች አሉ፡፡ ፕሮቶኮሉን በአብዛኛው አሠሪዎች ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ ጥቂቶች ደግሞ እያደረጉ አይደሉም፡፡ ደመወዝ አሳልፈው የሚከፍሉ አሉ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ሻሸመኔ ከተማ ማደጋቸውንና መማራቸውን፣ በአግሮ ሜካኒክስ በዲፕሎማ...

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....